Sunday, 03 September 2023 21:04

ከቡዳፔስት መልስ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ከዓለም ሻምፒዮናው ወደ ኦሎምፒክ
በሐንጋሪ መዲና ቡዳፔስት ላይ በተካሄደው 19ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዩና 202 አገራትን በመወከል ከ2100 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል። ሐንጋሪ ቱዴይ እንደዘገበው ሻምፒዮናው በተካሄደባቸው ዘጠኝ ቀናት ከመላው ዓለም የመጡ ታዳሚዎች በቡዳፔስት ከተማ በሚገኙ ሆቴሎች፤ ሆስቴሎችና ጊዜያዊ ማረፊያዎች ከ340ሺ በላይ አልጋዎች ተይዘው የዓለም ሻምፒዮናውን እንግዶች አስተናግደዋል። ከ70%  በላይ የሚሆኑት  እንግዶች ከጀርመን፣ እስራኤል፣ ከእንግሊዝ፣ ከጣልያን፣ ከስፔን፣ ከአርጀንቲና፣ ከህንድ፣ ከካናዳ፣ ከቻይናና ከአውስትራሊያ የመጡ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል። በተለያዮ አጋጣሚዎች ያነጋገርናቸው ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ሻምፒዮናው በፋክክር ደረጃውና በስታድየም በነበረው ድምቀት የላቀ ስኬት የተገኘበትና የማይረሳ ታሪክ እንደተሰራበት ገልፀውልናል።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 40ኛ ዓመቱን ሲያከብር በሐንጋሪ አስደናቂ መሥተንግዶ አግኝተናል ያለው የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮው ሲሆን አዘጋጅ ኮሚቴውንና በስታድዮም ከፍተኛ ድምቀት የፈጠሩትን ደጋፊዎች ባመሠገነበት የመዝጊያ ንግግሩ፤ ቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ከተማ እንደሆነች አረጋግጠናል ካለ በኋላ ወደፊት የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ እንደምትችል ምስክርነት ሰጥቷል። የዓለም ሻምፒዮና አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ባላዝ ፉርጄስ በበኩሉ በቡዳፔስት መስተንግዶ ዓለም አቀፍ አንድነት አሳይተናል ብለው ከአትሌቶች ባሻገር ከ4,000 በላይ አሰልጣኞችና ልዑካናት አስደናቂ ተሳትፎ ማድረጋቸው ለኦሎምፒክም ብቁ እንደምንሆን የሚያመለክት ነው ሲል ተናግሯል። በግዙፉ የቡዳፔስት ብሔራዊ የስፖርት ማዕከል  ከ125 በላይ ዜግነት ያላቸው ስፖርት አፍቃሪዎች ትኬቶችን በመቁረጥ ውድድሮችን በዘመናዊው ስታድዬም ተገኝተው ተከታትለዋል። በሻምፒዮናው የተመዘገበው ከፍተኛ የቲኬት ሽያጭ  በ2017 በለንደን ከተደረገው የአለም ሻምፒዮና የሚስተካከልም ሆኗል። 423,090 ትኬቶች ለሽያጭ ቀርበው 404,088 ቲኬቶች ተሽጠዋል። የትኬቶች ዋጋ ዝቅተኛው 3,000 የሐንጋሪ ፍሮይንት (8.50 ዶላር ገደማ) ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 6,900 HUF ($20) አካባቢ ነበር። ሙሉ ሻምዮናውን ለመታደም ከቀረቡት የቲኬት ፓኬጆችም እስከ 1,958,000 HUF እስከ $ 5,600 ተከፍሏል።

46 አገራት የሜዳልያ ሽልማቶችን
ለመጎናፀፍ በቅተዋል
የኢትዮጵያዎቹ አማኔ በሬሶና ጉዳፍ ፀጋይ፤ የኬንያዋ ፌዝ ኪፕየገን፤ የአሜሪካዎቹ አጭር ርቀት ሯጮች ሻካሪ ሪቻርድሰንና ፍሊፕ ቦል፤ የአግድመት ዝላይ ሻምፒዮኑ ጣሊያናዊ ታምቤሪ፤ ስፖንያርዶቹ የርምጃ ውደድር ሻምፒዮኖች፤ በጦር ውርወራ ያሸነፈው ህንዳዊ ኔራጅ ቾፕራ፣ የዩክሬኗ ከፍታ ዝላይ ሻምፒዮን ያጋስላቫ ማቹሂክህ… ሌሎችም አትሌቶች የስፖርት አፍቃሪውን ያስደሰቱና የውደድሩ ድምቀቶች ተብለው ከተወደሱት የሚጠቀሱ ናቸው። በሻምፒዮናው 1 የዓለም ሪከርድ ብቻ የተሰበረ ሲሆን 7 የሻምፒዮናው ሪከርዶች መሻሻላቸው እና 22 የዓመቱ ፈጣን ሰዓቶች እንደተመዘገቡ ተገልጿል። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው 148 የሜዳልያ ሽልማቶች የተበረከቱ ሲሆን 46 አገራት አንድና ከዚያም በላይ የሜዳልያ ሽልማቶችን ለመጎናፀፍ በቅተዋል። 23 አገራት የወርቅ ፤26 አገራት የብር እንዲሁም 24 አገራት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያገኙ ሲሆን 71 አገራት ከ1-8 ባለው ደረጃ በመግባት ከቀረበው የሽልማት ገንዘብ ለመቋደስ ችለዋል። አፍሪካካረቢያን፣ መካከለኛውና ሰሜን አሜሪካ በ4 አገራት 20 የወርቅ ሜዳሊያዎች፤ አውሮፓ በ9 አገራት 16 የወርቅ ሜዳልያዎች፤ አፍሪካ በ5 አገራት 9 የወርቅ ሜዳሊያዎች፤ ኤሽያ በ3 አገራት 3 የወርቅ ሜዳሊያዎች፤ ኦሽኒያ በአንድ አገር አንድ የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም  ደቡብ አሜሪካ በአንድ አገር አንድ የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ በሁሉም ክፍለአህጉራት የሜዳልያ ሽልማቶቹ ተዳርሰዋል።
የአፍሪካ አህጉር ስኬታማነት
የአፍሪካ አትሌቶች 26 ሜዳሊያዎችን ያሸነፉ ሲሆን፤  ከ6 አገራት በተውጣጡ አትሌቶች የተመዘገቡ ውጤቶች ናቸው። ኬንያ 10 ሜዳሊያዎች፤ ኢትዮጵያ 9 ሜዳሊያዎች፤ ኡጋንዳ፣ ሞሮኮና ቦትስዋና እያንዳንዳቸው ሁለት ሜዳሊያዎች እንዲሁም ቡርኪናፋሶ አንድ ሜዳልያ በማስመዝገብ የሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል።  ኬንያ 3 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሠብሰብ ከአፍሪካ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን፤ ፌዝ ኬፕዮገን በ1500 እና በ5000 ሜትር ድርብ ድሎችን በማስመዝገብና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች በመጎናፀፍ ከፍተኛውን ውጤት ያገኘች የአፍሪካ አትሌት ሆናለች። የአፍሪካ አገራት ስኬታማነት ኬንያ በሴቶች 800 ሜና በ3 ሺ መሠናክል ያስመዘገበችው ውጤት፤ ኡጋንዳ በወንዶች 10ሺና በማራቶን የተጎናፀፈቻቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች፤ ሞሮኮ በወንዶች 3ሺ መሠናክልና በሴቶች ማራቶን፤ ቦትስዋና በ100 ሜትርና በ200 ሜትር የአጭር ርቀት ውድድሮች እንዲሁም ቡርኪናፋሶ በስሉስ ዝላይ ጠንካራ ውጤት አግኝተዋል 3 የአፍሪካ አትሌቶች በ18ኛው የዓለም ሻምፒዮና ያስመዘገቡትን ክብር ያስጠበቁ ሲሆን ፌዝ ኬፕየገን ከኬንያ በ1500 ሜትር፤ ጆሽዋ ቼፕቴጊ ከኡጋንዳ በ10ሺ ሜትር እንዲሁም ሴፋኒ ኤል ባካሊ ከሞሮኮ በወንዶች 3ሺ ሜትር መሠናክል ናቸው። ከኢትዮጵያውያኑ መካከል ጓይተቶም ገብረስላሴ በማራቶን የሻምፒዮናነት ክብሯን ባታስጠብቅም የብር ሜዳልያ ለመጎናፀፍ ስትችል፤ ታምራት ቶላ በማራቶን እንዲሁም ጉዳፍ ፀጋይ በ5000 ሜትር የሻምፒዮናነት ክብራቸውን ሳያስጠብቁ ቀርተዋል። ኢትዮጵያውያን በሴቶች 10ሺ ሜትር  ከ1-3 ደረጃ በማግኘት ያገኙት ውጤት እንዲሁም በማራቶን የተገኙት የወርቅና የብር ሜዳሊያዎች የላቁ ስኬቶች ናቸው።  በሴቶች 1500 ሜትር በድርቤ ወልተጂና በወንዶች 3ሺ መሠናክል ለሜቻ ግርማ ያገኟቸ የብር ሜዳሊያዎች ከፍተኛ ስኬቶች ናቸው።ከፍተኛ ስኬቶች ናቸው። በወንዶች 10ሺ ሜትር ለ5ኛ ተከተታታይ የዓለም ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ መነጠቁ  በሰለሞን ባረጋ የነሐስ ሜዳሊያ ውጤቱ መወሠኑ ያነጋገረ ሲሆን በማራቶን ከፍተኛ ግምት ተሠጥቶ ልዑል ገብረስላሴ  ብቻ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቱ የኢትዮጵያን ውጤት አጥጋቢ ሳያደርገው ቀርቷል።
ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ 2ኛ ፤ እስከ 441 ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት
ኢትዮጵያ  በ2 የወርቅ፤ በ4 የብርና በ3 የነሐስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎች በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዥ 6ኛ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለሻምፒዮናው እስከ ስምንተኛ ደረጃ በሚመዘገብ ውጤት መሠረት 8.5  ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡድን ድርሻው 441ሺ ዶላር ሆኗል። በ9 ሜዳሊያዎች 350 ሺ ዶላር፤ እንዲሁም 4ኛ ደረጃ ሁለት ጊዜ፤ 5ኛ ደረጃ ሶስት ጊዜ፤ 6ኛ ደረጃ ሶስት ጊዜ፤ 7ኛ ደረጃ አንድ ጊዜና 8ኛ ደረጃን አንድ ጊዜ በማስመዝገብ ተጨማሪ 91ሺ ዶላር ተገኝቶ ነው።
በተያያዘ ከቡዳፔስት መልስ  በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አባላት የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል። የወርቅ ሜዳሊያ ላገኙ 60 ሺህ ብር፤ የብር ሜዳሊያ ላገኙ 40 ሺህ ብር እንዲሁም የነሃስ ሜዳሊያ ላገኙ  የ30 ሺህ ብር አግኝተዋል። አትሌት ፀሐይ ገመቹና ለአትሌት ያለም ዘርፍ የኃላው እያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር ሽልማት ሲሰጣቸው፤ ዲፕሎማ ለወሰዱት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ15 ሺህ ብርና ለሌሎች 16 አትሌቶች  ለእያንዳንዳቸው የ7 ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ድረገፅ ስኬትና የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ንቁ ተሳትፎ
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በድረገፁ በሰራው ዘገባ  በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛውን ትኩረት በማግኘት የቡዳፔስት መሥተንግዶ የዓለም ሻምፒዮና የሚጠቀስ ሆኗል። www.worldathletics.org የተባለው የማህበሩ ድረገጽ በሻምፒዮናው ሰሞን በቀን 1 ሚሊዮን ጎብኝዎች እንደነበሩት ፤ በደቂቃ 400ሺ በሰዓት 14ሚሊዮን ታዳሚዎች ከድረገፁ መረጃ ይጠይቁት እንደነበርም ተወስቷል። በዓለም አትሌቲክስ ማህበሩ ኦፊሴላዊ ድረገፁ ላይ ከ14ሺ በላይ ዜናዎች፤ አጫጭር ቃለምልልሶችና ዘገባዎች ታትመው ከ28.5 ቢሊየን በላይ ድምር ጎብኝዎች ማግኘታቸውንም መግለጫው አትቷል።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከዓለም ዙርያ በመሠባሰብ ከ75 በላይ አገራትን ወክለው የተሳተፉት የሚዲያ ባለሙያዎች ከ2ሺ በላይ ናቸው። ለ46 የብሮድካስት ኩባንያዎች የሰሩት ከ1200 በላይ የብሮድካስት ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ከ800 በላይ ጋዜጠኞች ደግሞ የህትመትና የዲጂታል ሚዲያዎችን በመወከል ሻምፒዮናውን በስፋት ዘግበዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያን የወከሉ ሚዲያዎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ተሳክቶላቸዋል። በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ተጋብዘው በሻምፒዮናው የሰሩት ግሩም ሰይፉ ከአዲስ አድማስ፣ ዳዊት ቶሎሳ ከሪፖርተር፣ ይስሐቅ በላይ ባለቀለሟ የስፖርት ጋዜጣ ሀትሪክና ከሐትሪክ ስፖርት ቲቪ፣ ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም ከልዩ ስፖርት፣ በሻምፒዮናው ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በፎቶግረፈርነት ቅዱስ ዮፍታሔ ከቲክቫህ ስፖርት ይሁኔ ይስማው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ እንዲሁም አረጋ ከፈለውና ግርማ በቀለ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ናቸው። እነዚህ የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሙያዎች በህትመት፤ በብሮድካስት፤ በዲጂታል የሚዲያ አውታሮች ዜናዎች፤ ቅደመ ሀተታዎች፤ የውጤት ዘገባዎችና ቃለምልልሶችን በቀጥታ ከቡዳፔስት በማቅረብ ሰፊ ሽፋን  የኢትዮጵያን ቡድን ተሳትፎ በመረጃ አጠናክረዋል።Read 531 times