“ብልፅግና” ሥልጣን ላይ እያለ ወደ አገራቸው ላይመለሱ ይችላሉ
በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በንቃት የታገሉት (በዋናነት ከገዢው ፓርቲ ጋር) የአፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፤ ከሰሞኑ ከፓርቲ ሃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ፖለቲከኛው ወደ አገር ቤት እንደማይመለሱም ነው የተናገሩት- ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ አለመመለስ ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካን መንግስት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ (በስተርጅና ዕድሜያቸው ለምን የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቁ? ብንል ተገቢ ጥያቄ ነው!።)
በኢትዮጵያ እየከፋ የመጣው የፖለቲካ ሁኔታ፣ በአገሪቱ “ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ለማካሄድም” ሆነ “የግል ነፃነት” ለማስከበር ተፅዕኖ እያደረገ መሆኑን የሚያምኑት አቶ በቀለ ገርባ፤ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁበትም ምክንያት ይኸው ለመስራት አስቸጋሪ የሆኑ ነው የፖለቲካ መልክአ ምድር መሆኑን ይናገራሉ፡፡
“ኢትዮጵያ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ ደህንነት አስጊ ሆናለች” ብለዋል ፖለቲከኛው፡፡ (ይኼ ማለት እኮ ቢያንስ የብልፅግና መንግስት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ወደ አገራቸው አይመለሱም ማለት ነው፡፡) ለምን ያህል ጊዜ? ምናልባት ለ10 ዓመት? ወይም ለ20 ዓመት? ወይም ከዚያም በላይ… (ያሳዝናል አልታደልንም!)፡፡
የማያምርበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከስደት፣ ከወከባ፣ ከመገዳደል፣ ከመፈራረጅና ከመጠላለፍ ወዘተ የሚላቀቀው መቼ ይሆን? (አንድዬ ይወቀው!)
በ2010 ዓ.ም የለውጡ መንግስት ስልጣን በያዘ ማግስት፣ ወህኒ ቤት የከረሙ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን በነፃ በመፍታቱ ብዙዎች የፈነደቁት፣ ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ መንገድ ለእስር የሚዳረግ ኢትዮጵያዊ አይኖርም በሚል ሙሉ ተስፋ እንደነበር እሙን ነው፡፡ የለውጡ መሪዎች (በተለይ ጠ/ሚኒስትሩ) በአንደበታቸው ደጋግመው የነገሩንም ይኼንኑ ነበር፡፡ የለውጡ መንግስት ስልጣን እንደተቆናጠጠ እኮ፣ ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ሪፖርት፣ በዚያው ዓመት ከመላው አፍሪካ አንድ ጋዜጠኛ እንኳን ያልታሰረባት ብቸኛ አገር-ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች። በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም!
ግን እንዳማረብን ለመዝለቅ አልታደልንም። (እፎይ አትበሉ የተባልን ይመስል!) ጋዜጠኞችም ሆኑ ፖለቲከኞች አሊያም አክቲቨስቶች እንደተለመደው መታሰራቸው ቀጠለ- እንደውም ይበልጥ ተባብሶ (ያደቆነ (ሰይጣን… እንዲሉ።)
አሁንም ይኸው የለውጡ መንግስት (“የለውጡ መንግስት” ግን የት ገባ!?) ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በባህር ማዶ በስደት ያሉና ወደ አገራቸው መግባት የማይችሉ የነበሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ እናት አገራቸው በነፃነት እንዲገቡ መፈቀዱ አስፈንድቆነ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደሞ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ሳቢያ ከአገራቸው ወጥተው ለስደት አይዳረጉም በሚል ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡ ይኼም ግን አልዘለቀም፡፡ ኢትዮጵያውያን (በተለይ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች) አንዴ እግራቸው ከአገር ከወጣ፣ ሰው አገር መቅረትን እየመረጡ ነው- በስደተንነት። (ተመልሰን ሌላ የስደት አዙሪት ውስጥ መግባት ይሏል ይሄ ነው፡፡) ለነገሩ ከአንዱ ጦርነት በቅጡ ሳናገግም ሌላ አዲስ ጦርነት ውስጥ መሰስ ብለን እየገባን፣ ዕጣፈንታችን እንዴት ከስደት የተሻለ ሊሆን ይችላል? ጦርነት ባለበት ሰላምና ዕድገት አይታሰብም፡፡ ጦርነት ባለበት ነፃነትና ዲሞክራሲ አይታለምም፡፡ ጦርነት ባለበት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያብባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ጦርነት ባለበት መደማመጥና መነጋገር የሚታሰብ አይደለም፡፡ በእንዲህ ያለ ጊዜ እንደ በቀለ ገርባ ያሉ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸው ብዙም ሊገርመን አይገባም፡፡ በጦርነቱ እስከቀጠልን ድረስ ብዙ የፖለቲካ ቀውሶች ይከሰታሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን በመቀላቀል ወደ ፖለቲካው የዘለቁት በቀለ ገርባ፤ በምክትል ሊቀመንበርነት ከሚመሩት ኦፌኮ ሃላፊነት መልቀቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ “አሜሪካ ተቀምጬ በፓርቲ ሃላፊነቴ መቀጠሌ ትርጉም የለውም” በማለት ነው- ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ፓርቲው ያለው ኦሮሚያ ክልል፣ እሳቸው ያሉት በታላቋ አሜሪካ! “ኢትዮጵያ ለህይወቴ (ደህንነቴ) አስጊ መሆኗን ለአሜሪካ መንግስት አሳውቄአለሁ” ያሉት አቶ በቀለ ገርባ፤ “አገር ቤት ከሞላ ጎደል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሮዎች በመንግስት ተከርችመዋል፡፡” ብለዋል - ለቢቢሲ። “በዚህ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ የምመለሰው ምን ፍለጋ ነው” እያሉ ይመስላሉ በቀጥታ ባይናገሩትም፡፡
የቀድሞው እስረኛ በቀለ ገርባ፤ የህግ ታራሚዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በመግደል፤ በጅምላ ግድያና እስራት የመንግስት ሃይሎችን ክፉኛ ይከስሳሉ እነሱ ባይቀበሏቸውም።
የድምፃዊ ሃጫሎ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ፣ በሽብርተኝነትና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ተከሰው ለ18 ወራት በእስር የከረሙት ፖለቲከኛው፤ በጃንዋሪ 2022 ከእስር ከተፈቱ በኋላ በሰኔ ወር ወደ በአሜሪካ የተጓዙ ሲሆን፤ ላለፉት 15 ወራትም በአሜሪካ ተቀምጠዋል። በእርግጥ ወደ አሜሪካ የተጓዙት የመቅረት እቅድ ይዘው አልነበረም፡፡ (የፖለቲካ ጥኝነት መጠየቅማ ትዝ ብሏቸውም የሚያውቅ አይመስለኝም።) ወደ አሜሪካ የተጓዙት እዚያ ከሚገኙና ከእስር እንዲፈቱ ጥረትና ድጋፍ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን ለማግኘትና ለማመስገን እንዲሁም በወደፊት ዕቅዶች ላይ ለመወያየት ነበር (ራሳቸው እንደተናገሩት)
ፖለቲከኛው በአሜሪካ በቆዩባቸው 15 ወራት ግን ነገሮች ተለዋወጡ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክአ-ምድር ተገለባበጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ አገር ቤት መመለሱ አስፈላጊ አይደለም የሚል ውሳኔም ላይ ደረሱ።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ “አደገኛው” ሲሉ የሚገልፁት የቀድሞው የዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ በቀለ ገርባ፤ ቀሪውን የአሜሪካ ህይወታቸውን በምን እንደሚያሳልፉት የሰጡት ፍንጭ የለም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን መንፈሳዊ ሊሆኑ እንደሚቸሉ ግምታቸውን እየሰጡ ነው -“የወንጌል ሰባኪ!”
Sunday, 03 September 2023 21:08
የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁት በቀለ ገርባ
Written by ኤሊያስ
Published in
ፖለቲካ በፈገግታ