Sunday, 10 September 2023 21:12

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከ50 ፎቅ በላይ ያለው መንትያ ህንጻ ሊገነባ ነው

Written by  -ሪፖርታዥ-
Rate this item
(1 Vote)

 •  የህንጻውን ዲዛይን አስተዋውቋል፤ የስምና የንግድ ምልክት ለውጥም አድርጓል
  •  ስሙን ከ “ደቡብ ግሎባል ባንክ” ወደ “ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ” ለውጧል
 •  ባንኩ ጠቅላላ ሃብቱን በሦስት ዓመት ውስጥ 50 ቢ. ለማድረስ አቅዷል

ደቡብ ግሎባል ባንክ የዋና መ/ቤት ህንጻ ዲዛይኑን ያስተዋወቀ ሲሆን፤ በቅርቡ ከ50 በላይ ፎቅ ያለው መንትያ ህንጻ ሜክሲኮ አካባቢ እንደሚገነባ ተገለጸ፡፡ ባንኩ የስያሜና የንግድ ምልክት ለውጥም አድርጓል፡፡

ባንኩ ትላንትና ቅዳሜ ጳጉሜ 4 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት፣በስካይ ላይት ሆቴል ባዘጋጀው ሥነስርዓት ላይ አሸናፊ የሆነው  የባንኩ ዋና መ/ቤት ህንጻ ዲዛይን ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ስያሜውንም ከ“ደቡብ ግሎባል ባንክ” ወደ “ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ“ መለወጡ ታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም፣ ኢትዮጵያ የሚል ቃል የያዘ የመጀመሪያው የግል ባንክ መሆኑን የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

የስያሜና የንግድ ምልክት ለውጡ ያስፈለገው ተለዋዋጭ በሆነው የባንክ ኢንዱስትሪ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆንና ኢትዮጵያዊ የሆነ ዓለማቀፍ ብራንድ ለመፍጠር  ነው ተብሏል፡፡
የባንኩን ዋና መ/ቤት ህንጻ ዲዛይን ለመሥራት 18  ባለሙያዎች የተወዳደሩ  ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም ኢላፕስ ቢዝነስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆኗል፡፡
 
በውድድሩ ከ1- 3 የወጡ ተወዳዳሪዎች እንደ ደረጃቸው  የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን 18ቱም ተወዳዳሪዎች የተሳትፎ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ “የፋይናንስ እምብርት” ተብሎ በሚታወቀው ሜክሲኮ አካባቢ፣  ለዋና መ/ቤት  ግንባታ የሚሆን 5ሺ500 ካሬ ቦታ መረከቡን የጠቆመው ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ፤ በቅርቡ ከ50 ፎቅ በላይ ያለው የዘመናዊ ህንጻ  ግንባታ እንደሚጀምር ትላንት ምሽት አስታውቋል፡፡

አዲስ የሚገነባው የባንኩ ዋና መ/ቤት ሁለት መንትያ ህንጻዎች እንደሚኖሩት የተገለጸ ሲሆን፤ ትልቁ ህንጻ ከ50 በላይ ፎቅ፣ ትንሹ ደግሞ ከ12 በላይ ፎቅ  ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የዋና መ/ቤቱ ህንጻ ለፓርኪንግና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል  3 የምድር ወለልም እንደሚኖረው ታውቋል፡፡
”አዲሱ የዋና መ//ቤት ህንጻ ግንባታ ለባለአክሲዮኖቻችን ተጨማሪ ሃብት ሲሆን፤ ለከተማችን ደግሞ ተጨማሪ ውበትና ድምቀት ይሆናል” ብለዋል - የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 ዓ.ም በጥቂት ባለሃብቶች ኢኮኖሚውን ለማስተሳሰር በሚል ራዕይ ተመስርቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ባንኩ፤ መሪ ቃሉ ”ለጋራ ስኬታችን” የሚል መሆኑን አሳውቋል፡፡ በአንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ቴዲ ማክ የተሰራው  የባንኩ  መሪ መዝሙርም ይፋ ተደርጓል - በምሽቱ፡፡

በተጠናቀቀው ባጀት ዓመት 820 ሚሊዮን ብር ማትረፉ የተነገረለት  ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ፤ በቀጣይ ዓመት 1 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ ማቀዱ ተጠቁሟል፡፡
ከ1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትና ከ152 በላይ ቅርንጫፎች  መክፈቱን ያመለከተው ባንኩ፤ የሰራተኞቹ ቁጥርም ከ2380 በላይ መድረሱን ጠቁሟል፡፡ ጠቅላላ የባንኩ ሃብት 20 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያስታወቁት የባንኩ አመራሮች፤ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት  50 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዛሬ 12 ዓመት የኢትዮጵያ  የባንክ ኢንዱስትሪን ሀ ብሎ የተቀላቀለው ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ፤ 18 ሺ ባለአክሲዮኖች እንዳሉትም ታውቋል፡፡

 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 1314 times