Sunday, 10 September 2023 21:17

ከ100 በላይ ለሚሆኑ የቀድሞ ሠራዊት አባላት የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በመዲናዋ የምሽት ክለብ የሚያቀነቅኑ ድምጻውያን 100 ሺ ብር ለግሰዋል
“እናንተን መንገድ ላይ የበትንን ዕለት ነው ኢትዮጵያ የታመመችው” -ፕሮሞተር ሰለሞን ገ/ማርያም-
የቀድሞ ሠራዊት አባላት ማህበር፣ ዛሬ የሚከበረውን ”የትውልድ ቀን” ምክንያት በማድረግ በችግር ላይ ለሚገኙ ከ100 በላይ  የቀድሞ ሰራዊት አባላት ለአዲስ ዓመት መዋያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

የቀድሞ ሰራዊት አባላት ማህበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ዛሬ 9 ሰዓት ላይ በአራዳ ክፍለከተማ አዳራሽ በድጋፍ አሰጣጥ ሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “እናንተ የአገር ባለውለታ ናችሁ፤ አገር በውስጥም በውጭም ጠላቶች ስትፈተን መስዋዕትነት ከፍላችሁ ለዛሬ አድርሳችኋታል፤ለዚህ ነው መንግሥት የተውልድ ቀን ብሎ በሰየመው በዛሬው ዕለት ከቅን ኢትዮጵያውያን ያሰባሰብነውን የገንዘብ ድጋፍ ልናደርግላችሁ የተሰባሰብነው፡፡” ብለዋል፡፡

የማህበሩ የውጭ ድጋፍ አሰባሳቢ ፕሮሞተር ሰለሞን ገ/ማርያም በበኩሉ፤ “እናንተ የአገር ባለውለታ ናችሁ፤ በየዓመቱ እናንተ ፊት ቆሜ ተመሳሳይ ነገር ነው የምናገረው፤ እንደ አገር እናንተ የአገር ባለውለታ መሆናችሁን ሁሉም ሲረዳ ነገሮች ይለወጡ ይሆናል፤እኛ አሁንም የምናደርግላችሁን ከቁምነገር አትቁጠሩት፤ እናንተ ነፍሳችሁን ሰጥታችሁ ነው አገራችሁን ያቆያችሁት፡፡” ሲል ተናግሯል፡፡

“እናንተ ላይ የፈጸምነው ግፍ ነው ኢትዮጵያ ላይ የምናየውን ችግር ያመጣው፤ እናንተን መንገድ ላይ የበትንን ዕለት ነው ኢትዮጵያ የታመመችው፤እናንተን ይቅርታ የጠየቅን ዕለት ሁሉም ነገር ይለወጣል ብዬ አስባለሁ” ብሏል፤ ፕሮሞተር ሰለሞን፡፡

 የገንዘብ ድጋፉን በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ደጋግና ቀና ኢትዮጵያውያን ማሰባሰባቸውን የገለጸው የማህበሩ የውጭ ድጋፍ አሰባሳቢ ፕሮሞተር  ሰለሞን፤ ድጋፉን ላደረጉት ወገኖች ሁሉ በቀድሞ ሰራዊት አባላት ማህበር ስም ያመሰገነ ሲሆን ለለጋሾቹም የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ድጋፉን ካደረጉት መካከል እዚሁ በመዲናችን  ፓስዎርድ ላውንጅ (በሌላ ስሙ ፍቅር ኮተት) በተባለ የምሽት ክለብ  የሚያቀነቅኑ ሦስት ድምጻውያን (ካሣሁን እሸቱ፣ አዲስ ሙላትና ታረቀኝ ሙሉ) የሚገኙበት ሲሆን፤የአንድ ምሽት ገቢያቸውን 100ሺ ብር መለገሳቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ፤ የጃሞ ትሬዲንግ ባለቤት 50ሺ ብር፣ በውጭ የሚኖር ሳምሶን ተሾመ የተባለ ኢትዮጵያዊ 50ሺ ብር፣ ጠበቃ ሼክስፒር ፈይሳ 30ሺ ብር፣ የትሬይ ትሬዲንግ ባለቤት ደግሞ 25ሺ ብር ለቀድሞ ሰራዊት አባላት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
 
በዛሬው ዕለት  የገንዘብ ድጋፍ  ከተደረገላቸው መካከል የአምስት ልጆች እናት የሆኑትና  ባለቤታቸው  በጦርነት ከተሰዋ አንድ ዓመት ቢሆነውም፣ መርዶውን የሰሙት ከሰሞኑ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የተናገሩት  ወ/ሮ አበበች ድሪባ ይገኙበታል፡፡

 ለአዲስ ዓመት በዓል በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ማህበሩን ያመሰገኑት ወ/ሮ አበበች፤ ከዚህ ቀደም ሻይ ቡና እየሸጡ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ እንደነበር ጠቁመው፣ አሁን ግን የሚሰሩበት ቦታ በመፍረሱ ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የተሻለ ድጋፍ ቢያደርግላቸው እንደሚወዱ የገለጹት  እኒሁ እናት፤ በተለይ ለእርሳቸውና ልጆቻቸው መንግሥት  ማረፊያ ቤት እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል፡፡

 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 1577 times