Monday, 11 September 2023 00:00

የሙጋቤ ትዝታ

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

‹‹Who trained Mandela?›› የሚል ድምጽ ከተሌቪዢናችን እንብርት ወደ ጆሮአችን ይተምማል። አባቴ ሙሉ ሰውነቱ ጆሮ ብቻ ሆኖ ጉባኤውን በተመስጦ እየተከታተለ ነበር፤ አባቴ ፈገግ ብሏል።    
‹‹Emperor Hailesillasie›› ጠያቂው መለሰ።
አባቴ በድጋሚ ፈገግ አለ።  
*  *  *
በተሌቪዢናችን እየተሰራጨ የነበረው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ነበር። አባቴ እየሳቀ ይከታተላል፤ እኔ ግን ምንም አልገባኝም። ለመሆኑ የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የሚያስቅ ነገር አለው እንዴ?
ደግሞ መሪዎች ምናቸው ያስስቃል?
በተሌቪዢኑ ውስጥ ከሚታዩ ትዕይንቶች መካከል፣ የኢትዮጵያ ዜግነት ቢኖራቸው መቄዶኒያ መግባት የነበረባቸውና ልክ እንደ ዳውድ ኢብሳ የደመና ቁራሽ የመሰለ ጸጉር ያደላቸው አዛውንት፣ የዝምባቢዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የሚያሳዩት ነገር ቀልቤን ሳይስበው አልቀረም።
እርጅና እንደ ጋኔን የሚፈታተናቸው ሮበርት ሙጋቤ፣ በቻይና ሠራሹ የጉባኤ አዳራሽ ውስጥ በአፍሪካውያን ገዢዎች አንደበት የሚባለውን ጅኒ-ቁልቋል ችላ ብለው እንቅልፋቸውን ይለጥጣሉ።
ምናልባት የበሉት ቁርስ ከሰውነታቸው ተስማምቶ እንቅልፍ የለቀቀባቸው እንደሆነስ ብዬ ገመትኩ። ግን፣ ዝም ብዬ ሳስበው ሙጋቤ የአዲሳባን ቁርስ የሚወድዱ ይመስለኛል።    
እንግዲህ እኒህ ጌኛ በቁርስ ሰዓት ሦስት ወይም አራት ጣባ ክትፎ ከሰለቀጡ በኋላ በእላዩ ላይ አንድ ጠርሙስ አምቦ ውኃ ቸልሰው ሲያበቁ፣ በአቅራቢያቸው የሚልሞሰሞሰውን አስተናጋጅ አናጥበው…
‹‹የቀመስኩት ቁርስ ተስማምቶኛል፤ ነገር ግን መጠጡ አስጋሳኝ… ምንድነው እሱ?›› ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ።
አስተናጋጁ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ ገንዞ…
‹‹የእኛው ምርት፣ አምቦ ውኃ ነው›› ብሎ ይመልሳል።
ሙጋቤ ይንጠረበባሉ፤ ‹‹አምቦ ውኃ ነው አልከኝ?... ወለጋ ወይም ጅማ ውኃ አይሻልም?›› ብለው ከአስተናጋጁ ምላሽ ሳይጠባበቁ ያፈተልኩ ይሆናል።  
በመሃል እናቴ ጥሞናውን ሰበረች…
‹‹አዪ እኒህ አዛውንት፣ እንዲህ በእንቅልፍ የሚዳፉት ሮንድ አድረው መሆን አለበት›› አለች።
‹‹ምን ነካሽ? ሰውዬው እኮ የዝምባቢዌ ፕሬዚዳንት ናቸው፤ ጓድ መንጌን የሸሸጉ ባለዎረታ›› አባቴ መለሰ።
‹‹ፕሬዚዳንት እንደሆኑስ፣ ሕዝቡን መጠበቅ የለባቸውም?››
‹‹ሕዝቡን የሚጠብቀውማ እርሱ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው!››
ሙጋቤ ግን አሁንም ተግተው እንዳሸለቡ ነው። ሰውዬው በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ውስጥ ፍሬ ያለው ነገር ባይሸምቱም፣ እንቅልፋቸው አልተስተጓጎለም። እና ለምን ሲባል ሁለት ያጣሉ?
ከመተኛት ጎን ለጎን አውሮፓውያኑን የሚያሸማቅቁበትን የስድብ ዶፍ የሚያሰላስሉ ይመስለኛል። ነገር ግን በሰውነታቸው ላይ ጋቢ ጣል አላደረጉም። ምክንያቱ ደግሞ የመፀዳጃ ቤት ሶፍትና ጋቢ በመልክ ስለሚመሳሰሉ ተፀይፈው ይሆናል።
*  *  *
ከተለቪዢናችን ውስጥ ለሚሰነዘረው ጥያቄ፤ ‹‹Emperor Hailesillasie›› የሚል ምላሽ ብቻ ይሰጥበታል። አባቴም የማይነጥፍ ፈገግታውን እያሳየ ይከታተላል።
እኔ ግን የጥፍር ቁራጭ ያህል አልበገርም ነበር። ወላ ተጠየቀ አልተጠየቀ ምን ሊደንቀኝ? ደግሞ፣ ምላሽ ቢሰጥ፣ ባይሰጥ ምንም አያገባኝም። ከሙጋቤ ውጭ ወደ ውጭ።
እናቴ በተደጋጋሚ፤ ‹‹Emperor Hailesillasie›› ብቻ የሚል ማሳረጊያ ስትሰማ ግር ያላትን ጠየቀች…
‹‹እኔ የምለው፣ አሜን ማለት በእንግልዚ አፍ ‹Emperor Hailesillasie› ማለት ኖሯል እንዴ?›› አለች።
አባቴ አሁንም ሳቀ፤ ነገር ግን በስብሰባው ይሁን በእናቴ ጥያቄ ተገርሞ አልገባኝም ነበር።
ጋሽ ማንዴላን ማንም ያሰልጥን ማን፣ እኔ ግን ለማወቅ ምን ገድዶኝ? እንግዲህ፣ እኔ እስከማውቀው ማንዴላ ኮልፌ ሰልጥነው አገራቸው ተመሙ፤ እኒህ ዕድለ-ቢስ። ብዙ ሳይቆዩ በአንገታቸው ተይዘው ጀሜ ተወረወሩ። እዚያው ሃያ ሰባት ዓመት የተባይ መናኃሪያ ሆነው አረፉት።
ቁንጫና ቅጫም የዘለዓለም ቤታቸውን ቀለሱባቸው። አሃ! ደቡብ አፍሪካ በተባለ አገር ቁንጫና ቅጫም ይኖር ይሆን? ቁንጫና ቅጫም የእኛ ብቻ መስለውኝ። ቢሆንም፣ ቁንጫና ቅጫም በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ወህኒ ቤቶች ውስጥ አይኖሩም ለማለት አልደፍርም። ትንሽ ሲቆይ መልሰው ‹‹የነጻነት አባት›› በማለት አሞካሹት። ‹‹ወንጀለኛ›› በማለት የረገሙት ነጮች ተቀልብሰው ‹‹የነጻነት አባት›› እያሉ ሸለሙት፤ ይኼ ክስተት ቁማር አይደለምን? ኮንነው ሲያበቁ ወዲያው መካብ አንዳች ድብቅ ሴራ የተቀባ እንደሆን መጠርጠር ተገቢ አይሆንም?
ምን ዶለኝ? እኔ የምወደው ሙጋቤን ብቻ ነው። ከምንም በላይ እንቅልፋቸው ያስቀናኛል። ቆይ - ቆይ፣ ዝምባቢዌ ውስጥ ያን ያህል የሚያሳስብ ችግር የሌለ እንደሆነስ? ደግሞ ኑሮ እስካልተወደደ ድረስ  በሰፊው የሚያሳስብ ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም። በሀሳብ የመብሰልሰላችን ዋንኛ ምክንያት ኑሮ ጥብስ መሆኑ እንጂ።
አባቴ ሰማ ሰማና…
‹‹ማሰልጠኑ ላይ እንጂ የሰለጠነ ማፍራትን መች ተካናችሁበትና?›› ብሎ አማረረ።
ከንግግሩ ‹ይህቺ አገር የሚያስፈልጋት ሕግ አስከባሪ ሳይሆን ሕግ አክባሪ ብቻ ነው› ማለቱ እንደሆነ ቀዳሁ። በእርግጥ ማሰልጠኛና አሰልጣኝ በአገራችን ተራኩተዋል። ማሰልጠኛውማ በእያንዳንዱ ሰው ደጃፍ መተከል ሲቀረው፣ አሰልጣኝ በበኩሉ ከሰልጣኙ ቁጥር በላይ ሆኗል።
‹‹አሰልጣኝስ መች ሰለጠነና!›› የእናቴ ጥያቄ ነው።
*  *  *
ዜናውን እየተከታተልን ሳለ፣ የአባቴ የሥራ ባልደረባና ከፈጣሪ በታች የቤተሰባችን የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ሆኖ የተሾመው፣ አስተማሪው ጎረቤታችን ደማቅ ሠላምታ ሰጥቶ ገባ። አባቴ፣ ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ከፊል ትኩረቱን እንደሰጠ በቀሪው ትኩረት ደግሞ ባልደረባውን አጎብድዶ ተቀበለ።
‹‹እንዴት ነው ነገሩ! ሰዎቹ የምሣ ረፍት እንኳን የላቸውም ማለት ነው?›› አለ ወኪልና ጎረቤታችን፣ ገና ከመግባቱ።
ተደብቷል ማለት ነው። እኔም የሙጋቤ ነገር ሆኖብኝ እንጂ ስብሰባውን ከምከታተል ሁለትና ሦስት ሽንፍላ ባጥብ በወደድኩ።
አባቴ መከተ…
‹‹ምሣ ምን ይሠራላቸዋል? እኛን በምሣሌ ያድክሙን እንጂ!›› ብሎ አረፈ።
በወንጌል መዝጊያ አሜን እንደሚባለው በዚህ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እስከ ምሣ ሰዓት ድረስ ‹‹Emperor Hailesillasie›› የሚል ምላሽ ብቻ ለጠቀ።
*  *  *
ወዲያው፣ ስለ ንጉሠ-ነገሥት ኃይለስላሴ ማወቅ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። የነበረኝ ኩርማን ግንዛቤ እንደማያወላዳኝ አጥብቄ ሳውቅ በእራሴ፣ በተለይ በእንዝኅላልነቴ ላይ እያነጣጠርኩ ተከዝሁ።     
ታናሽ ወንድሜ እንኳን በአቅሙ የንጉሡ ስዕል የታተመበትን ቲ-ሸርት ይለብስ እንደነበር አልዘነጋሁም። እርሱ ቢወዳቸውም ምንም አልጠረጥርም ነበር። ግን ዛሬ ገድላቸው ሲወሳ ሰማሁ። እ-ሺ ንጉሠ-ነገሥቱ አባባ ማንዴላን ያሰልጥኗቸው፣ ደግ፤ ለምን እኛንም አላሰለጠኑም ነበር? ስልጠናቸው ማፈግፈግን ያካትት ነበርን! ጃንሆይ ብልጥና ጮሌ ነበሩ፤ ጣሊያን አፈር ጎርሶ፣ አፈር ሲያጎርሰን የውጊያውን መላ ጀባ ካሉን በኋላ ጥለውን እንግሊዝ እብስ አሉ። ተእንግሊዝ እግር ለመውደቅ ነበር የሸሹት። ወዲህ ደግሞ፣ ከሶልዳቶ በተተኮሰ ሰናዲር ክልትው ቢሉ ማን ያመለክትልን ነበር?  
ይህንን ሳስብ ቅር አለኝ። ተናጋሪው ሰው፤ ‹‹Who did exile to Britain to fight Fascist?›› እያለ ባለመጠየቁ በጣም ተበሳጨሁ። ከዚያ ጸጉሬን እየነጨሁ ስብሰባውን እከታተላለሁ።
*  *  *
አሁንም እናቴ ጠየቀች…
‹‹እንግዲህ የመጻሕፉን ቃል የሻሩ ሰዎች እኛንም ላይሽሩ ነው?››



Read 775 times