Tuesday, 12 September 2023 19:54

“የማኅበራዊ ሚድያውን” የሚያሳምር መፍትሔ አለ? የአገራችን ችግርም እንደዚያው ነው::

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

በገዢው ፓርቲ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ነው። ጠቅላላ ሐሳቦችንና ወቅታዊ ጉዳዮችን በ35 ገጾች አቅርቧል። የማወያያ ሰነድ እንደሆነ በመጀመሪያው ገጽና በሽፋኑ ላይ ተገልጿል።
ሁሉም የፓርቲው አመራሮችና አባላት እንዲነጋገሩበት ብቻ አይደለም። በመላ ሀገሪቱ  ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር “ውይይት ለማካሄድ የተዘጋጀ ሰነድ ነው” ይላል- (ገጽ 1 መጀመሪያው ዓረፍተ ነገር)።
ሰነዱ፣ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር በርካታ መንስኤዎችን ይዘረዝራል። ከባዱ የፖለቲካ ችግርና ትልቁ መንስኤ ግን የትርከት ስህተት  እንደሆነ ይጠቅሳል።  ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ጋር የተያያዙ የፖለቲካ አደጋዎች፣ ለመፍትሔ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆኑም ይጠቁማል።
እንግዲህ… የትርክት ወይም የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ጉዳይ ድብቅ ምስጢሮች አይደሉም። በሌላ አነጋገር የአገሪቱ  ዋና ዋና የፖለቲካ ፈተናዎችና አደጋዎች በይፋ የሚታወቁ ነባር ችግሮች እንደሆኑ ሰነዱ ይገልጻል።  የሰነዱ ይዘት አቀራረብ፣ የሐሳቦቹ ክብደትና ጉድለት፣ በድጋፍም ይሁን በወቀሳ፣ ተጨማሪ ሀሳቦችን መለዋወጥ ቢቻል መልካም ነበር።
በይፋ የተለቀቀ በሰፊው ለሰው እንዲዳረስ የታሰበ ሰነድ ስለሆነ፣ ብዙ ሰው ደጋፊም ይን ተቃዋሚ ያን ያህልም ትኩረት ላይሰጠው ይችላል።
“ምስጢራዊ ሰነድ “የሚል ጽሑፍ፣ “ጥብቅ ምስጢር” የሚል ማኅተም ቢያይ ይመርጣል ብዙ ሰው። ለምን?
የአገር ችግሮችና አደጋዎች ውስብስብ ናቸው። የአገርና የታሪክ፣ የፖለቲካና የመንግሥት እውነተኛ መዘውር እጅግ ረቂቅ ምስጢር ይመስላቸዋል- ለብዙ ሰዎች። ጥልቅ ዋሻ ውስጥ ፈልፍለው አስሰው ድብቁን የፖለቲካ መዘውር ፈልቅቀው ለማየት ይጠብቃሉ።
በይፋ የታወጀና ተገልጦ የታየ ፖለቲካስ? እንደ ሽፋን እንደ ማስመሰያ ወግ ይቆጥሩታል። እውነተኛው የፖለቲካ ሞተርና መዘውር ድብቅና ስውር እንደሆነ ያምናሉ። ከግድግዳ የወፈረ የብረት ካዝና ውስጥ በደርዘን ቁልፎች ተዘግቶበት ቀን ከሌት በጥበቃ የተከበበና የተደበቀ አንዳች ፖለቲካ መዘውር ይኖራል ብለው ይገምታሉ።
በእርግጥ ቅዠት በበዛበት የፖለቲካ ዓለም ውስጥ፣አንዳንዴ አስገራሚና አስቂኝ ምስጢሮች መኖራቸው አያጠራጥርም።
ነገር ግን ሥውር የፖለቲካ መዘውሮችን ፈልፍለው ለማግኘት የሚመኙ ሰዎች የፈለጉትን የማየት ዕድል አያገኙም። ዕድለቢስነት አይደለም። የፖለቲካ ምስጢር ከአቅማቸው በላይ ስለረቀቀባቸው፣ ወይም በነሱ ስንፍናና የድክመት አይደለም።
ስውር ፖለቲካ ሞተር ወይም ድብቅ መዘውር አለመኖሩ ነው ተፈልጎ አለመገኘቱ።
ኢህአዴግ ሲፍረከረክ ታስታውሳላችሁ። የድብቅ ምስጢሮች ጎተራ ተበርግዶ ውስጡንና ጉዱን ለመጀመሪያ ጊዜ እናያለን ብለው የጠበቁ ሰዎች ብዙ ናቸው። የጠበቁትን አላገኙም።
በደርግ ውድቀት ማግስት ተዘርዝሮ የማያልቅ የምስጢሮች ክምር ላይ ወጥተው እየገመሱ በይፋ ማሳየት የሚችሉ፣ እየናዱ የሚዘረግፉ የመሰላቸው ሰዎችም፣ እንደ ገመቱት አልሆነላቸውም። የፖለቲካ ዋና እንዝርት፣ ትልቅ የሚስጥራት ቁልፍ አላገኙም። የሚስጢር ቅራቅንቦ ነበር የጠበቃቸው።
አዎ፣ ብዙ ጥቃቅንና ዝርዝር ምስጢሮች ይኖራሉ። እገሌ ምን ተናገረ፣ እከሌ ማንን ከሠሠ? ማን ላይ ፈረደ? የባለስልጣናት ቁርቁሶችን የሚያሳዩ ቅንጥብጣቢ የምስጢር መረጃዎችን ልናገኝ እንችላለን።
ነገር ግን ስውር የፖለቲካ መዘውሮች የትም መቼም አታገኙም።
የፖለቲካ ዋና መዘውሮች በጭራሽ የሉም ለማለት አይደለም። መኖርማ አሉ። ነገር ግን ሥውር አይደሉም። ካዝና ውስጥ የተቆለፈባቸው ምስጢሮች አይደሉም- የፖለቲካ መዘውሮችና ሞተሮች።
አንድ የፖለቲካ ጉዳይ ድብቅ ምስጢር ከሆነ፣ የፖለቲካ መዘውር አይደለም።
ሀገርን ዕለት በዕለት ለማሽከርከርና ሕዝብን ለመምራት የሚውተረተር የፖለቲካ መዘውር፣ እንኳን በድብቅ በይፋም ጉዞው ቀላል አይሆንለትም። በብርቱ ካልተፍጨረጨረ በስተቀር የፖለቲካ መዘውር ተቀናቃኞች ብዙ ናቸው፡፡ በልጦ ለመገኘትና የብዙዎችን ዐይን ለመሳብ  ይሽቀዳደማል። የዕለት ወሬ እንዲሆን ይፈልጋል።
የፖለቲካ መዘውሩ ከአደባባይ እንዳይርቅ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሁሉ ገንኖ ቢታይለት ይወዳል። ብዙ ሰባኪ፣ ብዙ ፕሮፓጋዳ እንከማሰማራት ድረስ ፓርቲዎች ብዙ የሚደክሙት መዘውራቸው ገንኖ እንዲታይና ያለ ብዙ ተቀናቃኝ ሀገሪቱን ማሽከረክር ስለሚፈልጉ ነው።
ምን አለፋችሁ!
የፖለቲካ መዘውርና ሞተር፣ የምስጢርና የሥውር ተቃራኒ ናቸው።
በእርግጥ፣ ለጥቂት ቀናት፣ ቢበዛ ለጥቂት ወራት ተደብቆ የሚቆይ ሐሳብና ዕቅድ ይኖራል። ግን በይፋ እስኪታወጅ ድረስ ብቻ ነው። የፖለቲካ መዘውር በዐዋጅ በነጋሪት ነው የሚንቀሳቀሰው።
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንደ ዐቅማቸው ይጣጣራሉ። ሰልፍ ይጠራሉ። በዝተው ለመታየት  ወደአደባባይ ይወጣሉ። በመግለጫ ያስነግራሉ። ዕወቁኝ እያሉ ይጮኻሉ። ባጭሩ የፖለቲካ መዘውራቸውን ለማሳየትና ለማነቃነቅ ይሞክራሉ።
ይህ ሁሉ አልሳካ ሲላቸው፣መንግስት የሚያሳድዳቸው ከሆነ የፓርቲ መሪዎችና አባላት ራሳቸውን ለመሰወር ይሞክራሉ፤ ወደ በረኻ ይወጣሉ። ወደ ዋሻ ይገባሉ። ነገር ግን፣ ድምፃቸው እንዳይጠፋ የማይሞክሩት መንገድ የለም። መግለጫ ይጽፋሉ። በበራሪ ወረቀት  አሳትመው ይበትናሉ። በሬድዮ ያወራሉ።
ዋና ሐሳባቸውንና አላማቸውን በስውር ደብቀው የማቆየት ቅንጣት ፍላጎት የላቸውም። በተቃራኒው  “እንዳንነጋገር መንግስት ያፍነናል” ይላሉ፤ ባገኙት ቀዳዳ ይጮኻሉ።
ታዲያ ለምንድነው ብዙ ሰው አንዳች ስውር የፖለቲካ መዘውር ለማግኘት የሚመኘው? ራሳቸውን ለማካበድ የሚሞክሩ ሰዎች፣ ውስጥ አዋቂ ሆነው ለመታየት ይፈልጋሉ፡፡ የጎረቤት ምስጢር በማወቅና በማጋለጥ አንዳች የበላይነት ስሜት የሚያገኙ ይመስላቸዋል፡፡
የመንግስትን ምስጢር ለማግኘት ቢጓጉ ታዲያ ምን ይገርማል? የባለስልጣንነት ስሜት ለመጎናፀፍ ይሞክራሉ፡፡
 ውስጥ አዋቂ ነኝ፣ የመንግስት ቤተኛ ነኝ የሚል ስሜት ያገኛል፡፡
አልያም፣ “ምስጢር የሚያወጣ ጀግና፣ የተሰወረውን የሚያጋልጥ ብልሀተኛ ነኝ” ብሎ ያስባል፣ ወይም ያስመስላል፡፡
አሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ?
የሀገሩን ሁኔታ ለማወቅና የታሪክ አቅጣጫውን ለመገንዘብ የሚፈልግ ብዙ ሰው፣ ምስጢር ለማነፍነፍ ጊዜውን በስንቱ ያባክናል፡፡
አንዳች ስውር የፖለቲካ ቁልፍ ለማግኘት ሲጠብቅ፣ በአደባባይ በገሀድ የሚታየውን መልካም እድልም ሆነ ክፉ አደጋ በቅጡ መመልከት ያቅተዋል፡፡ ፖለቲካውና መዘውሩ ታሪክና ጅረቱ ከፊታቸው በግላጭ ሲሽከረከር ወይም ሲላተም፣ ሲጎርፍና ሲንጠፈጠፍ፣ ሲጠራና ሲደፈርስ እያየም እንኳ፣ ልብ ብሎ ማገናዘብ ይሳነዋል፡፡ በይፋ የተነገረና በአደባባይ የታየ የፖለቲካ ሀሳብና ውሳኔ፣… እንደ ዋና ቁምነገር አይቆጥሩትም። እንደ ጭንብል እንደ ሽፋን ሆኖ እየታያቸው፣ ብዙም ትኩረት አይሰጡትም፡፡
እሺ፣… አንዳንዴ የመንግሥት ምስጢሮችና ድብቅ የፖለቲካ መረጃዎች አስገራሚ ወሬ ይኖራቸዋል፡፡ በደሎችንና ምዝበራዎችን የሚያሳዩ መረጃዎች ማግኘት ይቻል ይሆናል። ይህንንም ግን እውነተኛና የተረጋገጠ መረጃ ነው ብሎ ማመን ያስቸግራል። ባለስልጣናት እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ከተቀናቃኝነት ስሜት የተጻጻፏቸው ጭፍን ክሶች ሊሆኑ ይችላሉ።
እንዲያም ሆኖ፣ የፖለቲካ መሪዎች የእርስ በርስ ሽኩቻና ድራማ ለብዙ ሰዎች ማራኪ ትረካ ይሆንላቸዋል። ቤተመንግስትን እንደ ጎረቤት መቁጠር ቀላል እድል አይደለም፡፡ ቁጭ ብለን ቤተመንግስት ላይ ሀሜት ስናወራ ቤተኛ እንደመሆን ነው። የሲአይኤና የሞሳድ ልዩ ቢሮዎች ውስጥ እንደልብ የምንመላለስ፣ የመረጃዎቻቸው ቁልፍ በእጃችን የገባ ይመስል ስለ ድብቅ ሴራዎች ስናወራ ራሳችንን እጅግ ከፍ ለማድረግ ይጠቅመናል።
ነገር ግን የሀገርን ሁኔታና የፖለቲካውን አዝማሚያ ለመገንዘብ እንዳንችል ዓይናችንን ይጋርድብናል፡፡
የሀገር የፖለቲካ ችግሮችና ተስፋዎች፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችና የወደፊት አዝማሚያዎች፣… የፖለቲካ ሞተሮችና መዘውሮች… ድብቅ ምስጢሮች አይደሉም። ፓርቲዎች በይፋ ባዘጋጇቸው የፖሊሲናና የዓላማ ሰነዶች፣ ፖለቲከኞች በአደባባይ የሚያውጁት ሐሳብ፣ የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶችና መግለጫዎች ናቸው የፖለቲካ መዘውሮቻቸው። በእርግጥ እውነትን ሐሰት ትክክልና ስህተትን መለየት ትልቅ ፈተና ነው።  ከብዛቱ የተነሳ ሁሉንም አገናዝቦና አንጥሮ መጨበጥ ያስቸግራል። ግን ምስጢር አይደለም።
ይህን ከማህበራዊ ሚዲያ ፖለቲካ ጋር ማነጻጸር ይቻላል። ብዙ ሰው ይናደዳል፤ ይበሳጫል፤ ይጨነቃል፤ ያሳስበዋል። የኢንተርኔት ፖለቲካው በእርግጥም እንደ ሀገር ፖለቲካው እጅግ ውስብስብ ነው።
ግን በአንዳች ድብቅ ምስጢር፣ በአንዳች ስውር ቁልፍ አማካኝነት የኢንተርኔት ፖለቲካውን አብጠርጥሮ ማወቅና እንዲያምር አድርጎ ማስተካከል ይቻላል ብለን እናስባን?
በጣም ከባድ እንደሆነ መረዳት አያቅተንም። ብዙ ሐሳብና ልፋት ይጠይቃል።
የሀገራችን ፖለቲካም እንደዚያው። በገሀድ የሚታዩ ብዙ ችግሮች ላይ ብናተኩርና የመፍትሔ ሐሣቦችን ለማፍለቅ ብንሞክር ይሻላል። አለበለዚያ አደጋው ከምንገምተው በላይ እጅግ የከፋ ይሆናል።

Read 430 times