Sunday, 17 September 2023 21:07

‘እ.ኤ.አ በ2030 ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ለመግታት...’

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

እንኳን ለ2016 ዓ.ም አደረሳችሁ! አዲሱ ዓመት የሰላም እና የጤና እንዲሆን የላንቺ እና ላንተ ምኞት ነው።
“እ.ኤ.አ በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስ እንደ ማንኛውም በሽታ ይሆናል”
በጤና ሚንስቴር የኤችአይቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ ፍቃዱ ያደታ
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ ኤድስ ወረርሽኝ በተነሳበት በመጀመሪያ ወቅት ከ65 እስከ 113 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል። ከዚህ ውስጥም ከ32 እስከ 51 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2022 ከ33 እስከ 45 ሚሊዮን ሰዎች (በአማካይ 39 ሚሊዪን ሰዎች) ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ተረጋግጧል። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የኤችአይቪኤድስ ወረርሽኝን ለመቅረፍ ትልቅ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በጤና ሚንስቴር የኤችአይቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ፍቃዱ ያደታ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ስርጭቱ ቀንሷል። በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተደረገ ጥናት መሰረት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ከ1 በመቶ በታች መሆኑ ተረጋግጧል። ነገር ግን በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከ3 በመቶ በላይ ስርጭት መኖሩን መሪ ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። ስርጭቱ በይበልጥ ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች መካከል ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ይጠቀሳሉ። እንዲሁም ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በይበልጥ የቫይረሱ ተጠቂ ናቸው። በተጨማሪም በይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ አደንዛዥ እፅ የሚጠቀሙ እና ተንቀሳቃሽ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ተጠቃሽ ናቸው።
እ.ኤ.አ እስከ በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘90-90-90’ በሚል 90ከመቶ የቫይረስ ተጠቂዎችን የመለየት፣ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ደግሞ 90 በመቶ የሚሆኑትን ህክምና የማስጀመር እና ህክምና ካገኙት ውስጥ 90 በመቶ ላይ በሽታው ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግ ስራ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። በተመሳሳይ እ.ኤ.አ እስከ 2025 ‘95-95-95’ በሚል ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች 95 በመቶዎቹን ወደ ምርመራ እንዲሄዱ፣ ወደ ምርመራ ከመጡት ደግሞ 95 በመቶዎቹን የፀረ-ኤች.አይ.ቪ ሕክምና በማስጀመር እንዲሁም ሕክምና ከጀመሩት መካከል 95 በመቶዎቹ በደማቸው የሚገኘውን የቫይረስ መጠን ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ለማሳካት ከታቀዱት እቅዶች መካከል ቫይረስ የተገኘባቸውን ሰዎች ህክምና የማስጀመር እንዲሁም ህክምና ከጀመሩት መካከል 95 በመቶ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የማድረግ ስራ ሙሉበሙሉ ማሳካት ችላለች። ነገር ግን 95 በመቶ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ለመለየት ከተያዘው እቅድ ማሳካት የተቻለው 86 በመቶ መሆኑን መሪ ስራ አስፈፃሚ ፈቀዱ ያደታ ተናግረዋል። ይህም ማለት በጥናት ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ ተብለው ከተገመቱ ከ610 ሺ ሰዎች መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ምርመራ አድርገው ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን አረጋግጠዋል። በ1 ዓመት ውስጥ (በየዓመቱ) ከ8ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ እንዳለ ይገመታል።
መሪ ስራ አስፈፃሚው እንደተናገሩት ጤና ሚንስቴር በሽታውን አስቀድሞ የመከላከል፣ ፀረ ኤች አይቪ ኤድስ መድሀኒት በሚወስዱ ሰዎች ላይ በሽታውን ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ አቅም የመቀነስ እና የቫይረሱ ተጠቂዎች ጤናማ አኗኗር እንዲኖሩ የማድረግ ስራ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም የኤችአይቪ ኤድስ ምርመራ በይበልጥ እየተሰጠ ያለው ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለሚገመቱ የህብረተሰብ ክፍሎች እና አካባቢዎች ነው። ነገር ግን እነዚህ ተጋላጭ እና ተጋላጭ ያልሆኑ ተብለው የሚገመቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጋላጭነታቸው የሚለዋወጥበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም ይህ አሰራር በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይ በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት አመቺ እንዳልሆነ መሪ ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።  
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ 39 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 37.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ከ15 እስከ 49 የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ናቸው። ይህ መረጃ እንደ አከባቢው የተለያየ ቢሆንም የአፍሪካ አህጉር ይበልጥ ተጠቂ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በአዲስ አበባ ነዋሪነቷን ያደረገችው ነፃነት ግርማ ሀሳባቸውን ካጋሩን ወጣቶች መካከል እንዷ ናት። ነፃነት የከፍተኛ ትምህርቷን ባጠናቀቀችበት ተቋም ውስጥ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ከፍተኛ ነበር። ይህም ለበሽታው ትኩረት እንድትሰጥ አደረጓታል። እራሷን ከበሽታው ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ታደርጋለች። “በትምህርት ቤት፣ በመገናኛ ብዙሀን እና በተለያዩ መድረኮች ስለበሽታው ይነገር የነበረበት ሁኔታ መቀዛቀዝ ወጣቶች በሽታውን ችላ እንዲሉ አድርጓል” በማለት ተናግራለች። በተመሳሳይ በበሽታው ላለመያዝ የሚደረግ ጥንቃቄ መቀዛቀዙን የተናገረው ሰገነት ብርሀኑ ነው። እንደ ሰገነት ንግግር በቅርበት የሚያውቃቸው ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው ስለበሽታው በድጋሚ እንዲያስብ አድርጎታል እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስርጭቱ እንደጠፋ ይሰማው ነበር። “ምንም እንኳን እየተዘነጋ ያለ ቢመስልም አሁንም በጣም የምጠነቀቀው እና የምሰጋው በሽታ ነው” ያለችው ደግሞ ወጣት ሳምራዊት ምንተስኖት ናት። እንደ ሳምራዊት ንግግር ወጣቶች ከግብረስጋ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ እየዘነጉ ይገኛሉ። ከግብረስጋ ግንኙነት በተጨማሪም እምብዛም የማስተላለፍ እድል እንዳላቸው የማይታሰብ የደም ንኪኪዎች ላይም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ነው ሳምራዊት የተናገረችው። ለዚህም እንደምሳሌ የጠቀሰውችው አንዲት ሴት ልብስ በምታጥብበት ወቅት ልብስ ላይ ከነበረ ደም ጋር ንክኪ በመፍጠሩ የቫይረሱ ተጠቂ መሆኗን ነው። ስለሆነም በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ግልፅነት እንዲኖራቸው እና ሁሉም ማህበረሰብ ደግሞ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚል መልዕክት አስተላልፋለች።
የቫይረሱ ተጠቂ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ አበባ በፍርዱ በበኩሏ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ መቀዛቀዙን ተናግራለች። “እኔ በዙሪያዬ ላሉ ሰዎች በጣም ለመጠንቀቅ እሞክራለው። ሌሎች ሰዎች የእኔን ስህተት እንዲደግሙት አልፈልግም። ነገር ግን ብዙዎች በሽታው እንደጠፋ የሚያስቡ ይመስላሉ” ብላለች። አክላም “በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ለሌሎች ጥንቃቄ እያደረጉ፣ መድሀኒቱን በአግባቡ እየወስዱ እና የሰውነት እንቅስቃሴ እያደረጉ ጤናማ ህይወት እንዲመሩ እመክራለው” በማለት ተናግራለች። ሌላኛው ቫይረሱ በደሙ የሚገኝ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ወጣት እንደተናገረው በሽታው ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግ ሀላፊነት የሁሉም ማህበረሰብ ነው።
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ እና በተያያዥ ምክንያቶች የ630 ሺህ ሰዎች ህይወት አልፏል። የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ2030 በዓለም አቀፉ ደረጃ የኤድስን ወረርሽኝ ለመግታት እቅድ መያዙን ገልፃል። በጤና ሚንስቴር የኤችአይቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ፍቃዱ ያደታ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ በ2030 ቫይረሱ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመግታት እየተሰራ ይገኛል። ይህም ማለት ኤችአይቪ ኤድስ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ እንደማንኛውም በሽታ በመደበኛ የህክምና አገልግሎት ውስጥ የሚገኝ ይሆናል። ስለሆነም ከ7 ዓመታት በኋላ በሽታው በተለየ መልኩ ጉዳት የማያደርስበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይፈልጋል።
“አደገኛ የሆነ የህብረተሰብ ጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል” በማለት በጤና ሚንስቴር የኤችአይቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ፍቃዱ ያደታ ተናግረዋል። እንደ መሪ ስራ አስፈፃሚው ንግግር ኤችአይቪ ኤድስ የህብረተሰብ ጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ በበሽታው አዲስ የመያዝ ምጣኔን እና ሞትን መቀነስ ያስፈልጋል። እንዲሁም የመገናኛ ብዙሀን፣ የእምነት ተቋማት፣ የመንግስት አካላት እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ለበሽታው ትኩረት የማይሰጡ ከሆነ እንደገና ወረርሺኝ የመሆን እድል ይኖረዋል። ስለሆነም ማህበረሰቡ በሽታው በደሙ መኖሩን ከማረጋገጥ ጀምሮ ቫይረሱ ሲገኝ መድሀኒቱን በአግባቡ እስከ መውሰድ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ርብርብ በማድረግ በሽታውን መግታት እና መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ መሪ ስራ አስፈፃሚው በማሳሰብ ተናግረዋል።

Read 862 times