Sunday, 17 September 2023 21:22

ያላረጀው ገጣሚ፥ በ‹‹እናርጅና እናውጋ›› ግጥሙ. . .

Written by  ይሥሐቅ እንድሪስ
Rate this item
(0 votes)

የተገለጠው ሳይገባን በፊት
ስውሩን ፈለግን ያውም በሌሊት።
(እናርጅና እናውጋ፤ ገጽ 61)
‹‹በአሥተርእዮ መንገድ››  ይለናል ጌራወቅ ጥላዬ፤ በ“እናርጅና እናውጋ”  መጽሐፉ  መግቢያ፡፡ አሥተርእዮ የሚለው ሲፈታ መገለጥ፣ መታየት የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፤ ‹‹በአሥተርእዮ መንገድ›› የሚለው ደሞ በመገለጥ፣ በመታየት መንገድ እንደማለት ነው። ታዲያ በመታየትና በመገለጥ መንገድ ምን አሳየን? ምንስ አስገለጠን? ይህን መልስ ፍለጋ  መጽሐፉን መግለጥ የግድ ነው።
“እናርጅና እናውጋ” የተመረቀው በሐገር ፍቅር ቴአትር ትንሿ አዳራሽ ሲሆን፤ በዕለቱም ነፍሳቸውን ይማርና ዘሪሁን አስፋው(ተባባሪ ፕሮፌሰር) በመጽሐፉ ዙሪያ ጠለቅ ያለ  ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡ እኔም መጽሐፉን ሸምቼና አስፈርሜ የመጽሐፍ መደርደሪያዬ ውስጥ አስቀመጥኩት። ከብዙ ወራት በኋላም ልቤ አሰኝቶት በጥንቃቄ ካስቀመጥኩብት አንስቼ  ገልጬ ማንበብ ጀመርኩ።
መጽሐፉ 120 ገጾች ሲኖሩት፣ 60 ግጥሞችንም የያዘ  ነው። ዘለግ ያለ ሸጋ መግቢያ ያለው የቃላት መፍቻም ያጠቃለለና እጥፋትም የጨመረ ነው።
የመጀመሪያው እጥፋትም እንዲህ ይላል፦
. . .ልጅ እያለሁ ዘወትር ጠዋት፣ ጠዋት ሲሰቀል፤ ማታ፣ ማታ ደግሞ ሲወርድ የማየውን ያገሬን ሰንደቅዓላማ ‹‹ሁሌ ወደ ላይ ከመስቀል፤ ሁሌ ወደ ታች ከማውረድ፤ ለምን አንዴ ሰቅለው አልያም ለምን አንዴ አውርደው አይገላገሉም?›› እል ነበር በልጅነት አእምሮዬ።  . . .ለካንስ ኢትዮጵያ በዘመኗ አንዴ ከፍ ስትል፤ አንዴ ደግሞ ዝቅ ስትል ኗሪ መሆኗን ማሳያ ነበር። ሰንደቁን ሠቃዩ ሆነ አውራጁ ውክልናው መሪ ሲሆን፤ ከፍና ዝቅ ሲል ዝማሬ የሚያቀርበው ህዝቡ ነው፤ የሚመሸውና የሚነጋው ወቅት ውክልናው ደግሞ በዘመኑ የሚፈጠረው የችግር መከራና የተድላ መኸር ነው። ሰንደቁ ተሰቅሎ የሚውለበለብበት ምሰሶ ደግሞ በየዘመናቱ የሚፈጠረውና የሚለዋወጠው የገዥው የአስተዳደራዊ ሥርዓት ነው። ሰንደቁ ከነመስቀያው ከፍና ዝቅ ሲል የጸናበት ቦታ ደግሞ በዘመኑ ያለው ዘመነኛ(ኗሪ) ለሀገር የከፈለበትና ያስከፈለበት የመሰዕዋት ሥፍራ ኑሯል ለካ።
‹‹አረንጓዴ - ልምላሜን፣ ቢጫው - ተስፋን፣ ቀዩ ደግሞ መስዋዕትነትን ይወክላል›› በሚል አስተምህሮ ብቻ ላደግን ይሄ ጥሩ አንደምታዊ አረዳድ ይመስለኛል።
በመቀጠልም ‹‹በአሥተርእዮ መንገድ›› በሚለው መግቢያ፣ የነጻ ህዝብን ሰብዕና፣ ባሕርይ፣ አኗኗርና አስተሳሰብ ያስቃኛል፣ ያሳያል፣ ያስዳስሳል። በእጥፋቱ ሰንደቅ የጀመረው ጌራ፤ ሀገርነትን ሲገልጽም እንዲህ ይላል፦
እንደመታደል ሀገርን እየኖሩ የሚያኖሯት ሀገር ናት፤ እንዳለመታደል ግን የማይኖራት ኗሪ ካለወግ የሚያወራት ናት። ሀገርነት ሲኖሩት የሚገባ፤ ሲያወሩት ልክ እንደ አፈ ታሪክ ግራ የሚያጋባ ነው። (ይልና አከል አድርጎ) ደሞም ሀገራዊነት ከማለት ባሻገር የማድረግ ውጤት ነውና ቅድሚያ ሀገሬው እንደ ሀገር መግባባት ካልቻለ፤ እንደሆነ መንደር፣ እንደሆነ ቀዬ፣ እንደሆነ ጎጥ ልንተዋወቅና  ልንተማመን አንችልም። ምክንያቱም ሀገራዊነት፦
ካለም አለማነስ
ጥል አለመቋረስ
ፍቅርን መጓረስ
ሰው ወዶ መጨረስ
ካምላክ በልብ መድረስ።-- በመሆኑ። (ገጽ 17 – 18)
“እናርጅና እናውጋ” 60 ያህል ግጥሞቹን የሚያስጀምረን ‹‹የዕድሜ ዘላለሜ›› በሚል በጎንደር ላይ በሚያጠነጥን  ግጥም ነው። ግጥሙ ጎንደርን በተመለከተ የቁጭት፣ የብስጭት፣ የመከፋት፣ የትዝታ እጦትን፣ ከክብር በታች የመገኘትን በአራራይ ትካዜ እያሳዘነ የሚያሳይ ነው። በእነዚህም ስሜቶች ውስጥ ሆኖ ግን ያሽሞነሙናታል፡፡
ጎንደር!
የጽድቄ ዓለም፣ ቅዱስ መንደር
ማኅሌት፣ ዜማ፣ ቃል ምሥክር
ሞት መሞቻው፤ ውብ መቃብር. . . (ገጽ21) ይላታል። እያለም ይቀጥላል።
ታዲያ ወዲህ እንዲህ ሲል ያቆለጳጰሳት ከተማ እንደ ታሪኳ፣ እንደ ቅርሷ፣ እንደ ገናንነቷ መገኘት ከሚገባት ከፍታ ላይና  ክብር ላይ ባለመገኘቷ እንዲሁም ልጆቿ ባህሏን፣ ቋንቋዋን፣ ለዛዋን፣ ወዘናዋን፣ ወጓን፣ ሥርዓቷን፣ ዕውቀት፣ ጥበቧን፣ ምግባሯን ሳያዛንፉ ማስቀጠል ተስኗቸው ዕለት ከዕለት ውድቀት፣ ቁልቁለትና  ማፍረሱን ቢያያዙት፤ ከመፎከርና ከመሸለል የተሻገረ ሥራ መሥራት ቢያቅታቸው ጎንደርን እንዲህ ይጠይቃል፦
ወይዘሪት እምዬ! መሆንሽ ምነውሳ?
ቀባሪ እንዳጣ ሬሳ፣ በሰው እንደተረሳ፤
ዳዋ እንደወረሰው እንደገበሬ ማሳ፤
ምላሱ ከላንቃው እንደተጣበቀ፣
ገላው እንደልብሱ በላዩ እንዳለቀ፣
በወንጭፍ ድንጋይ ምት እንደተሰበረ እንደበኩር እሸት፣
ሞት እንደተጸየፋት፤ ኑሮ እንዳቀለላት፤ ደካማ አሮጊት፣
ጎታታ፣ ዳተኛ፣ እንደጉፋያ ከብት፣
በሚታየኝ ኹነት፣ ይሁን ያንቺ ሕይወት? (ገጽ 21) ብሎ ይቀጥልና የግጥሙንም መቋጫ በእንባ መባባት ስንኝ፦
የዕድሜ ዘላለሜ. . .
ጎንደር! የለቤ ከተማ፤ እንዳልነበርሽ ያገር አምባ!
ምነው ዛሬ ሳይሽ እኔ፣ ውብ ዐይኖቼ አነቡ እምባ?  (ገጽ 23) በማለት በቁጭት ይቋጫል።
እንዲያው ‹‹የዕድሜ ዘላለሜ›› በሚለው ግጥም ሳልገልጽው የማላልፈው፣ ጌራ የልጅነቱ  ማኅደር ስለሆነችው ስለ ጎንደር ገጠመ እንጂ ግጥሙን በፍካሬ ካየነው ግን ለጎንደርና ስለ ጎንደር ብቻ የተገጠመ አይደለም። እንደ ሀገር ኢትዮጵያን እንዲሁም ከእያንዳንዳችን  የልጅነት  ከተሞች (ቦታዎች) ውድቀት ጋር በሀቅ የሚያገናኝ ግጥም ነው። ‹‹በጥምቀት ጠበል ቀን›› በሚለው ደግሞ ክብራቸውን።
ወትሮም ላገር ኅብረት፣ ባርማ ስለ አንድነት
ወትሮም ሰው ለመውደድ፣ ለማላመድ ጠላት
ጎንደሬ ነኝ ብለሽ አትገይም ወዳጅ
ኢትዮጵያን በማለት ትሞቻለሽ እንጂ፤
እስቲ አንቺን ልሣለም ጎንደር ያርባራቷ
ኢትዮጵያ አይደለች ያገርሽ ታቦቷ። (ገጽ 103)
ጌራ ፍቅር የነገሮች መደምደሚያ መሆን እንዳለበትና ሰው ሲበቃ ለአፍቃሪነት እንደሚበቃ ‹‹ያምና ሲደርስ ከርሞ›› በሚለው ግጥሙ እንዲህ ይላል፦
አልፋው ሌላ ቢሆን፤ ሰው ሁሉ መነሻው
ግን ፍቅር ካልሆነ፥ ኦሜጋ መድረሻው
እንኳን ለመድረሻው፣ አልተነሳም ገና፥ ሊሄድ ከመነሻው። (ገጽ 71)
‹‹በሴት ፍጹም አቅም›› በሚለው ግጥም የመጨረሻ ስንኞችም፦
ከመቃብር አልጋ እንደሚያነቃ ሙታን
እንዳምላክ በፍቅር አውቃለሁ በማመን
ፍቅርም እንደ አምላክ የሚሳነው የለም፤
ከዓለት ያበቅላል እንኳን ከማህጸን። (ገጽ 55) ሲል የፍቅርን ፍጹም ሃያልነት ይገልጻል፡፡
‹‹የተባለው›› በሚለው ግጥሙ ደግሞ፦
የነበረው!
እንደ መስኖ ሐሳብ ጠልፎ
በቃል ቋንቋ ቅኔ ዘርፎ፤
በእምነት ሲጓዝ - ተሥፋ ታቅፎ
ስለ መውደድ፤ እውቀት ቢጥል - ድንገት ሰንፎ
ከመድረሻው ያልደረሰው፥ ተባለ እሱ ተደናቅፎ።
አውቆ - ንቆ፤ እውቀት ሰቅሎ - በሸምቆቆ
የረገፈው እንደ ቅጠል፣ የቀለለው ከሸምበቆ
የተባለው ቀረ ወድቆ፤ የተባለው ቀረ ደርቆ።
እሱ - ራሱ ወዲህ ግና
አገርሽቶ ከእንደገና፣
ከሰኔ እንኮይ አጎምርቶ፣
እንደ ውልብኝ ቀድሞ አሽቶ፤
ደርሦ- በቅቶ፤ ርቆ - መጥቆ፤ ረቆ - ልቆ
ከፍቅር ላይ ሲገኝ አልፎ፤ የወደቀው ታዬ ጸድቆ። (ገጽ 80)
ጽድቅና ኩነኔ በወደቅንበት ነገሮች አይጠፉም፤ ታዲያ ጌራ በኩነኔ ከወደቀ ይልቅ በፍቅር የወደቀ እንደሚጽድቅ፣ ከቡቃያ ጋር አመሳስሎ፣ በፍቅር የፍቅር ጻድቅ መሆን እንደሚቻል ያሳያል።
የሰው ልጅ  ሁሉ አነሰም በዛም የትዝታ ባለቤት ነውና፣ ትዝታም  መነሳቱ አልቀረም።
 ‹‹ወዬው ሆይ ትዝታ›› የሚለውን ግጥሙን  እንይለት፦
ልክ እንደ መዋደድ፣ መፋቀርን ፈቅዶ
ደሞ እንደመጋባት፣ ልጅን መውለድ ወዶ
ሊኖር ያሰበን ሰው፤ ሆኖ ሰው እንደ ሰዉ
ጊዜ ቢለያየው ____ ናፍቆት ባይመልሰው
ፍቅር የሞላውን ትዝታ አጎደለው። (ገጽ 91)  
የገጣሚ  ጌራወርቅ ጥላዬን “እናርጅና እናውጋ” የግጥም መድበል ከቦታ ውስንነት አንጻር በስሱ  ለመቃኘት ሞክሬአለሁ፡፡ በዚህ  ሥራው ግሩምና ተስፋ የሚጣልበት ገጣሚ መሆኑን አስመስክሯል ብዬ አምናለሁ፡፡ በቀጣይ ሥራው የበለጠ ረቅቆና ልቆ እንደሚመጣም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡



Read 480 times