Saturday, 23 September 2023 21:20

“አያልቅበት” – ኤፍሬም!!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነው – ኤፍሬም እንዳለ። አለቀ። ከዚህ ውጪ ስለ እሱ ግላዊ ሕይወትና ማንነት፣ ጥረትና ልፋት በሕትመትና ብሮድካስት ሚዲያዎች ሲነገር ሰምቼ አላውቅም። የእሱም ፍላጎትም፣ ግድም አይመስለኝም፤ አደባባይ መውጣቱ። ደም ለመመለስ ቤቱን አቃጥሎ የሸፈተ ሰው፣ መልኩን አይደለም ጥላውን ሳያሳይ ጫካና ጥሻን ተከልሎ ወደ ዒላማው ጥይቱን እንደሚልከው ሁሉ፣ እሱም ካለበት ጥጋት ተሰትሮ በብዕር ከመተኮስ ውጪ በታይታ ሰውነቱ አይታወቅም።
ኤፍሬም ወደ ሰላሳ ለሚጠጉ ዓመታት – በእኔ ዕውቀት ከ”ፀደይ” መጽሔት ጀምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ምፀት - ለበስ ወጎችንና ጨዋታዎችን ሲያስኮመኩመን አሁን ድረስ አለ። ዘወትር ቅዳሜ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት “ጨዋታዎቹን” የሚያስነብብባትን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣን ባገላበጥኩና ጽሑፎቹን ባነበብኩ ቁጥር እጅጉን የምደመምበት ነገር ቢኖር የጨዋታዎቹ ለዛቸውን ጠብቀው መቆየታቸው፣ ዕይታዎቹና የሚያነሳቸው ጉዳዮች፣ እንዲሁም የብዕሩ ከዘመን ዘመን ሳትከሽፍ የኅብረተሰባችንን ጉዳዮች በራሱ በኅብረተሰቡ ወቅታዊው አስተሳሰብና አነጋገር እነሆ ማለቱ ነው። ትናንት አራዳ፣ ዛሬም አራዳ ነገም አራዳ እንደሆነ ስለመዝለቁ ያሳብቃሉ – ለወጉ ማዋዣነት ጣል የሚያደርጋቸው አስቂኝ ቀልዶችና ገጠመኞች።
ኤፍሬም፤ በ”ፀደይ” መጽሔት “እንጨዋወት አምድ”፣ “Ethiopian Herald” ጋዜጣ “Between you and me” አምድ ላይ በአምደኝነት  በ”The Sun” ጋዜጣ  ከአንጋፋ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ጋር በአዘጋጅነት፣ በ”ምዕራፍ” ጋዜጣ ከእነ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጋር በመሆን በዋና አዘጋጅነት፣ ካለፉት 17 ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ደግሞ  በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ አምደኛ ነው።
መጻሕፍትን ለንባብ በማብቃቱም ረገድ፤ እጅግ ተነባቢና ተወዳጅ የነበረውን የሮበርት ሉድለምን መጽሐፍ “ፍንጭ” በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅቷል። የቱርካዊውን አዚዝ ኔሲን “እራሴን አጠፋሁ” የተሰኘ መጽሐፍም በኤፍሬም እንዳለ ተተርጉሞ ለህትመት የበቃ ነው። እሱ ያዘጋጀውን “ቤርሙዳ ትርያንግል”  የተባለ መጽሐፍም ከብዙ ዓመታት በፊት ማንበቤም ትዝ ይለኛል። “የዘመን ዱካ” እና “ሕይወት በክር ጫፍ”  የተሰኙ ሥራዎችም አሉት። በተለያዩ መጽሔቶችና “እፍታ” መጽሐፍ ላይ የወጡ የራሱንና ትርጉም አጫጭር ልቦለዶችን ለአንባቢያን አበርክቷል። “የጉራ ሊቅ”ን ያስታውሷል። “እንግሊዘኛን በቀላሉ” የተባለች ለእንግሊዘኛ መማሪያነት የምታገለግል በኪስ የምትያዝ ታዋቂ መጽሐፍም ነበረችው።  ጋዜጣና መጽሔት ላይ ወጥተው የተነበቡ ሥራዎቹንም በመጽሐፍ መልክ አሳትሟቸዋል።
በኢትዮዽያ ሬድዮ “ቅዳሜ  መዝናኛ” እና በሸገር ሬድዮ “የጨዋታ” ፕሮግራም ላይ የተላለፉ ተከታታይ እና አጫጭር አዝናኝ ድራማዎችን በመድረስና በመተርጎም ለአድማጮች እንዲደርሱ አድርጓል። ተደንቆበታልም።  “ስካይ ፕሮሞሽን” የሚል የማስታወቂያ ድርጅት አቋቁሞ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደ ነበር አስታውሳለሁ – አሁን ይቀጥልበት አይቀጥልበት ባላውቅም።
አንዲት ሚጢጢ መጽሐፍ አበርክቶ ሰማይ ልንካ የሚል ውርንጫ ጸሐፊ በሞላበት ሀገር፣ ይህን ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ድምፁን አጥፍቶ ትልቅ ተግባር የከወነን ሰው አለማንሳት፣ አለማውሳት ትልቅ ሀፍረት ነው – ለሁሉም። ክብር ለሚገባው ሁሉ ክብር ይሁን፤ አበቃሁ!!!
ማሳሰቢያ:– ከኤፍሬም እንዳለ ሰብዕና፣ ሥራዎችና ጥረት አንፃር ይህ ልጥፍ ጽሑፍ 1% ያህል አይሰጠውም ከመቶው። ይሁን እንጂ ከእኔ በተሻለ ስለ እሱና ስራዎቹ የምታውቁ፣ በዚህች ቅንጭብ ጽሑፍ ላይ የታያችሁን ስህተት በእርማት፣ የቀረውን ደግሞ በአስተያየት ታሟሉታላችሁ ብዬ በማመን ነው እዚህ ያሰፈርኩት። ተሳትፎአችሁ ይጠበቃል!!!

Read 2745 times