Saturday, 07 October 2023 20:40

“ይቅርታ”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

(የአጭር አጭር ልብወለድ)

ፊልም ለማየት ከባለቤቴ ጋር የገባሁ ዕለት ነበር ይህን ስህተት የፈጸምኩት፡፡ ወገግ የማይለው አታካቹ ፊልም የሲኒማ ቤቱን ከላይ እታች ድረስ አጨላልሞታል፡፡ በዚህ ላይ ፊልሙ የማያስደስት ነበር፡፡ ድብርታም የሚሉት ዓይነት፡፡
ከሩቅ ባትሪውን በራ ጠፋ እያደረገ አይስክሬም የሚሸጠውን ሰውዬ ሳይ፣ ለእኔና ለዱቪ አይስክሬም ለመግዛት አሰብኩና ተነስቼ ሄድኩኝ፡፡ ስመለስ ድርሻውን ለባለቤቴ ስሰጠው እጄን አጥብቆ ያዘኝ፡፡
“እወድሃለሁ ፍቅሬ” አልኩና በጆሮው ሹክ አልኩት፡፡ በአይስክሬም በታጨቀው አፉ እየተንተባተበ፣ እሱም እንደሚያፈቅረኝ ነገረኝ፡፡
“እዚህ ተቀምጬ ይህን ቀፋፊ ፊልም ከማየት ይልቅ ከአንተ ጋር ቤት ብንሆን እንዴት ደስ ባለኝ---” ስለው እጆቹን በአንገቴ ዙሪያ አደረገና አቀፈኝ፡፡
አንዲት ሴት መተላለፊያ መንገዱን በእግሮቼ ስለዘጋሁባትና ማለፍ ስላልቻለች ነው መሰለኝ፤ “ይቅርታ --” አለችኝ “እህት ይቅርታሽንና-”  የጀመረችውን ንግግሯን ሳትቋጨው እንድታልፍ ብዬ እግሮቼን ሰብሰብ አደረግሁ፡፡ ነገር ግን ካለችበት ቦታ ነቅነቅ ሳትል አሁንም ዳግም “ይቅርታሽን” ማለቱን መረጠች፡፡ የአሁኑ አነጋገሯ  ግን ጠብ ያለሽ በዳቦ ይመስላል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ “እህት ይቅርታሽንና የተቀመጥሽው በመቀመጫዬ ላይ ነው” አለችና ጮኸች፡፡
ሴትዬዋ ተናግራ ስታበቃና ፊልሙ ሲጨርስ አንድ ሆነ፡፡
ወዲያው መብራቱ በራና ሁለት ወንበር መደዳዎች ከፊት ለፊቴ ሳይ፣ በጭንቀት “የት ቀረች” ብሎ አንገቱን አስሬ የሚያዞረውን የእኔውኑ ባለቤት ዱቪን አየሁት፡፡
ምንም እንኳን ስህተቱን የሰራሁት እኔ ብሆንም፣ አሁንም ቢሆን “ይቅርታ” ብላ የጮኸችብኝ ሴትዮ፣ ለባሏ የሰጠሁትን የአይስክሬም ዋጋ መክፈል አለባት እላለሁ፡፡
ደራሲ፡- ባርባራ ዬቪስ
ትርጉም፡- አስፋው ደገፉ

Read 806 times