Saturday, 07 October 2023 21:04

በትግራይ ክልል በጥቅምት ወር መጀመሪያ የሦስት ቀናት ክልላዊ ሀዘን ሊታወጅ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

በሰሜናዊው የአገሪቱ  ክፍል  በትግራይ ሀይሎችና በፌደራል መንግስቱ መካከል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት  ህይወታቸው ያለፉ ተዋጊዎችን ለመዘከር በትግራይ ክልል በጥቅምት ወር መጀመሪያ የሦስት ቀናት ሀዘን እንደሚታወጅ፣ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ጀኔራል ታደሠ ወረደ ሰሞኑን በክልሉ ለሚገኙ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  አስታውቀዋል።
በክልሉ ለሶስት ቀናት ይደረጋል የተባለው ክልላዊ የሀዘን ቀን የሚታወጀው በጦርነቱ ሳቢያ በክልሉ ተቋርጦ የነበረውና በመስከረም ወር መጨረሻ ይሰጣል የተባለው  የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች፣ ሰማዕታቱን ለመዘከር የህሊና ጸሎት ሥነስርአት እንደሚያከናወን ጀነራሉ ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ቀን የሰማዕታቱ ቤተሰቦች መርዶ እንደሚነገርና ከዚያም ቀጥሎ ያሉት ቀናት ክልላዊ የሀዘን ቀናት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
በመቀሌ ከተማ ባለፋት ቀናት በርካታ ወገኖች የልጆቻቸውን መርዶ እየተረዱ ሲሆን፤ ይህ ሁኔታም ስርዓትን ያልተከተለ መሆኑን ጀነራሉ ገልጸዋል።  አንዳንድ ቤተሰቦች ክብራቸውን በማይመጥን መልኩ የልጆቻቸውን መሰዋት እየተረዱ መሆኑን የጠቆሙት ጀነራሉ፤  የሰማዕታቱ ቤተሰቦች የመንግስትን ይፋዊ መርዶ እንዲጠብቁ አሳስበዋል ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ሰሞኑን በክልሉ ለሚገኙ ጋዜጠኞች  በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ የሰማዕታቱ ሙሉ ታሪክ ስነዳ መጠናቀቁን አመላክተዋል። ወላጆች ልጆቻችን የት አሉ ብለው እንዲጨነቁና እንዲጠይቁ አይገባም ያሉት ጀነራሉ፤  ጊዜያዊ አስተዳደሩ በራሱ ሁሉንም ነገር ግልጽ ያደርጋል ብለዋል።
በቅርቡ የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከመርዶ ጋር በተያያዘ የሰማዕታቱን ክብር በሚመጥን መልኩ እንደሚከናወን መግለጻቸውን  ይታወሳል። አቶ ጌታቸው በዚሁ መግለጫቸው፣  በርካታ ቁጥር ያላቸው  ሰማዕታት አሉን፣ እያንዳንዱ ሰማዕት የየት አካባቢ ተወላጅ መሆኑንና የት እንደተሰዋ የማጣራት እና የመመዝገብ ስራ  ያጠናቀቅነው ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ላይ  ነው ብለዋል።



Read 1681 times