Saturday, 07 October 2023 21:05

የ“ነገራ ነገር” ነገር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የደራሲ አብረሃም ዮሴፍ “ነገራ ነገር” የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ በቃ፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ አንተነህ ይግዛው፣ ስለ ግጥም መድበሉ ያሰፈራት አጭር ማስታወሻ፣ መድበሉን ለመተዋወቅ ድልድይ ትሆናለች፡፡ እነሆ፡-
“ነገር እንደ ቁስል ሌት ተቀን ውስጥ ውስጡን የሚነዘንዛት፣ ሃሳብ እንደ ወንፊት ነጋ ጠባ ሳይል የሚወዘውዛት፣ የሆነች ባይተዋር ነገር የገባት ነፍስ በሃሳብ ስትባትል፣ የሆነ ጥግ ይዛ ካባዘተችው ቃል ባል አዘቦት ሳትል፣ የስሜት ልቃቂት ያሳብ ዘሃ ስንኝ የሐረጋት ፈትል ነው የተሸመነው - “ነገራ ነገር”፡፡
“ከገጣሚው ነፍስ የጎደለች አንዲት ሴት አለች፤ ከጎኑ የተነደለች አንዲት ሽንቁር፡፡ ገጣሚው በዚያች ሽንቁር በኩል አጮልቆ አለምን የሚያይባት፤ እውነትን፣ ህይወትን፣ እምነትን፣ ውበትን… መላ ጽንፈ አለሙን የሚያስስባት የሚታዘብባት፣ የሚፈክርባት፣ የሚዘክርባት የነፍስ ኪታቡ ናት - “ነገራ ነገር”፡፡
“በየነገራ ነገሩ መሃል ያቺ ሴት አለች፡፡ ሄዳለች ቢላትም በሄደበት ሁሉ የምትከተለው፤ ትታኛለች ቢልም ትታ የማትተወው፣ በሄደበት ሁሉ እየተከተለች የምትወዘውዘው፣ የምትጠዘጥዘው፣ የምትነዘንዘው ያቺ ቁስል አለች፡፡ ነገሩን ሲፈትሽ፣ ነገሩን ሲመዝን፣ ነገሩን ሲፈክር፣ ነገሩን ሲዘክር በእሷ በኩል ነው፡፡ የትም ብሎ ብሎ ዞሮ የሚያርፍባት፣ የትም የትም ቢበር ሰርክ የሚከንፍባት ዛፉም ክንፉም እሷ ናት፡፡
“ገጣሚው ጸጸትን ከተስፋ፣ ውዳሴን ከእርግማን፣ አብሮነትን ከመለየት፣ ፍቅርን ከጥላቻ፣ ሃዘንን ከደስታ እያሰናሰለ የሸመናት ጉራማይሌ ጥበብ ናት - “ነገራ ነገር”፡፡  
“ገጣሚው የቃላት ሃብታም ነው፡፡ የመነቸከውን የቀን ተቀን ነገር፣ ተራ እሚመስለውን የዕለት ከዕለት ጉዳይ፣ ሞልቶ ከተረፈው ሰፊ የቃል ሙዳይ ሁነኛ ቃል መርጦ በማልበስ የአዘቦቱን የክት አድርጎ ማቅረብ የተካነበት ነው፡፡ ቃል እያዳወረ ትዝታውን ያልማል፤ ተስፋውን ይዘክራል፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ይጫወታል፤ ከሳር ከቅጠሉ፣ ከዝናብ ከጠሉ ጋር ይነጋገራል፡፡”

Read 1499 times