Saturday, 14 October 2023 00:00

“የአእምሮ ጤና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን ግንዛቤ ለማስጨበጥና የአእምሮ ህመም ያለባቸውን ሰዎች መብት የማስከበር ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው “የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን” በየዓመቱ መስከረም 29 የሚከበር መሆኑ ይታወቃል። የመጀመሪያው የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን እ.ኤ.አ. በ1994 “የአእምሮ ጤና አገልግሎትን በአለም አቀፍ ደረጃ ማሻሻል” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
የዘንድሮው መሪ ቃል፣ “አእምሮአችን፣ መብታችን” የሚል ሲሆን ፤ ይህም የአእምሮ ጤና ጉዳይ እንደ ሰብአዊ መብት ሊታይ የሚገባ መሆኑን አፅንዖት የሚሰጥ ነው፡፡
የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን በአገራችን እየተከበረ  በመሆኑ  ቀኑን አስመልክቶ በየአገሩ እንደሚደረገው መሰረታዊ አለም አቀፍ መሪ ቃሉን አስመልክቶ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይከናወናል፡፡ ምክንያቱም የዓለም የአእምሮ ጤና ቀንን የማክበር ዋና ዓላማው፤ ስለ አእምሮ ጤና ጉዳዮች ግንዛቤን ለማስፋት፣ መገለልን ለመቀነስና ስለ አእምሮ ሁለንተናዊ ደህንነት ግልጽ ውይይቶች እንዲደረጉ ለማበረታታት ነውና፡፡  በተጨማሪም፣ ግለሰቦችንና ማህበረሰቦችን ስለ አእምሮ ጤንነት፣ በሰዎች ህይወት ላይ ስላለው ተጽእኖ ግንዛቤ ማስጨበጥን እንዲሁም እርዳታና ድጋፍ ለመፈለግ እንዲበረታቱ ለማስተማር ያለመም ነው። ስለዚህም በዚህ ቀን ካለንበት አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ስለ አእምሯዊ ሁኔታችን አንዳንድ ነገሮችን መነጋገሩ የሚጠበቅ ነው፡፡
እንደሚታወቀው አገራችን የረዥም ዓመታት የበለፀገ ባህልና ቅርስ ባለቤት፣ ታሪካዊትና ኩሩ ህዝብ ያላት ሀገር ነች፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ጦርነት፣ ግጭትና መፈናቀልን ጨምሮ ብዘ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ያለች ሀገር ሆናለች፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በአእምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይታመናል።
 የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ 10 በመቶ ያህሉ  የኢትዮጵያ ህዝብ (በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ)፣ እንደ ድብርትና ጭንቀት የመሰለ የተለመደ የአእምሮ መታወክ እንደሚያጋጥመው ይጠቁመናል። ይሁን እንጂ በህሙማኑ ላይ በሚደርስ መገለልና በግንዛቤ ማነስ ሳቢያ ብዙ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች፣ እርዳታ ወደሚያገኙበት የጤና አገልግሎት መስጫ ቦታ ሊሄዱ አይፈልጉም፡፡ የአደገኛ እፅ አጠቃቀምም በአገራችን ትልቅ ችግር ነው። ለምሳሌ ከመላው ህዝባችን ውስጥ አዲስ ነገርን ለማወቅ ጉጉት አለው የሚባለው አምራችና የኢኮኖሚው ኃይል የሆነው ወጣቱ፣ (40.1 ሚሊዮን ያህሉ) ከ15-35 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.4 % የሚሆነው የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነትና ተጋላጭነት ችግር እንዳለበት የሰራተኛ ማህበራዊና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡ የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ችግር፣ ከሌሎች ከባባድና ቀላል የአዕምሮ ችግሮች ጋር የሚወሳሰብ ችግር እንደሆነ  ይታወቃል፡፡ 50 በመቶ የሚሆኑት የአዕምሮ ጤና እክል ተጠቂዎች የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነት ተደራቢ ችግር እንደሚኖርባቸውና 50 በመቶ የሚሆኑት የአደገኛ እፅ ተጠቃሚዎች የአዕምሮ እክል ሊኖርባቸው እንደሚችል በርካታ ጥናቶች ይፋ  አድርገዋል፡፡
በአገራችን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር፣ የተለያዩ የአዕምሮ ጤና እክሎች፣ ትራውማና የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነት ችግር ወይም የሱስ ህመም በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምሩ የሚችሉ ተጠባቂ ጉዳዮች በማድረግ፣ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ሰፊ ስራ እንዲሰሩ መቀስቀስ ያስፈልጋል፡፡
በእርግጥ በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤናና የአደገኛ ዕፅ አጠቃቀም መቃወስ የህክምና አገልግሎት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ  እያደገ መጥቷል፡፡ ለዚህም መንግስት የሚያስመሰግነውን ሥራ  ሰርቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ሀገሪቱ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የአእምሮ ጤና ህክምና መስጫ፣ ባለሙያዎችና አነስተኛ በጀት ነው ያሏት።
በዚህ የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን፣ የአእምሮ ጤና ሁለንተናዊ ሰብአዊ መብት መሆኑን በማስታወስ ለጉዳዩ የምንሰጠውን ትኩረት እንዲጨምር ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው፤ ገቢው፣ ማህበራዊ ሁኔታውና የኋላ ታሪኩ ምንም ይሁን ምን፣ ጥራት ያለው የአእምሮ ጤና አገልግሎት የማግኘት መብቱ እንዲከበር ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በመንግስት ደረጃ በጤና ተቋማት በቀጥታ አገልግሎት የሚሰጡ ወይም በከፊል የሚደጎሙ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጫዎች በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ብንወያይበት መልካም ነው።
በአገራችን የአእምሮ ጤናና የአደገኛ ዕጽ አጠቃቀም የሱስ ህመም ችግር የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ሊደረጉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ልጠቁም፡-
 በአእምሮ ጤናና በአደገኛ ዕፅ አጠቃቀም የሱስ ህመም ችግር የህክምና አገልግሎቶች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን መንግሥት ቢያበረታታ፤
ተጨማሪ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን በየዘርፉ ማሰልጠን ቢቻል፤
 የአእምሮ ሕመም ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መገለልና መድልዎ በተደራጀ መልኩ በርካታ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፉ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመስራት ለመቀነስ ጥረት ማድረግ፤
 በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን ልክ እንደ ፆታዊ የመብት ጥያቄዎች ትኩረት የመስጠትን ጉዳይ፣ “የአእምሮ ጤና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ነው” የሚለው ሃሳብ፣ ህገ-መንግሥታዊ መብት መሆኑንም ጭምር በመጥቀስ፣ በስፋት የመነጋገሪያ አጀንዳ ብናደርገውና እርዳታ የመፈለግ አስፈላጊነትን ግንዛቤ ብናሳድግ፤ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ በአገራችን የአእምሮ ጤናንና ሁለንተናዊ ደህንነትን በማስተዋወቅ፣ ሁላችንም የየራሳችንን ሚና መጫወት እንችላለን። ሁሉም ሰው ጤናማ ህይወት የመምራት እድል የሚያገኝበት አለም ለመፍጠር በጋራ እንስራ።
አገር ማለት ሰው ነው! ቸር እንሰንብት!
***
ከአዘጋጁ፡- የጽሁፉ አቅራቢ የመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት፣ ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተርና ከሱስ የማገገም አማካሪና አሰልጣኝ (Recovery coach) ናቸው፡፡

Read 496 times