Saturday, 21 October 2023 00:00

ስለ ህጻናት ቁርጠት( Infantile colic) ወላጆች ማወቅ ያለባቸው አስር ነጥቦች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

* ወላጆችን በተደጋጋሚ ሀኪምን እንዲጎበኙ ምክኒያት ከሆኑ  ህመሞች አንዱ በተለምዶ ቁርጠት (Infantile colic) የሚባለው ነው። ቁርጠት በተወለዱ በመጀመሪው ወር በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰት ሲሆን በቀን ለሶስት ሰአትና ከዛ በላይ ፣ በሳምንት ለሶስት ቀናትና ከዛ በላይ እንዲሁም  ለሶስት ሳምንታትና ከዛ በላይ የሚቆይ የለቅሶና መነጫነጭ ስሜት ነው።  ስለዚሁ ህመም ወላጆች ማወቅ ያሉባቸው 10 ነጥቦችን በዛሬው ጽሁፍ ይዤ ቀርቤያለሁ እስከመጨረሻው አንብቡት።

1. የህፃናት ቁርጠት (infantile colic)  መንስኤው ምንድን ነው?

* በመንስኤው ላይ በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ወጥ የሆነ መግባባት ባይኖርም የአንጀትና ባጠቃላይ የስርአተ ልመት ኢንዛይሞች ከአለመጎልመስ ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ ይታሰባል።

2. ህመሙ እስከ መቼ ይቀጥላል ?

* በአብዛኛው ህጻናት ዘንድ ህመሙ እስከ ሶስት ወር የሚቆይ ሲሆን  አልፎ አልፎ ግን በጣም ጥቂት ህጻናት ላይ እስከ ዘጠኝ ወር ሊዘልቅ ይችላል።

3. የምታጠባ እናት ከምትበላው ምግብ ጋር የቁርጠት ህመም ምን ግንኙነት አለው?

* የምታጠባ እናት  ቡና፣ ቅመም የበዛባቸው ምግቦች ወይም የላም ወተት ብትቀንስ ቁርጠት ላለባቸው ህፃናትን ቁርጠቱ እንዲቀንስላቸው ሊያግዝ ይችላል።

4. የጣሳ ወተትን በመቀየር ቁርጠትን መከላከል ይቻላል?

* ህጻኑ የጣሳ ወተት ሲወስድ የመነጫነጭና ማልቀስ ምልክት ካለው የጣሳ ወተቱን ቢቀየር ይመከራል ።

5. ቁርጠት ላለበት ልጅ መድሀኒት ቢሰጠው ለህመሙ ይረዳዋል?

* የቁርጠት መንስኤ የተለያዩ ምክኒያቶች በመሆናቸው እንዲሁም የህመሙ ባህሪ ከልጅ ልጅ ስለሚለያይ ለቁርጠት ወጥ የሆነ ህክምና የለውም። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት መድሀኒት መስጠት ለቁርጠት ብዙ ጠቀሜታ አይሰጥም።

6. በወላጆች በኩል ቁርጠቱን ለማስታገስ ምን ቢደረግ ይመከራል?

* ህጻኑን ዘና እንዲልና እንዲረጋጋ የሚያደርጉ ለምሳሌ ገላን በሙቅ ውሀ ማጠብ፣ ለስለስ ባለ ብርድ ልብስ መጠቅለና፣ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ህጻኑን መወዝወዝ( rocking motion)፣ ለስላሳ ሙዚቃ መክፈትና እሹሹ እያሉ ማረጋጋት ህጻኑ ህመሙ ቀለል እንዲልለት ይረዳል።

7.  ለረጅም ሰአት ህጻኑ በማልቀሱ ምን ጉዳት ያመጣበታል?
* ህፃኑ ለረጅም ሰአት በማልቀሱ የሚመጣ ጉዳት የለም። ህጻኑ የአካል ጥንካሬው ጥሩ ከሆነ፣ በደምብ የሚጠባ እንዲሁም በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ካለና ቆዳ ከለሩም ካልተለወጠ፣ የ ትኩሳት ምልክት ካልታየበት ከሰላሳ ደቂቃ በላይ ቢያለቅስም ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም። ስለዚህ ወላጆች ህፃናትን ለማረጋጋት ከሚጠቀሙበት መንገዶች ውጪ ከ አምስት እስከ አስር ደቂቃ ህፃኑ እንዲያለቅሱ በመተው ራሱን በራሱ እንዲያረጋጋ ማድረግ ይቻላል ።

8. ቁርጠቱ ከሌላ ህመመ ጋር አለመያያዙን በምን ምርመራ ማወቅ ይቻላል?

* ለቁርጠት የሚደረግ ምርመራ የለም። ነገር ግን ቁርጠቱ ሲከሰት ህፃኑ በ ህፃናት ህክምና ባለሙያ እንዲታይ በማድረግ የችግሩ መንስኤ ቁርጠት ወይም ሌላ ህመም መሆኑን ማወቅ ይቻላል። ህጻኑ በህጻናት ህክምና ስፔሻሊስት   ከታየ በኋላ ከአንጀት ጋር የሚያያዝ ችግርን ከተጠረጠረ ራጅ ወይም አልትራሳውንድ ምርመራ እንደሁኔታው ሊታዘዝ ይችላል።

9. ቁርጠት የያዘውን ህፃን በሀኪም እንዲታይ ማድረግ ያለብን መቼ ነው?

* አብዛኞቹ የቁርጠት ህመሞች በተደጋጋሚ ጊዜ ሰአት ለይተው የሚከሰቱ ናቸው። ለምሳሌ ቁርጠቱ ማታ ማታ በተደጋጋሚ ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ለቅሶው ከተለመደው በጣም ከረዘመና ከህፃኑ ባህሪ ጋር ባልተለመደ መልኩ የሚከሰት ከሆነ ለሀኪም ማሳየቱ ይመከራል። ከዚህ በተጨማሪ የንቃት መቀነስ፣ ትኩሳት፣ ጡት አለመጥባት ወይም ምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ ተደጋጋሚ ትውከት፣ ያልተለመደ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ፣ እና በፊንጢጣ የሚወጣ ደም ካለ ቶሎ ለሀኪም ማሳየት ያስፈልጋል።

10. ልጁ ቁርጠት እንዳለበት ከታወቀ ለክትትል መቼ መምጣት አለበት?

* አንድ ህፃን ቁርጠቱ ከሶስት ወይም ከአራት ወር በኋላ ከቀጠለ በሀኪም መታየት ይኖርበታል። 
በዶ/ር ኤርሚያስ አበባው ሲኒየር የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ)

Read 492 times