Saturday, 28 October 2023 19:33

ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በግሉ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነው የአውሮፕላን ጠጋኝነት ስልጠና ፈቃድ አገኘ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎቹን ያስመርቃል
              የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባልና የናሽናል አየር መንገድ እህት ኩባንያ የሆነው ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ በግል አየር መንገድ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውን የአውሮፕላን ጠጋኝነት ሥልጠና እንዲሰጥና ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያስተምር ፈቃድ ማግኘቱን አስታወቀ።
ኮሌጁ ዛሬ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በተለያየ የሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ከ900 በላይ ተማሪዎች ያስመርቃል።
 የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ካፒቴን አበራ ለማ ለአዲስ አድማስ እንዳብራሩት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ይሰጥ የነበረው የአውሮፕላን ጠጋኝነት ስልጠና ለግሉም አየር መንገድ መፈቀዱ በዘርፉ ባለሙያዎችን ከማፍራትና የአቪዬሽን ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ከ10 ዓመታት በአቪዬሽንና በቢዝነስ ዘርፎች ተማሪዎችን እየተቀበለ ሲያስምር የዘለቀ ሲሆን፣ ዛሬም በአቪዬሽንና በቢዝነስ ዘርፎች በድህረ-ምረቃ (በሁለተኛ ዲግሪ) በመጀመሪያ ዲግሪና በቴክኒክና ሙያ የስልጠና ዘርፍና በሰርተፍኬት ፕሮግራሞች ያስማራቸውን ሰልጣኞች እንደሚያስመርቅ ተገልጿል።


ኮሌጁ በሌሎች መሰል የግል ተቋማት የማይሞከሩ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፎች በመሰማራት ለዘርፉ ብሎም ለሀገር እድገት የበኩሉን እያደረገ ስመሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ዘንድሮም በሁተኛ ድግሪ በአቪዬሽን ማኔጅመንት፣ በሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት፣ በሎጂስቲክስና ሰብላይ ቼይን ማኔጅመንት በቢዝነስ ሊደርሽፕ፣ በስትራቴከጂክ ማኔጅመንት፣ በባንኪንግና ፋይናንስ፣ በሪስክ እና ኢንሹራስ እንዲሁም በኢንተርናሽናል ትሬድና ኢኮኖሚክስ፣ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች የሚያስመርቅ ሲሆን በመጀመሪያ ድግሪ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም  በአቪዬሽን፣ በሆቴል ማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በቴክኒክና ሙያ ሰስልጠና ዘርፍም በአቪዬሽን ዘርፍ በፍላይት ኦፕሬሽን፣ በትኬቲንግና ሪዘርቬሽን እንዲሁም በሌሎችም የትምህር ዘርፎች በአጠቃላይ 943 ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለማ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። በምረቃ ስነ--ስርዓቱ ላይ በአቪዬሽን ዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች የተመራቂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተብራቷል።


Read 1637 times