Saturday, 28 October 2023 20:06

“ቤቴ የምላት ኢትዮጵያ” (የአርመኑ ትውስታ)

Written by  -አብዲ መሀመድ-
Rate this item
(1 Vote)

 ከውጭ የሚመጡ ምዕራባዊያን ስለ ሀገራችን ስነጽሑፍ ካነሱ ቀድመው የሚጠይቁት ከሌላ ቋንቋ የተመለሱትን ስነጽሑፋዊ ስራዎችን እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ከያኒያን ያስረዳሉ፡፡ የአለም ክላሲካል ትርጉም ስራዎችን ያካተተ ብሄራዊ ስነጽሑፍ ለአገራችን እንደሚያስፈልጋት አያጠያይቅም፡፡ ምንም እንኳን አመርቂ ነው ባይባልም የሩሲያ የወርቃማ ዘመን ደራሲያን የጥበብ ስራዎችን በተራራቀ ዘመን ቢሆንም ተራ በተራ ለማንበብ ችለናል፡፡ ከነዚህ መካከል በቅርቡ የፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ‹‹The Idiot - ነሆለሉ›› በሚል ርዕስ ተተርጉሞ መቅረቡ ለዚህ እንደ አብነት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡…ደራሲና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ ባሳለፍነው አመት መገባደጃ ላይ ለንባብ ባበቃው “ቤባንያ” በተሰኘ ልቦለድ ስራው፤ ይህንኑ ያለብንን ክፍተት አጮልቆ በማየት ኞኞ የተባለ ሁነኛ ተርጓሚ መልምሏል፡፡ ኞኞ ዘመን አይሽሬ የጥበብ ስራዎችን በተከታታይ እየተረጎመ (ቶልስቶይ፣ አንቷን ቼኮቭ፣ ኒኮላይ ጎጎል የመሳሰሉ) የአማርኛ ስነጽሑፍን ለማሟላት እሚተጋ ተብሰልሳይና ተቆርቋሪ ገጸባህሪ ነው፡፡ አለማየሁ በኞኞ በኩል ጥሩ የትርጉም ስራ ያለውን ልፋትና ድካም፣ ለአገር እሚኖረውንም ላቅ ያለ ፋይዳ እንዲህ በማለት ገልጧል…“የትርጉም ስራ ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልፋቱን የሚረዱት በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ አድካሚ ብቻ ሳይሆን የምስጢር ፈልፋይነት ተሰጥኦንም ይጠይቃል፡፡ ደራሲው ምን ለማመስጠር ፈለገ? በፊት ምን ብሎ ነበር? ከዚህኛው ጋር እንዴት ህብር ይፈጥራል?…እያልክ የሰው ጓዳ ስታተራምስ መዋል ነው፡፡ ዝም ብሎ ቃላትን በቃላት መተካት አይደለም፡፡ ባህል ነው፤ ምስጢር ነው የሚተረጎመው”፡፡(ገጽ.153)
ከጥበባዊ የትርጉም ስራዎች በዘለለ በአገራት የእርስ-በርስ መቀራረብና ወንድማማችነት ላይ አትኩረው ወደ ቋንቋችን የሚመለሱ መጻሕፍት ሚናቸው በቀላል የሚገመት አይደለም፡፡ ከባዕድ ህዝቦች ጋር ያለንን ታሪካዊ አንድነትና ትስስር ከማስገንዘባቸውም ባለፈ፣ ለዜጎቹም ፍቅር እንዲያድርብን የራሳቸውን በጎ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ነባር የዘመን ኩነቶችንም በተጨባጭ ከስረ-መሰረቱ ዘግበው የሚያኖሩ የባህልና የትውልድ መገናኛ ቋሚ አምዶች ናቸው፡፡ በትውልድ አርመናዊ በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነው የቫርትኬስ ናልባንዲያን ትውስታን የያዘው “ባንዲራ ሳይኖረኝ እንዳልሞት” የትርጉም ስራ የራሱን ጡብ በማኖር ረገድ ተጠቃሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ኢትዮ-አርመን
ባንዲራ ሳይኖረኝ እንዳልሞት የሚለው ሐረግና መጽሐፉ ለተደራሲ የሚያስጨብጠው ቁምነገር፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ትውልደ አርመናውያን፣ በአገራችን የዜግነት ፈቃድ አግኝተው የአንድ አገር ዜጋ ከመሆን ያለፈ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲሆን፣ ይህም በመጽሐፉ የመጀመሪያ ገጽ ላይ በሚማርክ ሁኔታ እንዲህ ተገልጿል…“አንዲት የዕድሜ ባለጸጋ አርመን ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ዜግነት እንዲሰጣቸው ለኢሚግሬሽን ቢሮ በድጋሚ አመለከቱ፡፡ መንቀሳቀስ እንኳን እንደተሳናቸው የታዘበው ጉዳዩ የሚመለከተው የቢሮ ኃላፊ በሁኔታቸው ተደንቆ፤ “እማማ፣ ግን ይኽ ዜግነት ምን ያደርግልዎታል?” ብሎ ቢጠይቃቸው፣ “ባንዲራ ሳይኖረኝ እንዳልሞት ብዬ ነው ልጄ፣ ብለው መለሱለት”፡፡…ይህን ያለችው የመጽሐፉ የፊት ሽፋን ላይ የምትመለከቷት፣ በኦቶማኖች ከተፈፀመው አሰቃቂ ግፍ አምልጣ፣ ከአገሯ አርመኒያ ተሰድዳ ተለዋጭ እናት አገር ለማግኘት ስትል በኢትዮጵያ ጉያ ውስጥ የሙጥኝ ያለችን አንዲት ሴት ፊት ነው፡፡ ባንዲራው ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ባንዲራ ነው፡፡ (በእርግጥ ጃንሆይ ለአርመኖች ጥግ በመስጠት አዲስ ህይወት እንዲመሰርቱና አዲስ አገርም እንዲኖራቸው ያስቻሉ ባለውለታቸው እንደመሆናቸው፣ ባለታሪኩ የባንዲራ ምርጫው ከዚህ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይገድም) ሁለቱ አገሮች በታሪክና በሃይማኖት ተቆራኝተው ያሳለፉት ዘመን የሸበተ ታሪክ አለው፡፡ አርመኖች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የኢኮኖሚ ስደተኞች ሆነው አልነበረም፡፡ ከራሳቸው ጥቅም ጋር ያልተገናኘ የሙያ አገልግሎት እየሰጡ፣ ከወንድማቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተጋገዝ አዲስ አበባን ገንብተዋታል፡፡ (የሰፈሩት በፒያሳና በአርመን ክበብ ዙሪያ ሆኖ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ አዲስ አበባ ባዶ ሜዳ ስለነበረች ነው፡፡)
 የዜግነት ፈተና በአርመናውያን ላይ ብቻ የተጫነባቸው ለምንድነው? ለአያሌ አመታት ታከተን ሳይሉ ኢትዮጵያን ያገለገሏት ሆነው ሳለ ሊያልፉትና ሊሻገሩት የማይችሉትን ፈተና ለምን እንዲጋፈጡ ተገደዱ?! የሚል ጥያቄ በንባባችን መሀል ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ይሁንና የዜግነት መብት እየተነፈጋቸውም እንኳን ቢሆን እራሳቸውን የሚቆጥሩት ግን እንደ ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ርዕሱ በራሱ የቫርትኬስና የቤተሰቡን ጥልቅ የሆነ ስሜት የሚያሳይና ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት ያላቸውን ቆራጥነት የሚመሰክር ነው፡፡…በተወለዱበት አገር ዜግነት የሌለው መባል ለአርመን ማህበረሰብ ቀላል ኪሳራ አልነበረም-ገና ያኔ፡፡ በተለይ የዜግነት መብት ክልከላው በእነርሱ ላይ ፀንቶ ለረጅም ጊዜያትም ቆይቷል፡፡ ታሪካዊ አሰፋፈርና የአመጣጣቸውን ታሪካዊ ዳራ ወደ ኋላ መለስ ብለን ያጤንን እንደሆነም የሚያስገነዝበን ይህንኑ ኩነት ነው፡፡ አፄ ኃይለ ስላሴ፤ የአፄ ሚኒልክን ሞት ተከትሎ በገጠማቸው የውስጥ ስልጣን ሽኩቻ ሳቢያ ከጎናቸው የነበሩትንና የቆሙትን አጋሮቻቸውን በተለይ ሰራተኛ የሆነውን የአርመን ማህበረሰብን የዜግነት መብት ነፈጓቸው፡፡ ንጉሱ ከጎናቸው ያላራቋቸው አርመኖች ጥቂት ብቻ ነበሩ፡፡ ለብዙ ምዕታት የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት መግባባትና መተማመን ክፍተቱ የሰፋበትና በዚሁ ሳቢያ የህዝቡም ቁጥር እየተመናመነ የመጣበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ አፈ-ታሪክ እንደሚያስረዳውም ከሆነ፤ ምንም እንኳን የሚያገናኛቸው የጋራ ድንበርም ሆነ የዘር ትስስር ባይኖራቸውም…  በመልክአ ምድርም ተራርቀው በተለያዩ ክፍላተ ዓለም የሚገኙ ቢሆንም፣ የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ከቅድመ አያት ጀምሮ በተለያዩ ጦርነቶች ጎን ለጎን ተሰልፈው ከተዋጉባቸው ባሻገር…መግባባታቸውና የእርስ በርስ መተማመናቸው እስከ 20‘ኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ጸንቶ ቆይቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የአርመን ፊደል ከግዕዝ ጋር ተዛምዶና ትስስር እንዳለው በተመራማሪያን ተደርሶበታል፡፡ ቢያንስ አስራ ሰባት የአርመን ሆሄያት ከግዕዙ የፊደል ገበታ የመጡ መሆናቸውን በጉዳዩ ገፋ ያለ ንባብ ያደረጉ ዶክተር አርሜናክ ዮግሂአያን የተባሉ አጥኚ በቤይሩት ያሳተሙት መጽሐፍ እንደማመሳከሪያ በማቅረብ በንጽጽር ያቀረቡት ተጨባጭና አሳማኝ ማስረጃ በመጽሐፉ ሰፍሯል፡፡ ቫርትኬስ ግዕዝ ሆሄያትን ከአርመን ቋንቋ ወሰደ መባሉን በማጣጣል፣ ሊሆን የማይችል ነገር መሆኑን  ታሪካዊ ምክንያት በማቅረብ፣ የተፋለሰውን የሀቅ ክፍተት በማቀራረብ ይሞግታሉ፡፡ ይልቁንስ የአርመን ፊደል ከግዕዙ ሆሄያትን ተውሶ ጭረቶችን በመጨመርና በመቀነስ መሻሻሉንና መዳበሩን በአፅንኦት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከልብ በመነጨ ለሚወዷት አገራችን በአንክሮ ይሟገታሉ፡፡
ቅድመ አብዮት መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ በግንባታውም ሆነ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪውም ሆነ በንግዱ፣ በባህሉም፣ በመዝናኛውም…ከሁሉም አቅጣጫ ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ ላይ በነበረችበት ጊዜ አርመኖቹ ወገባቸውን አስረው፣ ጥርሳቸውን ነክሰው፣ እጃቸውን እግር አድርገው ሰርተው ከጎናችን ያልተለዩ ብርቱ ህዝቦች ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ እንኳን የበርካታ ህንጻዎችና የከተማው የአቅጣጫ ማሳያ የሆኑ መታወቂያ ምልክቶችን የቀየሱ፣ ሞገስ አልብሰው ከደማቅ መንደርነት የእድገት እንፋሎት የሚትጎለጎልባት ከተማ ወደ መሆን ያንደረደሯት አርመኖች፣ በአገራችን ደማቅና ጉልህ አሻራ አላቸው፡፡
 የጽሕፈት መኪናን በመጠቀም ረገድ፣ መጽሐፍት በማተም ስራ…በአዲስ አበባ ከተማ ቀዳሚውን የመጽሐፍ መሸጫ መደብር በመክፈትም ፈር ቀዳጆቹ ሶርያውያን፣ አርመናውያንና ሌሎችም የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ፡፡
ለምሳሌ ፒያሳ የሚገኘውንና ለ70 ዓመታት ያህል አገልግሎት እንደሰጠ የሚነገርለት የአፍሪካዊያን የመጽሐፍ መደብር የመጀመሪያው ባለቤቶች የውጭ አገር ዜጎች እንደነበሩ ብርሃኑ ሰሙ ከዓመታት በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በጥናታዊ ዘገባው ያሰፈረውን ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ (የመርስኤ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ውስጥ፤ ኢትዮጵያን በማዘመን ሂደት ውስጥ በግንባታው ተግባር ረገድ አብዛኞቹ ሰራተኞች፣ ገንቢዎችና አናጢዎች ከኢትዮጵያውያን ውጭ ህንዶች ግሪኮችና አርመኖች እንዳሉበት ጽፈዋል፡፡
አያይዘውም፤ ዳግማዊ ምኒልክ ባቡር ለማስመጣት ባሰቡበት ጊዜ ከአዲስ አበባ እስከ አዲስ ዓለም ከተማ ድረስ ያለውን መንገድ በመሀንዲሶች ሲያስቀይሱ፤ መሀንዲሶቹ በደመወዝ ያስቀጠሩዋቸው የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡
 ከፈረንጅ አገር የመጣውና እምብዛም ሳያገለግል በአጭሩ ተሰናክሎ የቆመው በተለምዶ የሰርኪስ ባቡር እየተባለ የሚጠራው ሲሆን፣ ባቡሩን ገዝቶ አዲስ አበባ ያደረሰው አስመጪና ነጋዴ የሆነው ሙሴ ሰርኪስ እራሱ የውጭ ዜጋ ነበር፡፡
 ባቡሩ የቆመበት ቦታም ሰባራ ባቡር ተብሎ እስካሁን ድረስ በዚያ ስም ይታወቃል፡፡ የዘመኑ አዝማሪም ይህን ተገን አድርጎ “ብነግርሽ ብነግርሽ አታጠናቅሪ፣ እንደ ሰርኪስ ባቡር ተገትረሽ ቅሪ” ብሎ ገጥሟል፡፡)…በዚህ መልኩ በክህሎታቸው፣ በእውቀታቸውና በፈጠራ ስራዎቻቸው ለኢትዮጵያ ብዙ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አርመኖችን ካነበብናቸው መጻሕፍት፤ ካገላበጥናቸው ድርሳናት…አስታውሶ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአዲስ ስራ ፈጠራ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ፣ በዘመናዊ እርሻና በአነስተኛ ደረጃ ግብርና ስራዎች ላይ የተሰማሩም እንዲሁ፤…ይሁንና ምርጥ ዜጎች ብሎ እውቅና መስጠት ግን በአገራችን እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ በቫርትኬስ ትውስታም እንደ አንድ ተግዳሮት ተነቅሶ ሳይጠቀስ አላለፈም፡፡ ቫርትኬስ ድንቅ አስታዋሽና ሚዛናዊ ፀሐፊ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ አሁን የምናውቃት እናት አገራችን የሆነችው በህዝቦቿና በመሪዎቿ ታላቅነት መሆኑን እያወሱ፤ ነገር ግን በአለም ካርታ ላይ አዎንታዊ ገጽታ እንዲኖራት በማድረግ በኩል የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደረጉላትን ነባር ባዕድ አገራት እንዳትዘነጋ ያሳስባሉ፡፡  
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት “ተረትና ታሪክ በኢትዮጵያ” በተሰኘ ጥናታቸው፤“…ግለ-ታሪክ የሚዳስሰው ግለሰቡ ባሳለፋቸው ዘመናት ያከናወናቸው ድርጊቶች ላይ ይሁን እንጂ፤ በአብዛኛው የሚያተኩረው ግን በኃላፊ ዘመን በተፈፀሙ የታሪክ ድርጊቶች ላይ ነው” እንዳሉት ሁሉ…የቫርትኬስ መጽሐፍ የሚሸፍነው በርካታ የአገራችን የታሪክ አንኳር ጉዳዮችን እንደ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የሦስቱን ስርአታት አጀማመር፣ አካሄድና አፈፃፀም መቼና እንዴት እንደሆነ ሁሉ ተሰናስሎ ቀርቦበታል፡፡
 አጠቃላይ ታሪኩ ግለሰባዊ ብቻ አይደለም፡፡ ጸሐፊው ቫርትኬስ በዚህ ትውስታው ውስጥ ያሰፈራቸው አንኳር ጉዳዮች ከአርመን ይልቅ አገሬ የሚላትን ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ትውስታዎቹ ላይ በአመዛኙ አትኩሯል፡፡ በአገራችን ታሪክ ውስጥ በሦስቱም መንግስታት የተከናወኑ አበይት ታሪካዊ ክስተቶችን ከእነ መነሻ ምክንያታቸው ያሰፈረበት የመጽሐፉ ክፍል አስደማሚ ነው፡፡ ቫርትኬስ ለአገራችን ነባርም ሆነ ወቅታዊ ጉዳዮች የቱን ያህል ቅርበት እንዳለው በተጨባጭም የሚያሳይ ነው፡፡ ርዕሶቹን ለማሳያነት ብንጠቅስ እንኳን ሁነኛ አስረጂዎች ናቸው፡፡
 “መንግስቱ ነዋይ የከሸፈ ሙከራ”፣ “አብዮቱና ያለ ምንም ደም”፣ “የሶማሊያ ጥቃት”፣ “ኢሕአዴግና የዘውግ ፖለቲካው”፣ “የኢህአዴግ መጨረሻ…”ወዘተ፡፡ ከዚህ ባሻገር የአርመኒያውያን ኑሮዋቸውን እንደ አዲስ ሊጀምሩ፣ ትዳር መስርተውም-በስራ ተፍጨርጭረውም…ሊበለጽጉና አሁንም እየሰፋ ያለ የታሪካቸው አንድ አካል ሊሆኑ የቻሉበት፣ ሌላ አገር ያገኙ የአንድ ቤተሰብና ማህበረሰብ እጅግ ውብ የሆነ ጥልቀት ያለው ታሪክ ነው፡፡
በዚያው መጠን ለአገራችን ያላቸው ጥልቅ ፍቅር አስደማሚ ነው፡፡…“ቤቴ ለምንላት ለአንዲት አገር የሚሰማኝ ስር የሰደደ ፍቅር ነጸብራቆች እልፍ ናቸው፡፡
በምወዳት አገሬ ደህንነት ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ የምታደርጋቸውን ጥረቶችና ተጋዳይ ፍልሚያዎቿን መላው ህዝብ በእኔ ዐይን ያያቸውና ስሜቱንም ይረዳው ዘንድም ውስጣዊ ሐሳቦቼን አካፍላለሁ - በህይወት ቆይቶ ታሪኳን ለማየት በታደለ ህያው ምስክር አይን”፡፡(ገጽ.8)…አልፎ-አልፎም በተስፋ ማጣት ሂደት ውስጥ የተከሰቱ ክስተቶችም በምሳሌ ተዋዝተው የቀረቡበት ክፍል ተነባቢ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ምንጊዜም ተስፋ ሳይቆርጡ ተጀምሮ እስኪጨረስ ላለመረታት፣ ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልገውን ጽንአትና ቆራጥነት ጠብቆ የማቆየት ታሪክም ጭምር ነው፡፡
በመሆኑም ለአንዲት አገራችን ኢትዮጵያ ፍጹም ታማኝነትና የኃላፊነት ስሜት ካለው ከአንድ ሰው (ቫርትኬስ እና የናልባንዲያኖች ቤተሰብ) ጋር ጥልቅ የቁርኝት ስሜት፣ የአብሮነት ትዝታ ሳይፈጥሩ መጽሐፉን አንብቦ መጨረስና አጥፎ ማስቀመጥ የማይቻል ነውና…ሊነበብ የሚገባው ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት፤ የተዋጣለት ሸጋ የትርጉም ስራ ነው ስል ምስክርነቴን  መስጠት እፈልጋለሁ፡፡

Read 813 times