Monday, 30 October 2023 20:15

አቶ አብነት ገ/መስቀልን ጨምሮ በ5 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

Written by 
Rate this item
(5 votes)
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቶ አብነትገ/መስቀል እና 3 የመሬት አስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ በአምስት ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል።
 
አቶ አብነት ገ/መስቀል በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 2 የሚገኘውን ከሼክ አላሙዲን መሀመድ ጋር የጋራ ንብረታቸው የሆነውን የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር ይዞታ በ83 ሚሊየን ብር በመሸጥ ለግል ጥቅም አውለዋል በሚል በተጠረጠሩበት ወንጀል በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲቀርቡ እንደነበር አና ዐቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፖሊስ የተረከበውን የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት የ15 ቀን ይሰጠኝ ብሎ መጠየቁን ተከትሎ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ክስ የመመስረቻ ጊዜውን ለዐቃቤ ሕግ መፍቀዱን መዘገባችን ይታወሳል።
 
ይሁንና ዐቃቤ ሕግ ከተፈቀደለት የክስ መመስረቻ ጊዜ አስቀድሞ ዛሬ አቶ አብነትን ጨምሮ በአምስት ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል።
ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክሱን ለመመልከት ለፊታችን ዓርብ ቀጠሮ ይዟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አብነት ገ/መስቀል ባሳለፍነው 2015 ዓ.ም በ2 ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቦሌ ታወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጅምር ግንባታ ያለበት 3 ሺህ 383 ካሬ ሜትር ይዞታን ያለአግባብ ባለመብት በመሆን ይዞታው ላይ ካርታ በማውጣት ከ321 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሸጥ አድርገዋል ተብለው ከሌሎች ከመሬት አስተዳደር ሰራተኞች ጋር ተከሰው ነበር።
 
ይሁንና በአቶ አብነት ላይ ቀርበውባቸው ከነበሩ ሶስት ክሶች መካከል ሁለቱ ክሶች በችሎቱ ዳኛ ከአንድ ሳምንት በፊት እንዲቋረጡ ተደርገዋል።
(ኤፍ ቢ ሲ)
Read 1012 times