Saturday, 04 November 2023 00:00

መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረጋቸው ከ1,600 የሚበልጡ ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለፀ

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

ዜናዎችን በመዘገባቸው እና መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረጋቸው ብቻ በአለማችን ከ1,600 የሚበልጡ ጋዜጠኞች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅትUNESCO አስታውቋል። በሰሩት የዜና ዘገባ ምክንያት ከተገደሉ 10 ጋዜጠኞች የዘጠኙ ገዳዮች አለመቀጣታቸውንም ዩኔስኮ በዘገባው አክሏል ።
እ.አ.አ በየአመቱ ኅዳር 2 ቀን በመላው ዓለም ታስቦ የሚውለውን በጋዜጠኞች ላይ ካለተጠያቂነት የሚፈጸምን ወንጀል የማስቆም ዓለም አቀፍ ቀን ምክንያት በማድረግ ዩኔስኮ


ይፋ ባደረገው መረጃ ከአውሮፓውያን አቆጣጠር 1993 ዓ,ም ወዲህ ባሉት ዓመታት ዜናዎችን በመዘገባቸው እና መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረጋቸው ከ1,600 የሚበልጡ ጋዜጠኞች ተገድለዋል ። የተገደሉ ጋዜጠኞችን መረጃ ባለፈው በ2022 ማጠናቀሩን ያመለከተው
UNESCO ከተገደሉት 10 ጋዜጠኞች የዘጠኙ ገዳዮች አልተቀጡም።
ምንም እንኳን የመገናኛ ብዙሃን አንደበትን ለመለጎም ግድያ ዋናውና ጽንፍ የረገጠው እርምጃ ቢሆንም፤ ጋዜጠኞች ፈርጀ ብዙ ለሆኑ ስጋቶች፤ ለመታፈን፤ ለስቅይት እንዲሁም ለአካላዊ ጥቃት እና ወከባ የተጋለጡ ናቸው ።

አብዛኛውን ጊዜም በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እና ወከባ በወጉ ምርመራ እንደማይደረግበት ያመለከተው የዩኔስኮ መረጃ ፤ አጥፊዎቹ ያለመቀጣታቸው ወንጀለኞችን ከማበረታታቱም በላይ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በኅብረተሰቡ ላይ ፍርሃትን አስከትሏል ብሏል ።የሰብአዊ መብቶችን ረገጣ፣ ሙስና እና ወንጀሎችን በመሸፋፈን ተጠያቂነት የሌለበት አካሄድ ኅብረተሰብን እንደሚጎዳ ያመለከተው UNESCO እንዲህ ያለው ድርጊት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንም አመልክቷል ።የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ CPJ በበኩሉ በመላው ዓለም ከአምስት መቶ በላይ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል ። ድርጅቱ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረትም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የፖለቲካ ውጥረት ተከትሎ ቢያንስ ስድስት ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ገልጿል።


በየአመቱ ኀዳር 2, ቀን የሚከበረው በጋዜጠኞች ላይ ካለተጠያቂነት የሚፈጸምን ወንጀል የማስቆም ዓለም አቀፍ ቀን ዘንድሮ ለሁለት ቀናት ማለትም ኅዳር 2 እና 3 ቀን ይከበራል። ዕለቱ በተለይ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት፤ የምርጫ ተአማኒነት እንዲሁም የሕዝብ አመራር ሚና ላይ ባተኮሩ ውይይቶች እንደሚታሰብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት UNESCO አስታውቋል።
በየዓመቱ በዚህ ዕለት ጋዜጠኞች ላይ ካለተጠያቂነት የሚፈጸም ወንጀል የሚታሰበው ጎርጎሪዮሳዊው 2013 ኅዳር 2 ቀን ማሊ ውስጥ የተገደሉ የፈረንሳይ ጋዜጠኞችን በማሰብ ነው። በርካታ ጋዜጠኞች ከሚገደሉባቸው አካባቢዎች የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን አካባቢዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

Read 724 times