Sunday, 12 November 2023 19:56

ሙዙን ስታይ፤ መዘዙንም እይ!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 ከእለታት አንድ ቀን፣ አያ ዝንጀሮ፣ የአንበሳን ሚስት ሊያሽኮረምም አስቦ አንበሳ በሌለበት ወደ ሚስትየው ይሄዳል፡፡ የአንበሳ ሚስት የዝንጀሮን መላ ሰውነት ቃኝታ ስታበቃ፣
“አያ ዝንጀሮ፤ አይንህ ለምን ቀላ?” ብላ ትጠይቃለች፣ አይኑን አተኩራ እያየች፡፡
ዝንጀሮም፤
“የዐይኔ መቅላትማ የጀግንነት ምልክት ነው” ይላታል፡፡
ቀጥላ ወደ እጁና ወደ እግር ጥፍሩ እያስተዋለች፤
“ጥፍርህስ እንዲህ ረዝሞ ለምን አደገ?”  ትለዋለች፡፡
“ፍሬ ለመፈልፈል እንዲረዳኝ ብዬ ያሳደግሁት ነው፡፡ እኔ‘ኮ ምንም ነገር ያለ አንዳች ብልሃት አልሰራም!”
የአንበሳ ሚስት ከፊቷ የሚጎማለለውን ዝንጀሮ ዘወር ዘወር ብላ ተመለከተችና፤
“መቀመጫህስ በምን ምክንያት ተመለጠ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“እሱ ዓለም የሚያውቀው ነገር እኮ ነው፡፡ መቀመጫዬ የተመለጠው ህይወቴ በጦር ሜዳ ውሎና በጀብድ የተሞላ እንደመሆኑ፤ ከፈረስ ፈረስ ስዘል ነው” አለና መለሰላት፡፡
በመጨረሻም፤
“ይገርማል አያ ዝንጀሮ፤ ዛሬ ከቁመትህ ሁሉ በጣም የገረመኝ ደግሞ የጎፈርህ መንዠርገግ ነው፡፡ የአንበሳን ጎፈር መሰለኮ”
“ይሄማ ጠላትን መከላከያ ነው፡፡ ከሩቅ ግርማ - ሞገሴን እያየ የዱር አውሬው ሁሉ የሚሸሸኝ እኮ በዚህ በጎፈሬዬ ምክንያት ነው!”
አያ ዝንጀሮ እንዲህ እየፎከረ የአንበሳን ሚስት ሲያማልል ሲጎማለል፤ ድንገት አያ አንበሶ ከተፍ አለ፡፡ ከዚያም ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፤
“አያ ዝንጀሮ፤ ምነው ዐይንህ ቀላ?”
ዝንጀሮ ድምፁ ሁሉ ኮሰመነና ልቡ ከዳው፡፡
“ዐይኔ የቀላው በድህነት ምክንያት ነው” አለ፡፡
አንበሳ ቀጠለና፤
“ጥፍርህስ ለምን አደገ?”
“መሬት የምቧጥጥበት ነው ጌታዬ!”
“መቀመጫህን ደሞ ምን መለጠው?”
“ከተራራ ተራራ የምንፏቀቅበት ነው!”
“ፀጉርህንስ ምን እንዲህ አንጨፈረረው?”
“ለብርድ፤ ለብርድ ነው ያሳደግሁት ጌታ አንበሶ!”
አንበሳም ክፉኛ እየተኩራራ፤
“ሂድ ጥፋ ከዚህ! አስኮናኝ!” አለው፡፡
ዝንጀሮ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡
አንበሳም ወደ አንበሲት ዞሮ፤
“አንቺም ሁለተኛ ከእንደዚህ ያለ ተልካሻ ቡክን ጋር እየዋልሽ አታዋርጂኝ!” አላት፡፡
***
“እዩኝ እዩኝ ያለች ደብቁኝ ደብቁኝ ትላለች” ነው ነገሩ፡፡ ያልሆነውን ነን ማለትን የመሰለ ክፉ በሽታ የለም፡፡ ለአንዴና ለዛሬ ብቻ ያልሆነውን ነን በማለት ለማጭበርበር እንችል ይሆናል፡፡ ነገ ግን ማንነታችን ይጋለጣል፡፡
 “ጓሣና ድንግል አላንድ ጊዜ አይበቅል” የሚለውን ተረት አለመርሳት ነው፡፡ ለታይታ የምናደርገው ሁሉ የአፍታ ስም ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ በሆይሆይታና በግርግር የምንፈጥረው ማናቸውም ትልቅነት በቀላሉ እንደሚናድ ካብ ነው፡፡ በትህትናና በሥርዓት የተሰራ ነገር ሁሉ ግን ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ልባምነት ጽናትና ጥንካሬ ያለው፣ እርጋታ ውስጥ እንጂ ችኩልነት  ውስጥ አይደለም፡፡ ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል ይሏልና፡፡
“አደባባይ ሲበዛ የክት ልብስ ይጠፋል” የሚለውን አነጋገር መቼም ቢሆን አለመዘንጋት ነው፡፡ ብዙ ጉራ በመንዛትና አደባባይ በመታየት ውስጥ ብዙ ስህተቶችን እናፈራለን እንጂ ደርዛችን እፍኝ ታህል አትሆንም፡፡
“የማትሰግር በቅሎ ጌጧ ይበዛ” ነውና መመሪያ ብናበዛ፣ ገለፃ ብናዘወትር፣ ያላንዳች አማራጭ አዲስ ሀሳብ፤ ያንኑ ያንኑ ዲስኩር ደጋግመን ብንደሰኩር፣ ራሳችንን ከማድመጥ በቀር ወደፊት አንራመድም፡፡የሀገር ጉዳይ ሁሌም ረዥም መንገድ ነው፡፡ ብዙዎች የሀገር ችግሮች አቋራጭ የላቸውም፡፡ መሳለጫ መንገድም የላቸውም።
 አጫጭር አቋራጮችን ስንፈልግ መቸኮል ይመጣል፡፡ ሥረ-ነገሩን ትተን ላይ ላዩን ብቻ መነካካት ይበዛል፡፡ ሥር የሰደደ፣ “ለዘር ለቀለብ ይበቃል” የሚል ነገር ይጠፋል፡፡ በጭብጥ እህል ጠብ መጫር ይበዛል፡፡ “ስንቃችሁ ግማሽ ቁና፤ ነገራችሁ አህያ እማይችለው” የሚባልበት ወቅት ይሆናል፡፡
“የአዕምሮህ ዛጎሉ ውጪ ፀሐይ የሚሞቅ ከሆነ፣ ከውስጥም ዕንቁው አለመኖሩ ይታወቃል” እንዲሉ፤ ውዱንና ትልቅ ዋጋ ያለውን ቅርስ አለማርከስ ተገቢ ነው፡፡ በምናደርገው ነገር ውስጥ ሁሉ መላ፤ ጥበብና ስልት ካልታከለበት ፍሬያማ አይሆንም፡፡
ስለ ፖለቲካ ሸንጎ የሚያውቁ ፀሐፍት እንዲህ ይመክራሉ፡-
“ስለ ማሸነፍህና ድልህም ቢሆን ብዙ ጥሩምባ ከመንፋት ተቆጠብ፡፡ ስለ ራስህ በምትናገረው ሁሉ ቁጥብና ትህትናን የተላበሰ ሁን፡፡ ብዙ የምትሰራና እድገቱ ሁሉ የኔ ነው የምትል አትሁን፡፡ ማር ሲበዛ ይመራልን አትርሳ፡፡ ለተገቢው ነገር ብቻ ትኩረትን ሳብ፡፡
በተለመደና በአሰልቺ ልሳንና ዲስኩር አትናገር፡፡ ልሳንህ ሁኔታዎችን የሚገዛ መሆን አለበት፡፡ የመጥፎ ዜና ተሸካሚ ላለመሆን መጣር አለብህ፡፡ ከመናገርህ በፊት ሁለት ሶስቴ አስብ ይሏል፡፡
ህዝብን አለመናቅ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎች የነገ ቂም እርሾ ናቸው፡፡ ለሚሰሩ ሰዎች ምስጋናና ሽልማትን አትንሳ፡፡ የሰዎችን ሽልማትም በግፍ አትውሰድ፡፡ የበታቾችን ማንጓጠጥ የመሪዎች ታላቅ ህፀጽ ነው፡፡ የፈጠራዎች ሁሉ እናት መስተዋት ነው፡፡
ሌሎች እንደሚያዩን አድርጎ ራሳችንን ያሳየናልና፡፡ ራሳችንን የምናይበት መስታወት ከእጃችን መለየት የለብትም፡፡ ስሜቱን የማይቆጣጠር መሪ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ መንፈሱን ከጊዜው ጋር ካላጣጣመም የመምራት መላው ሰንካላ ይሆናል፡፡ ማንኛውም መሪ ነገን የሚያስብ ጭንቅላት ሊኖረው ይገባል፡፡
ራሳችንን ለሌሎች የደስታ ምንጭ ለማድረግ መሞከር ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወዝና ለዛ ያለው መሆን አለብን፡፡
ዣን ዴ ላብሩዩር የተባለ ፀሀፊ፤ “የፖለቲካ ሸንጎን የሚያውቅ ገጽና መልኩን (gesture) ለመቆጣጠር የሚችል፤ አይኑን መግራት የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ብቁና የማይደፈር፤ ከቶም የማይገሰስ ነው፡፡
መጥፎ ምግባራትን ማሟሸሽ፣ ለጠላቶቹ ፈገግ ማለት፤ ቁጣውን ማለዘብ፣ ስሜቱን መሸፈን፣ የልቡን በልቡ መያዝና አንዳንዴ የማይፈልገውን ከስሜቴም ውጪ ለመናገር መገደድን የሚችል ሰው ነው” ይለናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ሳይገነዘብ የሚጓዝ፣ “ሙዙን ስታይ፣ መዘዙንም እይ!” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የዘነጋ ነው!


Read 3233 times