Sunday, 12 November 2023 19:59

ፖለቲካ እንደ ወረደ!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(7 votes)

( እውነት እውነቱን ብቻ)
                  

                  ወዳጆቼ፤ በዚህ አምድ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ… በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ፖለቲካዊ ሁነቶችን እንደወረደ እናቀርባላችኋለን-እውነት እውነቱን ብቻ! ለዛሬ እስቲ ከትግራይ እንጀምር፡፡ የሳምንቱን የፖለቲካ ወሬ!
እናላችሁ ከሰሞኑ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዚዳንት ቢሮ በተፃፈ ደብዳቤ ከፍተኛ  ሃላፊዎች ከሥልጣናቸው መነሳታቸው ተሰምቷል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ከ10 ቀናት በፊትም 6 ከፍተኛ የዞን ባስልጣናትን ከሃላፊነታቸው አንስቶ ነበር፡፡ ሁለተኛው የመልቀቂያ ደብዳቤው የተፃፈው በፈረንጆቹ ኦክቶበር 28 ቀን 2023 ዓ.ም ቢሆንም፣ ለባለስልጣናቱ የደረሳቸው ግን ባሳለፍነው ሳምንት መሆኑ ታውቋል፡፡

(አሁን ወደ ገደለው እንግባ)
ከፕሬዚዳቱ ቢሮ የወጣው ደብዳቤ እንደሚገልፀው ከሆነ ከስልጣናቸው የተባረሩት ሃላፊዎች
አለም ገብረዋህድ (የፕሬዚዳንቱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ)፣
አማኑኤል አሰፋ (ዋና የካቢኔት ሃላፊ)
ተክላይ ገ/መድህን (የሰሜን ምእራብ ዞን አስተዳዳሪ)፣
ሊያ ካሣ (የደቡብ ምሥራቅ አስተዳዳሪ) ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ከስልጣናቸው የተነሱት ሃላፊዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት፤ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሰሙት በማህበራዊ ሚደያ ነው - እንደማንኛውም ሰው ማለት ነው፡፡ (ምናለ በግላቸው ቢነገራቸው?) የሚገርመው ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ ከተለቀቀው መረጃ ውጭ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የባስልጣናቱን መባረር አስመልክቶ እስካሁን በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም ተብሏል፡፡


ከሰሞኑ ከሃላፊነታቸው በድንገት ከተባረሩት ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ አማኑኤል፣ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት፤ ከስልጣናቸው የተባረሩበትን ምክንያት አያውቁትም፤ በዚያ ላይ እሳቸውም ደብዳቤውን ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው ያነበብኩት፡፡ ከሃላፊነት የመነሳቴን መረጃ የሰማሁት የመስክ ስራ ላይ ሆኜ ነው ያሉት ሌላው ተባራሪ አቶ ተክላይ በበኩላቸው፤ ከመስክ ስራ ሲመለሱ የዞን አስተዳደሩ ዋትሳፕ ላይ የእሳቸውን ጨምሮ አራት የመልቀቂያ  ደብዳቤዎች ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ከሃላፊነታቸው መባራቸውን በተመለከተ በስልክም ሆነ በአካል ማንም የነገራቸው እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡ የሆነ ሆኖ በምትካቸው ሰው እስኪሾም ድረስ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል - የህዝብ ሃብት እንዳይባክንና አገልግሎት እንዳይቋረጥ በሚል፡፡ (መቼም ከልባቸው ከሆነ መሸለም ይገባቸዋል!) የዛሬ ባለስልጣን እኮ እንኳንስ ሳይነገረው ከሃላፊነቱ ተባሮ ይቅርና በስልጣን ላይ እያለም ሃላፊነት ተሰምቶት አያውቅም፡፡


በነገራችን ላይ በመጀመሪያው ዙር፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሃላፊነታችው የተነሱት 6 ከፍተኛ የክልሉ ባስልጣናት በህዝብ የተጣለባቸውን ሃላፊነትና አደራ መወጣት ባለመቻላቸው ነው ከስልጣን የተባረሩት ተብሏል- በአስተዳደሩ!! ሰሞኑን የተባረሩት ግን ከስልጣን የተነሱበትን ምክንያት እስካሁን የሚያውቁት አይመስልም፡፡ (በቅርቡ ግን አስተዳደሩ ያሳውቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡)
 ከትግራይ ሳንወጣ፤ በክልሉ በተቃዋሚ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሰው ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከሰሞኑ ያወጣውን መግለጫ እንስማ። ፓርቲው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተፈረመበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከጦርነቱ ወዲህ በአማራ ሃይሎች ተይዟል በሚባለው የምእራብና ደቡብ ትግራይ አካባቢዎች ላይ የፌደራል መንግስቱ ሪፍረንደም ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ያለውን እቅድ ተቃውሟል፡፡ ዓሲምባ፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት በተሟላ መልኩ እንዲተገበር በአፅንኦት ጠይቋል - በመግለጫው፡፡

ስምምነቱ ከተፈረሙ ከአንድ አመት በኋላም ምላሽ ያላገኙ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሳው ፓርቲው፣ የኤርትራ ሃይሎች ከትግራይ ቁልፍ አካባቢዎች አለመውጣታቸውን በዋናነት ጠቅሷል፡፡ (የአሜሪካ መንግስትም ይህንኑ ጉዳይ አንስቷል ልበል?!) እንግዲህ ፓርቲውን እንመነው ከተባለ የኤርትራ ሃይሎች ከኢሮብ፣ ዛላምበሳ ባድመና አዲጉሹ አልወጡም ባይ ነው፡፡ የአማራ ሃይሎችና ሚሊሻዎችም በምዕራብና ደቡብ ትግራይ መኖራቸውን በመጠቆም፤ ከትውልድ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ትግራዋዮች በየቦታው ተሰደው ሱዳንን ጨምሮ እንደሚገኙ አመልክቷል ፓርቲው፡፡ በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ ለወራት መቋረጡን የተገለፀው ፓርቲው፤ በክልሉ በርካቶች በረሃብ-ህይወታቸውን እንዳያጡ አስጠንቅቋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ያልተፈቱ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ በሃይል የተያዙ አወዛጋቢ ቦታዎችን የፌደራል መንግስቱ በሪፍረንደም ለመፍታት መወሰኑን አሲምባ አጥብቆ አውግዟል፡፡
በሌላ በኩል፤ በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአማራና ትግራይ ክልሎች የሚወዛገቡበትን አካባቢ አስመልክቶ መንግስታቸው እንዴት መፍትሄ ሊያበጅለት እንዳቀደ መናገራቸው ይታወቃል፡፡ አሲምባ የተቃወመውም እሱን ይመስለኛል - “ሪፍረንደም የሚደረገው ሞቼ ነው ቆሜ” ያለ ይመስላል፡፡
መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች ከዚህ በኋላ የትኛውንም ልዩነቶቻቸውንም ሆነ ችግሮቻቸውን ከንግግርና ከውይይት ውጭ የሚፈቱበት ሌላ አማራጭ እንደሌለ አስቀድመው ማሰብና ራሳቸውን ማሳመን ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ለሁለት ዓመት በተካሄደው አስከፊ ጦርነት የደረሰብንን እልቂትና ውድመት እንዲሁም ኪሳራ ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ የጦርነትና የሃይል አማራጭን ከወዲሁ እርም ልንለው ይገባል፡፡ የአንድ አገር ህዝቦች በጋራ ለሚኖሩበት መሬት እርስ በርስ መተላለቅ አይገባንም፡፡ ህዝቡ እንደ ድሮ በሰላም ተቻችሎና ተከባብሮ የሚኖርበትን እድልና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በቀዳሚነት የመንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስራና ሃላፊነት ነው፡፡ አገሩን የሚበጠብጡት ፖለቲከኞቻችን መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው! ከሲዳማ ደግሞ ያገኘነው መረጃ እንዲህ ይላል (ድንገት እጃችን የገባ መሆኑ ይታወቅልን!) አንጋፋው የሲዳማ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሆነ የሚነገርለት የሲዳማ ፊደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ)፤ የሲዳማ  ክልላዊ መንግስት ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ዓ.ም አዋሳ በሚገኘው  የፓርቲው ዋና ፅ/ቤት በሃይል በመግባት፣ ንብረታችንን ከመዝረፍም በላይ አንድ አባላችንን አስሮ ወስዶብናል ሲል ከስሷል፡፡


የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች በበኩላቸው፤ ጥቂት የፓርቲው አባላት ረብሻ መቀስቀሳቸውን ተከትሎ፣ ህግና ስርዓት ለማስከበር የተወሰደ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ የፓርቲው ሴክሬተሪያት ሃላፊ አቶ ገነነ ሃሳናነ ግን ይሄን አይቀበሉትም፤ የፀጥታ ሃይሎች በተጠቀሰው ቀን ቢሮአቸውን እንደወረሩትና ሳሙኤል ላንካም የተባለ አባላቸውን አስገድደው እንደወሰዱት፣ እስካሁንም ያለበት እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ ሃይሎች ወደ ፓርቲያቸው ቢሮ በፖሊስ ተሽከርካሪዎች  በሃይል መግባቸውንና እንቅስቃሴ ማስተጓጎላቸውን አቶ ገነነ ተናግረዋል፡፡ “ህግ እንዲያከብሩ ሲጠየቁም፣ የሃይል ምላሽ ሰጥተው የስራ ባልደረባችንን ይዘውት ሄደዋል፤ እስካሁን ቤተሰቡም እኛም ያለበትን አናውቅም” ብለዋል የፓርቲው ሃላፊ፡፡
 ክልላዊ መንግስቱ ከቀድሞ የሲዳማ ፊደራሊስት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ጋር በመተባበር ፓርቲውን ለማዳከም እየሰሩ ነው ሲሊ የወነጀሉት ሴክሬተሪያት ሃላፊው፤ ፓርቲው በክልሉ የሚታየውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር በንቃት እየመረመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው ሴክሬተሪ ሃላፊ በተጨማሪም እንደተናገሩት፤ የፀጥታ ሃይሎች የቢሮአቸውን ቁልፍ በመለወጥ የፓርቲው አመራርና አባላት ወደ ቢሮው መግባት እንዳይቻሉ ገደብ እንደጣሉባቸው ተናግረዋል- አቶ ገነነ። “ከቢሮ ብዙ እቃዎች ተወስደዋል” ሲሉም አክለዋል ሃላፊው፡፡
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ቲሞጢዮስ፤ በተጠቀሰው ቀን የፓርቲው አባላት ረብሻ መቀስቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር ከአገር ከወጡ በኋላ፣ ውስጣዊ አለመግባባት መከሰቱንና ይህም የክልሉን መንግስት ጣልቃ ገብቶ ስርዓት እንዲያስከብር እንዳስገደደውና አንድ የፓርቲውን አባል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ጠቁመዋል፡፡ ሃላፊው አቶ ገነነ ግን፣ ፓርቲው በክልሉ መንግስት ወከባና ማስፈራሪያ ሲደርስበት የመጀመሪያው አይደለም ይላሉ፡፡ ባለፉ ወራት የክልሉ መንግስት የፓርቲ አባላትን የማስፈራራትና የማሰር ታሪክ እንዳለው የሚናገሩት ሴክረተሪ ሃላፊው፤ በአሁኑ ሰዓት 12 የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ሃላፊዎች ምላሻቸው ምን ይሆን? ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ 12 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ከታሰሩ ምን ተረፈ? (ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ቁጥር 12 ይደርሳል ወይ?) (ፓርቲው እኮ የለም!) እንግዲህ ችግሩ በጊዜ መፍትሄ ያገኛል ብለን ተስፋ እናድርግ (ሌላ ምርጫ የለንማ!)

Read 1823 times