Friday, 17 November 2023 19:55

ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማምረቻ ፋብሪካ ሊመረቅ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ14 .5 ሚሊዬን ዶላር የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማማረቻ ፋብሪካ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል፡፡
ፋብሪካውን “ኢ ዜድ ኤም ትሬድ እና ኢንቨስትመንት” የተሰኘው ኢትዮጵያዊ የንግድ ኩባንያና የቻይናው ዓለም አቀፍ ድርጅት ሪፎ በጋራ እንደገነቡት ተገልጿል፡፡
የፋብሪካውን ምርቃት አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የኩባንያዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ዕለት በጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ፋብሪካው በዘርፉ ያለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ያለመ ነው ተብሏል።
ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ 2ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን ፒፒአር ቱቦዎችና 1 ነጥብ 9 ሚሊዬን የፒፒአር መገጣጠሚያዎች ፣ 1 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን የፒቪሲ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችና 9 መቶ ሺህ የፒቪሲ መገጣጠሚያዎች እንዲሁም 3 ነጥብ 5 ሚሊዬን ሜትር በላይ የፒቪሲ ኮንዲዩት የማምረት ዓመታዊ አቅም አለው ተብሏል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት የሙከራ ምርት እያመረተ ሲሆን ፥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡
በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመሆን እውቅና ማግኘቱም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የቻይናው ሪፎ ኩባንያ በዘርፉ የ27 ዓመት ልምድ ያካበተና በመላው ዓለም እየሰራ እንደሚገኝ፣ በኢትዮጵያም ልምዱን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩንና ብራንዱን ይዞ እንደመጣ የተገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው ኢ ዜድ ኤም በበኩሉ፣ ላለፉት 6 ዓመታት የሪፎን ምርቶች ብቸኛ ወኪል አስመጪ ሆኖ ሲሰራ እንደቆየ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ እስመለአለም ዘውዴ፣ ምርቱን በማስመጣት ብቻ በአገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ማሟላት ስላልተቻለ በአገር ውስጥ ማምረቱ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር፣ 50 በመቶ ምርቱን ለጎረቤት አገራት ምርት እንደሚልክም ተገልጿል፡፡
Read 1455 times