Saturday, 18 November 2023 00:00

በ2023 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

- ታዋቂ አትሌትና ኮሜንታተር በክብር እንግድነት ይገኛሉ
- በዋናው ውድድር 500 አትሌቶች ይሳተፋሉ
- 812ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ቀርቧል
- ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱና በአፍሪካ 1ኛ መባሉ
- “ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ” 2.7 ሚሊዮን ታቅዶ፣ 2.3 ሚሊዮን ተሰብስቧል
- ከ12 አገራት ከ150 በላይ ተሳታፊዎች፣ ለአምባሳደሮች ውድድር ከ20 በላይ ኤምባሲዎች ተመዝግበዋል


23ኛው የሶፊ ማለት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 45ሺ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ በአዲስ አበባ
ይካሄዳል። ትናንት በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል በተካሄደው መግለጫ ላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ባሰማችው ንግግር “ለትውልድ የሚሸጋገር መሠናዶ በማድረግ፤ ሁላችሁንም ተሳታፊዎች ተዘጋጅተን እየጠበቅናችሁ ነው” ብላለች። በዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ስፖንሰሮች ትልቅ ቁርጠኝነት በማሣየት የተሻለ ውድድር ለማዘጋጀት አብረው መሥራታቸውን የጠቀሰችው ዳግማዊት ከእንግዲህ አጋሮች ብቻ
ሳይሆን አዘጋጆች ብለን ነው የምንጠራችሁ ስትል ተናግራለች።የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የበላይ
ጠባቂ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ሲናገር “ታላቅ የሆነው፤ ጥሩ ደረጃ የደረስነው በናንተው ነው፤
አትሌቶች ፣ተሳታፊዎች ፤ ሚዲያው፤ ስፖንሰሮችና መንግስትን አናመሠግናለን” ብሏል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ ውድድር በማዘጋጀት ያለውን ልምድ በመጠቀም በቀጣይ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድር የምታዘጋጅበትን ሁኔታ መፍጠር ይፈልጋል። ኃይሌ የዓለም አገር አቋራጭ፤ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ...ወዘተረፈ ለማስተናገድ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብሏል።
ታዋቂ አትሌትና ኮሜንታተር በክብር እንግድነት ይገኛሉ በ2023 የሶፊማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ሁለት ታላላቅ የአትሌቲክስ ባለታሪኮች ልዮ የክብር እንግዶች ሲሆኑ ውድድሮችን በማስጀመር ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። ደቡብ አፍሪካዊቷ
የቀድሞ አትሌት ኤለና ማየርና ታዋቂው እንግሊዛዊ የአትሌቲክስ ኮሜንታተር ቲም ሃቺንግሰን ናቸው። ደቡብ አፍሪካዊቷ ኤለና ማየር በ1992 ላይ በባርሴሎና ኦሎምፒክ በሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር ከደራርቱ ቱሉ ጋር ባደረገችው አስደናቂ ፉክክር ኢትዮጵያውያን ያውቋታል። ሜዳሊያ ያሸነፈች ነበረች። ኤለና ማየር ከዚያ ታሪካዊ ውድድር ባሻገር ከአፍሪካ ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች አንዷ ስትሆን በሩጫ ዘመኗ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሪከርድ ለአራት ጊዚያት መሥበር የቻለች ናት።
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መግለጫ ላይ በሰጠችው አስተያየት ውድድር ካቆመች ከ20 ዓመታት
በላይ እንዳስቆጠረች ተናግራ ታዳጊ አትሌቶችን በአካዳሚ ደረጃ በማሰልጠንና በመደገፍ እየሰራሁ ነው ብላለች። በሌላ በኩል ታዋቂው ኮሜንታተር ቲም ሃቺንግሰን ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ጊዜ የሚጎበኝበት አጋጣሚ ስለተፈጠረለት በእጅጉ ደስተኛ ሆኗል። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ እንግሊዝን በመወከል ካሳለፈው የሩጫ ዘመን በኋላ በስፖርት ኮሜንታተርነት ከ33 ዓመታት በላይ ያገለገለ ምርጥ ባለሙያ ነው። ዓለም አቀፍ
የአትሌቲክስ ውድድሮችና ታላላቅ ማራቶኖችን በመላው ዓለም እየዞረ በቀጥታ ስርጭት በማስተላለፍ ቲም ሃቺንግሰን ዝነኛ ሆኗል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ውድድሮችን በዓለም ዙርያ ተዟዙሮ በመዘገብም ይታወቃል። በኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገቡ ታሪካዊ ውጤቶችና ሪከርዶችን በልዮ ስሜት በማሰራጨትም ከበሬታን አትርፏል።
በ23ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቲም እንደተናገረው ኃይሌ ገብረስላሴ
በ1990ዎቹ በወጣቶች ውድድር በ5ሺና በ10ሺ ሜትር ካስመዘገበው ድል እስከ ትግስት አሰፋ የማራቶን ሪከርድ በኮሜንታተርነት መሥራቱን ገልጿል።
በዋናው ውድድር 500 አትሌቶች ይሳተፋሉበዋናው 10ኪሜ የአትሌቶች ውድድር በሁለቱም
ፆታዎች ከ500 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 35 ክለቦች ለተሳትፎ የተመዘገቡ ሲሆን ከውጭ አገራት ደግሞ ጥሩ ሰዓት ያላቸው የኡጋንዳ አትሌቶች የሚሮጡ ይሆናል፡፡ በወንዶች ምድብ ጎዳና ላይ ሩጫውን ለሦስት ጊዜያት
በማሸነፍ ባለታሪክ የሆነው አቤ ጋሻው ለወጣት እንዲሁም በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ የአመቱ ምርጥ አትሌት ለመባል የመጨረሻ እጩ የሆነችው መዲና ኢሳ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።
የጎዳና ላይ ሩጫው በትራክና በጎዳና ሩጫ የዓለም ታላላቅ አትሌቶችን በማሳተፍና አዳዲሶቹንም
በማውጣትም እንደተሳካት ይታወቃል። በወንዶች ምድብ ለሶስት ጊዜያት በማሸነፍ ባለታሪክ የሆነው አትሌት አቤ ጋሻው ተጠቃሽ ነው ይባላል። በ2017 ሰለሞን ባረጋ፣ በ2018 ሃጎስ ገ/ህይወት እንዲሁም በ2019 በሪሁ አረጋዊ ይህን ውድድር ያሸነፉ የዓለማችን ምርጥ ሯጮች ናቸው። በ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው የቦታውን ሪከርድ አትሌት ድሪባ መርጋ
በ28 ደቂቃ 18.16 ሰከንዶች አስመዝግቧል።በሴቶቹ ምድብም በ10ኪ.ሜ የዓለም ሪከርድን 29፡14 በሆነ ጊዜ የያዘችው ያለምዘርፍ የኋላው የወጣችበት ነው። በ2019 ስታሸንፍ ያስመዘገበችው 31 ደቂቃ ከ55 ሰከንዶች የቦታው ሪከርድ ሲሆን በ2019 እና
በ2021 እ.ኤ.አ ላይ የጎዳና ላይ ሩጫውን በማሸነፍከፍተኛውን ውጤት አስመዝግባለች። ዘይነባ ይመር በ2017፣ ፊተይ ተስፋዬ በ2018 እንዲሁም ፅጌ ገ/ሰላማ በ2020 እኤአ አሸንፈዋል።
812ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ቀርቧል የጎዳና ላይ ሩጫው በኢትዮጵያና በአፍሪካ
አትሌቲክስ ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት ያቀረበም ሆኗል። የውድድሩ አዘጋጆች እንዳስታወቁት
ለሽልማት የተዘጋጀው አጠቃላይ ገንዘብ ከባለፈው አመት 30 በመቶ እድገት በማሳየት 812ሺ ብር የቀረበበት ሆኗል። በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ 200ሺ ብር የሚበረከት ሲሆን ለሁለተኛ 100ሺ ብር እንዲሁም ለሶስተኛ 50ሺ ብር የሚሰጥ ይሆናል። በኢትዮጵያና በዓለም ዙርያ የሚሠሩ ታዋቂ የአትሌቲክስ ማናጀሮች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለሙያዎች በ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የሚሰማሩ ሲሆን ዋናው ምክንያት አዳዲስ አትሌቶች ለመመልመል የሚጠቀሙበት አመቺ መድረክ ስለሆነና ነው፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫ
የሚመዘገብ ውጤትና ሰዓት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ስለሚያስችል ነው።
ከ12 አገራት ከ150 በላይ ተሳታፊዎች፣ ለአምባሳደሮች ውድድር ከ20 በላይ
ኤምባሲዎች ተመዝግበዋል የጎዳና ላይ ሩጫው በስፖርት ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ የላቀ አስዋጽኦ ማድረጉንም ቀጥሏል። ዘንድሮ ከ12 አገራት ከ150 በላይ ተሳታፊዎች የጎዳና
ላይ ሩጫውን ለመሮጥ ተመዝግበዋል። የሕንድ፣ የብራዚል፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣
ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ዩኬና አሜሪካ ዜግነት
ያላቸው ናቸው። በ2015 እኤአ ለጎዳና ላይ ሩጫው ከ700 በላይ የውጭ አገራት ዜጎች ተሳትፈው በነበረበት ወቅት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መደገፋቸው በጥናት ተረጋግጧል።በተያያዘ ዘንድሮ በጎዳና ላይ ሩጫው በአምባሳደሮች ውድድር ለመሳተፍ ከ20 በላይ ኤምባሲዎች መመዝገባቸውን ያስታወቁት አዘጋጆቹ ይህም በውድድሩ አዲስ ክብረወሰን ሆኖ እንደሚመዘገብ አመልክተዋል።

“ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ” 2.7 ሚሊዮን ታቅዶ፣ 2.3 ሚሊዮን ተሰብስቧል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ሩጫውን ከበጎ አድራጎት ጋር በማስተሳሰርም ውጤታማ ሆኗል። “ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ” በሚል ዓላማ በሚከናወኑ ተግባራት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው
ተቋማት ገንዘብ ተሰባስቦ እንደሚበረከት ይታወቃል። ባለፉት 20 ዓመታት ከ15 ሚሊዮን
ብር በላይ በማሰባሰብ ከ32 በላይ ተቋማት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ከዘንድሮው ውድድር ጋር በተያያዘ በሚካሄደው ዘመቻ እስከ 2.7 ሚሊዮን ብር ለመሠብሰብ ታቅዶ 2.3 ሚሊዮን ብር ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት መገኘቱን አስተባባሪዎቹ ገልፀዋል።
ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱና በአፍሪካ 1ኛ መባሉ የኢትዮጵያ ብሮድስካቲንግ ኮርፖሬሽን
ለውድድሩ ለ3 ሰዓታት በቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን ሌሎች ሚዲያዎችም ከተለያዩ አገራት መጥተዋል። የኬንያው ሲትዚን ቲቪ ሙሉ ዘገባ ለመሥራት ባለሙያዎችን የላከ ሲሆን፤ የፈረንሳይ አርቴ ቲቪ ዘጋቢ ፊልም ለመሥራት እንዲሁም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከፓሪስ ኦሎምፒክ ጋር የሚያያዝ ዘገባ ለመሥራት አዲስ አበባ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል። ታዋቂው የአትሌቲክስ ዘጋቢ ራነርስ ዎርልድ በ10ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ
የዓመቱን ታላላቅ ውድድሮች ሲዘረዝር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በአንደኛ ደረጃ አስቀምጦታል። የጎዳና ላይ ሩጫው ግንባር ቀደም ሊሆን የበቃው የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉበት ውድድር መሆኑን ተጠቅሶ ነው። ቫይተሊቲ ለንደን 10,000
ከእንግሊዝ፣ ፓሪስ 10K ከፈረንሳይ፣ ስሞንሲያ ቤይ10K ከዌልስ እንዲሁም ራንኪላርኒ ከአየርላንድ እስከ አምስተኛ ደረጃ አከታትለው አግኝተዋል።
አፍሪካ ውስጥ በጎዳና ላይ ሩጫዎች ከሚንቀሳቀሱ አገራት ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄርያና ሞሮኮ ናቸው። ከ10ኪ ሜ ይልቅ በሚያዘጋጇቸው የማራቶን ውድድሮች ነው የሚታወቁ ሲሆን የሌጎስ፣ የናይሮቢ፣ የኪሊማንጃሮና የኬፕታውን ማራቶኖች በምሳሌነት
መጥቀስ ይቻላል።

Read 498 times