Sunday, 19 November 2023 00:00

እሷ ስትስቅ…

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(2 votes)

(በእውነተኛ ገጠመኝ ላይ የተመሰረተ ልብወለድ)

    ምን ልፃፍ? ሀሳቤ ከጭንቅላቴ ውስጥ ተናጥቦ ጠፋብኝ፡፡ የቃላት ርሀብ ሰቅዞኝ ህሊናዬ ሲጮህ ካጠገቤ ያሉትን ይበጠብጥ ጀመር፡፡ እንደ ንፋስ ያለ ባዶነት የማሰብ አቅሜን ተፈታተነው፡፡ ሆኖም ምጡ እንዳለ ነው፡፡ ትግል ያለበት የቃላት ምጥ ሲበረታ እንደ እብድ የሚያደርገው ነገር አለው፡፡ አሁኑኑ ከቤቴ ወጥቼ ሀሳብ መፍጠር አለብኝ፡፡ የሚፃፍ ሀሳብ፡፡ አሁን መሽቷል…ሆኖም አልኮሉን ገልብጦ እብደቱንና እንቅልፉን የሚያስስ አንድ ፍጥረት እንደማላጣ አውቃለሁ፡፡ የማውቃት መጠጥ ቤት አለች፡፡ ከዛ መጠጥ ቤት ውስጥ ታሪካቸውን አይኖቻቸው ላይ ተሸክመው የሚመላለሱ ሀቀኛ ጠጪዎች አሉበት፡፡ ከአንዱ መልክ ላይ ታሪኩን ነጥቄው ቤቴ በመግባት በወረቀት ላይ ፍፃሜውን ልከውነው ውሳኔ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ወጣሁ፡፡
እንዳጋጣሚ ሆኖ በመጠጥ ቤቱ ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን ተቀምጦ ነው ያለው፡፡ ከፊት ለፊቱ ሄጄ ተቀመጥኩኝ፡፡ ያሰብኩለትን ቀመር የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ ሙሉ ታሪኩን ዘርፌው፣ ትዝታውን ገፍፌው ለራሴ ላደርገው እንዳቀድኩኝ ምንም አይነት መረጃ የለውም፡፡ ቢራዬን አዝዤ ገና አንድ ፉት እንዳልኩት፣ ይህ እንግዳ ሰው በራሱ ሰዓት መናገር ጀመረ፡፡ የሚያወራው ግን ከኔ ጋርም ሆነ ከአስተናጋጁ ጋር አልነበረም…ሁላችንም ልናያት የማይቻለንን የአንዲት ሴት ስም እየጠራ ነው የሚያወራው፡፡
ከእግር እስከራሱ ፈጠን ብዬ ተመለከትኩት፡፡ ወፍራም፣ ቀይ፣ አይኖቹ ትላልቅ፣ አስተያየቱ ብልጥ ይሁን ሞኝ የማያስታውቅበት…ሰክሯል፡፡
ትንሽ ያወራና ዝም ይላል፡፡ ዝም ብሎም ግን በጭንቅላቱ ውስጥ የሚነጥረውን ሀሳብ ለማረጋጋት ይመስል አንገቱን ያወዛውዛል፡፡ የምሬን ነው…እያየሁት በቆየሁ ቁጥር ማዘን ውስጥ ገባሁኝ፡፡ አንዲት ጥያቄ ብጠይቀው ወይንም ለሁለት ሰከንድ ያክል ትክ ብዬ ብመለከተው ትዝታውንና የወደፊት እጣ ፈንታውን እንደሚተርክልኝ እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ የፅሁፍ አምላክ ሆን ብሎ እንዳገናኘን ገባኝ፡፡ ሁለታችንም ምጥ ላይ ነን…እሱ የሚሰማው ሰው ፍለጋ ….እኔ የምፅፈው ሀሳብ ፍለጋ፡፡ ሁሉም ነገር ከዚህች ቅጽበት ነው የተጀመረው፡፡
-------------------
ሦስተኛ ቢራዬ ላይ ስደርስ…መጠጡም ያሉትን ሴሎቼን ማንቃት ሲጀምር…አለምን የማይበትን መንገድ የያዝኩት መጠጥ ማስቀየር ከመጀመሩ በፊት የዚህን ሰውዬ ታሪክ መስማት እንዳለብኝ ወሰንኩኝ፡፡
ቀና ብዬ ተመለከትኩት፡፡ በስካር ብስል ብሏል፡፡ ሰዓቱ አሁን ነው፡፡ ዝርፊያው የሚከናወነው አሁን ነው፡፡
"አይተሃት አታውቅም?" ብሎ ጠየቀኝ፡፡
"ይቅርታ … ያልከው አልገባኝም?" አልኩት፤ ግርታዬን እንዲረዳልኝ ፊቴን ኮስተር አድርጌ፡፡
"ሎዛን ስትስቅ አይተሃት አታውቅም ወይ ነው ያልኩህ?" አለኝ፤ በእርግጠኝነት እንደማውቃት ልቡ ያመነ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡
አሁን ራሱ በራሱ ሰዓት መጥቷል፡፡ እኔ ላይ ማናችሁም እንደማትፈርዱብኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ መረቤ ውስጥ ገብቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ከኔ በቀር ይህን ሰው የሚያድነው የለም ብዬ አሰብኩ፡፡
"ሎዛን አላውቃትም…" አልኩት፡፡ እንደዚህ ስመልስለት የበደልኩት ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ግን እንጃ፡፡
"እንደው በህይወት ሳለህ አንዲት የምትስቅ ሴት አላየህም? ምነው ሄዋንን ከመፍጠሩ በፊት ፈጣሪዬ ትንሽ ቢያሰላስል ኖሮ…ምነው ሎዛ ትዝ ብትለው ኖሮ፡፡ ተወው እሱን አሁን…"
እሱ ይሄን እያወራ ከኋላ ኪሴ ውስጥ ያስቀመጥኳትን የማስታወሻ ደብተሬን አውጥቼ ማስታወሻዬንልፅፍ ጥቂት ብቻ ነበር የቀረኝ፡፡ የደራሲ ጭካኔ እዚህ ላይ ነው፡፡ ከሰው ልጅ ህመሙን ይወድለታል፡፡ ፈገግታውን እየተከተለ የእንባውን ገመድ ሲጎትት ይገኛል፡፡ "መደሰት" የሚባለው የህይወት ልምድ በጨካኝ ደራሲ ልብ ውስጥ አፈታሪክ ነው…በጥንት የተኖረ እና አሁን ላይ የተረሳ የሰው ልጅ ፈጠራ ነው፡፡
ለማንኛውም ፍልስፍናዬን ትቼ ወደዚህ ምስኪን ሰው (ለነገሩ በኋላ ላይ ስሙን ይነግረኝል፤ ከኔ ጋር ግን እኩል እንድትሄዱ ስሙን ቀደም አድርጌ ልንገራችሁ….በረከት ይባላል፡፡) ወደ ታሪኩ ልግባ፡፡
ጉልበቱን በግራ እጁ እየተመተመ ንግግሩን ቀጠለ፡፡
"ያቺን ሴትማ ታውቃታለህ…ፈገግ ያለችበት ስፍራ በሙሉ የፀሀይ ማህተም እንዳረፈበት የምድር መልክ ብርሀኑ አይጠፋም፣ ቃላቶቿ ያረፉበት ጆሮ በሙሉ ደርሶ የሚመለስበት ቦታ አለው፡፡ አይኖቿ ርቀት ያስኬዳሉ…
"በዛ የዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ አይተሃት አታውቅም? ከኔ ጋር ሆና…አይኖቼን ብቻ እያየች…ምድር ላይ የሚታይ ነገር የጠፋ ይመስል፡፡ ስትስቅልኝ…አቤት ስትስቅ፡፡ ታውቃለህ መጀመሪያ ቀን ሳያት እየሳቀች ነው፡፡ የዛን ቀን ያለምክንያት ነው የሳቀችው፡፡ ከኔ ጋር ታጠና ከነበረችው ዊንታና ጋር ትተዋወቃለች፡፡ ከርቀት ስላየቻት ብቻ ነው የሳቀችው፡፡ የዛን ቀን ግን እኔ እንዳየኋት ያያት ማንም አልነበረም፡፡ በሰውነቴ እወራረዳለሁ…ተሳስቼ ከሆነ ነፍሴን ወስደህ ለአማልዕክቶቹ አጫርታቸው፡፡ ጉዳዬም አይደለ፡፡
"ለማንኛውም ከሁሉም ነገሮቿ ቀድሜ ከፈገግታዋ ጋር ነው የተዋወኩት፡፡ ጥርሶቿ ምህረት የላቸውም፡፡ አተኩረህ ከተመለከትካቸው የማትመለስበት ጡዘት ውስጥ ገብተህ ስትጨፈለቅ ራስህን ታገኘዋለህ፡፡
"ተዋወቅን፣ ተዋደድን፣ ሰው እስኪቀናብን ድረስ ፍቅርን መስለን በዛ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ተመላለስን፡፡ አይኖቿን መርጬ እያየሁ ዘላለም መክረም እችል ነበር፡፡ እሷም ብትሆን እኔን ማንም እንዲያይባት አትፈልግም፡፡ አምናለች፤ የኔ ብቻ እንደሆነች፡፡ አምናለች፤ አይኖቼ ለፈገግታዋ ሲሉ ሲኦል ገብተው መውጣት እንደሚችሉ፡፡ አምናለች፤ የሁለታችን ግንኙነት መለኮታዊ ደባ እንዳለበት፡፡ አምናለች…አምናለች…አምናለች…"
መልሶ አቀረቀረ፡፡ መልሶ በሀሳብ ጭልጥ አለ፡፡ የትዝታ ሸክም አስጎነበሰው፡፡ ሆኖም ያ ፈገግታዋ ትውስ አለው መሰል፣ ፈገግ ብሎ ቀና በማለት አየኝ፡፡ እያዳመጥኩት እንደሆነ ገብቶታል፡፡
"የምልህ ልጅ ሎዛ ነች፡፡ ሎዛ… አንድ ቀን ተቀጣጠርን፡፡ ትዝ ይለኛል የቫላንታይን ቀን ነው፡፡ ክብሬን ከሰጠሁ ለማንም ሳይሆን ላንተ ብቻ ነው፡፡ ያንተ መሆኔን በተቀደሰው ቅዱስ ቫላንታይን ቀን አረጋግጥ ብላ ሙሉ ፍቃዷን ሰጠችኝ፡፡ የምወዳት ሎዛ…ስትስቅ የማልጠግባት ሴት ክብሬን ልስጥህ አለችኝ፡፡
"የዛን ቀን የምለብሰውን ልብስ የሰጡኝ ጓደኞቼ ናቸው፡፡ ብር እንዲያዋጡ ተደርጎ ገንዘብ ተሰበሰበ፡፡ እንደኔው መናጢ ድሀ ነበሩና የተሰበሰበው ብር የረባ ምግብ እንኳን የማይገዛ ሆኖ ተገኘ፡፡ ገንዘብ አጥቼ ነው ያልመጣሁት አልላት፡፡ በሰዓቱ ሞባይል ስልክ የለ አልተመቸኝም ብዬ ለመናገር፡፡ ያ የቀን ጎዶሎ አጎደለኝ፡፡ ምነው የተዋወኳት ቀን መልሶ መላልሶ መምጣት ቢችል፡፡ ሆኖም ይህ የቀን ጎዶሎ አጎደለኝ፡፡"
መናገሩን አቆመ፡፡ ወደ አስተናጋጁ ዞሮ እጁ ላይ ያለውን የአልኮል ብርጭቆ ቀና አድርጎ አሳየው፡፡ አስተናጋጁ ከእኔ እኩል የሚያወራውን በማድመጥ ላይ ስለነበር እንደባነነ ሰው ሆኖ፣የጅኑን ጠርሙስ አምጥቶ ያንን ነጭ ፈሳሽ ኮመረለት፡፡
"እና የዛን ቀን ሳትሄድ ቀረህ?"  ምን ሆኜ እንደሆነ እንጃ ብቻ ታሪኩ እንዲቋረጥብኝ አልፈለኩም ነበር፡፡
"እየሰማህኝ ነው ማለት ነው?" ብሎ ጠየቀኝ፡፡
"በሚገባ!" አልኩት፡፡
"የዛን ቀን አላገኘኋትም፡፡ በህልሜም አሰስኳት፡፡ ሎዛ የለችም፡፡ የዛን ቀን ለቀጠሮ የለበስኩትን የወዳጆቼን ልብስ እንደለበስኩት አልጋ ላይ ሆኜ እንደተከዝኩ ነጋብኝ፡፡ በበነጋታው እየተንደፋደፍኩ ሄጄ ሎዛን የማገኝበት ቦታ ላይ ሆኜ ጠበኳት፡፡ አልመጣችም …ከብዙ ጥበቃ በኋላ በመንገድ ላይ ያገኘኋትን ጓደኛዋን ጠየኳት….
"ሎዚዬ እኮ ሌሊት ትኬት ቆርጣ ወደ አዲስ አበባ ሄደች" አለችኝ፡፡ እንግዲህ አስበው የሚፈጠርብኝን ፍርሀት…ሎዛን አሁን አንጡልኝ? ብል ማንም መልስ የሚሰጠኝ አይኖርም፡፡ የት ትሂድ የት የማውቀው ታሪክ የለም፡፡ እንደው በአንድ ጊዜ "ጊዜ" የሚባለው ነገር የተሰወረብኝ መሰለኝ፡፡"
"ከዛስ በኋላ?" አለ አስተናጋጁ፡፡
በረከት ቀና ብሎ አስተናጋጁን ከተመለከተ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ፡፡
"እናማ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቴን ስጨርስ ወደ አዲስ አበባ መክተሚያዬን አደረኩኝ፡፡ ብዙ ፈለኳት…ብዙ፡፡ ላገኛት አልቻልኩም፡፡ ከሷ የቀረኝ የነበረው ፈገግታዋ ነበር፡፡ ያ ፈገግታ…"
ከዚህ በኋላ ታሪኩን ባይቀጥልልኝ ፈቃዴ ነበር፡፡ ቀሪውን ታሪክ በራሴው መንገድ ብጨርሰው ይመቸኝ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ሰው በስንት ዘመኑ አሁን ላይ ስለተጫነው ሀሳብ ተናግሮ መገላገል የሚፈልግ አይነት ሰው ነው፡፡ ታሪክህን አቁም ብለውም አያቆምም…ጥዬው ብሄድ ራሱ እየተከተለ የሚተርክልኝ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አማራጭ የለኝም…ቀጠለ፡፡
"ከብዙ ፍለጋ በኋላ እንዲህ ሆነ፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር እንዲሁ ስለ ፍቅር ጉዳይ እያወጋን ድንገት ያንተ ሄዋን ማናት ብሎ ሲጠይቀኝ…የማውቃትን…የምወዳትን…እየጠበኳት ያለሁትን የሎዛን ፎቶ አውጥቼ አሳየሁት፡፡ ተገርሞ ጠየቀኝ…"
"የት ነው የምታውቃት ይህችን ልጅ አለኝ?"
"አብረን በምንማርበት ወቅት ፍቅረኛዬ ነበረች…አሁን ግን የት እንዳለች አላውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ ሆነኝ ያለችበትን ሳፈላልግ፡፡"
"አውቃታለሁ …እኛ ሰፈር አንድ ቡቲክ ውስጥ ነው የምትሰራው፡፡" እርግጠኛ ሆኖ መለሰልኝ፡፡
"አሁን ልትወስደኝ ትችላለህ?" አልኩት፡፡ ይህን የሰማሁ ሰዓት ላይ መላው ሰውነቴ ውስጥ የልቤ ትርታ ሲደልቅ ይሰማኝ ጀመር፡፡ አይኔ ለብቻው ፈገግታዋን እያስታወሰ መሰቃየት ውስጥ ገባ፡፡ የምሬን ነው የምልህ በጣም ናፍቃኝ ነበር፡፡ እኔ በረከት …በረከቴን ላገኝ የሚቻለኝ ሎዛን ሳገኛት ነው፡፡ ያለ ምክንያት እየሳቀች፡፡
"ያለችበት ይዞኝ ሄደ፡፡ ወደ ቡቲኩ ከመግባቴ በፊት በድብቅ ፀለይኩኝ፡፡ ህልም ውስጥ ካለሁ ፈጣሪዬ እንዲያነቃኝ ለአፍታ የነፍሴን ጥያቄ ሰማይ አንጥሬ ወደ ጭንቅላቴ ወረወርኩት፡፡ ስገባ አየኋት…"
በፈገግታ ተሞልቶ እኔንና አስተናጋጁን ቀና ብሎ ተመለከተን፡፡
"አገኘኋት፤ የካሸር ቦታ ላይ ተቀምጣ፡፡ አቀርቅራ ስራዋን እየሰራች፡፡ ራሷ ናት፡፡ ደርቄ በቆምኩበት ቀና ብላ አየችኝ፡፡ ይገርምሀል ወዳጄ… ስታየኝ አልሳቀችም፣ ከተቀመጠችበት አልተነሳችም፡፡ ሁለታችንም ጊዜና ቦታ ስርዓታቸውን ስተውብን ባለንበት ደርቀን ቀረን፡፡"
"ምነው አትተዋወቁም እንዴ…?”የሚለው የጓደኛዬ ድምፅ ነው፣ ከተበታተንበት ቅፅበታዊ የትዝታ ወንጭፍ አስፈንጥሮ የመለሰን፡፡
ተቀጥራ እንደምትሰራ ብትነግረኝም ከግድግዳው ላይ ያለውን የንግድ ፈቃድ አይቼ ቡቲኩ የሷ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ለምን ይህን እንዳደረገች ግን ማወቅ አለብኝ፡፡ ስለዚህ ስላለው ነገር ላወያያት፣ ተስፋ ካለኝ ልትነግረኝ፣ የፈገግታዋን ብርሀን የኑሮ ደመና መጥቶ ከምድር ገፅ ላይ ካላጠፋው፣ አሁንም ልቧ እኔን መጠበቅ ችሎበት ትዕግስትን ካስለመዳት፣ አሁንም ቃላቷ ሳይዛነፍ እወድሀለሁ ካለችኝ ብዬ ቀጠርኳት፡፡ ያልኳት ቦታ መጣች፡፡
ስንገናኝመደናገጥ፣ ፍርሀት፣ የፍቅር ንዝረት፣ የህይወት ጥማት፣ ተስፋ፣ የናፍቆት ርቀት፣ ዝምታ…ብቻ የዛች ቅፅበት ላይ በምድር ላይ ያሉ ስሜቶች ሁላ እኛ ውስጥ ገብተው የሰው ልጅ ሁሉ ባዶውን ያስቀረነው እስኪመስለን ድረስ በጥልቀት እየተያየን ሳለን ስለተፈጠረብን ሀሳብ ምንም አልበልህ፡፡
ጠየኳት…. "ለምን ሎዛ…ለምን ያንን ሁላ ማንነቴን ይዘሽ ተሰወርሽብኝ?"
መለሰች…"አንተስ የዛን ቀን የት ነበርክ? ስጠብቅህ ምን ሰወረህ? ጠብቄህ እኮ ነበር በረከት፡፡"
መለስኩ… "ይገባኛል ሎዛዬ…የዛን ቀን የቀረሁት…"
አቋረጠችኝ…"አግብቻለሁ ቤኪ…ትዳር ይዣለሁ፡፡"
የመጨረሻ ጥያቄ…"ለምን?"
የመጨረሻዋ መልስ…" ታውቃለህ በረከት---እናቴ እንዴት እንዳሳደገቺኝ ታውቃለህ፡፡ መከራዋን አብረን አውርተንበታል፡፡ እኔም ቃል ገብቼላታለሁ፡፡ ያጎደልኩባትን ህይወት እንደምመልስላት፡፡ ስቃይዋን እንደ ጠዋት ጤዛ ከትዝታዋ ውስጥ አቅልጬ ልሸኝላት ቃል ገብቼላታለሁ፡፡
"ካንተ ተለይቼ አዲስ አበባ ስመጣ እናቴ ቀድማ ለአንድ ባለሀብት አጭታኝ ደረስኩኝ፡፡ አልዋሽህም እናቴ ላይ እናደዳለሁ ብዬ ከማስበው በላይ ነው የተናደድኩባት፡፡ ሆኖም ኑሯችንን ታውቀዋለህ፡፡ ግዴታ የሁለታችንንም ህይወት የሚቀይር አጋጣሚ ካገኘሁ ወደ ኋላ እንደማልል ታውቃለህ፡፡ ገባሁበት፡፡ ነገር ግን እንደፈራሁት አልነበረም፡፡ የታጨልኝ ሰው በእድሜ ከኔ ከፍ ቢልም መልካም ሰው ነው፡፡ ብዙ ነገር ቃል ገብቶልኛል፡፡ ከጊዜም ብዛት እየወደድኩት እየመጣሁ ነው፡፡ አንተን ግን ያላሰብኩበት ቀን ትዝ አይለኝም፡፡ የምሬን ነው ቤኪ…እወድሀለሁ፡፡ እወድሀለሁ እኮ…"
ይህቺ ሎዛ…
ተናደድኩኝ፡፡ መልስ ሳልሰጣት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወጣሁ፡፡ ረዥም መንገድ እያሰብኩኝ ተጓዝኩ፡፡ ትዝ አለችኝ…የእናቴን ሞትና የሎዛን ከኔ መለየት እያስታወስኩኝ የምፈተንበት የፈተና ወረቀት ላይ የወደቀችው እንባዬ…፡፡ እወዳት ነበር…አሁንም እወዳታለሁ…ነገር ግን አሁን ላይ ባለትዳር ነኝ፡፡ አንድ እጅግ የተባረከ ወንድ ልጅ ከባለቤቴ ወልጃለሁ…"
ድንገት ቀና ብሎ ተመለከተኝ፡፡ ፊቱ ያሳዝናል፡፡ ምንም ነገር ማሸነፍ አቅቶት ለመኖር ብቻ የሚታገል ወታደር ያየሁ መሰለኝ፡፡ አፍቅሬ የማውቅበት ቀን አሁን ላይ ትዝ ባይለኝም፣ እውነተኛ ፍቅር እንዴት እንደሚያደርግ ሊያሳውቀኝ የመጣ የፍቅር መሲህ ሆኖ ታየኝ፡፡
"አሁንም ጅኔን እየጠጣሁ ፈገግታዋን አሰላስላለሁ፡፡ ከትውስታዬ መዝገብ መዝዤ እያወጣሁ ፈገግታዋን አጠናዋለሁ፡፡ ትንግርቴ ነው…ፈገግታዋ፡፡"
ስልክ ተደወለለት፡፡
"ኦ…ስለተፈጠረችብኝ ሄዋን እያወሳሁ የተፈጠረችልኝ ህይዋኔ ደወለች፡፡" ከተቀመጠበት ተነስቶ እኔና አስተናጋጁን አፈራርቆ ካየን በኋላ፤
"ይሄው ነው፡፡ አንድ ቀን …የአንድ ቀን ምትሀት እዚህ ድረስ ይከተላል፡፡ እናንተም እድላችሁ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአንድ ደቂቃ ውስጥ እንዳያመልጣችሁ አድርጋችሁ ቅፅበቶቻችሁ ላይ አርምሞ አድርጉባቸው፡፡ ጅኑ ከትዝታዬ ጋር ተቀላቅሎ መንገዴን ሳያስተኝ በፊት ወደ እጣፈንታዬ ላዝግም፡፡ "
በረከት ጨብጦኝ ወጣ፡፡ እነዚህን ሰዎች ሚስጥራዊው የሁለንታ መለኮታዊ ጊኦሜትሪ መልሶ እንዲያገናኛቸው አስቤ ሳይሆን ታሪኩን ብታውቅለት ብዬ በማሰብ…ከዛም በላይ ብዕርና ወረቀትን የማዳራበት ሱሴን ለመወጣት ጊዜ ሳላባክን ቤቴ ገብቼ ሌሊቱን ስፅፍ አደርኩ፡፡ አሁን እናንተ የጨረሳችሁትን ታሪክ፡፡

Read 729 times