Saturday, 25 November 2023 19:32

ህብረት ባንክ ጠቅላላ ሀብቱ 84 ቢ. መድረሱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው
ለ10 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች 15 ሚሊዮን ብር ለግሷል


ህብረት ባንክ ጠቅላላ የሀብት መጠኑ 84 ቢሊዩን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ይህን የገለፀው የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል እያከበረ ባለበት ወቅት ነው፡፡
ባንኩ ከትላንት በስቲያ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል 25ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን፣ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሰራተኞች፣ የሌሎች ባንኮች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ማክበር የጀመረ ሲሆን፤ ለ10 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች 15 ሚ.ብር መለገሱም ታውቋል። ባንኩን በትጋት ላገለገሉ ሰራተኞችም እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ፤ የባንኩን የ25 ዓመት ጉዞና እድገት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት ባንኩ በፆታ በእድሜ በመልክ “አምድርና በማንኛውም ሁኔታ ሳይገደብ ሁሉን አሳታፊና አቃፊ እንዲሆን ተደርጎ በ1991 ዓ.ም መመስረቱን ያስታውሳሉ። “በህብረት ሰርተን በህብረት እንደግ” በሚል መሪ ቃሉ ብዙዎችን አቅፎ እየሰራና በየዓመቱ ትልልቅ ለውጦችን እያስመዘገበ የግል ከአገሪቱ ግንባር ቀደም ባንኮች አንዱ መሆን እንደቻለም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡ “ባንካችን በተቀማጭ በብድርና በትርፍ ደረጃ ከ25-30 በመቶ እያደገ የመጣ ሲሆን በቴክኖሎጂም ቢሆን ከ15 እና ከ16 ዓመታት በፊት ኢንተርኔትና ሞባይል ባንኪንግ በማይታወቅበት ዘመን ቀድሞ የጀመረ ስመጥር ባንክ ነው” ሲሉም አብራርተዋል-ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ፡፡
የኮር ባንኪንግ ሲስተም የሚሰራው በውጪ አገር ዜጎች ነው ያሉት ሃላፊው፤ ይሁን እንጂ ህብረት ባንክ ግን የውስጥ አቅሙን በማዳበር፣ በውጪ ዜጎች ላይ ያለውን አመለካከት ሰብሮ በራሱ ሰራተኞች ማሰራቱንና በዚህም 1ሚ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ የሞባይል መተግበሪያም እንደዚሁ በባንኩ የውስጥ አቅም መሰራቱ የተጠቆመ ሲሆን ከአፍሪካም ከኢትዮጵያም ባንኮች የህብረት ባንክን ተሞክሮ እየወሰዱ መሆኑንና ሶስት የኢትዮጵያ ባንኮችም የህብረት ባንክን ፕላትፎርም ለመጠቀም ስምምነት መፈራረማቸውን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡ባንኩ በ25 ዓመት ጉዞው ካሳካቸው አንዱና ዋነኛው ዋና መስሪያ ቤቱን ለገሀር አይን በሆነ ቦታ ላይ መገንባቱ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ በ2021 ዓ.ም መመረቁንና ግንባታውም 6 ዓመታት መፍጀቱን ተናግረዋል። የባንኩ ህንፃ ባለ 32 ወለል ሲሆን አራት ቤዝመንቶች ያሉት እጅግ ዘመናዊ ህንፃ ነውም ተብሏል። ባንኩ ለ20 ዓመት ያገለገለውን ሎጎ በመቀየር ትርጉም ያለውና ለባንኩ ስያሜ የሚመጥን አዲስ ሎጎ ማሰራቱን አስታወሰው አዲሱ ሎጎ የሁለት እጅ ትስስር የገበሬውን የገመድ ጉንጉንና የሐበሻ ልብስ ጥለትን ያጣመረ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለውም ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓን ለቀጣዩ አንድ ዓመት በፎቶ ኤግዚቢሽን፣ በበጎ አድራጎት ትጉህ ሰራተኞች በመሸለምና በተለያዩ ተግባራት እስከ ሰኔ ድረስ ማክበሩን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሀብቱ 84 ቢሊዩን የደረሰ ሲሆን የቅርንጫፎቹ ብዛትም ከ475 በላይ መድረሳቸውንና ከ8ሺህ በላይ ሰራተኞ ማፍራቱን የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ገልፀዋል፡፡

Read 1391 times