Saturday, 25 November 2023 21:00

ነጃሳው!

Written by  በውድነህ ክፍሌ
Rate this item
(6 votes)

መቼም ወደ አእምሮ አንድ ነገር አይግባ፤ከገባ ገባ ነው፤ምንም ማድረግ አይቻልም። ‘ምን ገባ ወደአእምሮዬ!?’ የአህያ ነገር። የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል አይደል ነገሩ?
ደግሞ የሚያናድደው እርቦኝ ጥብስ ነገር እየበላሁ መሆኑ ነው። የአስተኛኘኬ ማርሽ እየተለወጠ ሲሰማኝ ይታወቀኛል፤ነገር ገብቷላ።  ከራስ ጋር እንደ መጨቃጨቅ የሚሰለች ነገር የለም፤ችኮነት፣ድርቅና ይበዛዋል። ትተኸው አትሄደው ነገር እሱ አንተ ነህ፤ወይንም አንተ እሱ ነህ።
“ይሄ ስጋ የበሬ ስጋ አልመሰለኝም!” ሲል ነገር ፈለገኝ - የገዛ አእምሮዬ።
የምመዠርጠውን ገንዘብ እያወቀ እንዲህ ይባላል? እርሜን ስጋ ልብላ ብዬ፣አቅጄ ብበላ አንደኛው ማንነቴ ነጀሰኝ።
“ቃናው አልቀየረብህም ?” ሲል ደገመልኝ፤ነጃሳው።
ንጀሳው አናዶኝ እንዲህ ስል የመልስ ምት ሰጠሁት፤ “ጥብስ እንዲህ ጣፍጦኝ አያውቅም! ምርጥ ደረቅ ጥብስ ነው!” ቅስሙን ልሰብረው ፈልጌ ነው።
“ደረቅ ጥብስ ሊሆን ይችላል። ግን የምን?”
እንዴት ያለው ችካችኮ ነው? የእሱን ድምፅ ላለመስማት የአእምሮዬን ጆሮ ደፈንኩና ዙሪያ ገባውን በዓይኔ  አማተርኩ። ወጭ- ወራጁ በትዝብት የሚመለከተኝ መሰለኝ።
“ሰው የሚያይህ በድፍረት አደባባይ መሐል የአህያ ስጋ መብላትህ አስገርሞት ነው!” አለኝ ነጃሳው፣ጮክ ብሎ።
የግዴን ጥብሱን እያጣጣምኩኝ ወደ ሉካንዳው ቤት አይኔን ጣል አደረኩኝ። ስጋ ቆራጩ በስርቆት ሲመለከተኝ አየሁ።
“ለምን እንዳየህ ታውቃለህ?” አለኝ አሻጥረኛው ማንነቴ።
ነገሩን ቀለል አድርጌ “ድንገት ነው የተያየነው፤ ሚጥሚጣ ወይንም እንጀራ የፈለኩ መስሎት ነው!” አልኩት፣ከራሴ ጋር እየታገልኩኝ።
“አይደለም! የአህያ ስጋ እንደሆነ የደረስክበት ስለመሰለው ተጠራጥሮ ነው!” አለኝ።
አሁን እንዲህ ይባላል? ምናለበት የማኝከውን ስጋ እስክውጠው ቢጠብቅ።
አልዋጥ ያለኝን ስጋ ግራና ቀኝ ጉንጮቼ ውስጥ ማንከራተት ጀመርኩኝ። ጥርሴ ራሱ ለስጋው ባዕድ የሆነ መሠለኝ፤እያሰላሰልኩኝ ስጋውን እንደማስቲካ እያላመጥኩ፣ ፊቴን አጨፍግጌ ወደ አስፋልቱ መመልከት ጀመርኩ።
ያ ተንኮለኛው ማንነቴ፣ነጃሳው ሀሳቤን ተመርኩዞ ነገር ይሰነጥቅ ጀመር።
“ትዝ ይልሃል? አስፋልቱ ላይ የማይጠፉት እነዚያ ሦስት አህዮች?”
“ምን ያለው ከይሲ ነው! ደግሞ ምን ሊለኝ ነው?”
ቀጠለ። “እንደውም አንደኛው አህያ በሦስት እግር ነው የሚሄደው! እንደ ባጃጅ!”
ምነው ብትተወኝ ልለው ስንደረደር፣ ወሬው እንዳይቋረጥበት ፍጥነቱን ጨመረ።
“ሁለተኛው አህያ ደግሞ ‘መኪና ገጨው ‘ተብሎ የቀኝ እግሩ እንደ ደጋን ተቆልምሞ፣ የግዱን ነበር የሚራመደው፤ተማሪዎች እንደውም ፔንዱለም ይሉታል!”
በስጨት ብዬ “ይሄን ሁሉ ለምን ትነግረኛለህ!?” አልኩት።
“አይ ገርሞኝ ነው። አህዮቹን አይቻቸው አላውቅም!” ሲል ልቤ በድንጋጤ ጮኸ።
አንዴውኑ “አልታኘክ ያለህ ስጋ የእነሱ ነው” አይለኝም? ታርደዋል፣ ለገበያ ቀርበዋል ሊል ፈልጎ ነው።
ጭንቅ ጥብብ አለኝ፤ስለ አህዮቹ አሰብኩኝ። ነጋ-ጠባ ተገትረው ነበር የሚታዩት። የመኪና መንገድ እየዘጉ ጭምር መሰናክል ይሆኑ ነበር፤ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እኔም አይቻቸው አላውቅም።
ሉካንዳ ቤቱ ላይ ተበልተው የተንጠለጠሉት እነሱ መስለውኝ በዝግታ፣ በጎንዮሽ አምፖል እንደ ፀሐይ በደመቀበት ስጋ ቤት ዘወር አልኩኝ።
ስጋው ላይ የአይኔ ጨረር ተተከለ። የተንጠለጠለው ስጋ የበሬ አልመስል አለኝ፤ ላተተብኝ፤ታላቁ ታናሽ ሆነብኝ። ጎድኑ አነሰብኝ፤ደቀቀብኝ። ከስጋው መሀል የሻኛ ስጋ አጣሁበት። አህያ ሻኛ የላትም ስል አሰብኩኝ። በሬው የተሞሸረበት ሉካንዳ ቤት በአህያ ስጋ ያጌጠ መሰለኝ።
ስጋው መሀል ስለት ይዞ የቆመውን በላች፤ ተመለከትኩት። የእኔና የስጋ ቆራጩ አይን ተፋጠጠ። ቆራጩ በአይኑ ‘አይለመደኝም! አታዋርደኝ! አላስከፍልህም!’ የሚል ተማጽኖ ያቀረበልኝ መሰለኝ።
“አላልኩህም?” ይላል፤እኔ ውስጥ ያለው ነጃሳ፤ኢያጎ።
እኔና ቆራጩ አይናችን ተፋጧል፤አስተያየቱ እውነቱን አረጋገጠልኝ። የማኝከው ስጋ እንደ ኮረንቲ መላ ሰውነቴን ነዘረው። አጥወለወለኝ፤ወደላይ ታገለኝ፤ልቆጣጠረው አልቻልኩም።....
ከተቀመጥኩበት ድንገት ብድግ እያልኩ አካባቢውን በጩኸት ደባለቅሁት። ወደሌሎች ተመጋቢዎች እየቃኘሁ፣ ጮክ ብዬ መናዘዝ ጀመርኩኝ።
“ወገን የምትበሉት የአህያ ስጋ ነው!...የምትበሉት የአህያ ዱለት ነው! የምትበሉት ቅቅል የአህያ ጎድን ነው። የምትበሉት...” አልኩኝ። የሁሉም ፊት ማስመለስን ለመውለድ ሲያምጥ ተመለከትኩኝ።
ስጋ ሻጩ ፊቱ በንዴት እየተንቀጠቀጠ ስጋ የሚበልትበትን ቢላ ይዞ ሲቀርበኝ ምን እንደምለው ግራ ተጋባሁ፤መረጃ ቢለኝ ማንን ላቀርብ ነው? ያ ተጠራጣሪው፣ነጃሳው ማንነቴ እንደሆነ ለምስክርነት አይበቃም። ስለዚህ ያለኝ አማራጭ “እነዚያ አህዮች የት ሄዱ!?” ብዬ ላፋጥጠው ተዘጋጀሁ።
ግና ምን ያደርጋል። “የሰፈሩ አህዮች የት ጠፉ!?” ለማለት በዝግጅት ላይ እያለሁ ሦስቱ አህዮች ከመንገዱ ዳር ወደአስፋልቱ መሀል እያነከሱ ሲገቡ በዓይኔ በብረቱ ተመለከትኩኝ።
ያ ነጃሳ ነጅሶኝ ቀልብ አሳጥቶኛል።
እኔኑ ይበልተኝ እንጂ ምን መልስ አለኝ!?

Read 459 times