Saturday, 02 December 2023 19:40

ኢትዮጵያ በከፋ ችግርና የደህንነት ስጋት ውስጥ ትገኛለች ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ፍላጎት የለውም ተብሏል የአሜሪካ ህግ አውጭ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መክሯል
     የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክዕክተኛ ማይክ ሐመር
                          
        የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሲመክር ውሏል፡፡ ምክር ቤቱ በቀጥታ በሚተላለፈው የውይይት ውሎው አገሪቱ በከፋ ችግርና የደህንነት ስጋት ውስጥ እደምትገኝ ገልጿል፡፡
ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው በዚሁ የምክር ቤት ውሎው በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልኡክ ማይክ ሀመር እና በአሜሪካ አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ አይ ዲ) የአፍሪካ ቢሮ ረዳት ሀላፊ ቲለር ቤከልማንን ምስክርነትንም አድምጧል፡፡ ምክር ቤቱ የሁለቱን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ምስክርነትን ባደመጠበትና በጉዳዩ ላይ በስፋት በተወያየበት በዚህ ስብሰባው አባላቱ ለሁለቱ የስራ ሃላፊዎች በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጪ ጉዳዮች የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጆን ጄምስ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግኑኝነት እየሻከረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
“ስለኢትዮጵያ ብዙ ባወኩ መጠን የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው ተረድቻለሁ” ያሉት ጆን ጄምስ የኢትዮጵያ መንግስት ብቸኛ ፍላጎቱ እየተባባሰ ለመጣው የምጣኔ ሃብት ችግሩ ከአሜሪካ መፍትሄ ማግኘት ነው ብለዋል፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ማጥራትና የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግኑኝነት መፈተሸን አላማው ባደረገው በዚሁ ስብሰባ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሀመር ልዩ መልእክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ማስቆምና ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዘ ውጥረቶችን ማርገብ ላይ ትኩረት አድገው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ስራ በጀመሩበት ወቅትም ወደ ቱርክና የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች አቅንተው የቱርክ መንግስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለኢትዮጵያ ጦር መስጠቱ አሜሪካንን እንዳሳሰባት መናገራቸውን ጠቁመው ድሮኖቹ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ የበለጠ እያወሳሰቡት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
“በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚፈፀሙት ከህግ ውጪ የሆነ  ግድያዎች ስቃዮችና እስሮች በእጅጉ አሳስበውናል ያሉት ማያክ ሃመር ይህንንም ለኢትዮጵያ መንግስት በግልፅ ማሳወቃቸውንና የሰብአዊ መብት መከበር የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና አካል መሆኑን ግልፅ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
 አያይዘውም በአገሪቱ በሚታየው የሰብአዊ መብት አያያዝ ደስተኛ እንዳልሆኑና ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚታየው ተስፋና ስጋት በሚል በአሜሪካ የህዝብ  ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ በተደረገው በዚሁ ሰፋ ያለ ውይይት ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሃመር ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እጅግ ከፍተኛ በሚባል የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ መግባቷን ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡ የውጪ ምንዛሬ ክምችቷ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መውረዱን የገለፁት ልዩ መልእክተኛው የዋጋ ግሽበቱ ባለፉት ሁለት አመታት በአማካይ 30% መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ተጠቃሚ ሆና ከቆየችበት የአፍሪካ የእድገትና እድል ድንጋጌ (አጎዋ) መታገዷን ያስታወሱት ማይክ ሃመር በኢትዮጵያ የቀጠለው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት አገሪቱ የአጎዋ እድልን ዳግም ተጠቃሚ የምትሆንበትን እድል እንዲያሳካ ሊያደርግ ይችላልም ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ “የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” የሚለው ንግግራቸው በቀጠናው ካሉ አገራት አልፎ ለአሜሪካም ከፍተኛ የስጋት ምንጭ እንደሆነ የተናገሩት ማይክ ሃመር ቀጠናውን ዳግም ለጦርነት ከሚዳርጉ ጉዳዮች መቆጠብና ግጭቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሃመር በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲያደራድሩ መቆየታቸውን አስታውሰው በአማራ ክልልም እድሉ ከተሰጠ ሰላማዊ ንግግር እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል፡፡



Read 1999 times