Saturday, 02 December 2023 20:36

ከበሮአዊ አስተማስሎ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ በወፍ በረር ቅኝት

Written by  በትሬዛ ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ሙዚቃ ድም ድም ካላለ፣ እስክስ ካላስባለ፣ ወገብ ካልነቀነቀ፣ ዳሌ ካልወዘወዘ፣ ትከሻ ካላስመታ ምኑን ተሞዘቀ? ይላሉ የሀገሬ ሰዎች። ለዚህም ነው በሀገረኛ ሙዚቃዎቻችን (Folks songs) ላይ እስክስና ውዝውዝ የሚበዛው። ጠንከር ያለ ስልተምታዊ የሙዚቃ ባሕል (strong rhythmic music culture) ካላቸው ሕዝቦች ተርታ እንመደባለን። ከበሮኛ ነው ጨዋታችን። እስቲ ይሄን ጨዋታችንን ከየቀዬው እየዘለቅን እናውጋ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኘው ከወላይታ ብሔረሰብ እንጀምር።ጠንካራ ስልተምት ያለው የሙዚቃ ባህል (strong rhythmic music culture) አላቸው። ያለ ድም ድም ያለ ግም ግም ፣ ያለከበሮ ጨዋታም የላቸው። በአፍቃሪ ከበሮነታቸው ምክንያት ብዙ አይነት ከበሮ አላቸው። ባለ ሁለት በኩል ምቱ እና ባለ አንድ በኩል ምት ከበሮ ወይም ሴቴ ከበሮና ወንዴ ከበሮ ብለው የሰየሟቸው ከበሮዎች አሏቸው። ወንዴ ከበሮ ተለቅ ብሎ እንደ ተብአት የጎረነነ ድምጸት ያለው ሲሆን እንደ ስልተ ምት መቀየሻና ማስጀመሪያ ይጠቅማል። ሴቴ ከበሮ  አነስ ብላ ቀጠን ያለ የተሽኮረመመ ድምጽ ታወጣለች። የወንዴውን ከበሮ ስልት ተከትላ ትገባና ሙዚቃውን ታሞቀዋለች። ይሄኔ ነው ልጃገረዶቹ ድምጻቸውን አስረቅርቀው ዜማውን የሚጀምሩት። የውዝዋዜው ስልት በወንድየው ከበሮ ስልት የተቀነበበ ሲሆን ሴቴዋ ማሰማመሩ ላይ ትሰራለች።
በወንዴው ከበሮ ድልቅታ እንስቶቹ ያሾሩት ወገባቸው ዳሌያቸውን ሲወዘውዝ የተመልካቹ አይን አብሮዋቸው ሲቅበዘበዝ ልብ አብሮዋቸው ይደልቃል ስልታቸውን ተከትሎ። ወንዱም እንዲሁ ድልቅታው አርቆ ያስፈነጠረው ያህል አየር ላይ ከመንሳፈፍ ጥቂት ተርፎ መሬት ይረጋል። ደግሞ ሲደለቅ ደግሞ ርቆ ይስፈነጠራል። ታዲያ የዚህ ሁሉ ትርዕት መሪው ከበሮ መቺው ነው። እሱ ስልትን ያፈጠነ እንደሆን እንቅስቃሴን ማፍጠን፤ ያለዘበ እንደሆን ማረጋጋት ነው። ከበሮኛ ነው ሙሉ ትርሂቱ።
ከጎረቤቶቻቸው ዳውሮ የዘለቅን እንደሆነም እንዲሁ በተመሳሳይ ባለሁለት በኩል ምት ከበሮን አንግተው ከጫቻ ዛዬ (ትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ) ጋር ስልቱን ተከትለው ይሞዝቃሉ። በከበሮና በጫቻዛዬ ብቻ የሚሰራ ሙዚቃ ቅንብር (Instrumental composition) ይሰራሉ። በሀገራችን ለዚያውም በሀገር በቀል ሙዚቃ (folk tune) የመሳሪያ ብቻ ቅንብር የተለመደ አይደለም። በዳውሮ ግን ይሄ በሚገርም ስልት ይቀናበራል። ከበሮአዊ ስልቱም አስፈንጥሮ አስነስቶም ይወዘውዛል።  
እስቲ ደሞ ወደ ጋሞዎች እንዝለቅ። የከበሮ ጨዋታቸው አይጣል ነው። ልክ እንደ ወላይታ ብዙ የከበሮ አይነቶች አሏቸው። ባለሁለት በኩል ምት የሚነገት፣ ባለአንድ በኩል ምቱ ሴቴና ወንዴ ከበሮች አሏቸው። የዜማ ስልታቸው እንደ አብዛኛውን የደቡብ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ሙዚቃ ስልተምት (rhythm) የሚጎላበት ብቻ አይደለም። በጣም ዘመን አይሽሬ የዜማ አወቃቀር አላቸው። በአከባቢው ዜመኞቹ እንስቶች ናቸው። ዜማቸው ባለአንድ ድምጽ (single line melody) አይደለም። ይልቁንስ ህብረድምጽ (harmonycal)እና ምልልሳዊ ዝማሬ(contrapuntal) ነው። የተለያዩ ድምጾችን በአንድ በማዋቀር መዘመር። በሀገራችን ሀገር በቀል ሙዚቃዎች ላይ ያልተለመደ አይነት ነው። በጣምም ረቂቅ ነው። ስልተምታቸውም በአንድ ጊዜ ሁለት አይነት መጫወት ይችላሉ።
ይሄ ደግሞ እጅጉን የረቀቀ እውቀትና ጥበብ ይጠይቃል። መጀን ነው መቼም ለጋሞዎች! የረቀቀ የስልት አወቃቀራቸው በአንድ ሙዚቃ ጨዋታ ላይ ብቻ የተለያየ ከበሮ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል የስልት ውህደት ለመፍጠር። እነሱ ጋ ከወላይታ በተቃራኒው በከበሮ ንሸጣ የምትዘለው እንስቷ ነች። ደሞም በሙዚቃው ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው እንስቶች ናቸው በአከባቢው።  የሙዚቃ ስልጣኔያቸውም እጅጉን የረቀቀ ነው።
እስቲ ደሞ ከደማቅ ዠንበሪቱ ምድር ከሀመር አብረን እንዝለቅ። ከነካሎሆራ ቀዬ። እነ ካሎሆራ ከበሮኞች ብቻ ሳይሆኑ ቃጭሀኞችም ናቸው። በከበሮ ድልቅታ ተስፈንጥሮ ካየር ላይ የተንሳፈፈ እግራቸው ተመልሶ ከቀዩ አፈር ሲላወስ ቃጭላቸው ስልቱን ተከትሎ አይንና ጆሮን እኩል ሲያጥበረብር ነፍስ እንዴትስ ትርጋ?  ነገረ ስራቸው ደማቅኮ ነው። አፈራቸው ቀይ ደማቅ፣ ዠምበራቸው ደማቅ፣ መልካቸው ( አጠያየማቸው) ደማቅ፣ የሙዚቃ ስልታቸው ደማቅ። በከበሮ ድምታ ከአየር የተንሳፈፈው የጉብሎች እግር ከቀይ አፈራቸው ሲላወስ በደማቂቱ ዠምበር ተስተማስሎ ካይን የገባ ውበትስ በምን ይወጡታል? ያ ቃጭላቸውስ በውበት ከጆሮዋችን ተቀድቶም የለ? በስልተምታቸው የቀዬው ጎበዝ ወገቤን ጨምድዶ አንዴ ብቻ እንኳን በወዘበዘኝ? ብዬ እመኛለሁ። ምናለበት በውብ ስልታቸው ብወዛወዝበት?
ወዲህ እንበልና ደግሞ ደራሼዎቹ ቀዬ በክቡ ዙረት ስልት ሳናጓድል እንዝለቅ። እነሱ እቴ እንደነ ሀመሮች ርቀውም አይዘሉ የመሬቲቱን ስበት የሚጠራጠሩ ይመስል። ከእግራቸው ከታሰረው ቃጭላቸው በእጃቸው ከሚያማቱት ሙዚቃ መሳሪያ ውጪ ሚከተሉት ያለም አይመስል። ስልተምት አብራቸው የተፈጠረች ያህል ያውቋታል። ያምኗታል። እሷም ታምናቸዋለች። በነርሱ ስትያዝ ፍጹም አትሳትም። አትፎርሽም። ድም-ድም-ድም... ዙሩን አንዴ ዞረውት ድልቅ! ያስሩታል። ከዛ ሌላ ዙረት ድም-ድም-ድም...ድልቅ!ያስሩታል። ስልት የሚያዘው በእግራቸው ንቅናቄ ነው። ጆሮ ተአምርን ይሰማል እዛ የተዘለቀ እንደሆን። የማይሳት ጠንካራ ስልተምት ፣ ዞረው ሙዚቃውን ሲያስሩት የህይወትን ኑረት ያሰሩት ያህል ይጠነክራል።
እስቲ ደሞ ከወደሰሜን ጫፍ ከሹሩቤዎቹ ቀዬ እንዝለቅ። ስልታቸው እጅግ የተለዬ ነው። የሙዚቃ ላይ የጊዜ አቆጣጠራቸውም (timing) የተለዬ ነው። አምስት በስድስት ይሄዳል። ሀይለምቱ (strong beat) የሚገኝበት ቦታ የተለምዶ አገባብ አይደለም። አታሞአቸው ባለሁለት በኩል ምት ቢሆንም በአንድ በኩሉ ነው የሚመሰጡት። እጅግ ማራኪ የከበሮ ጨዋታ ነው ያላቸው። ዛር አለው፣ ያንዘፈዝፋል! ያሰክራል።
“ያንዘፈዝፈኛል እንደዶ ከብሬ
እጄ ሲርበተበት ይጨፍራል እግሬ።” ( እንዳለው ገብረክርስቶስ ደስታ)
የአታሞ ጨዋታቸው ብቻውን ትርዒት ይወጣዋል። ሙዚቃ በጥበብ፣ በእውቀትና በስሜት ጥምር ይሰራል። ይህ ጥምር በትግራይ አታሞ ጨዋታ ጊዜ ዛረኛ ነው ያንዘፈዝፋል! አስክሮ ጨርቅ ያስጥላል! ከድልቅታ እኩል ብድግ-ብድግ-ብድግ... ስያሾሩትማ አይጣል ነው። አንስተው ካየር ፣ ከመሬት፥ በቁም፣ በምብርክክ ያቁነጠንጣል። በስልቱ የተቃኘው (ውስዋስ) ማለቴ ውዝዋዝ...ዛርም አደል የሚለቀው... ቻሉት ጨዋታዬን የአደዬ ከበሮ የፈጠረብኝ ስካር ነው።
“ በግሬ ጣራ መርገጥ ፤
 ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ
 መፍረጥ፤ ዐይኔን ማገላበጥ፤
መርበትበት መንቀጥቀጥ፤
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፤ተነስቼ ልዝለል፤
ቡጊ ቡጊ ልበል።”
(እንዳለው ገብረክርስቶስ ደስታ)
አዎ ከሹሩቤዎቹ ቀዬ የአታሞ ድልቅታ የተሰማ እንደሆን ዛራም ነው ያንዘፈዝፋል። ልዕለ ስሜት አለው ያሰክራል። መጀን አልሁ እኔስ ከመቀመጫዬ ተነስቼ። ዛሩ ደሞ እስካሁንም አለቀቀኝ።
እስቲ ደሞ ወረድ ብለን ከጎረቤት ሰቆጣ ቀዬ እንዝለቅ። ገና ካቀበቱም አይል ሚጣራ አታሟቸው? ስድስት በስምንት (six eight)  ጊዜ ቆጠራ የተቃኝ ሙዚቃቸው፤ እንጃ ከትካሻ ዳሶ ነው ሚወርድ መሰለኝ  ቀዬ በሞላ ትከሻውን ይወዘውዛል። በከበሮ ድልቅታ የደነገጡ ያህል ከወገብ ድረስ ጎምበስ ቀና፣ ጎምበስ ቀና ጎምበስ ቀና፣ በጃቸው ወገባቸውን ያዝ አርገው አሁንም አሁንም ከስልቱ ጋር ጎምበስ ቀና ደሞ ትከሻቸውን የዛረኛ መምታ! ቺክቺካ ጸደቀች መሰል ከሰቆጣ ስትዘልቅ። አቤት ከበሮዋቸው ጉልበቱ! ያስፈነጥራል።
እስቲ ደሞ ከትካሻ ወርደን ወደ ደረቶቹ ቀዬ ከጎጃም እንዝለቅ። ኧረጌኝ አታሞው ተማዶ ነው ሚሰማ እናንተዬ? ፎጣ ከወገብ ሸብ ተደርጎ በአታሞ ድልቅታ ደረት ሲንቀጠቀጥም አይደል እንዴ ሚውል? እንቅጥቅጥ ይሉታል እነርሱም። የነርሱ አታሞ ደሞ ሲመታ ደረት ነው ሚበላ መሰል ያንቀጠቅጣል። ከነሸጣቸው ጠብመንጃቸውን መዝዘው ወደ ሰማ አንድ ሁለቴ ሳብ ሲሰጡት እውነትም ያንቀጠቅጣል። ተጎጃም ቲዘለቅ ሙዚቃም ጥበብ ብቻ ሳትሆን ወኔም  ነች።
 “ያመጣል ከጫካ ጎበዞቹን ይዞ
ጦር እየሰበቀ ጎራዴውን መዞ
ድምጽ ነው የሹመት
 ወይም የጦርነት
ጠላት መጥቶብሃል ቀስትህን አርቅ” (እንዳለው ገብረክርስቶስ ደስታ)
ተጎጃም አታሞ ተነሽጦ ሳይሆን አይቀርም የሰናኛት። (አሁን ይሄ የከበሮ ጨዋታ ይመስላል የጦርነት እንጅ?) ግን ከጎጃም ቀዬ የዋዛ ጨዋታ አይታሰብም ፤ እንቅጥቅም ከወኔ ነው። የከበሮ ስልትም መፎከሪያ መሸለያ ነው።
እስቲ ደሞ ከፈረሰኞች ቀዬ ከአዊ እንዝለቅ። ፈረስ አሸምነው አልብሰው፤ በፈረስ ድል ነስተው በፈርስ ኮቴ ስልተምት ፈጥረው ሞዝቀው በፈረስ ተሸልመው ያገቡበታል። ፈረስ የሌለው ነገር የለም መሰል ከአዊ ቀዬ። በከበሮ ምታቸው ፈረሱም ሳይደንስ ይቀራል? ስልተምቱን ያውቀዋላ።  ደሞ ከጎረቤታቸው የተለዬ ካንገት፣ ከትካሻ ፣ ከደረት ወርደው ከወገብ በታች ነው የከበሯቸው ድልቅታ የሚወዘዉዘው። ዳሌን ያሾራሉ እደወላይታዎቹ። (ይሄ ግን ከወገብ በላይ ከወገብ በታች  ተቃርኖአዊ ድልቅታ አልተያዘልኝም)
“የፈረሱ ኮቴ ሽምጡ ሶምሶማ
አዋራ ሲያስነሳ ድምፁን የሚያሰማ
ናዳው ሲንከባለል በጩኸት ደረጃ
መሬት የሚያናጋ ሰልፍ ነው እርምጃ
ጊዜን የሚለካ ሰዓት እየለየ ሲጠፋ ሲተካ”
(ይላል ገብረክርስቶስ ደስታ)
እስቲ ወዲህም ከዙረቱ ስንመለስ ወደ ፖሊስ ማርሽ ባንድ እንምጣ። እነሱ ደሞ ያለከበሮ ጨዋታ አላቸው እንዴ? ስልተምታቸው ራሱ ሁለት በአራት(two four) ጊዜ የተቀነበበ ነው። እንደውም ስልቱ ከነስያሜው ማርሽ ስልተምት(marsh rhythm) ይባላል። ያለከበሮና ዘሮቹ (percussions) አይሞከርም። ስልተምታቸው በእርምጃቸው ወይም እርምጃቸው በስልተምታቸው የተቀነበበ ነው። የከበሮዋቸው ድልቅታ ልብን የመሰቀዝ ሀይል አለው። ምክንያቱም ስልተምታቸው የልብን ድልቅታ ስልት ይዞ ነው ሚጓዘው።  ታ-ታ-ታ-ታ... ገጭ-ገጭ-ገጭ-ገጭ... የማይሳት በልብ ምት ያጸኑት በእግር እርምጃ ያስተማሰሉት ጽኑ ስልተምት።
ምን ማርሽ ባንዳችን ብቻ ብሔራዊ መዝሙራችን ራሱ ከበሮአዊ አደል እንዴ? በፈረንጅ ጡሩምባ (trumpet) የጀመረው ዝማሬ፤ በከበሮ ውሉን አስይዞ (percussion) ሚሉትን ምጣድ እያማታ ወንያችን እየተንተገተገ ይዘመራል።
ያ የፈረንጅ ጡሩምባ በወኔ ደም አሙቆ ምጣዱ ሲማታ የፈረንጅ ከበሮ ገጭ ሲል (የፈረንጅ ከበሮ እንደኛው ድልቅ የለውም) በጡሩምባው የሾረችውን ነፍሳችንን በከበሮ ድምታ ውሉን አሲይዞን በትራንፔቱ መልሶ ያንሳፍፈናል። ደሞ መልሶ ከበሮ ስልቱን (ውሉን) ያሲዘንና ያገባደዳል። ግርማዊ ነው ድምጸቱ ፣ ግርማዊ ነው ስልተምቱ ያስፈነጥራል። እስቲ እኛም ብሔራዊ መዝሙራችንንም ስለዘመርን ጨዋታችንን ገብረክርስቶስ ስለ ከበሮ በተቀኘው ግጥም እንቋጨ። ከበሮ አለው ሀያል ግርማ አለው፣ አለው፣ አለው
 ከሰው ሀያል ግርማ ይቀሰቅሰኛል
 ጩኸቱን ስሰማ በሰውነቴ ላይ
 ይፈጥራል መሸበር  ያቅበዘብዘኛል
 አለው መስተፋቅር አለው መስተፋቅር
መድፍ የተተኮሰ፣ እሳተ ገሞራ ገንፍሎ
የጨሰ መብረቅ የወረደ፣ ገደል የተናደ
ማዕበል ነጎድጓድ መስሎኝ እቀራለሁ
እደነግጣለሁ። ያንዘፈዝፈኛል እንደዶ ከብሬ
እጄ ሲርበተበት ይጨፍራል እግሬ።
የሠርግ አዳማቂ ነው አዶ ወሸባ
ሙሽራ ሲያባባ
በጩኸት ኳኳታ ድልቅ ድልቅ ብሎ
ሰው የሚያተራምስ ስካር አስከትሎ
ሐዘን መቃብር ነው ጸሎትና ፍትሐት
የሚመታው ደረት፣ያልቃሾቹ ስሜት።
ይጠራል ከጉድጓድ ሔዶ የጠፋውን
ባፈርና ድንጋይ ሊጎሸም ሣጥኑን።
የቤተክርስቲያን የሃይማኖት ፍቅር
የሼኮች ድቤ ነው ያምልኮት መደብር
ያመጣል ሁካታ የጥምቀት ጭፋሮ
ከበሮ፣ ከበሮ።
ያመጣል ጎትቶ ልጃገረዶቹን
“ሆ ብዬ. ሆ ብዬ.” ዕንቁጣጣሽ
 ብለው የሚጨፍሩትን ያመጣል
ከጫካ ጎበዞቹን ይዞ ጦር እየሰበቀ
ጎራዴውን መዞ ድምፅ ነው የሹመት
ወይም የጦርነት ያረመኔ ጥሪ የተነሳ ታጠቅ
ጠላት መጥቶብሃል ቀስትህን አርቅ
የፈረሱ ኮቴ ሽምጡ ሶምሶማ
አዋራ ሲያስነሳ ድምጹን የሚያሰማ
ናዳው ሲንከባለል በጩኸት ደረጃ
መሬት የሚያናጋ ሰልፍ ነው እርምጃ
ጊዜን የሚለካ
ሰዓት እየለየ ሲጠፋ ሲተካ
የሙዚቃ ውሉ ማሰሪያው ሸምቀቆ
ባይጮኽ እንኳን አለ ከስር ተደብቆ፣
የሚያስተጋባ ነው ዜማው ተሰብስቦ
ሂፕ ሆፕ ሮክን ሮል
ቻቻ ቡጊ ቡጊ ዘመናዊ ማምቦ
ዛር ነው ውዝዋዜ
 እብደት ነው ትካዜ
ያካል ንቅናቄ አገሩ ሙዚቃ
 አገሩ ሙዚቃ
 ሰው ያሽከረክራል መንፈስ እያነቃ
አቋርጦ ይመጣል ሲሮጥ ከሩቅ አገር፣
ቤቴን ለመበዝበዝ
ልቤን ለማሸበር፣ ልቤን ለማሸበር
ከበሮ
ከበሮ



Read 276 times