Saturday, 02 December 2023 20:45

በመጥፋት ላይ ያለ እሳት

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(1 Vote)

  [[...የገሃነም ማስፈራሪያ ፣
                 የገነትም ተስፋነት
               አይሽረውም እውነቱን፥ የሕይወትን ጠፊነት።
               ከዚች እውነታ በቀር ፥የለኝም እኔ የማምነው
                አንዴ የሞተች አበባ፥ሞቷ ለዘላለም ነው።]
                    (ድረስ ጋሹ )


        ከጎጆዬ ፊት ለፊት ዋርካ አለ። የአሞራዎች፣ የወፎች፣ የነፍሳቶችና የሰዎች መጠለያ ነው። ቀን ቀን ሰው ይጠለልበታል፤ በራሪ ነፍሳት ያርፉበታል። ማታ ማታ ቦግ - እልም የሚል ነዲድ እሳት ያለው ተንቀሳቃሽ አካል ይቆጣጠረዋል።
ከምሽቱ 3:00 ነው።
በመስኮቴ በኩል እያጮለቅኩ የእሳቱን ምንጭ መቃኘት ጀመርኩ። ከጀርባዬ በኩል ለስላሳ እጅ ድንገት ነካኝ _ሚስቴ ነበረች። በሕይወቴ እንደዛ ቀን ደንግጬ አላውቅም። ላዋራት አቃተኝ፣ ተንቀጠቀጥኩ ። አዳሬ በቃላት ሊመነዝሩት ይከብዳል። ቀናት ያልፋሉ፤ እንደ ሰው ልጅ ሕይወት ።
በዚህ ዕለት የነበረው የ2006 ቱ ቅዳሜ ሞቷል ፤አሁን በዚህ ዕለት ያለው የ2016 ቱ ቅዳሜ ነው። የሞተን በስም ለማቆየት የምንታገለው የበዛ ይመስለኛል። እንዲሁ በሕይወቴ ሆነ። ምንጩን በውል ያልተረዳኹት እሳት ባለቤቴን ከነጠቀኝ ብዙ ዓመት ሆነው።እንደ ሰው እየተራመደ መጥቶ ፣ እጆቹን ሲያነካካ በሚፈጠረው እሳት ላይ አስቀምጦ ሲወስዳት ፈዝዤ ቀረሁ።
መንፈስ ነው አሉኝ ። ባለ እሳት መንፈስ? እጁ እንደ እምቡራቡጭ ሲፋጭ እሳት የሚተፋ ?...ዋርካ ማረፊያው...እንደ ዝንጀሮ የሚንጠላጠል ...?...
ዓይኔ እያዬ እጁ ላይ ስለቀለጠችው ውዴ ብቻ ፍንጭ አለኝ። ስለ መሞቷ ብቻ ዓይኔ ይመሰክራል። ከአጠገቤ ከራቀች በኋላ ስለተፈጠረው አንዳች ማስረጃ የለኝም። ስለ ሕይወት እንድጠይቅ መነሻዬ መሆኗን አምናለሁ።
ከወራት በኋላ ወደ ዋርካው ኼድኩ (ተራርቀን ነበር የቆየነው)። ቅጠሎቹን ጨርሷል። ቅርንጫፎቹ መድረቅ ጀምረዋል። ዓይኔን ማመን አቃተኝ። አሻግሬ ሳይ ሌሎች ዛፎችም ወደ መድረቅ አዝግመዋል። ዛፍ ደረቅ ከሆነ ለማገዶነት ይታጫል _ምናልባት እኔም ስሞት ሥጋዬ ለዘመሚት እንጅ ሌላ አገልግሎት ላይኖረው ይችላል። ከደረቀ እንጨት መርከብ የሰራው ኖኅ፤ «ደረቅነትን»ሳ ሳንሰው እንዳይቃወመኝ እሰጋለኹ። ከመሰበር ወዲያ ሌላ ሕይወት እንዳለ በዓሉ ግርማ በሐዲስ መጽሐፉ እንዳያረዳኝ እሻለሁ።
ዓለት ላይ ሆኖ የሚዘፍነውን ልጅ ዜማና ግጥም ውበት አደመጥኩ። መንፈሴን ወደ አልታወቀ ዓለም አድርሶ መለሳት። ስለ ሕይወት ውብነት ይቀኛል። «መኖር»አፉ ላይ ሶሥቴ ነጠረች። በግርምት እያደመጥኩት እሪታ ተከተለ። ከተቀመጠበት ዓለት ተንከባሎ ገደል ውስጥ እንደገባ ለማየት ደቂቃዎች በቁኝ።  ኦ! ሕይወት ...ኦ  እኛ።
ወደ ዋርካው ከመሄዴ በፊት መልኬን በመስታወት አያለሁ። ከውዴ ሞት በኋላ ያለው ፊቴ የኔ አይደለም። ውበት እንደ አበባ እንደሆነች ይሰማኛል። የፋርሱ ሊቅ ተቀኝቶ ... የገለፀው ግን የእኔን የአሁን ስሜት ነው።
[Oh , threats of Hell and Hopes of paradise!
One thing at least is certain __This life flies;
One thing is certain  and the rest is lies;
The Flower that once is blown for ever dies.]
[[...የገሃነም ማስፈራሪያ ፣የገነትም ተስፋነት
አይሽረውም እውነቱን፥ የሕይወትን ጠፊነት።
ከዚች እውነታ በቀር ፥የለኝም እኔ የማምነው
አንዴ የሞተች አበባ፥ሞቷ ለዘላለም ነው።]]
 ወደራሴ ቋንቋ፣ ወደራሴ ስሜት፣ ወደራሴ መረዳት መለስኩት። የማያቸው ሁሉ የደረሱብኝ ኹሉ በዚች አራት መስመር የተቀነበበች እስኪመስለኝ አስባለሁ። ጸሎቴ ልትሆን ምን ቀራት?...
በሌላኛው ቀን ጠዋት ጥሩምባ ተነፋ። በሰፈራችን ሰው ሲሞት፣ ሰርግ ሲሆን ፣ የቀበሌ ሥራ ሲኖር ጡሩምባ አነፋፍ ይለያያል።የዛሬው አነፋፍ የሞት ነው።
«አቶ ዘላለም ሞቷልና አቃብሩኝ ተብላችኋል።»
የሚለው መልዕክት ተከተለ።«ስሙስ የሚሞት አይመስልም ነበር» ብዬ ጋደም አልኩ። ሰው ሲሞት እንደ ተራ ነገር ማየት ከጀመርኩ ቆይቻለሁ። ይኼ ስሜቴ ነው፤ ከሃገሬ ሕዝብ ጋር የሚያመሳስለኝ። ሁሉም ነገር ቋሚ እንዳልሆነ ከዚህ በላይ ምን ያስረዳልኛል?።ከ ዛሬ 20 ዓመት በፊት ሰው ሲሞት ፊት ይነጭ፣ ይለቀሰ፣ ደረት ይደቃ ነበር ። አሁን «ስንት ሰው ሞተ? »እንጅ እንባ የለም። የሞት መርከስ ኀዘኔታችችንን እኩል ሰርቆናል። ሞትን መላመድ እኩል ቸልተኞች አድርጎናል። ያ ርኅራኄ፣ ያ እንባ፣ ያ ሙሾ፣ ያ ኪነት የት ገባ?...ያላችሁ እንደሆን ሳታውቁት ወደ’ኔ ስሜት ተቃርባችኋል። ምንም ኗሪ /ቋሚ ነገር የለም_ ሕይወትም ብትሆን።
ትንሳኤ ጓደኛዬ ነው ።
ከእርሱ ሐሳብ መቃረን እንደምወድ ያስባል። አሁን ስሙን ስቃወምበት ምን ሊለኝ ነው?..ፊቱን ላየው እፈራለሁ። እኔ ቦታ ቆሞ ነገሮችን ካላየ በቀር ሐሳቤ አይዋጥለትም ። ሁሉም በቦታው እንዳይቆይ የተረገመ ይመስለኛል_በተለይ ውበት።  የሰፈራችን አድባር መልኳ ማረጋረጊያ እንዳልነበር፣ አሁን ላይዩዋት ታስጠገንናለች።
አበቦች ሁሉ ውብ መዓዛቸውን ሳንጠግበው አረግፈዋል ።
ቀናቶች ሁሉ የማይተካ 12 ሰዓት ሰጥተውን አልፈዋል።
ቅጠሎች ሁሉ ከቅርንጫፎቻቸው ተቀንጥሰው ወድቀዋል።
ወጣቶች ሁሉ ከሉጫ ጸጉር፣ ከሰልካካ አፍንጫ፣ ከዓይነ ግቡ ሥርጉድ ሸሽተው ወደ  እርጅና ከትመዋል።
ማን ባለበት የቆመ አለ? ሕይወት ጊዜያውነትና  ተቀያያሪነት ያጠቃታል። ውዴን ከእጄ ነጥቆ የበላት እሳት ትዝታ አለብኝ። ከቅጽበት ያልተናነሰ መገጣጠም።ምራቅ ተተፍቶ እስኪደርቅ ያልቆየ ሁነት።ከ «ነው»  ወደ «ነበር» የፈጠነ ሽግግር።የእኔ የዘላለምነት እሳቤ መናድ።ጊዜያዊነት እንደሚያጠቃን የመረዳቴ ፍጥነት..ኧረ ስንቱ...
ደስታዎች ሁሉ ጥጋቸውን ሳያሳዩ እንዲሁ ፈገግ አስብለው በኃዘን ተተክተዋል።
ግንኙነቶች (የቤተሰብ፣ የፍቅር፣ የጓደኛ) ተቋርጠዋል። ልጅ ከቤት ወጥቷል። ልሙትልሽ ያላት አፍቃሪ ፍቅረኛውን ገድሏታል። ታማኝ ያሉት ጓደኛ በርካሽ ዲናር እንደ ይሁዳ ሸጧል።
ሁነቶች በፀሐይ እንቅስቃሴ ተመርኩዞ እንደሚከረባበተው እንደ ጥላችን አቅጣጫ ይቀያይራሉ። እንደ ቀታይ ማዕበል በዜማ እያባበሉ የተወሰዱ አሉ።
ይኼን ኹሉ ትንሳኤ አያምነኝም። ሁሌም በእሱ ፊት እሳት ነኝ ሁሌ። ውኃ እሳትን ቢያጠፋው፤ እሳት ውኃን እንደሚያፈላ ይረዳል። እኔም የደረሱብኝን ሳልደርስ እንደማለቃቸው ያውቃል። የገባሁበት የሕይወት ጥያቄ ምናልባትም አለመለከተው ብሎ አይደለም። የእኔን ንትርክ ከዳር ቆሞ ማየት ስለሚሻ፣ ስለ ውዴ የምጽፈውን የኀዘን ግጥም ላለማድመጥ ይሆናል።
ሰማይ ላይ የሚታዩት ደመናት ቅርጻቸውን በየሰዓቱ ይቀይራሉ። አሸዋ ላይ ያሳረፍነው የእግር አሻራ በቀላል ንፋስ ቅርጹ ይጠፋል። በእጅ የያዙት በረዶ ቀልጦ ያልቃል። ከሰማይ ተገፍትራ የመጣች የዝናብ ጠብታ የምድር ንቃቃት ከተቀበላት ትዋጣለች። ከቤተሰቧ ተነጥላ የምትወረወረዋ ኮከብ_ስትመለስ አትታይም። በብርድ ቀን የምንተነፍሰው ይታያል፤ በሙቀት ጊዜ ግን አይታይም።
 ይኼ ሁሉ ለትንሳኤ ደንታው አይደለም። አይጠይቅም፤ መጠየቅም አይፈልግም። በኮረጆው ጥቅሶች አሉት _የአፍ ማዘጊያ። እኔ ጊዜያዊነት ዋጋ ያስከፈለኝ ግን ስለዚህ ጉዳይ ላወራ ግዴ ነው።
ክርስቶስ ምድር ላይ ሰብኳል _ለጊዜው።
ነገስታቱ ይቺን አገር አስተዳድረዋል_ለጊዜው ።
የሄሚንግዌይ  «The snow of Kilimanjaro » ተረክ፣ የሮበርት ፍሮስት «Nothing Gold can ay» ግጥም ህመሜን ያባብሳሉ። እሳት ላይ ጋዝ ማርከፍከፍ የወደዱት ለምንድን ነው?...
ከትንሳኤ ጋር ተገናኘን ።
«ጠፍተህ ሰነበትክ፤ በሰላም ነው» (ድንገት ጠየቅኩት)
«ለመናፈቅ »
«ከዓይን የራቀ ከልብ ይርቃል»
«ድሮም የአንተን ልብ የአመጽ እርሾ ነው የሞላት።» (ፊቱን አጠፈብኝ)
ወደ ዋርካው ኼደን ተቀመጥን ። መንገዶች ሁሉ መዳረሻቸው ዋርካው እንዲሆን ሆነው ተሰርተዋል። ስለ ውዴ እና እኔ ያለፉ ቀናቶች ተረኩለት። «እንደወጣሁ እንዳልቀር»ማለት ታበዛ እንደነበር በወሬዬ መሐል ትዝ አለኝ። አንገቱን እየነቀነቀ ያባሁትን እስክናገር ጠበቀኝ ።
«አይበቃም?» (ድንገተኛ ጥያቄ ጠየቀኝ )
ተንተባትቤ ዝም ስል ብሶቱን ይደረድርልኝ ያዘ ።
ዋርካው እሳት ወለደ (ውዴን በመዳፉ ይዟት የጠፋውን)። አየነው በድንጋጤ። መዳፉ ላይ ፍዝ እሳት አለ። አጠገቤ ያለው ትንሳኤም እንዲሁ እየፈዘዘ ያለ እሳት ነው።
ለመጨረሻ ጊዜ።
ለመጀመሪያም ጊዜ።
«እውነትም ነገሮች ባሉበት አይቆሙም» አለኝ።
ሜዳ ላይ ያስቀመጡት ድንጋይ በዓመቱ ወይ ተንሸራቶ ወይ ተወርውሮ ይገኛል። ሜዳ ላይ የጣሏት ዘር አድጋ ተመንድጋ ታሸታለች። «ሚጣ ስታድጊ ልምጣ » ብለው ያለፏት ህጻን፤ በውሎ በአዳር ነፍስ አዋቂ ትሆናለች። ነገሮች ሁሉ በአሉበት አይቆሙም። ትንሳኤ ስለ ጊዜያዊነት ያወራል ብሎ ማን ጠበቀ?_እሱስ በቅጽበታት ቢቀየር አይደል።
ደቂቃዎች አለፉ ።
የትንሳኤ አካላት በፍዝ እሳቱ መዳፍ ላይ አረፉ።
እጁን ለ «ደህና ሰንብት» አነሳ።
ዓይኔ በውዴ ኀዘን ያቋተውን እንባ አፈሰሰ። ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ለምን የወደድነውን ፈጥነን እናጣለን አልኩ። እንደ መሬት ቶሎ ግላ ቶሎ እንደምትበርደዋ፣ እንደ ወረተኛ ጓደኛ ቶሎ ወዶ ቶሎ እንደሚጠላው...እንደዛ እንደዛ ለምን ሆነ?። ወደ ሽቦ አልጋዬ ተወረወርኩ። አልጋዬ ታረገርጋለች፤ ሕይወትም እንዲሁ መሆኗ ነው። ዓይኔን ወደ ጎጆዬ ጣሪያ ልኬ የሸረሪቷን ልፋት አየሁ። ገረመኝ። ላትኖርበት ቤት፣ ላትለብሰው ሸማ መማሰኗ ደነቀኝ። ሕይወት አትተውምና መቀጠሏን እያነሳች እየጣለች ...ጋደም አልኩ። ልሞት_በትልቁ እንቅልፍ።



Read 331 times