Friday, 08 December 2023 20:48

የዐማራ ባንክን ከ460 ሚ. ብር በላይ ለሚሆን ኪሳራ ዳርገዋል የተባሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና መኰንን ከሓላፊነታቸው ተባረሩ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የዐማራ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚውን አቶ ኄኖክ አበበ ታደሰንና የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና መኰንኑን አቶ ክንዴ አበበን፣ በአፈጻጸም ድክመት ከሓላፊነታቸው አነሣ።

የባንኩ ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ዛሬ ዐርብ፣ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲኾን፣ ኹለቱም ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ፣ በየጊዜው በሚሳዩት የሥራ አፈጻጸም ድክመት፣ የባንኩን ስትራቴጂያዊ ግቦች እና ቁልፍ የአፈጻጸም መመዘኛዎች ለማሳካት ያልቻሉና የማያስችሉ ናቸው፤ በሚል፣ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡና ከባንኩ እንዲሰናበቱ መወሰኑን፣ ለኹለቱም በየስማቸው በአደረሳቸው ደብዳቤ አስታውቋል።

በ2014/15 ዓ.ም. ባንኩ ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ለማስመዝገብ ዐቅዶ የነበረ ቢኾንም፣ 460,286,000 ብር  ኪሳራ በማስመዝገብ፤ በሌላቸው ሥልጣን ባሳለፉት አስተዳደራዊ ውሳኔ፣ ከ89 ሚሊዮን በላይ ብር እንዲከፈል በማድረግ፣ የባንኩን ካፒታል ለብክነት የመዳረግ አደጋ ውስጥ በማጋለጣቸውና ሌሎችንም አጠቃላይ የአፈጻጸም ድክመቶችን በአስረጅነት የጠቀሰው የዲሬክተሮች ቦርዱ፣ ሓላፊዎቹ በቦታቸው መቀጠል እንደማይችሉ ገምግሞ አንሥቷቸዋል።

ከሓላፊነታቸው በተነሡት አቶ ኄኖክ አበበ ቦታ፣ የባንኪንግ አገልግሎቶች ከፍተኛ መኰንን አቶ ጫን ያለው ደምሴ፣ ከነገ ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጊዜያዊነት የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን ቦታ  ደርበው እንዲይዙ እንደመደባቸው ታውቋል።

Read 2241 times