Sunday, 10 December 2023 20:19

በ43ኛው የሮተርዳም ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ታቅዷል

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

አዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2024 ከገባ በኋላ ከሚካሄዱ ግዙፍ ማራቶኖች አንዱ የሆላንዱ 43ኛው የሮተርዳም ማራቶን ነው። የሮተርዳም ማራቶንን በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይታወቃል። ዋናው ምክንያት የአትሌት በላይነህ ዴንሳሞ አንፀባራቂ ታሪክ ነው። አትሌት በላይነህ በ1988 እኤአ ላይ የዓለም ማራቶን ሪከርድን 2:06:51 በሆነ ሰዓት በኢትዮጵያዊ ለመጀመሪያ ጊዜ በማስመዝገብ ፈርቀዳጅ ታሪክ ከመስራቱም በላይ ለአራት
ጊዜያት በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቦበታል። 43ኛው የሮተርዳም ማራቶን 126 ቀናት የሚቀሩት ቢሆንም ሰዋኑን መነጋገሪያ ነበር። የዓለም ማራቶን ሪከርድን ዘንድሮ ያስመዘገበው ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕቱም በመሳተፉ ዓለምአቀፍ ትኩረትን ስቧል። በሁለቱም
ፆታዎች የዓለም ምርጥ ሯጮችን በማሳተፍ ለሪከርድ የተመቸ የማራቶንን ውድድር መሆኑን ለማስመስከር ማቀዳቸውንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል። በሮተርዳም ማራቶን ላይ ኬልቪን ኪፕቱም ሲሳተፍ የመጀመሪያው አይደለም። በ2019 እኤአ ላይ በአሯሯጭነት የተሳተፉ ሲሆን በ2022 እኤአ ደግሞ በዋና ተወዳዳሪነት ተመዝግቦ በጉዳት ሳቢያ ሳይሮጥ ቀርቷል።“ በምቹዎቹና ቀጥ ባሉት ጎዳናዎች ላይ መሮጥ እፈልጋለሁ። እቅዴ በሮተርዳም ማራቶን የታሪክ መዝገብ ለመስፈር ነው። የያዝኩትን የማራቶን ሪከርድ ማሻሻል እንደምችል አውቃለሁ። ወሳኙ ጥሩ ልምምድና ወቅታዊ ብቃቴ ነው። ምናልባትም ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የምገባበት ዕድልም ይፈጠራል።” በማለትም የዓለም የማራቶን ሪከርድ ባለቤ አስተያየትት ሰጥቷል።
 የሮተርዳም ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የወርቅ ደረጃ ተሰጥቶታል። በስፖንሰሩ ምክንያት ኤንኤን ሮተርዳም ማራቶን ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ በሆላንድ ከሚዘጋጁት NN Rotterdam Marathon የአምስተርዳምና የአይንድሆቨን ማራቶኖች ተርታ ይጠቀሳል። ከ35ሺ በላይ ተሳታፊ ያለውና በሮተርዳም ጎዳናዎች ከ1ሚሊየን በላይ ታዳሚ የሚያገኝ ነው። ባለፉት 42 የሮተርዳም ማራቶኖች ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡት የምስራቅ
አፍሪካ አትሌቶች ናቸው። በሁለቱም ፆታዎች 27 አሸናፊዎችን (18 ወንድና 9 ሴት) በማስመዝገብ ኬንያ ከፍተኛውን ውጤት ይዛለች። ኢትዮጵያ 16 አሸናፊዎችን (8 ወንድና 8 ሴት) ያስመዘገበች ሲሆን ሆላንድ 8 አሸናፊዎች (1 ወንድና 7 ሴት) በማግኘት ተከታታይ ደረጃ አላቸው።
በሮተርዳም ማራቶን ላይ ኢትዮጵያ በወንዶች ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈችው ከ7 ዓመት በፊት ቢሆንም በሴቶች ግን ያለፈውን 42ኛው የሮተርዳም ማራቶን ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊ ነበረች። በወንዶች ምድብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አሸናፊ በ1986 እኤአ ላይ አበበ መኮንን ነበር። በላይነህ ዴንሳሞ በ1987 ላይ ካሸነፈ በኋላ በ1988 ላይ የአሸናፊነት ክብሩን ሲያስጠብቅ 2:06:50 በሆነ ሰዓት የዓለም ሪከርድም አስመዝግቦ ነበር። በተጨማሪ ደግሞ በ1989 እና በ1996 እኤአ ሁለት ድሎች በመጎናፀፍ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል። የማነ ፀጋዬ በ2012፤
ጥላሁን ረጋሳ በ2013 እና አበራ ኩማ በ2015 እኤአ ላይ ያሸነፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው። በሴቶች ምድብ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ
አሸናፊ በ2006 እኤአ ጊሹ ምንዳዬ ስትሆን አበሩ ከበደ በ2010 እኤአ ላይ ለማሸነፍ በቅታለች። ቲኪ ገላና በ2012 እኤአ ስታሸንፍ እስካሁን ያልተሰበረውን የቦታውን ሪከርድ 2:18:58 በሆነ ሰዓት አስመዝግባ ነበር። አበበች አፈወርቅ በ2014 ፤ ለተብርሃን ሃይላይ በ2016፤ መሥከረም አሰፋ በ2017 ፤ እሸቴ በከሬ በ2019 እና ሐቨን ኃይሉ በ2022 እኤአ ላይ አሸናፊዎች ነበሩ።

Read 242 times