Sunday, 10 December 2023 20:56

‘ጆሮ በሊዝ እንስጥ እንዴ!'

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንግዲህ አየሩም ‘ቀዝቀዝ' እያለ ነው፡፡ “ያወቁ ተሟቁ” ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ልጄ አዋዋልና አመሻሻችሁን… አለ አይደል… ክረምት-ተኮር ካላደረጋችሁት በኋላ “ወጋኝ…ቆረጠኝ” ማለት ዋጋ የለውም፡፡ ስኳር እንኳን ከወርቅ ጋር ‘የውድነት' ፉክክር በያዘችበት ዘመን… “እድሜ ለሃኪም” ማለት እንኳን አስቸግሯል፡፡ [ስሙኝማ… ደህናው ነገር ሁሉ እየተወደደ… ‘ረከሰ' የሚለው ቃል እንደናፈቀን 2000 ዘመን ልትደፍን! ለነገሩ እዚያስ ድረስ ‘ቁልጭ' ብሎ… “አይ አያ ጊዜ ማለት ተገኝቶ ነው!]  
በነገራችን ላይ አዋሳዎች ብራቮ! ‘ሚሊዮን በሚሊዮን' በጀት የለም… እንደ አራስ ሶስት መቶ ስድሳ ምናምን ቀን መታረስ የለም… ‘ሙያ በልብ' ማለት እንደናንተ፡፡
ስሙኝማ… እንደገና ዬ‘ኳስ ሰሞን' መጣ አይደል፡፡ አንድ ወዳጄ የነገረኝን ስሙኝማ፡፡ ‘ቱባ' ሰው ናቸው አሉ፡፡ እናላችሁ ይሄ የፈረደበት ቡድናችን ጎሉን ሲቅም አዩና ምን አሉ መሰላችሁ… “የቡድናችን መሰረታዊ ችግር አጨዋወቱ ጎል-ተኮር አለመሆኑ ነው፡፡” አሪፍ አይደል!
ጋዜጠኞች አንድ አለ ፍሬንቻ መንገድ የምናሳብርባት ‘ብልሃት' አለችን፡፡ እዚችም እዚያችም ከነካኩን በኋላ “የዛሬ አነሳሳችን እንኳን ስለዚህ ለማውራት ሳይሆን…” ብሎ ከመጋቢት መንገድ ወደ አስፋልት ብቅ ማለት ነዋ! እና… ተግባባን መሰለኝ፡፡
አድ ወዳጃችን አለ “የፈለገ ነገር ቢመጣ ስቄ ነው የምቀበል…” የሚል፡፡ የምርም ተዋጥቶለት ነበር፡፡ ታዲያላችሁ በቀደም “አሁንስ ለማንስ አቤት ይባላል!” ብሎ ምርር ሲል ነበር፡፡ መስሪያ ቤት በሆነ ባልሆነ ‘አበሳውን' እያሳዩት ነበር፡፡
ምን መሰላችሁ… እየበዛ ሲሄድ… አለ አይደል ነቃ ብሎ… “የሄ ሁሉ ምሬት ከየት መጣ!” ማለት ደግ ነው፡፡ አሃ… ልክ ነዋ! አለበለዚያ ዘፈኑ ‘የድሮ'… ዳንሱ ‘አሁን' ይሆንና ነገርዬው ብልሽት ነው የሚለው፡፡
የምር'ኮ …. አለ አይደል… ግራ እየገባን ነው፡፡ ‘ጉልበተኝነት'… በሰርኩላር ይፈቀድ ይመስል… ትንሹም ትልቁም ሰውን “አሁንስ ለማን አቤት ይባል!” እያሰኘው ነው፡፡
በቀደም… አንድ እድሜው ከስምንት ወይ ከዘጠኝ የማይበልጥ ልጅ ማስቲካ ሲሸጥ አንድ የቀበሌ ዘብ ያስቆመዋል፡፡ [ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… እዛው አካባቢ ሌሎች ተለቅ ያሉ ካልሲ፣ ጢም መላጫ ምናምን የሚሸጡ ነበሩ፡፡ “ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን አለ” የሚሉት ይሄን ነው እንዴ!]
እናላችሁ ልጁ ማስቲካዎችን በሙሉ ሰብስቦ እንዲያነሳው አደረገና ምን አደረገው መሰላችሁ… የደረደረበትን ካርቶን በጫጭቆ ጣለበት፡፡ ‘ጉልበት የሌለው' ህፃን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ በልጅ እንባው “ለማን አቤት ይባል?” እያለ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር… “ነገ'ኮ…” ምናምንም አሰኝቶ ‘ቴረር ቢጤ አይለቅባቸውም! ለቀበሌው ዘብ የሰው ንብረት የማበላሸት ‘ጉልበት'… ያፀደቀለት የፀጥታው ምክር ቤት ነው?
ምን ግርም ይልሃል አትሉኝም… ለምንድነው ‘ኮምፕሌይን' ባደረግን ቁጥር… የግድ ‘የጀርባ አላማ' የሚፈልገው? “ስራችሁ አላማረኝም” ለማለት የግድ ‘ብክኪ' መኖር አለበት!! እናስ “አሁንስ ለማን አቤት ይባል!” የሲ.ኤን.ኤን ላሪኪንግ ድምፅ ቀነስ አድርጎ… ‘ከአጥር ውጪ የምንጮኸው እኛን መስማት ግድ ነው፡፡ የምር… በተለይ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎች…‘ጉልበት መፈተኛ' ሲሆኑ አያሳዙንዋችሁም!
አንድ ሁለት ወር ገደማ ይሆናል፡፡ ሴትዬዋ ጠዋሪ ቀባሪ የሌላቸውን በጣም የደከሙ አሮጊት ናቸው፡፡ በአሮጌ ሳህን ሀያም የማይሞላ ሙዝ አድርገው መንገድ ዳር ተቀምጠዋል፡፡ አንድ ‘የስነስርአት አክባሪ' ልብስ የለበሰ የሚመስል ሰው መጣና ሳህናቸውን በእርግጫ መትቶ ሙዙን በተነባቸው፡፡ እናላችሁ ልክ መቶ ጋሻ የማያጠጣ ቦይ የቀደደ ይመስል በትእቢት ተነፋፍቶ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ተላላፊዎች ሙዙን ሲሰበስቡላቸው… አሮጊቷ ምንም ሳይንቀሳቀሱ እንባቸው ኮለል ይል ነበር፡፡ የሚማቸው የለም እንጂ “ለማን አቤት ይባል!” እያሉ ነው፡፡
እኔ የምለው… ዘቡ ንብረታቸውን በእርግጫ በትኖ አለጠያቂ የሄደበት ‘የነፃነት ስሜት' አያስፈራቸውም፡፡ ወይ “የማሳርፍበት ልጣ!” የሚል አይነት የሚወዘውዘው ዱላ ሲሰጡ… የ“ስትፈልግ ቅደድ… ስተፈልግ እርገጥ…” ልዩ መብት ተሰጥቶታል እንዴ!
‘በደንብ ልብስ' ሽፋን… ‘ጉልበተኝነት' እንዳልታየ ሲያልፍ… አለ አይደል… “ጉልበተኝነት እንማን ጋር ሲደርስ ነው የሚቆመው?” ትላላችሁ፡፡ አሀ ልክ ነዋ… አለበለዚያ ‘አርጩሜ የሚያዝብን' ይበዛና… መመለሻ አይኖረወም፡፡
እኔ እምለው… ዘንድሮ'ኮ ጡንቸኛ መስሪያ ቤቶች… ‘ጉልበተኛ' ያደርጋቸዋል፡፡ “ይሄ ሰው የሚሆነው ምንድነው?... አቅም አለው ወይ?... የቤተሰቡ ኑሮ አይናጋም ወይ?” ብሎ በሚጠይቅ የለ፡፡ ብቻ በዚህም በዛም “አምጣ…” “ጨምር…” እንደገና “ጨምር…” ነው፡፡ ይሄኔ ሰው በየኮሊደሩ ሆነ በሚፀልይበት ቦታ “ለማን አቤት ይባላል?” ይላል፡፡  ምን ይደረግ… ሰሚ የለ! ‘ማሳመን' … እንኳን የለም፡፡ በቃ “ወይ ክፈል… ወይ ዞር በል” አይነት ነገር ነው፡፡
ስሙኝማ… በቴሌቪዥን እንኳ አቤት እንዳንል… የኛ ቴሌቪዥን ለ‘እኛ ብቻ' ነው የተተወው፡፡ አሀ… ‘ውሳኔ ሰጪዎች' በ‘ዲሽ' ነዋ አለምን የሚቃኙት፡፡ እንደውም ሃሳብ አለኝ… በቃ ብሶታችንን ሁሉ ሄደን ለላሪ ኪንግ እንንገረው፡፡ ልክ ነዋ… ‘አለቆች' እንደኛ “የላንጋኖ ሃይቅ…” የ“ሰሜን ተራራዎች…” አይነት ‘ሚዩዚካል' [ቂ…ቂ…] የለባቸውም፡፡ ስለዚህ በላሪ በኩል “ለማን አቤት ይባላል…” የሚል እየበዛ ስለሆነ መላ ፈልጉ ይባልልን፡፡
ሶስት ቀን ቢሆነን ነው፡፡ ሚኒባሱ ሶስት ሰከንድ እንኳን ሳይቆም አንድ ተሳፋሪ አውርዶ ሲንቀሳቀስ ከቆመበት የሚንቀሳቀስ መኪና መንገድ ይዘጋበት እና ሊያሳልፈው ቆም ይላል፡፡ ብዙም እንደ ጆሴፍ እስታሊግ ሪዝ የለውም እንጂ መኮሳተሩ እሱን የሚያስመስለው የ‘ፓርኪን' ሰራተኛ “ቆመሃልና ልክፈል አለው፡፡ አሽከርካሪ… ረዳቱ… ፊት የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ሊያስረዱ ሞከሩ፡፡ ወይ ፍንክች፡፡ ሾፌሩ ለረዳቱ ምን አለው መሰላችሁ “ንጉሱ እሱ ነውና ስጠው፡፡” እንዲህ አይነቱ ሰራተኛ ነገር ማርሽ ለማቀዝቀዝም ጎተት ያለ ታክሲን “ቆመሃልና ክፈል…” ቢል ‘ለማን አቤት ይባላል፡፡'
እናላችሁ… በየደረጃው የደንብ ልብስ የለበሰ ‘ቆመጥ የያዘው' ለአምስት ሰው የሚባቃ ቆዳ ወንበ “የሚንጪለለው” “ተቀባይነት ያለው የኔ ቃል ብቻ ነው…” በሚል እንደ ልቡ ሲሆን… እኛ የዜግነታችን ደረጃ እየወረደ የመጣው “ለማን አቤት ይባል!” በንል ምን ይገርማል! ነው… መናገራችን አንሶ ለመደመጥ ጆሮ በሊዝ እንስጥ!
ደና ሰንብቱልኝማ!
Read 1206 times