ሩሲያ የሆነው ኢትዮጵያ ይደገማል። ወይም ሌላ አገር እንደ አዲስ ይከሰታል። ወጉ ግን ለሁሉ ይተርፋል። ሩሲያውያኑ ሲቀልዱ ይሆን አምርረው ባይታወቅም እንዲህ ይላሉ።
አትክልተኛው ሰውዬ የመስሪያ ቤቱን አትክልት በየጊዜው አላጠጣህም ተብሎ በድክመት ተገምግሞ በማስጠንቀቂያ ታልፏል። በልቡ “ይቺን ስህተት ሁለተኛ አልደግማትም” ሲል በጓዶቹ ስም ይምላል። (“ስጋ ብጽወት!” እንደ ማለት መሆኑ ነው)
በሚቀጥለው ቀን በጠዋት ይነሳና የውሃ ማጠጫ ጎማውን ከቧንቧው አገናኝቶ ሲያበቃ በረዥሙ እየረጨ አትክልቶቹን ውሃ ማጠጣት ጀመረ። በአጋጣሚ አህያ የማይችለው ዝናብ ይመጣና ዶፉን ይለቀዋል። ሰውየው ውሃውን ማጠጣቱን ይቀጥላል።
በዚያ መ/ቤት አጠገብ ዣንጥላ ይዘው የሚያልፉ ሰዎች ነገሩ ገርሟቸው፤
“ምን ሆነህ ነው ዝናብ እየዘነበ አንተ እንደገና የቧንቧ ውሃ የምታጠጣው?” ብለው ይጠይቁታል። አትክልተኛውም ስራውን እየቀጠለ፤
“መመሪያ ነው ጎበዝ! በመመሪያ ቀልድ የለም!”
***
እንደዚሁ ሌሎች ሁለት ሩስያውያን ከአለቃቸው መመሪያ ወርዶላቸዋል። መመሪያውም፡- አንደኛው ይቆፍራል፣ ሌላኛው የቧንቧውን ትቦ ይከታል የሚል ነው። ከዚያ የመጀመሪያው መልሶ ይደፍናል። እንዲህ እያሉ “በነገው እለት 200 ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ ቧንቧ አስገብተው እንዲጨርሱ” የሚል ትዕዛዝ ደርሷቸዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ በነጋታው ግን ቆፋሪ መጥቶ ቁፋሮውን መቆፈር ቢጀምርም ባለቧንቧው እክል ገጥሞት ትቦውን ይዞ ሳይመጣ ይቀራል። ያም ሆኖ ቆፋሪው ስራውን አላቋረጠም።
በሜትር እየለካ ሁለት ሜትር ያህል ርዝመት ይቆፍርና መልሶ አፈሩን እየከፈተ ይደፍነዋል። ይቀጥላል ሌላ 2 ሜትር። ደሞ ይደፍናል። እንዲህ እንዲህ እያለ 200ውን ሜትር ቆፍሮ ደፍኖ ይጨርሳል። ነገሩ ግራ የገባቸው የመ/ቤቱ ሰራተኞች፤ “ምን አይነት የሞኝ ስራ እየሰራህ ነው? ‘ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ’ አደረግከው እኮ?” ሲሉ ይጠይቁታል።
“መመሪያ እኮ ነው ጎበዝ! እኔ የተሰጠኝን ሃላፊነት ተወጥቻለሁ። መመሪያውን በሚገባ አክብሬአለሁ” አለና መለሰ።
***
በኢትዮጵያ ደግሞ እንዲህ ያለ ወግ አለ።
ጊዜው ጥቂት ዓመታት ቆየት እንደማለት ብሏል። ታጋዮች በአንድ መኪና ሞልተው ሲሄዱ የመኪናው ፍሬን ይበጠስና ሹፌሩ ሲቸገር ቆይቶ የአንድ ትልቅ መ/ቤት ግንብ ጥሶ አስገብቶ ያቆማታል። ሹፌሩ ክፉኛ ይጎዳል። ደም በደም ይሆናል። ሌሎቹ ያልተጎዱት ታጋዮች በፍጥነት መኪና ቀይረው በአስቸኳይ ሹፌሩን ወደ አንድ ሆስፒታል ይዘውት ይበራሉ።
ሆስፒታሉ ደጃፍ ሲደርሱ መታወቂያ ይጠየቃሉ። ከደከመው በሽተኛ በስተቀር ሌሎቹ መታወቂያቸውን አውጥተው ያሳያሉ። ዘበኛው የሁሉንም የመታወቂያ ፎቶና መልካቸውን ካስተያየ በኋላ ወደተኛው በሽተኛ እያየ፤
“የሱስ መታወቂያ የታለ?” ሲል ይጠይቃል።
“ጓድ እሱማ በሽተኛ ነው። አታየውም ደም በደም ሆኖ መንቀሳቀስ እኮ አይችልም” አሉት።
“መታወቂያ ከሌለው እናንተ ግቡ እሱ ይቆያል!”
“እንዴ ምን ማለትህ ነው ጓድ…”
“መመሪያ ነው መመሪያ ነው! ከፈለጋችሁ እናንተ ግቡ አለበለዚያ በሽተኛችሁን ይዛችሁ ተመለሱ! መመሪያ ለሁሉም እኩል ነው የሚሰራው!”
***
አንዳንዱ መመሪያ ከጅማት ይጠነክራል። ያለ አንዳች ህሊናዊ ዳኝነት፣ ያላንዳች ማመዛዘን እንገልገልብህ ሲሉት ራሱን መመሪያ አውጪውን ጭምር እግር ተወርች ቀይዶ አላላውስ አላስተነፍስ ይላል። “የዝንጀሮ ንጉስ ራሱ ይከምራል ራሱ ያፈርሳል” ይሏይ ይሄ ነው። አንዱ ቦታ ስራ ሲቆም መላው ስራ በድን የሚሆንበት አይነት መ/ቤት አለ። ያ እንግዲህ አንድያውን ይሞታል ማለት ነው። የሚገርመው መመሪያውን በጥብቅ ስራ ላይ አውላለሁ ብሎ የሚውተረተረው ሰው መነሻ በመመሪያው ማመን ሳይሆን የግምገማ ስራቸው መሆኑ ነው። ይህ በፈንታው የሚያረጋግጥልን አንድ እውነት አለን። ግምገማ ስህተትን ማረሚያ መሆኑ ቀርቶ የበታቶች በበላዮች አይን ደካማ እንዳይባሉ፣ አልፈው ተርፈው “የባህሪ ለውጥ አመጣ!”፣ “የሚታወቀው ስህተቱን በማመን ነበር ዛሬ አመሉን ለውጧል”፣ “የችግሩን ስሯን መዝዘን ስናያት መነሻዋ ሌላ ናት” ወዘተ እባላለሁ የሚል ፍርሃት በውስጡ በመንገሱ ነው። ይሄ ደግሞ በፈንታው የገዛ የስራ ባልደረቦችን መቆጣጠርን፣ ለአለቃ ማጎብደድን፣ የየአይነቱን ሙስና፣ የጌታና የሎሌ ግንኙነትን ወዘተ ይወልዳል። መመሳጠር ይበረክታል።
“የልቡን የሚሰራ ለእናቱ አይነግርም” እንዲል መጽሐፉ፤ የጥቂቶች ዱለታ ያይላል። ስራ ይዳከማል። ሲከፋም ከነጭራሹ ይቆማል። ባለው የቢሮክራሲ የቆላ ቁስል ላይ የአይጥና ድመት ደፈጣ ሲጨመርበት አንድያውን ወደ ልብ ድካም ያመራል። የአቅም ግንባታው የአቅም መፍረስን ጽንስ ተሸክሞ ይጓዛል። ልማቱ ንቅዘትን አርግዞ የሚራመድና ቀኑን የሚጠብቅ በሽተኛ ይሆናል። ነጻ የሲቪክ ማህበረሰብ ይፈጠርበታል የሚባለውም እቅድ ውስጡን በግንደ-ቆርቆር የተበላ አፋዊ የፖሊሲ ዋርካ ብቻ ሆኖ ይቀራል። በዚህ ሁሉ ላይ የፖለቲካ ጫና ሲጨመርበት “የማይታጠፍን እንጨት ልለምጥህ ብሎ ማንከት” እንደተባለው ይሆናል።
የማይጠየቅ መመሪያ፣ የማይሻሻል ህግ፣ የማይለወጥ እቅድና መርሃ ግብር ጥቂት ታማኞችን እንጅ እንደ ልቡ ለማሰብ የሚችል፣ የሆዱን ለመናገር የሚደክም፣ በነጻ ውይይት የሚያምን ነጻ ህብረተሰብ ለመፍጠር አያስችልም። ይልቁንም ፈሪና ግልጽነት የጎደለው፣ በራሱም በሌሎችም የማይተማመን ዜጋ ማሳደግ ነው የሚሆነው። በመሃል ጌታው ያፈጣል፣ በጨለማ ሎሌው ያፈጣል የሚባለው አይነት ግንኙነት እየበዛ የአጥቢያ አምባገነኖች (Local dictators) እንዲፈለፈሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ፓርቲና መንግስት መለያየት አለባቸው በሚባልበት በአሁኑ ሰዓት የመመሪያ ትርጉም በፓርቲና በመንግስት ውስጥ ይለያይ ይሆናል ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው። የተለያዩ የቲያትር መድረክ ላይ የሚተውን ተዋናይ መብራቱና መጋረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ ተዋናዩ ገጸ-ባህሪው ያው ነው። ወዲህ ፓርቲያዊ ግለሰብ፣ ወዲያ መንግስታዊ ግለሰብ ለመሆን አይቻልም። በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ከመሆን በቀር። በሩስያ የታየውና ፓርቲውንና የመንግስትን ቢሮክራሲ ለመለየት ከማይቻልበት ደረጃ (Bureaucratization of the party) የሚባለው ማለት ነው። አስቀድሞ ነገር የፓርቲው ጤና አለመሆን ነው። ገዥው ፓርቲ ጤና ሳይሆን የሚወርዱት መመሪያዎች፣ የሚሰጡት ትዕዛዛት ጤና አይሆኑም። እንደ ኢትዮጵያ ባለው አገር ደግሞ ጭራሽ ከቢሮክራሲ ጋር ፓርቲው አንዴ ከተፈጣጠመ በኋላ እናፋታህ ቢሉት፣ ከስልጣን ናፋቂነት እስከ ጥቅም አጋባሽነት ያለውን የግለሰቦችና የድርጅቶች ህልውና ማናጋት ይሆናል።
የውስጥ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ደረቅ ወይራ የሆኑበት ሰዓት አውራ ገዥ ለሆኑት ሃያላን መንግስታት የተሸበበ የበቅሎ ልጓም በቀላሉ እንደመሳብ ይሆንላቸዋልና ውሃውን ወደፈለጉት ቦይ የሚነዱበት ቀጫጭን መመሪያ ማድረግ የበለጠ ቀና ይሆንላቸዋል። ታዛዡ ያለችግር ይታዘዛል፡፡ መመሪያ ነዋ! ስለዚህ የወረደው መመሪያ መሬት አይወድቅም። በዚህም ሃያላኑ በሰሜን የተሳካውን ድል በምስራቅም ቤተ-ሙከራ ውስጥ ለመክተት የረጋ መደላድል ማግኘታቸው ነው ማለት ነው። ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ህብረተሰብ ውስጥ የጌቶች መዋቅር ብዙ ነው። ጌቶቹ ሰማየ ሰማያት ላይ የተቀመጡ፣ የማይታዩ ሃያላን በሆኑ ጊዜ ደግሞ የትዕዛዙ መነሻ ጫፍ አይታይም። ውጤቱ እንጅ። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ህዝብ አልተዘጋጀበትምና በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መልኩ እሺ ወይም እንቢ ለማለት (React ለማድረግ) አቅም አይኖረውም። የቅዱስ ጊዮርጊስ ጦር ሲወጋ እንጅ ሲወረወር አይታይም እንዲል መጽሐፉ። በተጠመደለት ወጥመድ ውስጥ ዘልሎ ጥልቅ ለማለት የሚጣደፍ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የሙያ ማህበር ያልታደለ ነው። ከሚቀመርለት ቀመር፣ ከሚታጠርበት አጥር ማዶ ለማየት የማይችል ህብረተሰብ እንደተገለበጠች ኤሊ ነው። ወደ ጤናማው አቋሙ የሚመልሰው የውጭ እርዳታ ይጠብቃል።
ዝናብ ሊመጣ ሲል ጆሮዋን ለምታቆመው አህያ፣ ለውጥ ሊመጣ ዳር ዳር ሲል ጆሮውን የሚያነቃ፣ ለውጥ ወዳድ፣ ሀገር ወዳድ ምሁር ያስፈልጋል። ሀገር ወዳድ ምሁር የህዝብ አይን የህዝብ የጉዞ አቅጣጫ ጠቋሚ ቀስት ነው። በአንጻሩ ለውጥ ፈላጊ፣ ተንቀሳቃሽ ምሁር ያጣ ህዝብ ያልታደለ ነው። የኩሬ ውሃ ነው። አይፈስም። አይጠራም። አይጸዳም። አይሻሻልም። ሕዝብን በመልካም አስተዳደር ንፍቀ-ክበብ ውስጥ የማይከቱና የታዘዘውን ተቀባይ የሚያደርጉ መመሪያዎች እንደተሸነቆረ እቃ ናቸው። ምንም አይነት ቀና ነገር ቢሞሉባቸው፣ ምንም አይነት የለውጥ አስተሳሰብ ቢከቱባቸው ያፈሳሉ። ይህም ውሎ አድሮ መመሪያ አውጪዎችን፣ ፖሊሲ ቀራጮችን ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ አይቀሬ ነው። መርማሪዎች ተመርማሪዎች፣ ጠያቂዎች ተጠያቂዎች የሚሆኑበት ጊዜ እየመጣ መሆኑ ግልጽ ነው። የማረጋገጫና የማጣሪያ መንገድ ደግሞ በህዝብ እጅ አለ። ማ ወሳኝ፣ ማ ጽዱ፣ ማ ኢዲሞክራሲያዊ፣ ማ ዲሞክራሲያዊ፣ ማ ተቻቻይ፣ ማ ገፊ፣ ማ ለአገር የቆመ፣ ማ ራሱን የሚሰዋ መሆኑ ይለያል። ጊዜው ሲደርስ “የተሰነጠቀ ቅልን ለማወቅ ውሃ ጨምርበት” ማለት ብቻ ነው።
Published in
ርዕሰ አንቀፅ