Saturday, 23 December 2023 11:03

ቢጂአይ- ኢትዮጵያ በማስፋፊያና ማዘመን ስራዎች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈስ አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አመታዊ ምርቱን 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ለማድረስ አቅዷል


          ቢጂአይ- ኢትዮጵያ በአሰራሩ፣ በማምረት ሂደቱና በስርጭት ሞዴሉ ላይ ወሳኝ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ሊያደርግ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ ኢንቨስትመንቱ የኩባንያው ፋብሪካዎች የማምረት አቅም መጨመርና ታሪካዊውን  የአዲስ አበባ ፋብሪካ ሰበታና ማይጨው ወደሚገኙት ሁለቱ የቢራ ፋብሪካዎቹ ማዛወርን እንደሚያካትት   ጠቁሟል።የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚ/ር ሄርቬ ሚልሃድ ባለፈው ማክሰኞ ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ይህ ኢንቨስትመንት ኩባንያችንን የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቹን ለውድ ደንበኞቹ ለማቅረብ ከምንሰራቸው ዋና ዋና ፕሮጀክቶች አንዱ ነው” ብለዋል። የቢጂአይ- ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ለውጥ መተግበር ያስፈለገው ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የገበያ ለውጥ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚታየው አጠቃላይ ተወዳዳሪነት ጋር እርምጃውን ለማስተካከል፣ እንዲሁም የኩባንያውን እድገት ለማፋጠንና ጠቅላላ አመለካከቱን ለማሻሻል ነው ተብሏል።
“በኢትዮጵያና በገበያዋ ከፍተኛ አቅም እንዳለ እናምናን” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ “ኢትዮጵያ እያደረገችና እየተለወጠች ስትሄድ ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አሰራር ለመዘርጋት ተዘጋጅተን ወደ ተግባር ገብተናል” ብለዋል።“ራዕያችን በሚቀጥሉት ዓመታት የማምረት አቅማችንን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት ወደ 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ ለማድረስ ነው” ሲሉ ሚልሃድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ይህን ትልቅ አላማ ለማሳካት በሰራተኞቻችን፣ በምርቶቻችን፣ በደንበኞቻችንና በምንኖርበት ማህበረሰብ ላይ ኢንቨስት እናደርጋለን” ያሉት ሥራ አስፈጻሚው “በመካሄድ ላይ ካሉት ዋና ዋና ተግበራት አንዱ በማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት በማድረግ የድርጅታንን የማምረት አቅሙን ማሳደግ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“በውሃ አቅርቦት ውስንነትና የሎጅስቲክስ ተግዳሮቶች ምክንያት በአዲስ አበባ መሀል ከተማ የሚገኘውን ታዋቂውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካችንን ለማዛወር የተገደድን ቢሆንም፣ ይኸው ችግር ራሱ የሌሎች ፋብሪካዎቻንን የማምረት አቅም ለማሳደግ እድ ፈጥሮልናል” ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ። ቢጂአይ- ኢትዮጵያ ድርጅታዊ መዋቅሩን በማደስ ተመራጭ አሰሪ ድርጅት ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስፈፃሚ ገልጸዋል።
ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባሉት ሰባት ፋብሪካዎች ለ3,500 ቋሚ ሰራተኞችና 2,000 ጊዜያዊ ሰራኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ የለውጡ ግብም በእያንዳንዱ የሥራ ክፍል ውስጥ ያሉትን አስፈላጊ ክህሎቶችና ሂደቶችን በመለየት፣ የተግባር ልህቀትን በመላ ኩባንያው ማምጣት ነው ተብሏል።
ቢጂአይ- ኢትዮጵያ አገሪቱ ከሚገኙ የግል ድርጅቶች ትልቁ ግብር ከፋይ እንደሆነና በዓመት ከ7.4 ቢሊዮን ብር በላይ ታክስ ለመንግስት እንደሚከፍል ለማወቅ ተችሏል።


Read 534 times