Saturday, 23 December 2023 11:13

ኢትዮ ቴሌኮም፤ የዲጂታል የፋይናንስ ገበያና የዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ አገልግሎቶችን በይፋ አስጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ኢትዮ ቴሌኮም፤ የፋይናንስ ተቋማት፣ አገልግሎቶቻቸውን በቴሌ ብር ለደንበኞቻቸው ለማቅረብ የሚያስችላቸው  የዲጂታል የፋይናንስ ገበያና የዲጂታል የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ   አገልግሎቶችን  ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡
    ኩባንያው፤ ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ኢንሹራንስና ሌሎችም በዘርፉ ያሉ ተቋማት የቴክኖሎጂ አቅምን ተጠቅመው፣ የፋይናንስ አገልግሎታቸውን ተደራሽና አካታች ለማድረግ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የሚያስችላቸውን የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ (Digital Financial Marketplace) ሶሉሽን ማቅረቡን አመልክቷል፡፡  በተጨማሪም፣ በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ተቋማት በርካታ የአክሲዮን ባለድርሻዎች ያሏቸው እንደመሆኑ የአክሲዮን ግዢና ሽያጭ ሂደታቸውን ዲጂታል በማድረግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድሩበት የዲጂታል አክሲዮን ገበያ (Digital Share Sell/Buy) ሶሉሽኖችንም ማስተዋወቁን ጠቁሟል፡፡  
ኢትዮ ቴሌኮም ባወጣው መግለጫ፤ “የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ገበያ፤ የፋይናንስ ተቋማት የማይክሮ ፋይናንስ፡-የብድር፣ ቁጠባና ኢንሹራንስ አገልግሎቶቻቸውን ለደንበኞቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ፕላትፎርም  በዲጂታል አማራጭ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ሶሉሽን ሲሆን፤ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የእጅ ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ አገልግሎቱ የደንበኞችን የብድር እንቅስቃሴና በወቅቱ የመመለስ ልምድን በማገናዘብና የሰው ሠራሽ አስተውሎትን  በመጠቀም በሚሰራ የብድር ቀመር  መሰረት የሚከናወን በመሆኑ ያለምንም የንብረት መያዣ  የብድር አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል።  ከዚህ ቀደም ከዳሽን ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በቀረጸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ከ3.6 ሚሊዮን ደንበኞች በላይ በብድር አገልግሎት ተደራሽ ማድረጉን ያስታወሰው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዛሬው ዕለት የቀረበው የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ሶሉሽን፣ ባንኮች ምንም አይነት የካፒታል ኢንቨስትመንት ማድረግ ሳይጠበቅባቸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም በገነባው ፕላትፎርም ተጠቅመው የፋይናንስ አገልግሎቶቻቸውን ከ40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የቴሌብር ደንበኞች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበት አገልግሎት መሆኑን አመልክቷል፡፡ ”የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ አገልግሎት ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን፤ ባንኮች ይህንኑ እንዲያውቁ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ፕላትፎርሙን ለመጠቀም ከአሀዱ ባንክ፣ ከሲንቄ ባንክ፣ ከእናት ባንክና አዋሽ ባንክ ጋር ውይይት ተጠናቆ ከብሔራዊ ባንክ በሚያገኙት ይሁንታ መሰረት አገልግሎቱን በቅርቡ የሚጀምር ይሆናል፡፡” ብሏል፤ኩባንያው፡፡


Read 441 times