Saturday, 23 December 2023 21:03

በሃዋሳ በ280 ሚ. ብር የተገነባው ባለ 3 ኮከብ ሆቴል ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በሃዋሳ ከተማ በምሥራቅ ክፍለ ከተማ በ280 ሚሊዮን ብር ወጪ በ700 ካ.ሜ ቦታ ላይ የተገነባው ባለ 3 ኮከቡ ፌኔት ሆቴል፣ በዛሬው ዕለት የክልሉ የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመረቀ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "ሃዋሳ የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ ሆቴሉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል" ብለዋል።

አዳዲስና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ያካተተው ፌኔት ሆቴል፤ የኮንፍረንስ ቱሪዝሙን መደገፍ የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች ጭምር የያዘ ነው ተብሏል፡፡

 ለ41 ቋሚና 10 ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል የተባለው ሆቴሉ፤ የከተማዋን የቱሪስት እንቅስቃሴና ገቢ ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡

በ1992 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ጥቂት ሰራተኞችን ይዞ በ50ሺ ብር በጀት በኪራይ ቤት የተጀመረው ሥራ፣ ለረዥም ዓመታት በከተማዋ ተወዳጅ ሆኖ ወደዘለቀው ፌኔት ክትፎ ቤት እንዳደገና  ዛሬ  የተመረቀውን ባለ 3 ኮኮብ ሆቴል ማዋለድ እንደቻለ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡

 ፌኔት ሆቴል፤ በቀጣይ በከተማዋ ባለ 4 ኮኮብ ሆቴል ለመገንባት ያቀደ ሲሆን፤ ለክልሉ የመሬት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጤናዬ ዋርጌ ተናግረዋል፡፡

Read 1831 times