Saturday, 30 December 2023 19:53

ከ30 ዓመታት በላይ በህክምና ሙያ ውስጥ....

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

“እናታቸው ከታመመችባቸው ልጆች ጋር አብሬ አልቅሻለው...”
በዓለም አቀፍ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ተሸላሚ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ    
ዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) እ.ኤ.አ በ2023 ባካሄደው የሽልማት እና የእውቅና መርሐ ግብር ላይ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ በሙያው ላይ ለረዥም ዓመታት በማገልገል እውቅና አግኝተዋል። ከ16 ሀገራት ለተመረጡ ሴት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሼሊስቶች የተሰጠው እውቅና ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 4 ሀገራት ተካታች ሆነዋል። ኢትዮጵያን ወክለው እውቅና የተሰጣቸው የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ናቸው።
“የህክምና ትምህርት ከልጅነቴ ጀምሮ እፈልገው እና እወደው ነበር” በማለት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ተናግረዋል። ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ በጎጃም ክፍለሀገር ቢቸና አውራጃ ነው የተወለዱት። በልጅነታቸው ወላጅ አባታቸውን በሞት የተነጠቁ ሲሆን እድገታቸውን ከእናታቸው ወንድም ጋር አደረጉ። አጎታቸው መምህር ስለነበሩ ወደ ትምህርት ዓለም የገቡት ልጆች ትምህርት መጀመር አለባቸው በሚባልበት እድሜ ላይ ነበር። ከ1 እስከ 4ኛ ክፍል በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተማሩ። አባታቸው (አጎታቸው) ወደ አዲስ አበባ ሲመደቡ ዶ/ሰላማዊትም ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ቀጠሉ። ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩት ፊት አውራሪ ላቅ አድገህ ፣መካነ ኢየሱስ እና እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ነበር።
በትምህርት ቆይታቸው የአባታቸው እገዛ መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር ሰላማዊት የህክምና ሙያ ለመግባት የአጎታቸው አስተዋፅኦ እንደነበር ተናግረዋል። “አባቴ(አጎታቸው) ከልጅነቴ ጀምሮ የማንበብ ባህል እንዳዳብር ይከታተለኝ ነበር” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ። የዶ/ር ሰላማዊት አባት ታመው ሆስፒታል በሚሄዱበት ወቅት አብረዋቸው ይሄዱ የነበሩት ዶ/ር ሰላማዊት የህክምና ሙያ ውስጥ የመግባት ፍላጎት ይበልጥ አደረባቸው። እንደ ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ንግግር በዚህ ወቅት የህክምና ሙያ ውስጥ የመግባት ፍላጎታቸውን የተረዱት አባታቸው (አጎታቸው) እስከ መጨረሻው ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ነገሯቸው። ከዚህ በተጨማሪም በልጅነታቸው ዘመድ ከክፍለሀገር ለህክምና ሲመጣ እና ሆስፒታል ሲሄድ አብረው መሄዳቸው የህክምና አከባቢን የመቃኘት እድል ፈጥሮላቸዋል።
ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ከልጅነታቸው ጀምሮ የህክምና ሙያ ውስጥ መግባት ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም ሁኔታዎች የተመቻቹ እና ቀላል አልነበሩም። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እስከ ገቡበት እንዲሁም በፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻላይዝድ አድርገው ስራውን ሲቀጥሉ የተለያዩ መሰናክሎች አጋጥሟቸዋል። ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በተመደቡበት በ1971 ዓ.ም በሀገሪቱ በነበረው ሁኔታ (አለመረጋጋት) ምክንያት በአባታቸው ዘንድ ስጋት መፈጠሩ፣ ዩኒቨርስቲው የህክምና ባለሙያ(ዶ/ር) ሲያስተምር የመጀመሪያ ዓመት በመሆኑ የግብአቶች አለመሟላት፣ ከዩኒቨርስቲው ትምህርታቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ስፔሻላይዝ ለማድረግ የምርጫ እና የሁኔታዎች አለመመቻቸት እንዲሁም በስራ ዓለም ውስጥ ከአሰራር ጋር በተያያዘ መሰናክሎች መኖራቸው የሚጠቀስ ነው።
ዶ/ር ሰለማዊት አሻግሬ በህክምና ሙያ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ጠቅላላ ሀኪም ሆነው ሙያውን ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ሆነው እያገለገሉ እስከሚገኙበት ድረስ በተለያዩ የህክምና ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል። ከዚህም ውስጥ አፍሪካ ህብረት የህክምና ማዕከል፣ አፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የህክምና ማዕከል(ኢ.ሲ.ኤ)፣ ፓሊስ ሆስፒታል፣ አየር መንገድ እንዲሁም ሄመን የእናቶች እና ህፃናት የህክምና ማዕከል ተጠቃሽ ናቸው። ዓለምአቀፍ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) ለዚህ አገልጋሎታቸው ነው እውቅና የሰጣቸው።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ በመቶኛ ሲሰላ 1 የህክምና ባለሙያ ለ10 ሺ ሰዎች ነው የሚደርሰው[የሚያገለግለው]። በኢትዮጵያ ደግሞ ለ1000 ሰው የሚደርሰው የህክምና ባለሙያ ብዛት በመቶኛ ሲቀመጥ ከ1 ባለሙያ በታች ነው።
እስከ 2016 ዓ.ም ባለው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር ውስጥ ከ7መቶ በላይ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች አባል ሆነው ይገኛሉ። እንደ ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ንግግር የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ውስጥ ለመግባት አርአያ ያደርጉት የህክምና ትምህርት ተማሪ በነበሩበት ወቅት የነበሩ ጀምርመናዊት አስተማሪያቸውን ነው። አስተማሪያቸው (የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት) በሙያቸው ላይ በጣም ጎበዝ እንደነበሩ ዶ/ር ሰላማዊት ተናግረዋል። የመምህራቸው በጎ ተፅእኖ በእሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተማሪዎችም ላይ ነበር። ከዶ/ር ሰላማዊት በተጨማሪ ከእሳቸው ጋር አብረው ሲማሩ ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 2 ሀኪሞች የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች ሆነዋል።
“የፅንስ እና ማህፀን ህክምና እውቀት እና ጥበብ (Art and Skill) ስለሚፈልግ ነው የምወደው” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ። የፅንስ እና ማህፀን ህክምና የህክምናውን ውጤት በአጭር ጊዜ በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ነው ባለሙያዋ የተናገሩት። ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ልጅ እንድትወልድ ለማድረግ የሚሰጠውን ህክምና ነው። “ለሰው ሰርቼ፤ ወገኖቼን ረድቼ” የሚል ሀሳብ ወደ ሙያው እንዲገቡ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።
“የህክምና ሙያ እና ስሜታዊነትን ለመለየት ልምድ ያስፈልጋል” ያሉት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ የህክምና ሙያ ከተቀላቀሉ በኋላ ብዙ የማይረሱ አጋጣሚዎች አጋጥመዋቸዋል። ከዚህም ውስጥ ሁልጊዜ የሚያስታውሷቸው 3 አጋጣሚዎች አሉ። ሁለቱ  የህክምና ሙያ በተቀላቀሉ ሰሞን ያጋጠሟቸው ሲሆኑ 1 አጋጣሚ ደግሞ በፅንስ እና ማህፀን ስፔሻላይዝ ለማድረግ እየተማሩ በነበሩበት ወቅት ያጋጠመ ነው።
 የመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪ በነበሩበት ወቅት እናታቸው ታመው ሆስፒታል የገቡባቸው ልጆች በእናታቸው መታመም ምክንያት ሲያለቅሱ ይመለከታሉ። ዶ/ር ሰላማዊትም ከልጆቹ ጋር አብረው ማልቀስ ጀመሩ። “በስራ ላይ የመጀመሪያ ቀን አጋጣሚዬ ስለነበር አልረሳውም። በ1977 ዓ.ም ነበር” በማለት ተናግረዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ። ሌላኛው የማይረሱት አጋጣሚ ደግሞ መሬት ላይ እያደሩ የሚያስታምሙ የአንድ ታካሚ እናት ታሪክ ነው። እኒህ እናት ልጃቸው እያገገመ ባለበት ሁኔታ እሳቸው ህይወታቸው አለፈ። በሞት እና በሕይወት መካከል ሆነው “ወይኔ ልጆቼ....” በማለት ስለራሳቸው ሳይሆን ስለ ልጆቻቸው መጨነቃቸውን የተመለከቱበት ክስተት 3ኛው የዶ/ር ሰላማዊት አጋጣሚ ነው። ህይወታቸው ያለፈው እናት ነፍሰ ጡር ሲሆኑ ወደ ህክምና ተቋም የሄዱት ዘግይተው ነበር። ጽንሱ ሆድ ውስጥ እያለ ሕይወቱ አለፈ። ማህፀናቸው ተተርትሮ ሕይወታቸውን ማትረፍ በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ነበር። ከዛም ስለ ልጆቻቸው ተናግረው ህይወታቸው አለፈ። እነዚህ 3 አጋጣሚዎች ዶ/ር ሰላማዊት በህክምና ሙያ ውስጥ በጣም ስሜታዊ ያደርጓቸው ወቅቶች ነበሩ። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር እንደዚህ አይነት ስሜቶች በልምድ የሚስተካከሉ ቢሆኑም እንደ ሰው ግን ስሜታዊነት ይኖራል።
ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ እናቶች ወደ ህክምና ተቋም እንዳይሄዱ የሚያደርጉ የገንዘብ፣ የትራንስፖርት፣ የእውቀት እና በዙሪያቸው ያለ ሰው ድጋፍ ያለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል። ይህም ለእናቶች እና ህጻናት ሞት መንስኤ በመሆን ለዘመናት ቆይቷል። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር የእናቶች እና ህጻናት ጤና አጠባባቅ ላይ ለውጦች አሉ። ስለሆነም ይህን ለማስቀጠል እና የተሻለ ለመስራት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባው የጽንስ እና የማህጸን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ተናግረዋል።

Read 346 times