የዓለማችን ስፖርት ኢንዱስትሪ በኮቪድ 19 ከተፈጠረበት ኪሳራ እያገገመ መጥቷል። በመላው ዓለም በስፖርቱ ገበያ የሚንቀሳቀሰው መዋዕለ ንዋይ ከግማሽ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። ዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር FIFA እና የዓለም አትሌቲክስ ማህበር World Athletics የሚያስተዳድሯቸው እግር ኳስና አትሌቲክስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ ውድድሮች ማደጋቸውን ቀጥለዋል። በዓለም አቀፍ ውድድሮች መሥተንግዶ ታላላቅ ከተሞች በገቢ ትርፋማ እየሆኑ ናቸው። በቱሪዝም ፤ በስፖርት መሠተልማቶችና በገፅታ ግንባታ ተጠቅመዋል። ከሚዲያ ብሮድካስት መብት የሚገኘው ገቢ እየጨመረ ሲሆን ማህበራዊ የሚዲያ አውታሮች የስፖርቱ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እየተቀላጠፉ ይገኛል። በስፖንሰርሺፕ፤ በስታድየም ትኬቶች ሽያጭ፤ ከተለያዮ የስፖርት ምርቶችና ተያያዥ ንግዶች የሚገኙት የገቢ ምንጮች እየተስፋፉ ናቸው። በቴክኖሎጂ የሚታየው አስደናቂ ምጥቀት በሁሉም ስፖርት አይነቶች ፈጣን እድገትና ለውጥ በመፍጠር ላይ ነው።
በ2024 እኤአ ላይ በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው ኦሎምፒያድና በጀርመን የሚዘጋጀው የአውሮፓ ዋንጫ የስፖርቱን ገበያ በማሟሟቅ ከፍተኛ ትኩረት የሚስቡ ይሆናል። ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ የዓለማችን ስፖርት ኢንዱስትሪ በ2023 የነበረውን እንቅስቃሴ በ23 የተለያዩ ሁኔታዎች ይዳስሳል። ዓለም አቀፍ የስፖርት አስተዳደር፤ ሚዲያና ቢዝነስ ተቋማት የሚያወጧቸውን ዓመታዊ ሪፖርቶች፤ ጥናታዊ ሰነዶች ፤ የውጤት ክለሳዎች፤ ዘገባና ትንታኔዎችን በመፈተሸ የተዘጋጀ ነው።
1.ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎችና 15 ሜዳሊያዎች በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልታ የምትወጣበት የስፖርት ውድድር እንደሆነ ይታወቃል። በሐንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 የወርቅ ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ በ9 ሜዳሊያዎች ከዓለም 6ኛ ደረጃ ተገኝቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ በተደረገው የዓለም ጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮንሺፕ ደግሞ 2 የወርቅ ፤ 4 የብርና 1 የነሐስ በድምሩ በ7 ሜዳሊያዎች ከዓለም 2ኛ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ተችሏል።
2.ቡዳፔስት የምስራቅ አውሮፓዋ የስፖርት ከተማ
በሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ195 አገራት 2100 አትሌቶች የተሳተፉበት ነበር። ከ400 ሺ በላይ የስታዲየም ትኬቶችን ከ120 የተለያዮ አገራት የተውጣጡ ስፖርት አፍቃሪዎች በመግዛት ሻምፒዮናውን ታድመዋል። ከ850 በላይ ጋዜጠኞችና ፎቶግራፈሮች እንዲሁም 36 የብሮድካስት ኩባንያዎችን የወከሉ ከ1200 በላይ ባለሙያዎች ከ75 አገራትን በመወከል ለሻምፒዮናው ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል። ከ14ሺ በላይ የሻምፒዮናው ዜናዎችና ዘገባዎች ከ28.5 ቢሊዮን በላይ ድምር ተከታታይ ነበራቸው። የዓለም አትሌቲክስ በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ከፍተኛ ትኩረት በማግኘቱ ነው። በኢንስታግራም፣ በፌስቡክ፣ በዮቲውብና በትዊተር ከ11 ሚሊየን በላይ ተከታታዮችን አፍርቶበታል። በዓለም ሻምፒዮናው 46 አገራት ሜዳሊያ ያሸነፉ ሲሆን 23 አገራት የወርቅ ፤ 26 አገራት የብር እንዲሁም 29 አገራት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ሰብስበዋል።
3.በሁለቱም ፆታዎች የማራቶን ሪከርዶች ተሰብረዋል
በሁለቱም ፆታዎች የአለም ማራቶን ሪከርዶች የተሻሻለበት የውድድር ዘመን ነበር፡፡ ኬኒያዊው ኬሊቨን ኪፕቱም የቺካጎ ማራቶንን ሲያሸንፍ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ይዞት የቆየውን ሪከርድ በ34 ሰከንዶች አሻሽሎታል። አዲሱ ሪከርድም 2፡00፡35 ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚህ ስኬቱ በኋላም ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ይገባል? የሚለው አጀንዳ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል። በሴቶች ማራቶንም የውድድር ዘመኑ ከ40 አመታት በኋላ በሰዓት መሻሻል ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ትግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን ስታሸንፍ ያስመዘገበችው አዲስ ክብረወሰን 2:11:53 ነው። አስቀድሞ የነበረውን ሰዓት በ2 ደቂቃ ከ15 ሰኮንዶች ያሻሻለችበት በመሆኑ ከፍተኛ አድናቆት አስችሯታል። በሴቶች ማራቶን ከ2 ሰዓት 10 ደቂቃዎች በታች መግባት እንደሚቻልም ተስፋ አሳድሯል። ኬልቪንና ትግስት በዓለም አትሌቲክስ ማህበር በጎዳና ላይ ሩጫ የዓመቱ ኮከብ አትሌት ሽልማትን ተጎናፅፈዋል።
4.የትልልቅ ማራቶን አሸናፊዎች ከኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በ2023 በታላላቅ ማራቶኖች ድሎችን ተቀዳጅተዋል፡፡ በሴቶች ሐቨን ሃይሉ በኦሳካ ማራቶን፤ መሰረት አበባየሁ በሸይናሜን ማራቶን፤ ትግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን፤ መሰረት በለጠ በአምስተርዳም ማራቶን፤ ስራነሽ ይርጋ በሻንግሀይ ማራቶን እንዲሁም ወርቅነሽ ደገፋ በቫሌንሺያ ማራቶን አሸንፈዋል፡፡ በአለም አትሌቲክስ የማራቶን የዓመቱ ምርጥ ሰዓቶችና ውጤቶች ደረጃ ላይ ትግስት አሰፋ በ1488 ነጥብ ስትመራ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው አማኔ በሪሶ በ1462 ነጥብ ሁለተኛ ነች። በወንዶች ሲሳይ ለማ በቫሌንሺያ ማራቶን፣ ጫላ ደሶ በቶኪዮ ማራቶን፣ አምደወርቅ ዋለልኝ በሲዮል ማራቶን እንዲሁም ታምራት ቶላ በኒውዮርክ ማራቶን አሸንፈዋል፡፡
5. የጉዳፍ ልዮ ሐትሪክ
በረጅም ርቀት 10 ሺና 5ሺ ሜትር ውድድሮች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የበቃችው ጉዳፍ ፀጋዬ ናት። በውድድር ዘመኑ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ከመብቃቷም በላይ በ5ሺ ሜትር የአለም ሪከርድን በ14፡00.21 ጊዜ በማስመዝገብና የዳይመንድ ሊግ ዋንጫንም በመቀዳጀት ስኬታማ ሆናለች፡፡በ10ሺ ሜትር ሴቶች የአለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው ጉዳፍ ፀጋዬ በ29፡29.73 የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች። ሰዓት በማስመዝገብ በ1307 ነጥብ ስትመራ ለተሰንበት ግደይ ደግሞ በ1382 ነጥብ የዓለም አትሌቲክስ ደረጃን በመሪነት አጠናቅቃለች።
6.ድርቤ በትራክና ጎዳና
በመካከለኛ፤በረጅም ርቀትና በጎዳና ላይ ሩጫ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ድርቤ ወልተጂ ናት፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በ1500 ሜትር ሜትር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ድርቤ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮንሺፕ በ1 ማይል የወርቅ ሜዳልያ ከመጎናፀፏም በላይ በ4፡27.79 አዲስ የዓለም ሪከርድ ለማስመዝገብ ችላለች።
7. ዮሚፍ ፤ ሰለሞንና ሐጎስ
በወንዶች 5ሺ ሜትር በዓመቱ ፈጣን ሰዓቶች የደረጃ ዝርዝር በሪሁ አረጋዊ በ12፡40.43 የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል። ዮሚፍ ቀጀልቻና ሐጎስ ገ/ህይወት 3ኛና 5ኛ ደረጃ ላይ ናቸው። በዓለም አትሌቲክስ ዓመታዊ ደረጃ ደግሞ ዮሚፍ በ1455 ነጥብ መሪ ሆኖ የውድድር ዘመኑን ሲጨርስ፤ በሪሁ አረጋዊ በ1430 ነጥብ እንዲሁም ሐጓስ ገብረህይወት በ1412 ነጥብ ተከታታይ ደረጃ በመያዝ የውድድር ዘመኑን አጠናቅቀውታል። በ10ሺ ሜትር ወንዶች ከኢትዮጵያ ከፍተኛውን ውጤት ይዞ የሚገኘው 26፡50.66 በሆነ ጊዜ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው በሪሁ አረጋዊ ሲሆን ሰለሞን ባረጋ 26፡51.87 በማስመዝገብ ተከትሎታል። ሁለቱም አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ዓመታዊ ደረጃ በ1306 ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
8.ፌዝ፤ ኖህና 6 የዓለም ኮከብ አትሌቶች፤
የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫው በ3 የተለያዩ የሽልማት ዘርፎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰጥቷል። በሁለቱም ፆታዎች በትራክ ፤ በጎዳና ሩጫ እና በሜዳ ላይ ስፖርቶች 6 አሸናፊዎች ተመርጠዋል። በትራክ የዓለም ኮከብ አትሌት ሆነው የተሸለሙት አሜሪካዊው ኖህ ናይልስና ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕየገን ናቸው። የዓለም ማራቶን ሪከርድን በሁለቱም ፆታዎች በቺካጎ እና በበርሊን ማራቶኖች የሰበሩት የኬንያው ኬልቪን ኬፕቱምና የኢትዮጵያዋ ትግስት አሰፋ በጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ኮከብ አትሌት ተብለዋል። በሜዳ ላይ ስፖርቶች የዓለም ኮከብ አትሌት የተባሉት ደግሞ ስዊድናዊው የምርኩዝ ዘላይ ተወዳዳሪ ሞንዶ ዱፕላንቲስና ቬንዝዋላዊቷ ሥሉስ ዘላይ ዮልሚ ሮጃስ ናቸው። ኬንያዊትዋ ፌዝ ኪፕየገን በመካከለኛና በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የዓመቱን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች። በ1500 ሜትር እና በ5000 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኗም በላይ 3 የዓለም ሪከርዶችን በ1500 ሜትር፤ በማይልና በ5000 ሜትር አስመዝግባለች፡፡ አሜሪካዊው ኖህ ላይነስ ደግሞ በ200 ሜትር ከዮሲያን ቦልት የላቀ ውድድር ያደረገ ሲሆን በ100 ሜትርና በ200 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን እንደሆነ ይታወቃል።
9.ገመዶ የዓመቱ ስኬታማ አሠልጣኝ
አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ የተቀዳጀ ሲሆን በሶስት ማራቶኖች በማሸነፍና በሴቶች የዓለም ማራቶን ሪከርድ በማስመዝገብ ስኬታማ ሆኗል ። በዴደሞና አትሌቲክስ ክለብ ማናጀር ሆነው ከሚሠሩት ጂያኒ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ውጤት አግኝቷል። በዓለም አትሌቲክስ አስደናቂ የሆነው የማራቶን ሪከርድ በትግስት አሰፋ አሰልጣኝነት ተጎናጽፏል። የዓለም ሻምፒዮኗ አማኔ በሬሶ፤ የቫለንሺያ ማራቶን ያሸነፈችው ወርቅነሽ ደገፋና የኒውዮርክ ማራቶንን ያሸነፈው ታምራት ቶላ አሰልጣኝም ነው።
10. ትልቅ ህልም በሳውዲ
በመካከለኛው ምስራቅ የሳውድ አረቢያ ስፖርት እንቅስቃሴ የዓመቱ ክስተት ማለት ይቻላል።ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በስፖርት ኢንዲስትሪው ላይ ከ6.3 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጭ መሆኑ አንዱ ማሥረጃ ነው፡፡
በተለይ በእግር ኳሰ የሳውዲ ፕሮፌሽናል ሊግ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። PCW በመካከለኛው ምስራቅ የ2023 የስፖርት እንቅስቃሴ በልዩ ሁኔታ ባደረገው ጥናት ክርስትያኖ ሮናልዶ እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ወደ ሊጉ በከፍተኛ ገንዘብ መምጣታቸው ፈጣን እድገት ፈጥሯል። ሮናልዶ አልናስርን ሲቀላቀል ሊጉ የብሮድካስት ውል በማግኘት በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎችና በ36 የተለያዩ አገራት ለመሰራጨት በቅቷል። የአልናስር ክለብ ኢንስታግራም ገፅ ተከታዮች ከ800ሺ ወደ 15 ሚሊዮን ተተኩሷል። የካሪም ቤንዜማና የሳዲዮ ኦማኔ ዝውውሮችም ተመሣሣይ መነቃቃት ፈጥረዋል። የሊጉ ስታድየም ትኬቶች ሽያጭ በ1200% አድጓል። የሊጉ አስተዳደር ለሚቀጥሉት 8 ዓመታት በነደፈው ስትራቴጂ አጠቃላይ የሊጉን የዋጋ ተመን ከ 800 ሚሊዮን ዶላር ወደ 2.14 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ዓመታዊ ገቢውን ከ120 ሚሊዮን ዶላር ወደ 480 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ነው።
11.በኳስ ተጨዋቾች ዝውውር 7.3 ቢሊዮን ዶላር
በዓለም እግር ኳስ የተጫዋቾች ዝውውር ገበያ 7.36 ቢሊየን ዶላር ወጪ መደረጉን በመጥቀስ International Transfer Snapshot በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የፊፋ ሪፖርት ክብረወሰን መመዝገቡን አመልክቷል። በውድድር ዘመኑ 10,125 ተጫዋቾች በዝውውር ገበያው መሳተፋቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በግዢና ሽያጭ ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማንቀሳቀስ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሷል። የሳዉድ አረቢያ ሊግ 874.5 ሚሊየን ዶላር፤ የፈረንሳይ ሊግ ዋን 859.7 ሚሊየን ዶላር ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 762.4 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም የስፔኑ ላሊጋ 405.6 ሚሊየን ዶላር በዝውውር ገበያው በማንቀሳቀስ እስከ አምስተኛ ደረጃ ተጠቅሰዋል። በዓለም እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ ላይ አስቀድሞ የነበረው ሪከርድ በ2019 እ.ኤ.አ ላይ የተንቀሳቀሰው 7.35 ቢሊየን ዶላር ነበር።
12. ሜሲ በአሜሪካ
ከታላላቅ ተጫዋቾች በዝውውር ገበያው ከፍተኛ ትኩረት የሳበው 8ኛውን የወርቅ ኳስ ሽልማት የተቀዳጀው ሊዮኔል ሜሲ ነው፡፡ አርጀንቲናዊው አለም ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ የስፔኑን ክለብ ባርሴሎና ለቅቋል። በሳውድ አረቢያ ክለቦች የቀረበለትን የሪከርድ ክፍያ በመተው በአሜሪካው ሜጀር ሶከር ሊግ ለሚጫወተው ኢንተር ማያሚ ፈርሟል። የአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ በከፍተኛ ደረጃ ያነቃቃ ዝውውር ሲሆን በዓመት እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል።
13.የገቢ ሊጉን የመራው ማንችስተር ሲቲ
ዴሊዮቴ ቢዝነስ ግሩፕ (Deloitte) ባሰራጨው ጥናታዊ ሪፖርት መሰረት የእግር ኳስ ክለቦች የገቢ ሊግን በዓመታዊ ገቢ የመራው ማንችስተር ሲቲ 808.38 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት ነው። ሪያል ማድሪድ በ788.47 ሊቨርፑል በ776.05፤ ማን ዮናይትድ በ761.56 እንዲሁም ፓሪስ ሴንት ጀርመን በ723.52 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢያቸው እስከ አምስተኛ ደረጃ አከታትለው ወሥደዋል።
14.የሃብታም ስፖርት ሊጎችን የተቆጣጠረችው አሜሪካ
ታዋቂው የቢዝነስ መጽሄት ፎርብስ (Forbes) ይፋ ባደረገው የሃብታም ስፖርት ሊጎች የደረጃ ሰንጠረዥ ግንባር ቀደም የሆኑት በአሜሪካ የሚካሄዱት ናቸው። የመሪነት ስፍራውን የያዘው የአሜሪካ ፉትቦል ሊግ (NFL) በ18.6 ቢሊዮን ዶላር ነው። የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ማህበር (NBA) በ10.58፤ የአሜሪካ ሜጀር ቤዝቦል ሊግ (MLB) በ10.32፣ የህንድ ፕሪሜርሊግ በ8.4 እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ6.6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋቸው በተከታታይ ደረጃዎች ተቀምጠዋል። ፎርበስ እንዳመለከተው የዓለማችን 50 ፕሮፌሽናል የስፖርት ሊጎች አጠቃላይ ሐብት በዋጋ ሲተመን ከ126 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል ። የስፔኑ ላሊጋ 5.3 ቢሊየን ዶላር፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 3.8 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 3.3 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ በመያዝ የደረጃ ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።
15. ቦክስ በ4.7 ቢሊዮን ድምር ተመልካቾች
በዓመት ውስጥ ከፍተኛ ተመልካቾች ያገኘው ስፖርት ቦክስ ሲሆን 4.7 ቢሊዮን ድምር ተመልካቾችን በማስመዝገብ ነው። እግር ኳስ 3.5 ቢሊዮን፣ ክሪኬት 2.5 ቢሊዮን እንዲሁም ሆኪ 2 ቢሊየን ተመልካቾች በውድድር ዘመኑ አግኝተዋል።
16.ከፍተኛ እድገት ያሳየው የሴቶች ዓለም ዋንጫ
በአውስትራሊያና በኒውዝላንድ አዘጋጅነት የተካሄደው 9ኛው የሴቶች ዓለም ዋንጫ በውድድር ዘመኑ ከፍተኛ ስኬት ካስመዘገቡ አለምአቀፍ ውድድሮች ተጠቃሽ ነው። ይህ ዓለም ዋንጫ 900 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሆኖበታል። ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ነበር።
17.ደቡብ አፍሪካ የዓለም ራግቢ ሻምፒዮን
በፈረንሳይ አዘጋጅነት የተካሄደው የዓለም ራግቢ ዋንጫ በፉክክር ደረጃው ከፍተኛ ድምቀት ያገኘ ዓለም አቀፍ ውድድር ነበር። በራግቢ የዓለም ዋንጫው ደቡብ አፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን መብቃቷ ያልተጠበቀ ነበር። ከ2.5 ሚሊየን በላይ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች መሸጣቸውን 40 ሚሊዮን ዮሮ ትርፍ መገኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።
18.ግማሽ ትሪሊዮን የደረሰው የስፖርት ገበያ
በSport Market ሪፖርት መሰረት በ2023 እ.ኤ.አ ላይ የዓለም የስፖርት ገበያ ከ512.14 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ሆኗል። በ400 ገፆች የተሰናዳው ሪፖርት እንዳመለከተው የዓለማችን የስፖርት ገበያ ካሟሟቁ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል ሊበርቲ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ላይፍ ታይም ፊትነስ ዋንኞቹ ተዋናዮች ናቸው። ከእግር ኳስ ክለቦች ደግሞ ባርሴሎና፣ ማን ሲቲ፣ ማን ዩናይትድና ጁቬንትስ የተጠቀሱ ሲሆን ከአሜሪካ የስፖርት ቡድኖች ደግሞ ዳላስ ካውቦይስ እና ኒውዮርክ ያንኪስ ይገኙበታል። የስፖርት ገበያው ሪፖርቱ ከሚዲያ መብት፤ ከስፖንሰርሺፕ፤ ከትኬት ሽያጭና ከተለያዩ ንግዶች የሚገኘውን ገቢ ያሰላ ሲሆን ሰሜን አሜሪካ ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ እንደሚወስድና የአፍሪካ አህጉርም በገበያው ተፈላጊነት እየጨመረ ነው ብሏል።
19.የሮናልዶ ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ 136 ሚሊዮን ዶላር
በከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ ከስፖርተኞች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት በእግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቦክስ፣ ጎልፍና የሜዳ ቴኒስ ስፖርቶች የሚወዳደሩት ናቸው። ክርስትያኖ ሮናልዶ 136 ሚሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ በመሰብሰብ ይመራል። ሊዮኔል ሜሲ 130፣ ከላያን ምባፔ 120፣ ሌብሮን ጀምስ ከቅርጫት ኳስ 119.5፣ ካኔሎ አልቫሬዝ ከቦክስ 110፣ ደስቲን ጆንሰን ከጎልፍ 107፣ ፊል ማርክስን ከጎልፍ 106፣ ስቴፈን ኩሪ ከቅርጫት ኳስ 100.4፣ ሮጀር ፌደረር ከሜዳ ቴኒስ 95.1 እንዲሁም ኬቨን ዱራንት ከቅርጫት ኳስ 88.1 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በመሰብሰብ እስከ 10 ተከታታይ ደረጃ አላቸው። ከሁሉም ስፖርቶች በትርፋማነቱ የሚጠቀሰው በዓመት እስከ 50 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማስገኘት ሲሆን፤ የአሜሪካን ፉትቦል 17 ቢሊየን ዶላር፤ ቅርጫት ኳስ 7 ቢሊየን ዶላር፤ ክሪኬት 3.5 ቢሊየን ዶላር፤ ፎርሙላ ዋን 1.5 ቢሊየን ዶላር ፤ ነፃ ትግል 1.27 ቢሊዮን ዶላር፤ ቦክስ 1 ቢሊዮን ዶላር፤ ቴኒስ 700 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሞተር ስፖርት 300 ሚሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ አላቸው።
20.የሚዲያ መብት ገቢ ከ56 ቢሊዮን ዶላር በላይ
Sport business global media report 2023 በሚል የተዘጋጀ ሰነድ እንዳመለከተው ከስፖርት የሚዲያ ወስጥ በ2023 የተመዘገበው ገቢ 56 ቢልየን ዶላር ነበር። በ2024 እ.ኤ.አ ላይ ከፓሪስ ኦሎምፒክና ከአውሮፓ የእግር ኳስ ስፖርት 19.183፣ የአሜሪካ ፉትቦል ሊግ 12.43 ቢሊየን ዶላር ገቢ ከሚዲያ መብት ያገኛሉ።
በሌላ በኩል YouGov የተባለው ተቋም (The Global Sports media landscape) በሚል ርዕስ በሰራው ጥናት 67% የዓለም ስፖርት አፍቃሪዎች ሁሉንም የስፖርት እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የሚዲጣ አውታሮች በቋሚነት ይከታተላሉ። የብሮድካስትና ዲጂታል ሚዲያ አውታሮች ከስታድዬም ባሻገር ስፖርትን ለመከታተል አማራጭ ሆነዋል። በስፖርት ይዘቶችን በመከታተል 77% ድርሻ የሚወስዱት ወንዶች ናቸው። ከሮም ስፖርት አፍቃሪዎች 51% የሚሆኑት የቲቪ ብሮድካስት የሚመርጡ ናቸው። 33% በማህበራዊ ሚዲያ፤ 25% ለህትመትና በድረገፅ፤ 25% በቪዲዬ ቅጅዎች እንዲሁም 15% በራድዬ ስፖርትን የሚከታተሉ ናቸው።
21. ናይኪ፤ አዲዳስና ፑማ
በስፖርት ትጥቅ ንግድ እስከ 193.89 ሚሊዮን ዶላር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ከ2023-2030 በሚኖረው የዓለም ገበያ ላይ ጥናት ያደረገው Fortune Business insights ነው። የጥናት ሪፖርቱ እንዳመለከተው በሚቀጥሉት 7 ዓመታት በስፖርት ትጥቅ የዓለም ገበያ 307.63 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። ከስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች የአሜሪካው ናይኪ በሽያጭና የብራንድ እድገት የዓለም ገበያን የሚመራ ሲሆን በዓመት ውስጥ ከ44.5 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ ነው። የጀርመን ኩባንያዎቹ አዲዳስ 23.6 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ፑማ 6.2 ቢሊየን ዶላር ሽያጭ ያደርጋሉ።
22. ፓሪስ አንደኛ የስፖርት ከተማ
ዓለምአቀፉ የኮምኒኬሽን ኩባንያ BWC በሰራው ሪፖርት ከ100 የዓለማችን ከተሞች መካከል በምቹ የስፖርት ከተማነት አንደኛ ደረጃ የተሰጣት 33ኛውን ኦሎምፒያድ በቀጣይ የምታስተናግደው የፓሪስ ከተማ ናት። ሎሳንጀለስ ለንደን ኒውዮርክ ማንችስተር ማድሪድ ባርሴሎና ሉዛኔና ቡዳፔስት በተከታታይነት እስከ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።
22. በአፍሪካ እግር ኳስ የዓመቱ አበይት ክስተት የነበረው በካፍ አዘጋጅነት የሚካሄደው የዓመቱ ኮከቦች ምርጫ ነው። በጣልያን ሴሪአ የሚጫወተው ናይጀሪያዊ ቪክቶር አሺሚሄን የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ሲሸለም ግብፃዊው መሐመድ ሳላህ እና ሞሮካዊው ሂካም አቸረፍ ሁለተኛና 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል።
Saturday, 30 December 2023 19:57
23 የስፖርት ሁኔታዎች በ2023
Written by ግሩም ሰይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ