Saturday, 30 December 2023 19:57

ከውጥንቅጥ ማግስት

Written by  ሙሉቀን ሽብሩ
Rate this item
(2 votes)

  አንድ
ጥቁሩ መነጽሬ የፀይኔን  መቅበዝበዝ እንጅ የነፍስና የሥጋዬን  ኀዘን መሸፈን አለመቻሉን ሁኔታዬ ያሳብቅ ነበር። ኀዘኔ ትንሽ ጋብ ያለ ሲመስለኝ ዙሪያ ገባውን ለማስተዋል ሞከርኩ። ከአብዛኛው ተስተናጋጅ ተገንጥለን ከወደ ጥግ ነው የተቀመጥነው። አሁን ባንበት ሁኔታ ለምን ያህል ሰዓታ እንደተቀመጥን እንጃ።
የገረጣ ፊቱን እንዳላየ ማለፍ ከባድ ነው። ከጊዜ ጋር መጣላቱን የሚያሳይ ከባድ የአካል ለውጥ አድርጓል። ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ቢሞክርም፣ የደረሰበትን መከራ ለመገመት አልቸገረኝም። በሌላ በኩል፣ በየመሀሉ “ትር… ትር…” የምትለው ሳሉ ዕረፍት ነሥታዋለች።
አሁንም በትዝታ ባሕር ውስጥ ሆነን፣ አንዳችን በሌላችን ላይ የተጠነጠነውን የኀዘን ልቃቂት እያዳወርን ያለን ይመስለኛል። የእርሱን ባላውቅም፣፤ የቀድሞ ወዳጄን ፍለጋ የሐሳብ መወርወሪያዬን ከወዲህ ወዲያ መወርወር ከጀመርኩ ቆየሁ። ከብዙ የሀሳብ መኳተን በኋላ፣ የጥለቴ የመጀመሪያው ቀለም የመለያያ ቃሌን አስታወሰኝ፤ ከጥልቁ አእምሮዬ መዞ አመጣልኝ። ስንለያይ የመጨረሻው ቃሌ “ይመችህ!” የሚል ነበር።
“ይመችህ!” እርግማንም ምርቃትም ነበረበት። ለሁለት ቤት ሁለት ዳንቴል የምትሠራ ሴትን ከጉያው ሸጉጦ ሳየው “ይመችህ!” ከማት ውጪ ምን ማለት እችል ነበር? የሕይወቱን ብሎን የምታላላ ጠመዝማዛ የኮረኮንች መንገድ ከፊት ለፊቱ እንደተዘረጋች ውስጤ ቢነግረኝም፣ ትቅርብህ ለማለት ድፍረቱ አልነበረኝም።
የመጀመሪያ ሰሞን ከሰው ጋር ተግባቢ እንደሆነች አስብ ነበር። ልዩ ጸጋዋ እንደሆነ እቆጥርም ነበር። ከሰው ጋር ተግባቢ አድርጌ ስያትም ነበር። “ቀላል፣ ለሰው የማትከብድ” የሚለው አባባሌን “ቀላል ለሰው ዋጋ የሌላት” በሚል እስከምተካው፣ በቅናትና ጥርጣሬ ችንካር እስክትቸነክረኝ ድረስ ልዩ  ሴት ነበረች። በፍጹም በማልረሳት አንዲት ዓርብ ምሽት ያየሁት ትዕይንት  ልክ አሁን እንደተፈጸመ ይሰማኛል።
የእኔ መኖሪያ ከእነ ሲራክ መኖሪያ ጀርባ ባለ መንደር ውስጥ በመሆኑ፣ ወደ እነሲራክ ቤት ለመሄድ ሁለት አማራጭ መንገዶች  አሉኝ። አንደኛው መንገድ ለአውራው ጎዳና ቀረብ ስለሚል፣ ቀንም ማታም የሰው እግር አይለየውም። ሌላኛው መንገድ ጨለምለም ሲል ብዙም የሚመረጥ ባይሆንም፣ በቀንም ሆነ በማታ ይሄ መንገድ ይቀናኛል። እና በዚያች አርብ ምሽት፣ ጠጠር በሚያስለቅም የጨረቃ ብርሃን ውስጥ እየዋኘሁ፤ ከሥራ መልስ የሲራክን እናት ለመጠየቅ ጨለማ በሚውጣት ቀጭን ዳገታማ መንገድ ስሄድ፣ ከፊት ለፊቴ በስተቀኝ ካለው ከትልቁ ግንብ ስር የሰው ቅርጽ  ያየሁ መሰለኝ። ክፉ ቀን ማጅራ መቺ ላይ ጣለኝ ብዬ እያጉተመተምኩ፣ ስፈራ ስቸር ጉዞዬን ቀጠልኩ። በቀረብኩኝ ቁጥር በጣም ተጠጋግተው የቆሙ፣  አፍላ ፍቅር ላይ የሚመስሉ ጥንዶች መሆናቸውን አየሁ። የሰጋች ልቤን አረጋግቼ ትንሽ ቀረብ ስል ደግሞ ጥንዶቹ እነማን እንደሆኑ በቀላሉ ለየኋቸው፤  ሲራክ እና ሳባ ነበሩ።
እኔን የሳመችኝ ቦታ ላይ የልቤን ሰው ስትስመው ሳይ  ነገሮች ተምታቱብኝ። እግሬ በሚስማር ከመሬቱ ጋር ተታብቆ የተመታ ይመስል መላወስ አቃተኝ። የጨለማው ንጉስ ሆን ብሎ የቅናት ዛር በውስጤ ሊተክል ነው ብዬ ራሴን ለመሸንገል ብሞክርም፣ ሃቁን መካድ አልሆነልኝም። በስሜት ሲተሸሹ ሳይ በመሀላቸው የተለኮስኩ የመለያየት ሰደድ እሳት እንደሆንኩ ተሰምቶኝ፣ መንገዴን ቀይሬ ተመለስኩ።
ምን ያህል እና ወዴት አቅጣጫ እንደተጓዝኩ አላውቅም። ከቤቱ ተርፈው በእግረኛ መንገድ ላይ ወንበር እና ጠረጴዛ ደርድረው በሞቅታ ሲያሽካኩ የነበሩ ሰዎች ከሰመመኔ አነቁኝ። ከሰፈሬ ብዙ ርቄ ተጉዣለሁ። ትንሽ ዐለፍ ብሎ ካለ መሸታ ቤት እስከ መንፈቀ ለሊት ብቻዬ ስብከነከን አምሽቼ ወደ ወንደላጤ ቤቴ ተመለስኩ።
በነጋታው፣ በተለመደው ሰዓት እና ሁናቴ ጨረቃዬ ፍልቅልቅ እያለች ወደኔ መጣች። አንድ እርምጃ ወደኔ በቀረበች ቁጥር፣ መልአከ ሞት የመሞቴን ዜና ሊያረዳኝ የመጣ እየመሰለኝ ተሳቀቅሁ፤ የኋሊት ለመሮጥ ዳዳኝ። ግን የምወዳትን የምሳሳላትን ጥዬ ወዴት ልሂድ? የሞ…ት…ሞ…ቴ…ን… ሲጋራዬን ቆሜ ጠበቅኋት። ሱስ ነውና፣ ሳንባዬ እንደሚፈርስ እያወቅሁ፣ በቁም እየሞትኩ እንደሆነ እየታወቀኝ፣ አንድ ጊዜ በረጅሙ ጉንጯ ላይ ሳምኳት።
ፊቷ ላይ ደስተኝነት እንጂ፣ ጥፋተኝነት አይታይባትም።  ትናንት  ስንለያይ ያለችኝን ደገመችልኝ።
“እንዴት እንደማፈቅርህ ታውቃለህ አይደል? “ስትለኝ፣
“በምን አውቄ” ከማለቴ፤
“ይኸው!” ብላ ከንፈሬን ሸረፍ አድርጋ፣ ጉንጬ ላይ ሳመችኝ። ቸ…ሰ… ስስስስስስስ… የሚል ድምጽ ከጉንጬ ላይ የሰማሁ መሰለኝ። ሲቃጠል ያደረው ሰውነቴ፣ በአንድ መሳም እንዲህ  ሲበርድ፣… ክፉ ደም ፍላቴ ሊላቴ ሊቀዘቅዝ ይታወቀኛል።
ጣቶቻችንን አቆላልፈን፣ ፍቅርን ከመሀላችን ተክለን ዳገቱን መጓዝ ጀመርን። ከዳገቱ መሀል ላይ “መንታ እህት አለሽ እንዴ?” አልኳት።
“ኧረ በፍጹም፣ ምነው?” አለችኝ።
ለጥያቄዋ ምላሽ  ሳልሰጣት ከመንገዱ ላይ ያገኘሁትን ጠጠር እየጠለዝኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ነገር እየበላሁ እንደሆነ ገብቷታል። ጣቷን ከጣቴ አላቃ በግራ እጇ የፀሐይ ጨረሩን እየተከላከለችና ሽቅብ እያየችኝ “ምነው? መልስልኝ እንጂ” ብላ ወዝወዝ አደረገችኝ። “ተይው ምንም አይደለም፣ ጨረቃዬ “ አልኳት።
ጨረቃዬ ስላት፣ በብርሃኗ ተመስጬ ይመስላት ይሆናል። ግን ዑደቷን በተከተለች ቁጥር የራሴን አቋም በዛው ልክ ማስተካከል የየወሩ ሥራዬ መሆኑን አላስተዋለችውም። ሙሉ ጨረቃ ስትሆን ሁሉን የመሳብ ኃይል አላት። ብርሃኗ ያሳሳል፤ አቅል የሚያሳጣ፣ የሚያሳብድ ነገር አላት። በሳምንቱ፣ ፊቷ ላይ ግማሽ ፈገግታና ግማሽ ኀዘን ረብቦ ይታያል። በሚቀጥለው ሳምንት፣ ከፊቷ ላይ ሲሶውን ለፈገግታ ትታ ሌላውን ታጨፈግገዋለች። በመጨረሻ ሳምንት ሳባ ማንም ሊቀርባት የሚያስችል ፊት አይኖራትም።
በሐሳብ መብሰልሰሌን አስተውላ፣ “ለምን እኔን በግዑዝ ነገር ትመስለኛለህ?” አለችኝ። “በተለይ በጨረቃ! አሁን ጨረቃ ምኗ ነው እኔን የሚመስለው?” ከማለቷ፣ “ሁናቴያችሁ” አልኳት በደመነፍስ። በደመነፍስ አልኳት ልበል እንጂ ጭንቅላቴ ውስጥ ሲብላላ የነበረ ሀሳብ ነው። ጣያቄዋን ሳልጠብቅ ማብራራቴን ቀጠልኩ።
“አንቺም ሆንሽ ጨረቃ፣ እንዳውቅ የምፈልገውን ብቻ ነው እንዳውቅ የምታደርጉኝ። ሁለታችሁም ዑደታችሁን ጠብቃችሁ- ትሞላላችሁ፣ ትጋመሳላችሁ፣ ታንሳላችሁ በመጨረሻም ትጠፋላችሁ፣” ብዬ  ትንፋሽ በወሰድኩበት የጊዜ ቅንጣት ውስጥ “ዐውቃለሁ። ምክንያቱም ሁለታችንም የራሳችን የሆነ ብርሃን የለንም። ከሌላ ያገኘነውን መልሰን የምናንጸባርቅ፣ ምስኪን መስታወቶች ነን። ታዲያ የተፈጠርነው ለእንደዚህ ከሆነስ?” ብላ አፈጠጠችብኝ። ምን አልመለስኩላትም።
በዝምታ ውቅያኖስ ውስጥ ሰጥመን መንገዱን ተያያዝነው። የእርሷን ባላውቅም እኔ ግን የተገናኘንበትን አጋጣሚ ሳወጣና ሳወርድ ነው ግማሹን መንገድ የጨረስኩት።
እኔ እና ሲራክ ሳባን በአንድ አጋጣሚ ነው እኩል ነው ያወቅናት።… አንዲት ቆንጆ ሰንበሌጥ፣ የተጠና አረማመዷን ትታ፣ በድንገት በቁሟ ዧ ብላ ልትወድቅ ቁልቁል ስትንሸራተት፤ እኔ እና ሲራክ የእርሷን እንቅስቃሴ ስንከታተል የነበርን ይመስል፣ ሰውነቷ ከመሬት ሳይጋጭ ደርሰን ስንይዛት አንድ ሆነ። ሲራክ ከወገቧ በታች እኔ ደግሞ  ከወገቧ በላይ ተሸክመናት ወደ ጥግ ወስደን ዐየር እንድታገኝ ረዳናት፤ ነፍሷ መለስ እስክትል ታግሰን ጠበቅናት።
ስትነቃ፤ እንደሁልጊዜው  ሰውነቷ በውኃ ርሶ፣ ነድደው ያለቁ የክብሪት እንጨቶች በዙሪያዋ ተበታትነውና የራሳቸውን ችግር ረስተው እኔን የሚሏት እናቶችን አላገኘችም። ከዚያ በተቃራኒው ሁለት አብሮ አደግ ጓደኞች መንቃቷን በጉጉት እየጠበቁ፣ ጭናቸው ላይ አግድም በክብር አስተኝተዋት ነው ራሷን ያገኘችው።
እኩል ያጠናነው ይመስል “ትንሽ ዕረፍት አድርጊ እንጂ?” አልናት ከእቅፋችን በፍጥነት ወርዳ ለመቆም ስትሞክር።  እንዴ ሲራክን፣ አንዴ እኔን፣ አንዴ ዙሪያ ገባውን በማፈራረቅ ስትመለከት ቆይታ፤ “የመታኝ ነገር አለ? የትስ አካባቢ ነው ያለሁት?” አለችን። ለጥያቄዎቿ መልስ ከመስጠት ባሻገር ነጻነትና ደህንነት እንዲሰማት የቻልነውን ጣርን።
“ይቅርታ  እንግዲህ፣ እስካሁን አላመሰገንኳችሁም። ሕይወቴን ስላተረፋችሁልኝ አመሰግናለሁ። አልፎ አልፎ ያጋጥመኛል። ንዴቴ ገደቡን ሲያልፍ፣ ከሰው መኖር እጅ እጅ ሲለኝ፣ አንስቶ የሚፈጠፍጠኝ ነገር አለ። ለነገሩ ሳይደግስ የማይጣላው አምላክ እየጠበቀኝ እስካሁን የከፋ ጉዳት አልደረሰብኝም።” መሃላችን ከነበረው የድንጋይ ንጣፍ ላይ ቁች አለች። የባጡን የቆጡን ስናወራ ከቆየን በኋላ አድራሻ ተለዋውጠን ተለያየን።
በጋራም ይሁን ለየብቻ እየተገናኘን ቀላል የማይባል ጊዜ አሳልፈናል። በኔ በኩል የተገናኘን እለት የተሸከምኳቸውን አካላቷን፣ በተለይ አይንና ከንፈሯን እጅጉን ወደድኳቸው። ቀስ በቀስ ለሷ ያለኝ የፍቅር ስሜት ግልጽ እየሆነላት መጣ። ይህንን ስሜቴን ሲራክ እንዳያውቀው በጣም ነው የምጠነቀቀው። አንድም እንዳይቀና፣ አንድም ብቸኝነት እንዳይሰማው በማለት በእሱ ፊት ለሳባ ያለኝን ስሜት ተንፍሼው አላውቅም። የሆነው ሆኖ ከብዙ ደጅ ጥናት በኋላ እኔና ሳባ ለጾታዊ ፍቅር የሚፈላለጉ ጥንዶች ሆነን ተገኘን፤ በኔ አስተሳሰብ።
ከባድ የመኪና ጥሩንባ ከሰመጥንበት የሀሳብ ውቅያኖስ ፈጥሮ አወጣን። ሳናስበው ሲራክ ከቀጠረን ቦታ ርቀን ብዙ ተጉዘናል። ተያየን። ሁለታችንም ነገር እየበላን እንደሆነ ምንም ሳንባባል ተግባባን። ምንም ትንፍሽ ሳንል ተለያየን።
በሌላኛው ቀን፣ ሲራክን ለብቻችን ስንገናኝ እንደ ሳባ ሰጠየኩት። ለነገሩ በስጋ የሚወለደው ሌላ ወንድም እንደሌለው ባውቅም፣ ያየሁትን ላለመቀበል እየታገልኩ መንትያ አለህ ወይ አልኩት። ጥያቄዬን በግርምት አድምጦኝ “ካንተ ሌላ መንታ ወንድም የለኝም፣” ብሎ ባጭሩ መለሰልኝ። ሆኖም እንደ ሳባ ለምን ጠየቅከኝ ብሎ ምክንያቴን አልጠየቀኝም።
ከዚያን እለት ጀምሮ ውስጤ ሲጨልም፣ የሆነ ነገሬ አንድ በአንድ ቅርጥስ… ዝንጥፍ… እያለ ሲረግ ይታወቀኝ ነበር። መራቅ አሰኘኝ። መጥፋት አማረኝ። ማንም የማያውቀኝ ማንንም የማላውቅበት የብቸኝነት ኑሮ የምገፋበት ስፍራ ተመኘሁ። ረዥም የመስክ ስራዬን እንደ ትልቅ መፍትሄ ቆጠርኩት። ስራዬ መደበቂያ ዋሻ ሆነኝ። በሄድኩበት ስፍራ ያለው የስልክ አገልግሎት አስቸጋሪ መሆኑ ለተወሰኑ ወራት  በአካልም በመንፈስም እንድለያቸው እረዳኝ። ብቸኝነቱም ወደራሴ እንድመለስ፣ ብስሉን ከጥሬው እንድለይ አገዘኝ።
ከወራት የመስክ ስራ በተመለስኩ ምሽት ሰውነቴን ሳላሳርፍ ለሲራክ እናት ያመጣሁትን ቡና ይዤ ወደ ሲራክ እናት ቤት ስከንፍ፣ ከወራት በፊት ያጋጠመኝ ክስተት ሞቅ ደመቅ ብሎ በድጋሚ ሲያጋጥመኝ በሳባ ላይ የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋ ድርግም ብሎ ጠፋ።  እንደበፊቱ ወደኋላ አልተመለስኩም። ከእናቱ ጋር ትንሽ ተጫውቼ ያመጣሁላቸውን ቡና ሰጥቼ በምላሹ ተመርቄ ልወጣ በሩ ጋር ስደርስ፣ በሩን ለአመል ቆርቆር አድርጎት ወደ ውስጥ ሲገባ አይን ለአይን ተገጣጠምን። ስላልጠበቀኝ ነው መሰል ደነገጠ። እኔም የማላውቀው ስሜት ረበሸኝ። ሳላውቀው ተጠመጠምኩበት። ለእናቱ እምቢ ያልኩትን  እራት ከሲራክ ጋር በልቼና ጥሩ ቡና ጠጥቼ ስጨርስ ድጋሚ እናትየውን ተሰናብቼ ወጣሁ። ሊሸኘኝ ተከትሎኝ ወጣ። ልንለያይ ስንል ስለ ሳባ ምን አይነት ስሜት እንዳለው ጠየቅሁት። ስሜቱን ከሀ እስከ ፐ ነገረኝ። እንደሚያፈቅራት ግን ደግሞ ልቧን ሙሉ በሙሉ ማግኘት እንዳልቻለና ምክንያቱን ማወቅ እንደተሳነው ባጭሩ ነገረኝ። ያለው የፍቅር ስሜት ባለፉት ወራት እለት በእለት በመገናኘታቸው እንደናረ አረዳኝ። “ደህና እደር” ከማለት ውጪ ምንም አስተያየት አልሰጠሁትም።
በሰልስቱ እሷንም ጠየቅኳት። አይኗን በጨው አጥባ ከእኔ ውጭ ለሌላ ሰው ስሜት እንደሌላት ምላ ተገዝታ ነገረችኝ። ግራ ተጋባሁ። ከአንዴም ሁለቴ ከግንቡ ስር ሲተሻሹ በስሜት ሲቃ ውስጥ የነበረውን ድምጻቸውን ሰምቻለሁ። ሲራክ የተደበቀውን አውጥቶ ሲነግረኝ ጨረቃዬ ግን አሁንም በጨረቃነቷ ቀጠለች። ልቤ እንዳኮረፈ፣ በጥርጣሬ ደመና እንደተጋረደ ጥቂት ጊዜያት ዐለፈ፡፡
በዓመት አንዴ የሚደርስብኝን የመስክ ሥራ ከቀጣይ ዓመት ተበድሬ ድጋሚ መስክ ለመውጣት ከአለቃዬ ጋር ብማከርም አልሳካ አለኝ፡፡ ድንገት ያገኘሁት ሌላ የመስክ ስራ ትዝ አለኝ፡፡ ከተማውን ጥዬ መሄድ እንዳለኝ ስወስን የጊዜ ቅንጣት አልወሰደብኝም፡፡ ከራሴው ጋር ተማክሬ ወሰንኩ፡፡ ለሥራ ጉዳይ ከከተማ ልወጣ እንደሆነ ለሁለቱም ነገርኳቸው፡፡ ሲራክ ላይ መከፋትን ባነብም፣ ሳባ ላይ ያየሁት ስስ ፈገግታና እንባ ጭንቅላቴ ውስጥ አድፍጦ የተኛውን የቅናት ዛር ቀሰቀሰው፡፡ የተዳፈነውን እሳት ቆሰቆሰችው፡፡ የኔ መራቅ ነጻነቷን እንደሚሰጣት የተሰማት መሰለኝ፡፡
እናቴ ያወረሰችኝን የወንደ ላጤ ቤቴን ላልተወሰኑ ወራት አከራይቼ፣ ያለኝን ጥቂትና መዝናኛ ዕቃዎቼን ላሳደጉኝ የሲራክ እናት በአደራ ሰጥቼ ኑሮዬን በአንድ ሻንጣ ከፍኜ፣ ለጉዞ ስዘጋጅ ሲራክ መጣ፡፡ አመጣጡ  ለምን ከተማውን ጥዬ ለመሄድ እንደወሰንኩ ለማወቅ የመጣ ይመስላል፡፡ የባጡን የቆጡን ስንቀባጥር ቆይተን ልንለያይ ስንል “አሁን ያለህበት ሁኔታ እንዴት ነው አልኩት?” ደስተኛ እንደሆነ አስረዳኝ፡፡ ሳባ ፍቅሯን በእርሱ ልክ ባትገልጽለትም፣ ያለምንም ማቅማማት እርሷን በማፍቀሩ ደስተኛ እንደሆነ ሲነግረኝ “ይመችህ!” አልኩት፡፡ ተለያየን፡፡ በአካልም በመንፈስም ተለያየን፡፡
ሁለት
ለናታን ያለኝን ስሜት ምንም ሳላቅማማ መናዘዜን አውቃለሁ፡፡ ናታንን ያለከልካይ ነበር ማፍቀር የምፈልገው፡፡ የስጋዬ ትኩሳት እንዲበርድ የምፈልገው ከናታን ጋር ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል? እርሱ ዛሬን አንቆ እየገደለ ነገን ለማዳን ይፍጨረጨራል፡፡ እኔ ዘጠና ዘጠኙን እርምጃ ተራምጄለት እርሱ አንድ እርምጃ መራመድ አቃተው፡፡ ስሜቱን ለመቆጠብ የሚያደርገው ግብግብ ጭራሽ የሚያበግን ነው፡፡ የልቤን ሰቀቀን ካዳመጠኝ፣ የስጋዬን ትኩሳት ካላበረደ አጥብቆ ልሳመኝ ደፍሮ ካላቀፈኝ ጣት ለጣት ተቆላልፎ መንገድ ለመንገድ መጓተት ምን ይበጃ? ምንም! እጅን ከማዛል ውጪ፡፡
ያም ሆኖ መፍትሄ ያልኩት ነገር ሌላ መዘዝ ይዞ መጣብኝ፡፡ ሲራክ ለእኔ ያውን ስሜት ተጠቅሜ ናታንን ለማስቀናት ወንድነት እንዲሰማውና ሴትነቴን እንዲያውቀው የዘየድኩት መላ ጦሱ ከባድ ሆነ፡፡ ያቺ ዓርብ ምሽት ትዝ ትለኛች፣… ጀርባዬን ለግንቡ ሰጥቼ ሲራክን አጓጉል ሳባልገው ናታን እንዳየን በነጋታው ጦፎ ይጠይቀኛል፤ በቅናት አብዶ ይንጨረጨራ ስል ዓይኑን ማመን ትቶ እኔ የነገርኩትን አምኖ ቀለል አድርጎ ዐለፈው፡፡ ለማስቀናት ብዬ የማደርጋቸው ጥቃቅን ነገሮች ሳይቀሩ ሲራክን ባልጠበቅሁት መጠን በማፍቀር አናወዙት፡፡
ናታን እና ሲራክን ስስማቸው ስሜቴ የተለያየ ነው፡፡ ሲራክን ከጭንቅላቴ በተሰላ በተጠና መንገድ ነበር የምስመው፡፡ ናታንን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከልቤ እስመው እንደነበር ማን ይንገረው?
ይባስ ብሎ ሲራክ በእኔ ፍቅር አቅሉን አጣ! ናታንም ባልገመትኩት ሁኔታ አድራሻውን አጥፍቶ ተሰወረ፡፡ ቆይ ናታንን አፍቅሬ እንደተሰቃየሁት ሲራክ መሰቃየት ነበረበት? በፍጹም፡፡ እኔ ያጣሁትን ለሲራክ ሰጠሁት፡፡ እኔ በናታን እንደተጎዳሁት ሲራክ በእኔ መጎዳት አልነበረበትም፡፡ ስለዚህ ለናታን ያዘጋጀሁትን እግሬን ለሲራክ ከፈትኩለት፡፡ ሲራ እርምጃውም ትልሙም ቅርብ ቢሆንም ያን ያህል አልከፋኝም፡፡ ቢያንስ እኔ ፍቅሩን እርሱ ደግሞ ትኩሳቴን ተጋግዘን ለማብረድ ሞክረናል፣ ሩቅ ለመጓዝ ባይሳካልንም፡፡
ከሲራክ ጋር ያለን የግንኙነት ቅርጽ መቀየር የጀመረው አንድ ቀን በጠየቀኝ አብግን ጥያቄ ነው፡፡ አንድ እሁድ ከሰዓት ቴያትር ለማየት ሰልፍ ላይ ቆመን ሳለ ፣ “መቼ ነው ትዳር መስርተን ልጅ ወልደን ልጃችን አድጎ አብሮን ቴያትር የሚያየው?” አለኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ የሲራክ የፍቅር ትኩሳት ጎጆ ከመቀለስ ዐልፎ ልጅ ስሞ አሳድጎ አብሮ ቴያትር ለማየት ወደ መመኘት አደገ፡፡ እንዳልሰማሁ ባልፈውም ውስጤ ላይ የጫረው እሳት ይፈጀኝ ጀመር፡፡ በተለያየ ጊዜ ቆንጠር እያደረገ ጣል የሚያደርጋቸው የምኞት ጠጠሮች እየከበዱኝ መጡ፡፡ በሌላ ጊዜ “መቼ ነው በአንድ ጣራ የምንጠቃለለው?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ይሄንን ጥያቄውን መቼም ቢሆን አልመልስለትም፡፡ መልሴ ‘መቼም!’ ቢሆንም ቃል አውጥቼ ግን አልመልስለትም፡፡ ምን አልባት ስለልጅ መውለድ ቢጠይቀኝ ኖሮ መልሴ ትንሽ ይለዝብ ነበር፡፡ ከማግባት መውለድን እመርጣለሁ እንጂ፣ ለልጅ ብዬ በትዳር ካቴና መጠፍነግ አልፈልግም፡፡ ማግባት ሌላ ልጅ መውለድ ሌላ፡፡
የእውነቴን ነው የሴትነቴን ጸጋ ማጣጣም እፈልጋሁ፡፡ አርግዤ አምጬ ብወልድ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ነገር ግን እኔ ለምወልደው ልጅ እንጂ ለማገባው ወንድ መጉበጥ አልፈልግም፡፡ ከወንድ ዘሩን እንጂ እስሩን አልመርጥም፡፡ በርግጥ ለልጁ ጤናማ ህይወት እናት እና አባት ባንድ ጥላ መኖራቸው አስፈላጊ እንደሆነ አይጠፋኝም! ለልጄ ጥሩ እናት መሆን ብችልም እንኳ የአባቱን ቦታ መሸፈን እንደማልችል ዐውቀዋለሁ፡፡ ግን ልጄ የግድ ሁሉ ተሟልቶለት ማደግ የለበትም፡፡  እኔስ ያአባት አድጌ የለ? ምን ሆንኩ? እንደውም ሙሉ ቤተሰብ ያላቸው ልጆች ያዩትን የህይወት መንገድ ዐይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ማግባት ግዴታ አይደለም፡፡ ልጅ መውለድ ግን ግድ ነው፡፡ ግን ከሚወዱት መሆን አለበት፡፡
ከሲራክ በኋላ በጥሩ ወንድ ፍለጋ ውስጥ ከንፍጣሙ ምራቁን እስከዋጠው ድረስ ተግባብቼ ከተመቹኝ ጋር ተዋድጄ ተዋዝቻለሁ፡፡ ግን ምን ያደርጋል እንደእናቴ አባባል ‘ሁሉንም ወንዶች እንደአባቴ አድርጌ መቁጠሬ እንደንስሀ አባቴ ገላጻ  ‘ያለብኝ ዓይነ ጥላ’ እንደ የስነ ልቦና ሀኪሜ ማብራሪያ ‘በገጠመኝ የማንነት መጣለዝ’ ምክንያት መቼ ልቤ ካረፈበት ጋር እንድጸና ያደርገኛል፡፡ ማናቸውም ቢሆኑ የፈለጉትን የማለት መብት አላቸው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከናታን በኋላ (ሲራክን ጨምሮ) ከመጡ ወንዶች ጋር የጀመርኩ ግንኙነት መስመር ሲይዝ ፍቅር ፍቅር ሲያሰኛቸው ወደ ትዳር ሰለማምራት ወሬ ሲጀምሩ ነገር ነገር ይለኛል፡፡  ግንኙነታችን መስመር ያዘ ብለው ደስ ሲላቸው ባንዱ ላይ ሌላ መደረብ ያምረኛል፡፡ በሌላ መልኩ ስንት የጓጓሁለት በእጄ ላይ ሲሆን ድብርቴ ጣራ ይነካል፡፡ ሁሉን ነገሩን እየወደድኩለት እንኳ ከሱ የምርቅበትን ቀጭን ቀዳዳ ፈልጌ ተመልሶ እንዳይገጥም አድርጌ አሰፋዋለሁ፡፡ ሲራክም አሁኑነ,ን ትቶ ስለነገ ማሰብ ሲጀምር ነበር አፍንጫው ስር እያለሁ ለዓመታት እንዳያየኝ አድርጌ የተለየሁት፡፡ ሲጎዳ እያየሁት ካንዴም ሁለቴ ታሞ ሲሰቃይ ‘እግዜር ይማርህ’ ሳልለው ጨክኜበታለሁ፡፡ እናቱም ሲያርፉ ‘ፈጣሪ ያጽናህ’ ሳልለው እርሙን በልቻለሁ፡፡
ሦስት
የናታን እና የሳባ ጉዳይ አሁንም ድረስ ይከነክነኛል፡፡ ዘግይቼ ባስተውልም ናታን ከእኔ መራቁ ሆነ ብሎ ያደረገው ነገር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ያለእማዬ እናት ያለ’ኔ ወንድም የሌለው ብቸኛ ሰው እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ አስተዋይነቱ እርጋታው እና አመስጋኝነቱ ሰብእናውን ከፍ ያደርጉታል፡፡ ዘግይቼም ቢሆን የደረስኩበት ከእኔ እና ከሳባ ለመራቅ ብሎ እንጂ መስሪያ ቤቱ ከተማ ወደሚያስለቀቅ የመስክ ስራ አስገድዶ አልላከውም፡፡ ያን ያህል ከእኛ መራቅ እንደፈለገ የገባኝ የአዲሱ መስሪያ ቤት አለቃውን የመስክ ስራ ላይ ላልተወሰነ ጊዜ በቋሚነት እንዲመድበው እንደለመነው ስሰማ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰሞን ከሳባ ጋር የነበረንን ህልም ይሁን ቅዠት ያለየለትን ግንኙነት ለናታን መናገር ከበደኝ፡፡ ቢያንስ እኔ ለእርሷ ያለኝ ስሜት መስመር ያዘ ብዬ ባመንኩበት ጊዜ ነገርኩት፡፡ ግን በፍቅር እፍ ክንፍ ብለን እንደነበር ልነግረው ያቻኩት እርሱ ካጠገቤ ስላልነበር ነው፡፡ እርሱ በሌለበት ሳባን አጣኋት፡፡ እርሱ በሌለበት እናቴን ቀበርኳት፡፡ አይ ሳባን አጣኋት ሳይሆን ተገላገልኳት ነው ማለት ያለብኝ፡፡ እናቴን እና ናታንን ሳጣቸው ጊዜ ግን ራሴን አጣሁት፡፡
ሳባ ለእኔ ንግስት ንብ ነበረች፡፡ ጋሻ ዣግሬዎቿን ልካ ከሀገሬ ነቅላ አታሰድደኝ እንጂ የሆነው ነገር እንደዛ ነው፡፡ የዕለት ዕለት ዕቃ እቃችንን ትተን ትዳር እንመስርት ጎጆ እንቀልስ ካልኳት እለት ጀምሮ ነገረ ስራዋ ሲቀየር ይገባኛ፡፡ በነጋታው በቀጠርኳት ስፍራ ላይ ከሌላ ወንድ ጋር ሆና አገኘችኝ፡፡  ይባስ ብላ እኔን ላለማግኘት ያደረገችው ጥረት የለም፡፡ ምክንያቷ ምን እንደሆነ ሳላውቅ ወይም እንጋባ ማለቴ ጥፋት ሆኖ ነው መሰል ተሰወረችብኝ፡፡ አንዳንዴ እርሷን ያየሁ ይመስለኛል፡፡ ግን አይደለችም፡፡
ከባድ ወቅት አሳለፍኩ፡፡ በተለይ እናቴ ያረፈች ሰሞን በጣም ከባድ ወቅት አሳለፍኩ፡፡ ናታን ካጠገቤ ቢሆን ተመኘሁ፡፡ የእናቴ ሰልስት በዋለ በነጋታው ወደናታን መስሪያ ቤት ሄድኩ፡፡ ከሰዓታት ጥበቃ በኋላ የቀድሞ አለቃውን አግኝቼ በስንት ጉትጎታ እና ልመና ናታን ያለበትን አድራሻ ለማወቅ ቻልኩ፡፡
ከአለቃው ባገኘሁት ስልክ ቁጥር ደውዬ የሆነውን ነገርኩት፡፡ ‘ወይኔ እናቴን ሳልቀብራት?’ ብሎ ሳይሰናበተኝ ስልኩን ዘጋው፡፡
ከቀናት በኋላ ከሻይ ቤቱ ደጃፍ አቀርቅሬ መሬቱን በስንጥር ስጭር የሰው ጥላ ሙንጭርጭሬን ሸፈነብኝ፡፡ ቀና አልኩ፡፡ ረዘም ያለ ዓይኑን በጥቁር መነጽር ፊቱን በሪዝ የሸፈነ ሰው እንደ ጅብራ ከፊቴ ቆሟል፡፡ ናታን ነው፡፡ እርሱ መሆኑን ለየሁት እንጂ ተክለ ሰውነቱ የእርሱ አይደለም፡፡ በቀኝ እጁ ከጀርባው ላይ አንጠልጥሎ የነበረውን ሻንጣ መሬት ላይ ጣለው፡፡ በተቀመጥኩበት መሬት ላይ ተንበርክኮ ተጠመጠመብኝ፡፡
ከተንበረከከበት ተነስቶ ሻይ ቤቱ ውስጥ ወደ ጥግ ካለ ጠረጶዛ ሄዶ ፊቱን ጠረጴዛው ላይ ደፍቶ፣ ከኪስ ቦርሳ ውስጥ ያወጣውን የእናቴን ፎቶ በደረቱ ታቅፎ ምንም ድምጽ ሳያሰማ ሰውነቱ እየተንዘፈዘፈ ተንሰቀሰቀ፡፡ በአርምሞ ዕንባውን እየረጨ እርሙን አወጣ፡፡ ለረጅም ሰዓታት ማናችንም ትንፍሽ አላልንም፡፡ ከተደፋበት ቀና ሲል አይኑ ድልህ በርበሬ መስሏል፡፡ ግን ቶሎ ብሎ በጥቁሩ መነጽሩ ሸፈነው፡፡ ዓይኔን ማየት ጠልቷል ወይም ፈርቷል፡፡ በመካከላችን ያለው ዝምታ ያስፈራል፡፡ ከተገናኘን ረጅም ሰዓታት ቢሆንም ከሻይ ውጪ ምንም አላዘዝንም፡፡ እሱንም ማናችንም አልጠጣነውም፡፡ ከነበረበት ስሜት ከወሰደው የሀሳብ ማዕበል ሲመለስ ጉሮሮውን ጠራርጎ፤ “የተመቸህ አትመስልም?” አለኝ፡፡
ራሴን ነቅንቄ “አዎ አልተመቸኝም፣” አልኩት፡፡
ድንግዝግ ያለው ነገር መጥራት ሲጀምር የታወቀኝ መሰለኝ፡፡ ሲለየኝ የንግግሩን መጨረሻ     ‘ይመችህ’፣ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ሲያገኘኝ ደግሞ ‘የተመቸህ አትመስልም’ ያለው ነገር ቆረቆረኝ፡፡ ዕረፍት ነሳኝ፡፡ ሳሌ አጣደፈኝ፡፡ ከቀልቤ መሆን አቃተኝ፡፡ አስተናጋጇ ያመጣችውን ውኃ ወደ’ኔ ገፋው፡፡
ከተረጋጋሁ በኋላ “ለምን ይሄን ያህል ለመራቅ ወደድክ?” ብዬ ስጠይቀው ዓይን ዓይኔን እያየኝ “አንተ እና ሳባ እንዲመቻችሁ በተለይ አንተ እንዲመችህ ብዬ ነው ሀገሩን ጥዬ የተሰደድኩት” አለኝ፡፡ “እምነቴን ፍቅሬንና ተስፋዬን መስታወት ነው ብለው በጠጠር ሰብረው ትንሽ ለማድረግ የሚጥሩ፤ ለምልክት የሚሆን ስንጥቅ ጥለው ከማለፍ ውጪ መስታወትነቴን ሊያጠፋት አለመቻላቸውንና ይህንንም መዘንጋታቸው ይገርመኛል፡፡ እውነቴ ጎማ ሆኖባቸው ብንጠመዝዘው አይበጠስም ብለው የመጠምዘዝ ልኬን የሚፈታተኑኝ ሰዎች እንደአሸን መብዛታቸው ይደንቀኛል” አለኝ፡፡ አልገባኝም፡፡ የምር ጠጠር፣ የምን መስታወትና የምን ጎማ ነው የሚያወራው? እምነት፣ ፍቅርና ተስፋውን ለምን በመስታወት ወከላቸው? ንጹህ ሁሉን የሚያሳይ ግን ተሰባሪ ናቸው ማለት ነው? ለምንስ እውነቱን በጎማ ወከለው? እውነተነቱ ከትናንትና እምነቱ ከዛሬው ፍቅሩና  ከነገው ተስፋው የተቀዳ አይደለምን? ታዲያ እነዚህ በክህደት ጠጠር በትንሽ ትንሹ ሲሰበሩ እውነቱስ አብሮ አያንስም? ወይስ መስታወቱ ምን ያህል ቢያንስ ከማሳየት ስለማይቦዝን ይሆን እውነቱን ቢጠመዝዙት የማይበጠስ ጎማ የሆነው? ጥምዘዛው ከማንነቱ ፈቅ የማያደርጉት  ለዚያ ይሆን? እንጃ! ጭንቅላቴ ዛለብኝ፡፡ ጠጠሩ እኔ እሆን? ወይስ ባለጠጠሩ? ነገሮችን መለስ ብዬ ለማውጠንጠን ብሞክርም አልገባህ አሉኝ፡፡
ሁሉን ነገር እንዲያስረዳኝ ለመንኩት፡፡ ከለመንኩት በላይ እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር አረዳኝ፡፡ ማመን አቃተኝ፡፡ ጆሮዬ ላይ ጭውውውውውውው ከሚል ውጪ ሌላ ነገር አልሰማ አለኝ፡፡ ሁሉም ነገር ህልም ቢሆን ተመኘሁ፡፡


Read 864 times