Saturday, 30 December 2023 20:38

ዳሽን ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የክፍያ አማራጭ አስተዋወቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዳሽን ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ደንበኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ክፍያውን ቆይተው የሚከፍሉበትን ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ የተሰኘ አዲስ የክፍያ አማራጭ አገልግሎት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በጋራ አስተዋውቀዋል፡፡  
የዳሽን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን አቶ ዮሐንስ መኮንን እንደገለጹት፤ ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ የተሰኘው አዲሱ  የክፍያ አማራጭ  በደንበኞች ምርጫ መሰረት በ6 ወር ወይም በ12 ወር የብድር ክፍያ የሚሰጥ ነው፡፡  ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሽን ባንክ የሂሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚገባቸውና በተጨማሪም በባንኩ ቢያንስ ለሦስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡
አዲሱን አገልግሎት ለመጠቀም አንድ ደንበኛ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ካሟላ በኋላ በቅርንጫፉ የተፈቀደለትን የብድር መጠን የሚወስድ ሲሆን፤ የተፈቀደለትን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያስችል የአንድ ጊዜ መለያ ቁጥር መልዕክትም በተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚደርሰው ይሆናል።
 በመቀጠልም ደንበኛው የተሰጠውን መለያ ቁጥር በአየር መንገዱ የሞባይል መተግበሪያ ላይ በማስገባት ትኬት መቁረጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።
በሁለቱ ተቋማት ስምምነት በቀረበው በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈቀደው የብድር ገንዘብ መጠን እስከ ስድስት መቶ ሺ ብር የሚደርስ ነው። የሚፈቀደው ብድር ወለድ የሚታሰብበት ሲሆን፤ ይህም ደንበኛው በመረጠውና ብድሩን በወሰደበት የጊዜ ገደብ ከብድሩ ጋር አብሮ የሚከፈል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ተኮር አሰራርን እንደመከተሉ የተለያዩ ዘመናዊና ለመጠቀም ቀላል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል። የምናበለጽጋቸው ቴክኖሎጂዎች ለደንበኞቻችን ምቹ መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆኖ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጋርም የተጣጣሙ እንዲሆኑ እናደርጋለን። ዛሬም አጋራችን ከሆነው የዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር ለደንበኞቻችን ያቀረብነው አዲስ የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያችን ከአዲሱ የክፍያ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ እንዲሆን አድርገናል” ብለዋል።
ደንበኞች የተፈቀደላቸው የብድር መጠን ሲያልቅ ማደስ የሚችሉ ሲሆን፤ በአንዴ የወሰዱትን ብድርም ለተለያዩ በረራዎች ከፍለው መጠቀም እንደሚችሉ ታውቋል፡፡  አገልግሎቱ በተለይም በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ ጅምላ አስመጪዎችና ለዕረፍት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ውጭ ለሚሄዱ ደንበኞች አመቺ ነው ተብሏል።

Read 362 times