Saturday, 06 January 2024 21:12

ለሰው የወረወሩት ቀስት፣ ራስን ይቀስፋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በአይሁዳውያን የሚነገር የአንድ ብልጥ አይሁድ አፈታሪክ እንዲህ ይላል።
አንድ ጊዜ አንድ ህጻን ልጅ በአንድ አይሁዳውያን መንደር ሞቶ ይገኛል። የመንደሩ አይሁዳውያን ተጠሪ የግድያ ተጠርጣሪ ይሆንና ፍርድ ቤት ይቀርባል። ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም እንዲቃጠል ይወሰናል።
ዳኛው አይሁዳውያንን አይወዱም። ስለዚህ በአደባባይ እንዲህ አሉ፤ ወደሰማይ እየተመለከቱ፤
“እንግዲህ ፍርድ የአምላክ ነው። ሁለት ወረቀቶች ላይ እጣ እጽፋለሁ። “ወንጀለኛ” እና “ከጥፋት ነጻ” አይሁዱ “ወንጀለኛ” የሚለውን ካወጣ እንዲቃጠል ተፈረደበት ማለት ነው። “ከጥፋት ነፃ” የሚል የሚለውን ካወጣን በነጻ ይለቀቃል ማለት ነው።” አሉ።
ዳኛው ይህን ካሉ በኋላ ግን በልባቸው አይሁዱ በምንም አይነት ነጻ የማይወጣበትን ዘዴ እየፈለጉ ነበር። ማንም እንደማይጠረጥራቸው እርግጠኛ ነበሩ። ያገኙት ዘዴ በሁለቱም እጣ ወረቀት ላይ “ወንጀለኛ” የሚል መጻፍ ነበር። ጻፉና ሳጥኑ ውስጥ ከተቱ።
አይሁዱ ወደ እጣ ማውጫው ሳጥን እንዲመጣ ተጠራ። አይሁዱ ግን ዳኛውን ጠርጥሯቸዋል። ስለዚህ እሱም በበኩሉ ዘዴ ሲያጠነጥን ቆይቶ ኖሯል።
ከሳጥኑ ውስጥ አንዱን የተጠቀለለ እጣ አውጣና ሳይገለጥ በፊት እንደተጠቀለለ ወደ አፉ ከተተና በፍጥነት አኝኮ ዋጠው።
ዳኛው አይናቸው ፈጠጠ። ደነገጡ።
“ይሄ ምን ማለት ነው? ምንድን ነው ነገሩ?” ሲሉ ጠየቁ።
“ነገሩ ቀላል ነው። ሳጥኑ ውስጥ የቀረውን እጣ በማየት ወንጀለኛ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ይቻላል” ሲል  ሀሳቡን ገለጸ። የቀረው እጣ  ይታይ በሚለው ላይ ተስማሙ። በኋላም ሳጥኑ ውስጥ ያለው እጣ ወጣ። ተገልጦ ሲታይ “ወንጀለኛ” ይላል። ዳኛው “ይሄዋ ወንጀለኛ ነህ” አሉት።
አይሁዱ፤ “ወንጀለኛ አይደለሁም። ምክንያቱም ይሄ ማለት እኔ የዋጥኩት “ከጥፋት-ነጻ” የሚለውን እጣ ነው ማለት ነው። ስለሆነም መፈታት ይገባኛል” ሲል አብራራ። ዳኛው ምንም ሰበብ ፈጥረው ወንጀለኛ ሊደርጉት ባለመቻላቸው እንዲለቀቅ ወሰኑ።

ያላግባብና በጥላቻ “ጥፋተኛ ነህ” የመባል አደጋ ሊኖር እንደሚችል መጠራጠር ተገቢ ነው። በቀላሉ ለመገመት እንደሚቻለኝው፤ ማንም የባላንጣውን ትክክለኛ መልስ የማረጋገጥና አበጀህ የማለት ቀናነት የለውም። በተለይም ድክመቱን የሚያሳይ ገጽታውን አይፈልገውም።
ከስር መሰረቱ ጥፋቱን እንጂ ልማቱን የማይፈልጉ ባላንጣን ምንም ቀዳዳ ሊሰጡት አይሹም። ይልቁንም ህይወቱን አደጋ ላይ “ወንጀለኛ” ብሎ ጽፎ መገላገልን ይመርጣሉ።
አንዳንድ ጊዜ ንጹህና ሀቀኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ብልህ መሆንን እንደሚያሻ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢበዛ ብልህነት ቢያንስ ደግሞ ብልጠነት እንደሚያጡ ልብ ማት አለብን። በሁለቱም እጣ ወንጀለኛ ላለመሆን አንዱን በንጥሩ ለመጨበጥ የረባ እርምጃና አስተሳሰብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ያረጀ ልማድና የአመለካከት ዘዴን መለወጥ ዋና ጉዳይ ሆኗል። የምትበድለውን ማወቅ ከበቀሉ ያድንሃል። “አትዋልባት እንዳትውልብህ፣ አትሳላት እንዳታርድህ” እንዲል መጽሐፈ-ምሳሌያዊ አነጋገር። ጭፍን ጥላቻ በየትም መልኩ ቢመጣ የሀገራችን ጠላት ነው። ከኔ ካልሆንክ ከጠላቴነህ ላይ የከፋ ጽንፉ የመሆኑን ያህል ከእኔ ጋር ቆይተህ ድክመት ከታየብህም የጠላቴን ፖለቲካ አጠናክረሃል ማለትም ያው የተሳሳተ ድምዳሜ ነው። ዞሮ ዞሮ ከጠላት የመፈረጃ መካከለኛ ሞገድ ነው። በወጉ በመደራጀት በመብዛትና በመባዛት ፓርቲን ማጠናከር ዋና ነገር ነው። “አትጎብዙ ማለት ነው እንጅ እርግማን አትባዙስ እርግማን አይደለም” የሚለውን ተረት ልብ እንበል። “ጠንካራ ተቃዋሚ ይስጠን” ማለት ጥሩ ጸሎት ነው። ተቃዋሚ እንዳይጠናከር እንቅፋት መፍጠር ግን ከሃጥያት አንዱ ነው። ተቃዋሚው አልጠነክር ማለቱ የራሱ ችግር ነው ማለት ክፉ ነገር አይደለም። ሆን ብሎ የሚበተንበትን መንገድ መተለም ግን ይሁነኝ ብሎ ወደ ጥፋት ማምራት ነው።
ከአንድ ተቋም፣ መ/ቤት የፖለቲካ ፓርቲ፣ ድርጅት ወይም ፓርቲ፣ በማናቸውም መዘዘኛ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ለመቀነስ/ለማስወገድ እርምጃ መውሰድ (ዱሮ ሌኒን Purging is purfying ይለው ነበር)/ ማባረር ማጥራት ነው እንደማለት ነው/ በደፈና ሲያዩት ቀላል ይመስላል። በውስጡ ያዘለው ነገር ግን ውስብስብ ነው። ቢያንስ ሶስት ነገሮችን ያዝላል፡-
1ኛ/ በማን ይተኳል 2ኛ/ ልምዱን በምን ያካክሰዋል? 3ኛ/ በእድሜ ብቻ የሚበለጽገው ብስለት ከወዴት ያመጣዋል? ከዚህ በተረፈ ግን ያ የተወገደ ወይም የተባረረ ግለሰብ ቡድን ወዴት ይሄዳል፣ ከማን ይወዳጃል? ድንገት ከባላንጣ ቢወግን ምን አይነት መከላከያ አለ? ወዘተ በታሪክ ሆኖ ዛሬ ተቋሞቻችን፣ ፓርቲዎቻችን መፍትሄ ያላበጁላቸው፣ ዝግጅት የማያደርጉባቸው ክስተቶች ናቸው። የፖለቲካ ሃይል መመናመን፣ መሰነጣጠር፣ ተከፋፍሎም የእኔ ሃይል የሚያክል የታለ ብሎ በባዶ መኩራራት፣ ከእኔ የወጣ ከሀዲ ከእኔ ጋር ያለው ሀቀኛ ቢኖር ፍጹም ማለት ወዘተ ብርቱ ጉድለቶቻችን ተደጋጋሚ ድክመቶችን ናቸው። እነዚህን ሁሉ የሚያካትትልን ደግሞ ወደሌላ የምንልከው ውንጀላ ወደሌላው የምንለኩሰው ጥይት መልሶ ራሳችንን ሊያጠፋን እንደሚችል ማሰባችን ነው። ሁሉም የጊዜ ጉዳይ ነዋ!  ፈረንጆች ወደፊት ተወርውሮ መልሶ ወደራስ መጥቶ የሚወጋ ቀስት/ሹል እንጨት ቡመራንግ ይሉታል (Boomerang):: ከዚህ መዳን አለብን። ቀስቱን ሰትረን ከመቀሰታችን በፊት አላማችንንና ግቡን በውል ማጤን አለብን። የምንፈልገውን በፍትሃዊነት መመዘን አለብን።
በዚህ መንፈስ ዛሬን በጋራ እናስብ፣ እንስራ፣ በዓላችንን እናክብር። መልካም የልደት በዓል፡፡Read 957 times