Saturday, 13 January 2024 00:00

IUCD…. በማህጸን ውስጥ ሊረሳ ይችላል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  በአገራቸን በተለምዶ ሉፕ የሚባለው በትክክለኛው ስያሜው IUCD የተባለው ያልተፈለገ እርግዝና መከላ ከያ ባህርይ እና አጠቃቀሙ ምን ይመስላል የሚለውን ከአሁን ቀደም ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ምናልባትም በጊዜው ይህ እትም ከእጃችሁ ያልገባ ወይንም በጊዜው ማንበብ ላልቻላችሁ መልእክቱን ታገኙ ዘንድ በድጋሚ እነሆ ብለናል፡፡ ማብራሪያውን ሰጥተውን የነበሩት ዶ/ር ሙሁዲ አብዶ ሲሆኑ የጽንስና ማህጸን ሐኪምና በተጨማሪም የመካ ንነትና ሌሎች የስነተዋልዶ ጤና ችግሮች እስፔሻሊስት ለመሆን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒ ታል በስልጠና ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡በመደበኛነት ግን በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል በመስራት ላይ ናቸው፡፡


ዶ/ር ሙሁዲን የ IUCD መጠሪያ በተለይም በአገራችን በአማርኛ ቋንቋ ሉፕ በሚል ስያሜ የተለመደ  መሆኑ ከምን እንደመጣ ለጊዜው ባይታወቅም ትክክለኛው ስሙ ግን IUCD ነው፡፡ ሉፕ የሚለው ልማዳዊ አጠራር በጭራሽ የማይገልጸው እና የቃሉም ትርጉም  IUCD ከተባለው የእርግዝና መከላከያ ተግባር ጋር የማይገናኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ በአጭር አጠራሩ IUCD ወይንም IUD በመባል የሚጠራው መከላከያ በማህጸን ውስጥ እንዲቀመጥ በማድረግ እርግዝናን እንዲከላከል የሚያደርግ መከላከያ ነው ብለዋል፡፡


በመጀመሪያ ይህ የመከላያ ዘዴ ባህርይው ምንአይት ነው፤ ጥቅሙስ ምንድነው፤ ለምን ያህል  ጊዜስ ያገለግላል ምን አይነት መከላከያ ነው የሚለውን ስንመለከት IUCD በማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን በሁለት አይነትም የሚከፈሉ ናቸው ፡፡ ይህ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ
አንዱ አይነት ሆርሞን የሌለው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ፕሮጀስትሮን የተባለው ሆርሞንን የያዘ ነው፡፡ በእኛ ሀገር በስፋት የሚገኘው እና ተግባር ላይ የዋለው ግን ሆርሞን የሌለው IUCDአይነት ነው፡፡ IUCD በየጊዜው ፍተሻ እየተደረገለት ነገር ግን ከአስር እስከ አስራ ሁለት አመት
ድረስ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል መከላከያ ነው፡፡ ግልጋሎቱን በሚመለከት በተለይም በእኛ ሀገር ግልጋሎት ላይ በስፋት የሚውለው ሆርሞን የሌለው አይነት በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በጤና ባለሙያዎች ዘንድ እጅግ ተመራጭ የሆነ ለእናቶችም ቢሆን አብዛኛው ውን ጊዜ
የጎንዮሽ ጉዳቱ እጅግ ያነሰ በመሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ በሆርሞን ምክንያት አንዳንድ የጤና ችግር ያለባቸው እናቶች በሆርሞን ምክንያት የነበረባቸው የጤና ችግር እንዳይባባስ ስለሚያደርግ እና መከላከያው የተለያዩ የጤና ችግሮች ያለባቸው እናቶችም ሊጠቀሙበት የሚችሉት ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ግልጋሎቱም የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረዥም ጊዜ በመሆኑ እና እርግዝና በሚፈለግበት በማንኛውም ጊዜ ግን ከማህጸን እንዲወጣና እርግዝናው እንዲከሰት ማድረግ ስለሚቻል ተመራጭ ያደርገዋል፡፡


IUCD በማህጸን ውስጥ በመቀመጡ ብቻ የወንድ የዘር ፍሬ ከሴትዋ እንቁላል ጋር እንዳይገናኝበማድረግ እና በማስተጉዋጎል እንዲሁም የእርግዝናው አካባቢ ለእርግዝና ምቹ እንዳይሆን በማድ ረግ ተግባሩን የሚያናውን መከላከያ ነው፡፡ ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያዎች
አይነታቸው ብዙ እንደመሆኑ ውጤታቸውም ሲለካ ከሌሎች መከላከያዎች ይልቅ IUCD እጅግ የተሳካ ውጤት ያለው መሆኑ ተመስክሮለታል፡፡ መከላከያው በትክክለኛው መንገድ በማህጸን ውስጥ ከተቀመጠ እና አጠቃቀሙም በትክክለኛው መንገድ ከሆነ እስ 99%እና ከዚያ በላይ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል እንደሚችል ተረጋግጦአል፡፡ ሌሎቹን መከላከያዎች በተመለከተግን የዚህ አይነት ከፍተኛ የመከላከል ብቃት ያላቸው አይደሉም ፡፡ ስለዚህም ይህ IUCD የተባለው ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በየትኛውም የአለም ክፍል የእኛን ሀገር ጨምሮ
በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል ነው ብለዋል ዶ/ር ሙህዲን፡፡


የእርግዝና መከላከያን ለመጠቀም በአለም የጤና ድርጅት በወጣው መመሪያ መሰረት አራት ክፍሎች ያሉ ሲሆን ይህ መከላከያ ግን ካለምንም ስጋት በማንኛዋም ሴት ከጥቅም ላይ ሊውል የሚችል መከላከያ መሆኑ ተጠቅሶአል፡፡ ለምሳሌ እንደ ኪኒን፤መርፌ፤በክንድ ላይ የሚቀ
በረው…የመከላከያ ዘዴ ሆርሞን ያላቸው በመሆናቸው እንደ ስኩዋር፤ደም ግፊት፤የልብ  ህመም፤የደም መርጋት የመሳሰሉት ችግሮች ላለባቸው ሴቶች እንዲጠቀሙባቸው የማይመከሩ  መከላከያዎች ናቸው፡፡ IUCD ግን እንደዚህ ያሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸው እናቶችን ጨምሮ
ማንኛዋም እናት ካለምንም ስጋት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ስለዚህም ደህንነቱ አስተማማኝ ስለሆነ  ማንኛዋም በመውለድ ክልል ያለች እናት አስቀድማ ልጅ የወለደችም ትሁን ያልወለደች ብትሆን  መጠቀም ትችላለች፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ስለ IUCD አጠቃቀም አንዳንድ የሚነገሩ ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌም ቀደም ሲል የወለደች እናት እንጂ ሌላ እናት IUCD የተባለውን መከላከያ መጠቀም አትችልም የሚል የተሳሳተ አስተያየት ይሰጥ ነበር፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ማንኛዋም በመውለድ የእድሜ ክልል ውሰጥ ያለች ሴት አስቀድማ ልጅ ወለደች አልወለደች የሚለው ጥያቄ ሳይነሳ ሁሉም መጠቀም ይችላሉ፡፡


በአኑዋዋር ደረጃ IUCD ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች እዚህ ቦታ ይኑሩ እዚህ ቦታ አይኑሩ፤ ይህንን ስራ ይስሩ ይህንን አይስሩ የሚል የተለየ መመሪያ የለውም፡፡ ማንኛዋም ሴት በተለይም በቋሚነት ትዳር ያላት ሴት ከሆነች መከላከያውን ለመጠቀም አሳሳቢ የሚሆንባት ነገር የለም፡፡    IUCD ወደ ማህጸን ከመግባቱ በፊት እርግዝና መኖር ያለመኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህ ትልቁ  መስፈርት ሲሆን በተረፈ መከላያውን ከመጠቀም በፊት የወር አበባ ያየች መሆን ሌላው መከላከያውን ለመስጠት አስፈላጊው ነገር ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጥንቃቄዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ለምሳሌም መከላከያውን ያደረገች ሴት የወር አበባዋ የሚበዛባት ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ከወር አበባ ጋር አብሮ የመውጣት ነገር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በእርግጥ ይህም በአብዛኛው የሚያጋጥመው መከላከያው በተደረገ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህም አንዲት
እናት መከላከያው በማጸንዋ ከገባ በሁዋላ ከሚመጣው የወር አበባ ተከትሎ መከላከያውን ወደ አደረጉላት ባለሙያዎች በመሄድ መከላከያው በማህጸን ውስጥ መኖር አለመኖሩ እንዲረጋገጥ መታየት አለባት፡፡ ከዚህ በሁዋላ ግን ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ  ወደ
ህክምና ተቋሙ እየሄደች እየታየች እስከ አስር እና አስራ ሁለት አመት ድረስ ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡


IUCD በማህጸን ውስጥ በሚቀመጥበት ጊዜ ከስር በማህጸን በር በኩል እስከ ሁለት ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ክር ወደ ውጭ ይቀራል፡፡ ይህ ክር IUCD በትክክል በማጸን ውስጥ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው፡፡ ይህ ወደ ውጭ የሚቀረው ክር መከላከያው ከማህጸን
እንዲወጣ በሚያስፈልግበት ጊዜ የሚጎተትበትም ነው፡፡ ስለዚህ አንዲት እናት በማህጸንዋ መከላከያው በመቀመጡ ምክንያት ልታደርገው የሚገባት የተለያ ጥንቃቄ የሌላት ቢሆንም ነገር ግን እንደኢንፌክሽን ያሉ ህመሞችን መጠንቀቅ፤ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት የመሳሰሉትን
ነገሮች ማስወገድ ይገባታል፡፡ በተረፈ ግን ካለምንም ስጋት እንቅስቃሴ ማድረግ፤ ማንኛውንም ስራ እየሰራች ኑሮዋን መኖር ትችላለች፡፡
IUCD በማጸን ውስጥ እያለ እርግዝና የመከሰቱ ጉዳይ በጣም በጥቂቱ ምናልባትም ከአንድሺህ ተጠቃሚዎች ውስጥ በሁለት ወይንም በሶስት ሴቶች ላይ ሊከሰት ይችል ይሆናል፡፡ ይህም በህክምና እና በቤተሰብ ምክክር አስፈላጊው ሀሉ ተደርጎ እርግዝናው ካልተፈለገ የሚወገድበት
ወይም IUCD በማህጸን እያለ ልጁ የሚወለድበት ሁኔታ በጤናማነት ይስተናገዳል፡፡


 IUCD በጣም ሰላማዊ የመከላከያ ዘዴ በመሆኑ እናትየውንም ሆነ ጽንሱን የማይጎዳ ነው፡፡ እንዲያውም በጣም ሰላማዊ በመሆኑ በማህጸናቸው ውስጥ እያለ የወር አበባ ጊዜያቸው ሲያበቃ እየተረሳ መውጣት ያለበትን ጊዜ እያሳለፉ በተለያዩ የህክምና አጋጣሚዎች ምርመራ ሲደረግ መኖሩ
እየታወቀ የሚወገድላቸው ሴቶችም አጋጥመዋል፡፡ በእኛ ሀገር ባይሆንም አንዲት ሰት IUCD ወደማህጸንዋ በገባ በ50/ አመቱ እንደተገኘ እና እንደወጣላት ሪፖርት ያሳያል፡፡ IUCD ከአስር እስከ አስራ ሁለት አመት ድረስ የመቆየት እና የማገልገል ባህርይ ያለው ሲሆን በሌላ በኩል
ደግሞ በአመት አንድ ጊዜ መታየት እንዳለበት መረሳት የለበትም፡፡

Read 444 times