አንባቢ ርእሱን ሲያነብ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? እንደሚል እርግጠኛ ነኝ። ያለፉትን ስልሳ ስምንት አመታት የመረጥኩት በምን ምክንያት እንደሆነ በአጭሩ በመግለፅ ፅሁፌን እጀምራለሁ።
ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መስርታ ሀገር ማስተዳደር የጀመረችው ኃይለስላሴ ስልጣን ከያዙበት ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ብል ብዙ የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ - ከ1848 እስከ 1983 ዓ.ም.” ብለው በሰየሙት መፅሀፋቸው ውስጥ የኃይለስላሴን ዘመነ መንግስት በሁለት ከፍለው በማብራራት በጣም ጥሩ የሚባል ግንዛቤ እንድናገኝ አድርገውናል። የመጀመሪያው ከ1923 ዓ.ም. እስከ ከ1948 ዓ.ም. ያሉት 25 አመታት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከ1948 ዓ.ም. እስከ ከ1967 ዓ.ም. ያሉት 19 አመታት ናቸው። እንደ እሳቸው አገላለፅ በመጀመሪያው 25 አመታት ውስጥ ንጉሱ የሀገር ምስረታ(Nation building) ስራ ላይ ተወጥረው ነበር ያሳለፉት። ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት በመፍጠር የሀገር ምስረታ ስራውን በሚገባ ተወጥተውታል የሚል እምነት አለኝ።
ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1967 ዓ.ም. መባቻ ድረስ ግን በዘመኑ የነበረው የፊውዳል ስርዐት ወቅቱ ግድ የሚሉ መሻሻሎችን (ለምሳሌ የመሬት ስሪት) ተቀብሎ ተገቢ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦችን ማምጣት ስላልቻለ ሀገሪቷን ለእርስ በርስ ሽኩቻና ምስቅልቅል የዳረገ መሆኑን ማስረጃ በተደገፈ መልኩ አብራርተዋል። ከላይ ያቀረብኩትን የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ሙያዊ ትንተና መሰረት በማድረግ ነው የመጀመሪያዎቹን 25 አመታት፤ ማለትም ከ1923 ዓ.ም. እስከ ከ1948 ዓ.ም. ያሉትን አመታት ትቼ፣ ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2016 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን 68 አመታት በወፍ በረር ለመዳሰስ የሞከርኩት።
እኔ የትምህርት መሰረቴ የተፈጥሮ ሳይንስ፤ ቴክኖሎጂና የማህበራዊ ሳይንስ ድብልቅ ቢሆንም (ማስተርሴን MBA ሰርቻለሁ)፤ የስራ ልምዴ ወደ ቴክኖሎጂው የሚያደላ በመሆኑ ከዚህ በታች ያቀረብኩትን ትንተና ከወፍ በረርነት በጠለቀ መልኩ ማቅረብ ባለመቻሌ አስቀድሜ አንባቢን ይቅርታ እጠይቃለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በታች ባነሳኋቸው የታሪክ አጋጣሚዎች በመመርኮዝ የተሳሳትንባቸው ናቸው ብዬ በለየኋቸው ጉዳዮች ላይ አተኩሬ ለማብራራት የሞከርኩት የትኛውንም አካል ለመውቀስ ሳይሆን፤ ለወደፊቱ ያለፉ ስህተቶቻችንን በማረም ይህቺን ሰው፤ ትክክለኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ማግኘት ባለመቻሏ በድህነት ውስጥ የምትዳክረውን አገራችንን ከድህነት ለማውጣት እንችል ዘንድ በማሰብ ነው።
ከዚህ በታች ያለውን ትንተና ከማቅረቤ በፊት ጉዳዩን ከምን አቅጣጫ አይቼ፤ ወይም ምን ሞዴል ተጠቅሜ እንደሆነ ግልፅ ማድረግ አለብኝ። በዚሁ መሰረት የተጠቀምኩት “ጆን ሮቢንስንና” እና “ዳሮን አኬ ሞግሉ” የተባሉ የመፅሀፍ ደራስያን በጋራ “Why Nations fail” በሚለው መፅሀፋቸው ውስጥ ያነሱትን ፅንሰ-ሀሳብ ነው። ሁለቱ ደራስያን በመፅሀፋቸው ውስጥ እንዳብራሩት፤ የተለያዩ የአለም ሀገራት በታሪክ ሂደት ውስጥ የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች(ፀሀፊዎቹ “Junctions” የሚል ስም የሰጡት) ያጋጥማቸዋል፤ እነኚህ የታሪክ አጋጣሚዎች ሀገራቱ በኢኮኖሚ እንዲያድጉ ወይም እንዳያድጉ ምክንያት ይሆኗቸዋል። በነሱ አባባል “Inclusive Political Institutions” እና “Inclusive Economic Institutions” እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነው ኢኮኖሚያቸው ያድጋል፤ ወይም “Extractive Political Institutions” እና “Extractive Economic Institutions” እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነው ኢኮኖሚያቸው ባለበት ይረግጣል፤ ወይም አያድግም፤ የሚል ትንተና ሰጥተዋል። እኔ “Inclusive” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል “አካታች” ያልኩት ሲሆን፤ “Extractive” የሚለውን ቃል ደግሞ በቀጥታ “በዝባዥ” በሚለው ቃል ምትክ በኦፐሬሽናል ወይም በተግባራዊ ትርጉሙ “ወገንተኛ” በማለት “Inclusive Political Institution” እና “Inclusive Economic Institution” ያሉትን “አካታች የፖለቲካ ተቋም” እና “አካታች የኢኮኖሚ ተቋም” ያልኳቸው ሲሆን፤ “Extractive Political Institutions” እና “Extractive Economic Institutions” ያሉትን ደግሞ “ወገንተኛ የፖለቲካ ተቋም” እና “ወገንተኛ የኢኮኖሚ ተቋም” ብያቸዋለሁ።
ለዚህ አባባላቸው ማሳያ እንዲሆን ብለው በተለያዩ ሀገራት የተፈጠሩትን የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አንስተው ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው ወይም ውድቀታቸው እንዴት ምክንያት እንደሆኑ አብራርተዋል። ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ሀገራት መሀከል ፈረንሳይና ጃፓን ይገኙበታል። በ1789 ዓ.ም የተካሄደውን የፈረንሳይ አብዮት እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ (Junction) ወስደው ተንትነውታል። በዚህ አብዮት ምክንያት በፈረንሳይ ሀገር የፊውዳል ስርዓት ተገርስሶ የካፒታሊዝም ስርዓት የተጀመረበት ወቅት ሲሆን፤ እንደነጆን ሮቢንሰን አባባል “አካታች የፖለቲካ ተቋማት” እና “አካታች የኢኮኖሚ ተቋማት” እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኖ ሀገሪቱ በሂደት በኢኮኖሚ ልታድግ ቻለች፤ ከራሷም አልፋ ለጎረቤት ሀገራትም ተረፈች ብለዋል። ጃፓን በታሪኳ የሜይጂ ማሻሻያ(Meiji restoration) በመባል የሚታወቀውና በ1868 ዓ.ም የተካሄደውን የታሪክ አጋጣሚ(Junction) አሳልፋለች። ጃፓን ከሜይጂ ማሻሻያ በፊት ለ500 አመታት ሀገሪቱ ለውጪው አለም ሙሉ በሙሉ በሯ ዝግ ነበረ። ከሜይጂ ማሻሻያ በኋላ ግን ሀገሪቱ ለውጪው ዓለም እራሷን ክፍት በማድረጓ ምክንያት ንግድ፤ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተስፋፉ። ይህ የታሪክ አጋጣሚዋም አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኖ በሂደት ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ልታድግ በቃች። በመፅሐፉ ውስጥ የተጠቀሰችው ሌላ ሀገር ኢትዮጵያ ስትሆን፤ የኃይለስላሴና የደርግ መንግስታት አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት መገንባት ስላልቻሉ፣ ሀገሪቱን ከድህነት ማውጣት አለመቻላቸውን አብራርተዋል።
የኢህአዴግን መንግስት በትንታኔያቸው ውስጥ ያላካተቱበት ምክንያት መፅሀፉን ለመፃፍ ቅድመ ዝግጅት የተደረገው በኢህአዴግ የመጀመሪያ አመታት አካባቢ ስለሆነ ነው የሚል የራሴን ግምት ሰጥቻለሁ። ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ሀገራት በተጨማሪ ከተለያዩ ክፍለ አለማት ለማሳያነት የቀረቡ በርካታ በኢኮኖሚ ያደጉም ሆነ ያላደጉ ሀገሮች ተካተውበታል። ሌላው እነ ጆን ሮቢንሰን ያነሱት ነጥብ ወገንተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት የነገሱበት ሀገር በሚወስዱት የተሳሳተ ርምጃዎች ሀገሪቱ ከአንድ ችግር ወደ ሌላ ችግር ውስጥ እየገባች ከ “Vicious circle” ውስጥ መውጣት እንደሚቸግራት ሲገልፁ፤ አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማቷ ሊገነቡ የቻሉ ሀገራት በበኩላቸው፤ በተለያዩ ወቅቶች የሚወስዱት ተገቢነት ያለው ርምጃ ሀገሪቱን ከዕድገት ወደ ዕድገት እያሸጋገረ እንደሚሄድ አስረድተዋል፤ ይህንንም እውነታ “Virtuous circle” ብለው ሰይመውታል።
እስቲ ደግሞ አሁን ወደሀገራችን ኢትዮጵያ መለስ ብለን የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችን (Junctions) በመመርመር የተፈጠረውን ሁኔታ ለመቃኘት እንሞክር። ሚዛናዊነቴን ላለማጣት ስል በሀገራችን ያለፉትና አሁን ያሉት መንግስታት፤ ማለትም ከዓፄ ኃይለስላሴ መንግስት እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይ አሕመድ መንግስት ድረስ፤ ሁሉም የራሱ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው። ለጠንካራ ጎናቸው ሁሉንም እያመሰገንኩ፤ እኔ የማተኩረው መሻሻል ይኖርባቸዋል ብዬ በለየኋቸው ነጥቦች ላይ ነው። የትኛው መንግስት ከየትኛው በምን ይሻላል የሚለውን ጥያቄ ለታሪክ ባለሙያዎች ትቼ፤ በኔ እምነት ባለፉት 68 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ 6 የታሪክ አጋጣሚዎችን (Junctions) አሳልፋለች የሚል እምነት አለኝ። የታሪክ አጋጣሚዎቹ ምን ፈየዱላት የሚለውን በቅደም ተከተል እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
የጃፓን መልካም ትብብር፡
ጃንሆይ(ኃይለስላሴ) በስልጣን ዘመናቸው ከሚመሰገኑበት ነገር አንዱ በውጪ ግንኙነት ወይም በዲፕሎማሲ አዋቂነታቸው ነው። የዚህ ማሳያ አንዱ ከጃፓን መንግስት ጋር የነበራቸው የቅርብ ግንኙነት ነበር። ለዚህ ርዕሳችን ይጠቅመን ዘንድ በኃይለስላሴ ዘመን የነበረውን የፖለቲካ ሽኩቻ እዚህ ላይ በአጭሩ ላንሳ። “ረዥሙ የኃይለስላሴ የስልጣን ጉዞ” የሚል ርዕስ ባለው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መፅሀፍ ውስጥ በግልፅ እንደተብራራው…፤ በንጉሱ የስልጣን ዘመን ወቅት ሁለት ትላልቅ ተቃራኒ የፖለቲካ አመለካከት የነበራቸው ቡድኖች በስራቸው ነበሩ። የመጀመሪያው የፊውዳል አመለካከት ያላቸው፤ ለውጥ የማይፈልጉ የመሬት ከበርቴ ቡድን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የተማረ፤ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበረውና ለውጥ ፈላጊ ቡድን ነበረ። እንደ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አባባል፤ ኃይለስላሴ በግላቸው ወይም በልባቸው የተራማጁን ወይም ለውጥ ፈላጊውን ወገን የሚደግፉ ቢሆንም፤ የመሬት ከበርቴውን ፊውዳል ቡድን ከተተናኮሉት ያለውን ሀብትና ስልጣን ተጠቅሞ ሊያጠፋቸው ወይም ቢያንስ ከስልጣን ሊያወርዳቸው እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ያለተራማጁ ወገን ዕውቀት፤ ስራና ድጋፍ ሀገር መምራትና መገንባት እንደማይችሉም በደምብ ያውቃሉ። (እዚህ ላይ አንባቢ ልብ እንዲለው የምፈልገው ነጥብ፣ ተራማጅ ወይም ለውጥ ፈላጊ የተባለው ቡድን ኃይለስላሴ ራሳቸው አውሮፓና አሜሪካ ልከው እንዲማሩ ካደረጉ በኋላ በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ መድበዋቸው ይሰሩ የነበሩ እንደ ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድና አቶ ከተማ ይፍሩን የመሰሉ ፕሮፌሽናል ሰዎች ስለነበሩ፣ አምባሳደር ዘውዴ ኃይለስላሴ በግል ወይም በልባቸው ተራማጅ ወገኑን ይደግፋሉ ያሉትን አባባል ትክክለኛነት ሚዛን እንዲደፋ ያደርጋል።) በመሆኑም ሁለቱን የማይታረቅ ቅራኔ ያላቸውን ቡድኖች አቻችለው(compromise እያደረጉ) ነበር የስልጣን ዘመናቸውን የገፉት።
አፄ ኃይለስላሴ ከላይ የተጠቀሰውን ከጃፓን መንግስት ጋር የነበራቸውን የቅርብ ወዳጅነት ተጠቅመው በ1940ዎቹ አመታት መጨረሻና በ1950ዎቹ አመታት መጀመሪያ ላይ ጃፓኖቹን ”የናንተ ሀገር በስልጣኔ ያደገች ናት፤ የመንግስት አገዛዝ ስርዓታችን ደግሞ የሁለታችንም ንጉሳዊ ነው፤ በመሆኑም የናንተ ሀገር ባደገችበት መንገድ ሀገሬ እንድታድግ ሙያዊ እገዛ አድርጉልኝ” ብለው ጃፓኖቹን ጠየቋቸው። ከዚያም ጃፓኖቹ ምንም ሳያቅማሙ በጃንሆይ ሀሳብ ተስማምተው አንድ የባለሙያ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ። ለጥናት የተላከው የባለሙያ ቡድን ጥናቱን በዝርዝር አካሂዶ ብዙ ገፅ ያለው ሪፖርት ካዘጋጀ በኋላ ለጃንሆይ አቀረበ። የሪፖርቱ ፍሬ ሀሳብ “ወደፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የፖሊሲ ሪፎርም ፐሮፖዛል ከመግባታችን በፊት መወሰድና መስተካከል የሚገባቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስላሉ እነሱን ለማስተካከል የሚከተሉት ዝርዝር አስተዳደራዊ ርምጃዎች መወሰድ አለባቸው” የሚልና መወሰድ ያለበትን ዝርዝር ያካተተ ሪፖርት ነበር። ጃንሆይ ሪፖርቱ ከቀረበላቸው በኋላ እሺ ወይም እምቢ ሳይሉ ለረዥም ጊዜ አቆዩት። ምክንያቱም ይወሰዱ የተባሉት አስተዳደራዊ ርምጃዎች ቢወሰዱ ስርዓቱን፤ በተለይም ለውጥ የማይፈልገውን የመሬት ከበርቴ ስልጣንና ጥቅም በቀጥታ የሚጎዳ በመሆኑ ጃንሆይ ለህይወታቸውና ለስልጣናቸው በጣም የሚያሰጋ ሆኖ ስላገኙት በጃፓኖቹ የተሰራውን ጥናት ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ግልፅ በሆነ አነጋገር የጥናቱ ተግባራዊነት የደም ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ ስለተገኘ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። ከዚያም ጃፓኖቹ ብዙ ጊዜ ጠብቀው መልስ ሊያገኙ ባለመቻላቸው “ያቀረብነው የአስተዳደራዊ ሪፎርም ተግባራዊ ካልሆነ ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የፖሊሲ ሪፎርም ፕሮፖዛል ስራ መግባት አንችልም፤ እኛ ደግም ሀገራችን ትፈልገናለች” ብለው ወደሀገራቸው ተመለሱ።
ይህን ታሪክ ከቅርብ ጊዜ በፊት ለአንድ ጓደኛዬ ሳጫውተው፤ “አዎን ልክ ነህ፤ ይሄንን ታሪክ እኔም አውቀዋለሁ፤ በወቅቱ ጃፓን ያቀረበችው ሀሳብ በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ ጃፓኖቹ ሁለቱን ሀገራት በኮንፌደሬሽን እስከማዋሀድ የሚደርስ ፍላጎት ነበራቸው” ሲል አጫወተኝ። አንድ የታላቅ ወንድሜ የህይወት ዘመን ጓደኛ ደግሞ(ለአርባ ሰባት አመታት በጓደኝነት ከኖሩ በኋላ ሞት ነው የለያያቸው።) ይህንን ፅሁፍ አንብብልኝ ብዬ ሰጥቼው ካነበበ በኋላ “ጃፓኖች ለምን ይሄን ያህል እኛን ሊረዱን ፈቃደኛ እንደሆኑ ታውቃለህ?” አለና “አሜሪካ ጃፓንን በአቶሚክ ቦምብ ሂሮሺማና ናጋሳኪ ላይ መትታ ጃፓን በትልቅ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት የጃፓንን መንግስት 5 ሚሊዮን ዶላር ረድቷል፤ ይህን ውለታ ቆጥረው ነው ከላይ ያጫወትከኝን አቋም የወሰዱት” አለኝ። አይገርምም? በዚያን ዘመን የነበረችዋ ኢትዮጵያ፣ በዚያን ዘመን የነበረችዋን ጃፓን የመርዳት አቅም ነበራት ማለት ነው! ሌላ አንድ ነገር ልጨምርላችሁ። ሰሞኑን ደግሞ ለአንድ የኮንሰልተንሲ ኮንትራት ስራ ወደ ቢሾፍቱ ሄጄ ነበር። በመንገድ ላይ ለስራ ባልደረቦቼ ይህንን ታሪክ ሳጫውታቸው አንዱ ጓደኛዬ “ይገርማል! በወቅቱ ጃፓኖቹ ሁለቱን ሀገራት በኮንፈደሬሽን ለማዋሀድ አስበው ነበር ነው ያልከኝ?” አለና፤ “እኔ የማውቀው እንግሊዝና አውስትራሊያ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በኮንፈደሬሽን አንድ ላይ እንደነበሩ ነው” አለኝ። የእንግሊዝና የአውስትራሊያ አይገርምም! ምክንያቱም የአውስትራሊያ ህዝብ ማለት፤ አቦሪጂኖችን ሳይጨምር፤ በዋነኛነት በስደት ከእንግሊዝ ሀገር የሄደ ህዝብ ማለት ነው።(አካሄዳቸው ራሱ የሚገርም ታሪክ አለው።አቦሪጂኖች የእንግሊዝ ህዝብ ወደአውስትራሊያ ሄዶ ከመስፈሩ በፊት እዚያው አውስትራሊያ ውስጥ ይኖር የነበረ ባለሀገር(Indegenous) ህዝብ ነው።) ጃፓኖች ግን ከእኛ ጋር ምንም የደም ትስስር ሳይኖራቸው፣ እንደ አንድ ሀገር አብሮ ለመኖር ማሰባቸው ምን ያህል መልካም ነገር ቢያስቡልን ነው አያስብልም?
በእኔ እምነት በታሪካችን ከተከሰቱት ትልቅ የታሪክ አጋጣሚዎች መሀከል ይህ ክስተት አንዱና ትልቁ ነው ባይ ነኝ። ትልቅ እጥፋት(turning point) ይሆነን ነበር። ውሳኔው ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ከባድ ውሳኔ ነበር ባይ ነኝ። ሀገራችንም ቀደም ብላ እስካሁን ያልሞከረችው የካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ ትገባ ነበር ማለት ነው። የካፒታሊዝም ስርዓት የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም፣ ሁሉም ያደጉ የአለም ሀገራት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል “ቅይጥ ኢኮኖሚ” በሚል ስም ተከትለውት ያደጉበት ስርዓት መሆኑ ይታወቃል። አሁን ዞር ብዬ ሳወዳድራቸው የጃፓኖቹን ምክር ተግባራዊ የማድረጉ ውሳኔ ከላይ እንደገለፅኩት የደም ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም፤ እንደ ስልሳ ስድስቱ አብዮት ውጤቱ በተለያዩ መንገዶች አሳዛኝ ይሆን ነበር የሚል ግምት የለኝም። በመሆኑም ጥናቱ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ እንደ እንግሊዝና ጃፓን ንጉሳዊ ስርዓቱ ለምልክት እንዲኖር ተደርጎ(ጃንሆይም ህይወታቸውን ሳያጡ ብቻ ሳይሆን ከስልጣንም ሳይወርዱ፤ (የፊውዳሉ ቡድን ከሚፈጥረው ጫና ከተረፉ ማለቴ ነው)) የፖለቲካ ስልጣኑ ተራማጅ አስተሳሰብ ባላቸው የተማሩ ወገኖች(በእነ ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሐብተወልድ) እጅ ስለሚገባና ስርዐቱ ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ስለሚቀየር የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እምብዛም አስቸጋሪ አይሆንም ነበር ባይ ነኝ።
ወቅቱ የሚጠይቀውን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት በራሳችን እውቀት ተጠቅመን መወሰድ ያለበትን እርምጃ አልወሰድንም፤ በራሳችን መውሰድ ያለብንን እርምጃ ለመውሰድ ዕውቀቱና ጥበቡ ካነሰን ደግሞ የሰውን ምክር(የጃፓኖቹን ማለቴ ነው) ሰምተን፤ ለራሳችን እንዲመቸን(customize) አድርገን ተግባራዊ ማድረግ አልቻልንም። ስለዚህ በድህነታችን እንድንቀጥል ምክንያት የሆነን ነገር እራሳችን መረጥን። በመሆኑም አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት ለመፍጠር የሚያስችል ሌላ ታሪካዊ አጋጣሚ (Junction) መጠበቅ ግድ ሆነብን። ጃንሆይም ውሎ አድሮም ቢሆን የፈሩት አልቀረላቸውም፤ ስልጣንና ህይወታቸውን በአሳዛኝ መንገድ አጡ፤ ጦሱም ለእነኛ የተማሩና ተራማጅ አስተሳሰብ ለነበራቸው ባለስልጣኖቻቸውም ተረፈ።
የኤርትራ ፈደሬሽን መፍረስ፡
ኤርትራ ለ60 አመታት በጣሊያንና በእንግሊዝ ከተገዛች በኋላ የተባበሩት መንግስታት የሀገሪቷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን የውሳኔ ሀሳብ እንደያቀርቡ አምስት ሀገራት የሚገኙበት ኮሚቴ አቋቋመ። ሀገራቱም ኖርዌይ፤ ጉዋቴማላ፤ ፓኪስታን፤ ደቡብ አፍሪካና በርማ ነበሩ። ሀገራቱም በጉዳዩ ላይ ተወያይተውበት በድምፅ ብልጫ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፈዴሬሽን እንድትወሀድ የውሳኔ ሀሳብ አቀረቡ። በዚሁ መሰረት በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ በ1945 ዓ.ም. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፈደሬሽን ተዋሀደች። በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ መሰረት፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ከተወሰነ በኋላ ጥቂት ጊዜያት ቆይቶ የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር ወዳድ ኤርትራውያን ጋር ውስጥ ውስጡን በመነጋገር ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ሰፊ የፖለቲካ ስራ ተሰራ።
ይህንን የፖለቲካ አካሄድ በሚገባ የተረዱ፤ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ቢደረግ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ቀድመው ያወቁ፤ የወደፊቱ የፖለቲካ አካሄድ እንደራዕይ ፍንትው ብሎ የታያቸውና በንጉሱ የመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ተራማጅ ባለስልጣናት የሁኔታው አካሄድ አልተዋጠላቸውም። በመሆኑም ለንጉሱ፤ “ጃንሆይ ይሄ ፌዴሬሽኑን አፍርሶ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር የመቀላቀሉ እርምጃ ለመንግስትም ለሀገርም አይበጅም፤ የረዥም ጊዜ መዘዝ ይዞብን ይመጣብናልና ቢቀርብን ይሻላል፤ ማለትም የተባበሩት መንግስታት በወሰነው መሰረት ኤርትራ በፌዴሬሽን ብትቀጥል ይሻለናል” የሚል ጊዜውን የጠበቀና በሳል ምክር አቀረቡ። ይሁን እንጂ ጃንሆይ እነኚህን በትምህትና በልምድ ላይ የተመሰረተ ብስለትና አርቆ አስተዋይነት የተላበሱ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሀሳብ መደገፍ ሲገባቸው ፌዴሬሽኑን የማፍረስ ሀሳባቸውን ገፉበት። ንጉሱ ሀገር ወዳድ ከሚባሉት ኤርትራውያን ጋር ውስጥ ለውስጥ የፖለቲካ ስራ ሰርተው ከጨረሱ በኋላ በ1953 ዓ.ም. ፌዴሬሽኑን አፍርሰው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል አደረጉ። ከቅልቅሉ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እንደግብፅ አይነቶቹ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሁኔታዎች ተመቻቹላቸው። በመጀመሪያ ጀብሐን ቀጥሎም ሻዕቢያን አደራጅተው “የነፃነት” ትጥቅ ትግሉ ጀመረ። የኛም የኢትዮጵያውያን የሰሜኑ የ30 ዓመታት የጦርነት ገፈት ቀማሽነት ታሪክ አብሮ ተጀመረ። በኔ ግምት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ትቀጥል ወይስ አትቀጥል የሚለው ጥያቄ ትልቅ አጀንዳ የነበረበት የ1953 ዓ.ም. ዘመን ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ ወይም መንትያ መንገድ(Junction) ላይ የደረስንበት ጊዜ ነበር። በዚህን ወሳኝ ወቅት ሀገሪቷ መከራ በበዛበት መንገድ እንድትገፋ ወይም በተሻለ መንገድ እንድትሄድ የሚያደርጋት በጣም ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ወቅት ነበር። የተማሩት ተራማጅ ቢሮክራቶች ንጉሱን በመከሩበት መንገድ፤ ማለትም ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት በወሰነው ውሳኔ መሰረት በፌዴሬሽን እንድትቀጥል ማድረግ ሲገባን፤ በተሳሳተ መንገድ በኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል በመደረጉ ከፍተኛ ስህተት ፈፀምን። ንጉሱ ይሄንን ሲወስኑ ሀገርን ከመውደድና ከመወገን አንፃር በቀናነት ያደረጉት ነው ብዬ ባምንም፤ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂያዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ከመሆኑ አንፃር ስመዝነው የውሳኔ ስህተት የተፈፀመ ይመስለኛል።
በመጨረሻም ኤርትራ መገንጠሏ ላይቀር ሀገሪቷ ሰላሳ አመት በፈጀ ጦርነት ቁም ስቅሏን አየች። የእነኚያ ተራማጅና በሳል የንጉሱ ባለስልጣናት ወርቃማ ምክር ተግባራዊ ባይሆንም በጊዜ ሂደት ዕውነተኛነቱ ተረጋገጠ። በዚሁ አጋጣሚ አንድ ታሪክ ላንሳ። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የምናደርገው ጦርነት እየተካሄደ እያለ ሶማሊያ በ1956 ዓ.ም. በቶጎ ውጫሌ በኩል ሀገራችንን ወረረች። በዚህም ደም አፋሳሽ ጦርነት መካሄዱ በታሪክ ተዘግቧል። ይህ ጦርነት እራሱን የቻለ የታሪክ መፅሀፍ የሚወጣው ቢሆንም፤ እኔ እዚህ ጋ ያነሳሁት ሀገራችን አንድ ጦርነት ማካሄድ አልበቃ ብሏት በአንድ ጦርነት ላይ ሌላ ጦርነት ተደርቦባት ባልጠና የኢኮኖሚ ወገቧ ሁለት ጦርነቶችን የተሸከመችበት የታሪክ ወቅት እንደነበረ ለማስታወስ ነው። የ1956 ዓመተ ምህረቱ የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት በተነሳ ቁጥር ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶምን አለማንሳት የታሪክ ሚዛናዊነትን ማዛነፍ ይመስለኛል። ከአዲሱ ትውልድ ጋር ለማስተዋወቅ ያህል ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም በደርግ የስልጣን ዘመን መባቻ ላይ የደርጉ ዋና ሊቀመንበር ሆነው ለአጭር ጊዜ ከሰሩ በኋላ በሀሳብ ወይም በአቋም ከደርግ ባለስልጣናት ጋር መስማማት ባለመቻላቸው፣ ደርግ ሊይዛቸው ቤታቸው ሲመጣ የእራሳቸውን ህይወት ያጠፉ የኢትዮጵያ ስመ-ጥር ጀነራል ነበሩ። ስመ-ጥር ካስባላቸው ታሪኮች አንዱ በ1956 ዓ.ም. ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ከባድ ጦርነት ወቅት በፈፀሙት ጀብዱ ነው። በታሪክ አንደሚታወቀው፣ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ይመራ የነበረው በጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም ሲሆን፤ ቶጎውጫሌ ላይ በተደረገው ከባድ ጦርነት የኛ ጦር ካሸነፈ በኋላ ጀነራል አማን ጦራቸው ወደ ሶማሊያ ዘልቆ በመግባት ሞቃዲሾን ለመያዝ ቢያስቡም ከንጉሱ “የጠላት ጦር ከወሰናችን ከወጣ ተመለስ” የሚል ትዕዛዝ ስለደረሳቸው መመለሳቸው በሰፊው ይነገር የነበረ ታሪክ ነው።
የ1953 ዓ.ምህረቱ የጀነራል መንግስቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ
በ1953 ዓ.ም. እነጀነራል መንግስቱ ንዋይ የሞከሩት የመንግስት ግልበጣ ሙከራ በታሪክ የሚታወቅ ነው። በመሰረቱ የሚሊታሪ መፈንቅለ መንግስት አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት በመፍጠር ሀገሪቷን ወደ ትክክለኛ የዕድገት መስመር ያመጣል የሚል እምነት ባይኖረኝም፤
1ኛ - የእነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ዋና ቅራኔ ከፊውዳል ስርዓቱ ጋር ስለነበረ የፊውዳል ስርዓቱን አፍርሰው በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን ወደ ካፒታሊዝም ስርዓት የማስገባት ሂደት ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ስለነበረ፤
2ኛ - እነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ከተራማጁና ለውጥ ፈላጊው የንጉሱ ባለስልጣናት፤ ማለትም ከነጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተወልድ ጋር በአመለካከት ተመሳሳይ ስለሆኑ በጋራ ሀገሪቷን ወደ ትክክለኛ የዕድገት መስመር ሊያስገቧት ይችሉ የነበረበት ዕድል ነበር የሚል ግምት ስላለኝ፤
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ(Junction) ወስጄዋለሁ። ለዚህም ጥሩ ማስረጃነት ከእነጀነራል መንግስቱ ንዋይ ጋር በማበር ከመፈንቅለ መንግስቱ ዋና አስተባባሪዎች አንዱ የነበረው ሌ/ኮሎኔሌ ወርቅነህ ገበየሁ የሚባል ግለሰብ ነበር። ይህ ሰው በጣም አስተዋይ፤ ቆፍጣና፤ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበረውና በዘመኑ የፀጥታ ፅ/ቤት ኃላፊ የነበረው ይገኝበታል። አቶ ብርሀኑ አስረስ “የታህሳሱ ግርግር” የሚል ርዕስ በሰጡት መፅሀፋቸው ውስጥ “የዚህ ሰው ታታሪነትና ችሎታ ታይቶ የንጉሱ የቅርብ ባለሟል የመሆን ዕድል አግኝቶ ነበር” ብለዋል። ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ንጉሱ በሀገሪቱ ላይ የፖለቲካ ለውጥ እንዲያደርጉ ለመምከር ቢጥርም ሰሚ ጆሮ ማግኘት ባለመቻሉ፣ በሂደት ወደ መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሹ ቡድን ውስጥ መቀላቀሉን አብራርተዋል። የመንግስት ግልበጣው ከከሸፈ በኋላ በሀገሪቱ ላይ ነገሮች እየተባባሱ መሄድ ቀጠሉ። በአንድ በኩል የሰሜኑ የእነሻዕቢያ ጦርነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመሬት አስተዳደሩ ከፊውዳል ስርዐት አለመላቀቁ ችግሮች እየተባባሱና እየተወሳሰቡ ለመሄዳቸው ምክንያት ሆኑ።
(አንባቢን እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምፈልገው ከላይ እንደገለፅኩት የመፈንቅለ መንግስቱ ተዋናዮችን ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ ግምት ውስጥ አስገብቼ ነው እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ(junction) የወሰድኩት። ይሁን እንጂ ከመፈንቅለ መንግስቱ ተዋናዮች በስተጀርባ በሀገሪቷ ላይ ሊሰራ የታሰበ ሴራ ይኑር አይኑር እኔ የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ይህ የታሪክ አጋጣሚ ወደተሻለ መንገድ ሊወስደን የሚችልበት ዕድል ነበረው ብዬ ስል ትንተናዬ በማውቀው ልክ መሆኑን ነው።)
በዚህ ውስብስብ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ሆነንም ቢሆን በ50ዎቹ መጨረሻና በ60ዎቹ መጀመሪያ አመታት በሀገሪቷ ውስጥ እያቆጠቆጠ የነበረው ዘመናዊ እርሻ “Mechanized farming” እና የግል ኢንዱስትሪ ማበብ ለሀገሪቷ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ ነበር። በግሌ የማውቀው ታሪክ በ60ዎቹ አመታት መባቻ ላይ ከሀሮማያ እርሻ ኮሌጅ በዲግሪ እንደተመረቁ የሽርክና ኩባንያ (Share company) በመመስረት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ወስደው በቀጥታ ወደሜካናይዝድ እርሻ ስራ የገቡ ምሩቃን እንደነበሩ አስታውሳለሁ። እንዳለመታደል ሆኖ በመጨረሻ የዘመኑ የሜካናይዝድ እርሻ ተዋናዮች ድካም፤ ጥረትና የስራ ተነሳሽነት በ66ቱ አብዮት አፈር በላ። (በዚያ ዘመን የነበረውን የብልፅግና ተስፋና አንዳንድ የአተገባበር ችግሮችን በተመለከተ ትክክለኛ ታሪክ መሰረት በማድረግ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።)
(ይቀጥላል)