የብቃት ቤተመቅደስ፣ የጥበብና የብርታት ድግስ ለመቋደስ እልፍ አእላፍ ሰዎች በሚታደሙበት የብቃት ቤተመቅደስ፣… በታላቁ ስታዲዬም፣ በችሎታ የመጠቁ ስፖርተኞች ልሕቀትን በሚያሳዩበት የእግርኳስ ሜዳ ላይ፣… አለመግባባት ሲፈጠር፣ መጎሻሸም ሲከሰት ብዙ ጊዜ አይታችኋል። እንደ ድሮ ላይሆን ይችላል። ዛሬ ዛሬ ኳስ ሜዳ ውስጥ የሚፈጠር አምባጓሮ በጣም እየቀነሰ እንደመጣ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የውጭውን የአውሮፓውን ማለቴ ነው።
የኢትዮጵያማ፣ እግርኳስ በሰላም መጫወትና መመልከት በጣም ከባድ ስራ ሆኖብን፣ በወጉ በየከተማው የደርሶ መልስ ወድድር ማካሄድ ካቃተን በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ያው፣ የብቃት ማዕከል ሳይሆን፣ የጸብ ማሕበር ሲያደርጉት፣ “አይሆንም” ብለን መከላከል አልቻልማ። ለምን?
የተቀናቃኝ ቡድን ተጫዋቾችን የሚሳደቡ፣ ወይም የወዲያ ማዶ ደጋፊዎችን ለማብሸቅ የሚሞክሩ ባለጌዎችና ስዶች ናቸው የረብሻና የነውጥ መነሻዎች።
በእርግጥ፣ ባለጌዎችና ተሳዳቢዎች፣ ያለ አጃቢና ያለ አጨብጫቢ ብዙም እድሜ አይኖራቸውም። ለነውጠኞችም አመቺ የጸብ ዕድል አይከፈጠርላቸውም።
እንደ “አሪፍ መዝናኛ” የሚቆጥራቸውና የሚስቅላቸው ካላገኙ፣ እንደ “ሐቀኛ ቲፎዞ” የሚያያቸው አይዞህ ባይ ካልተከተላቸው፣ ስድብ አቀባባይና አዳማቂ ካላጀባቸው፣ አፋቸውን አበላሽተውና አቆሽሸው ኩምሽሽ ብለው ይቀራሉ።
ባለጌ ተሳዳቢዎች በአጨብጫቢዎች ከታጀቡስ? የሚስቅላቸው አይዞህ ባይ ተከታይ ካገኙማ፣ በቃ… ይብስባቸዋል። ከስድብ ወደ ውንጀላ፣ ከውንጀላ ወደ ዛቻ ይሸጋገራሉ።
እንደገና፣ ዙሪያቸውን ይታዘባሉ። አይዞህ ባይና ተከታይ ካገኙ፣ የጸብ መሪ ይሆናሉ። ድንጋይ ውርወራ ይጀምራሉ።
ከወዲያ ማዶም፣ ሌላ ባለጌ ሌላ ነውጠኛ፣ “ተሰደብን፣ ተደበደብን፣ ተፈነከትን፣ ተናቅን፣ ተዋረድን” እያለ የራሱን አጃቢዎች ይቀሰቅሳል። በጎራ ያቧድናል። የአጸፋ ምላሽ ዕጥፍ እየጨመረ፣ የስድብና የድንጋይ መዓት ያወርዳል።
“ሕዝብ” በጎራ በተቧደነበት ቦታ፣ ጩኸትና ግርግር ሲበረክት፣ መያዣ መመለሻ ያጣል።
የወዲህኛው ቡድን ደጋፊዎች “የወገን የወዳጅ ጎራ ናቸው” ተብለው ወደ ጸብ የመዝመት ሐላፊነት ይጫንባቸዋል።
የወዲያኛው ቡድን ደጋፊዎች ደግሞ፣ “የባእድ የጠላት ጎራ ናቸው” ተብለው የድንጋይ ኢላማ እንዲሆኑ ይፈረድባቸዋል።
“ኧረ እንረጋጋ!” ብሎ ለመናገር የሚደፍር ይጠፋል። “ስድብ መጥፎ ነው። ይቅር። ድንጋይ ውርወራ ወንጀል ነው። ይቁም” ብሎ በዙሪያው ላሉ ሰዎች ቢናገር፣ ነውጠኛ ቀስቃሾች ይናደዱበታል። “ከሐዲ፣ ባንዳ፣ ሰርጎ ገብ ጠላት” ብለው ይወግሩታል።
ገና ጸብና ግርግር ሳይፈጠር በፊት፣ የመደባደብና የመፈነካከት ዘመቻ ሳይጀመር በፊት፣ ገና የብሽሽቅና የስድብ ምልክቶች የታዩ ጊዜ በእንጭጭ እንዲቀሩ ለመከላከል ቢሞክር ኖሮ፣ በቀላሉ ይሳካለት ነበር።
አካባቢው ከተናወጠ በኋላ ግን፣… ጎጂና ተጎጂ ለመለየት የማይቻልበት፣ ጥፋትና ዓጸፋ፣ ጥቃትና በቀል ከተደበላለቁ በኋላ፣… ነገሩን የመግታት፣ የማብረድና የማስቆም ዕድል ይጠፋል። የየጎራው ስዶችና ነውጠኞች ከወዲህና ከወዲያ ይነግሣሉ። ሊናገራቸው የሚሞክር አይኖርም። ቢኖርም አፉን ያስይዙታል። ካንገራገረ፣ እዚያው ይዘርሩታል፤ ይደፉታል።
ለዚህም ነው፣ ስድብና ዛቻ ወደ ድብድብ ከተለወጠ፣ አብዛኛው ሰው ከድንጋይ ለማምለጥ፣ ከስታዲዬሙ ለመውጣትና ርቆ ለመሸሽ የሚሯሯጠው። በአብዛኛው ሰው በይሁንታ ወይም በዝምታ እያየ ነው፣ የጸብ ግርግር የሚፈጠረው። ጸብ ከተፈጠረ በኋላ ግን፣ ወይ ከዳር ሆኖ ይመለከታል። ወይ ከአካባቢው ይጠፋል።
አብዛኛው ሰው የድብድብ ተሣታፊ አይሆንም። ተጎጂ ሠለባ ለመሆንም አይፈልግም። አካባቢውን ጥሎ ለመሸሽ ይንጋጋል እንጂ፣ ጸብና ግርግር ለማስቆም አይሞክርም። ቢሞክርም አይችልም።
የስድብ ቅብብል ገና ከመነሻው ክፉ ነገር እንደሆነ ተገንዝቦ፣ ስድብ ወደ ዛቻና ወደ ድንጋይ ውርወራ ሳይሸጋገር በፊት በአጭር ለማስቀረት ከመሞከር ይልቅ፣ በዝምታ አይቷል። ባለጌዎች ሲሰዳደቡ፣ በይሁንታ ተቀብሏቸዋል፤ ወይም በአይዞህ ባይነት “ስቆላቸዋል”። “በድምጽና በጭብጨባ አጅቧቸዋል”።
ያኔ ነው ስዶችንና ነውጠኞችን ያነገሣቸው።
ለምንድነው ያነገሣቸው?
ቀድሞውንስ ለምንድነው በዝምታና በይሁንታ ለስድብና ለዛቻ የተመቻቸ መንገድ የከፈተላቸው? ለምን ሳቀላቸው? ለምንስ አጀባቸው? እሱን ስላልሰደቡና እሱ ላይ ስላልዛቱበት ነው በሳቅና በጭብጨባ የሚያጅባቸው? ስድባቸውና ዛቻቸው ለወዲያኛው ጎራ የተነጣጠረ ስለሆነ ነው?
“ስድብ ይቁም፤ ዛቻ ይቅር” ብሎ ባይናገር እንኳ እንዴት አይደብረውም? እንዴት ቅር አይለውም? በዙሪያው የተሰበሰቡ ስዶችና ነውጠኞች፣ “የኛ ጎራ፣ የኛ ወገን ናቸው፤ ለኛ ቡድን ተቆርቋሪ ናቸው” ብሎ ስላሰበ ነው?
ምንም ቢሳሳቱና ምንም ጥፋት ቢሰሩ፣ እንደ ስህተትና እንደ ጥፋት አይቆጥርባቸውም። “ለበጎ አላማ ነው፤ ለኛው ቡድን አስበው ያደረጉት ነው” ብሎ ይቀበላቸዋል፤ ተከታይ ይሆንላቸዋል። የቱንም ያህል ቢደብረው እንኳ፣ ሊያርማቸው ሊያስተካክላቸው አይጥርም። በዝምታ ይሸከማቸዋል - አብዛኛው ሰው።
ገሚሱ ደግሞ በዝምታ ከመሸከም አልፎ ይሟገትላቸዋል። ሰበብና ማመካኛ ይደረድርላቸዋል። በጠበቃ ሊሆንላቸው ከጎናቸው ይቆማል። በውሸት ይመሰክርላቸዋል።
ከወዲያኛው ጎራም እንደዚያው ነው።
ምናለፋችሁ፣ አብዛኛው ሰው፣ አውቆም ይሁን ሳያውቅ፣ የስዶችና የነውጠኞች ምርኮኛ ይሆናል።
በጥቂት ባለጌ ተሳዳቢዎች አማካኝነት ነው አብዛኛው ሰው በጭፍን ስሜት መጮኽና በተቀናቃኝ ጎራዎች መቧደን የሚጀምረው። ከስካር በባሰ መንፈስ፣ ለጥቂት ጋጠወጥ ነውጠኞች ታዛዥና ተከታይ ይሆንላቸዋል።
ያኔ ጭፍን የቡድን ጥላቻ ይካረራል፤ ይቀጣጠላል። የምላስ እንቅስቃሴዎች ይበረክታሉ፤ የዛቻና የፉከራ ድምፆች ይራገባሉ። አንድ ቀን፣ ሁለት ቀን፣ ስድብና ዛቻ ወደ ክፉ መዓት ሳይደርስ በዚያው ሊያልቅ ይችላል። ግን በዚሁ አያበቃም። የሚያበቃ እየመሰለው ይሆን አብዛኛው ሰው በጎራ እየተቧደነ የተሳዳቢዎችና የነውጠኞች አጃቢ የሚሆነው? ከምላስ በኋላ እጆች መወናጨፍ ሲጀምሩስ? የድንጋዮች ውሽንፍር ከግራና ከቀኝ አካባቢውን ሲያናውጡትስ?
አብዛኛው ሰው፣ ከምር ባለጌ ወይም የለየለት ነውጠኛ ስላልሆነ፣ ለጤናውም ለሕይወቱም ስለሚያስብ፣… አካባቢውን ጥሎ ይሸሻል። ሲንጋጋ በግፊያ እየተላተመ፣ እየወደቀና እየተረገጠ እዚያው ካልቀረ ዕድለኛ ነው።
ቀልድና ጨዋታ መስሎት፣ ሲያጨበጭብና ሲያራግብ ቢቆይም፣ የተቆሰቆሰው መጨስ ሲጀምር፣ የተራገበው ሲቀጣጠል፣ እየተንቀላቀለ ሲዛመት፣ ከተማው ሲበጠበጥና አገሬው ሲናወጥ፣ አብዛኛው ሰው ወደየቤቱ ይቸኩላል። በሩን ዘግቶ ይውላል። ደግ አደረገ።
ነገር ግን፣ ቀድሞኑ ማወቅ ነበረበት። ማወቅ ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ ለመከላከል መሞከር ነበረበት። ባይከላከል እንኳ፣ አጨብጫቢና አጃቢ ከመሆን መቆጠብ ይችል ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው? በጭፍን የመቧደን ስሜት በጣም ያሳስታል። በይሁንታ ወይም በዝምታ መንገድ ካመቻቹለት በኋላ፣ አንዳንዶችም በጭፍንና በደመነፍስ ዳር ዳሩን ከነካኩት ገኋ፣ በራሱ ጊዜ እየጎተተ ያስገባቸዋል። እየገፋና እየነዳ ይወስዳቸዋል።
የብርሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ፖለቲካ እጅግ አደገኛ የሚኖኑትም በዚህ ምክንያት ነው።
በዘረኝነት ወይም በጭፍን እምነት ስር የመቧደን የስካር ስሜት ሳይባባስ በፊት በጊዜ ካልገቱት በስተቀር፣ በይሁንታ ወይም በዝምታ መንገድ የሚከፍቱለትና በሆታ የሚያጅቡት ሰዎች ከተበራከቱ በኋላ፣ አገርን ሳያተራምስ እልፍ አእላፍ ዜጎችን ሳይማግድ አይመለስም።
መዘዞቹን እያግተለተለ የሚመጣው ዛሬውኑ ላይሆን ይችላል።
በአሰቃቂ የእልቂትና የውድመት ጎርፍ የሚያጥለቀልቀን፣ በዘርና በእምነት በተቧደንን ማግሥት ላይሆን ይችላል።
ነገር ግን የጥፋት ማዕበሎችን እያስከተለና እየደጋገመ መምጣቱ አይቀርም።
እየተደጋገመ ሲደርስብን አይተነው የለ!
በአንድ ቀን ወይም በማግስቱ ባይመጣብንም፣ ከተዛመተና ከተባዛ በኋላ፣ ኢምንት የእሳት ጭረት፣ አንዲት የክብሪት እንጨት፣ ቅንጣት የሰበብ ጠብታ ይበቃዋል። በማንኛውም ቅጽበት፣ በትኛውም ቦታ፣ ማንኛውም ሰበብ፣ የጥፋት መለኮሻ ለመሆን ያገለግለዋል።
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሁለት ተማሪዎች ተራ አምባጓሮ፣ አገርን የሚያተራምስ ሰበብ ይሆናል።
ስታዲዬም ውስጥ የሁለት ተጫዋቾች ጭቅጭቅ ወይም የሁለት ተመልካቾች ግፊያ፣ ከተማውን የሚቀውጥ የረብሻና የብጥብጥ መነሻ ሊሆን ይችላል።
አገሬው ለነውጥ ተመቻችቶ የተዘጋጀ ከሆነ፣ በትንሽ ሰበብ ይቀጣጠላል።
የሁለት ተጫዋቾች ንትርክ፣ እንዴት በቀላሉ እንደሚበርድ ወይም እንዴት በቀላሉ እንደሚቀጣጠል አልታዘባችሁም?
የዚህኛውና የዚያኛው ቡድን አምበሎች በየፊናቸው የየራሳቸውን ተጫዋች ለማረጋጋት ከሞከሩ፣ ነገርዬው ወዲያውኑ ይበርዳል።
ለየራሳቸው ቡድን ተጫዋች ተደራቢ ሆነው የግጭት ተሳታፊ ከሆኑ ደግሞ፣ ነገርዬው ይባባሳል፤ ይዛመታል። ለማገላገል ሲሞክሩ እንኳ፣ በቅድሚያ የራሳቸውን ተጫዋች ገለል ለማድረግ ነው መሞከር ያለባቸው። የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን ለመያዝና ገለል ለማድረግ ከሞከሩ ግን፣ “ለማስመታት” የፈለጉ፣ በጭፍን ለራሳቸው ቡድን ተጫዋች ያገዙ ሊመስል ይችላል።
ይህም፣ ለነውጠኞች ጥሩ ሰበብ ይሆንላቸዋል። ጸብ ለማዛመት ይጠቀሙበታል። “አስመታው፤ አስመታን” እያሉ ይቀሰቅሱበታል።
በሌላ አነጋገር፣ ጦርነትን ለመከላከል የሚያስችል ቀላሉ ዘዴ፣ በየፊናችን ለጸብ የሚያቧድኑ ሰዎችን ለመግታትና ለመገሰጽ የመሞከር፣ እንደ ሰበብ ሊቆጠሩና ለመቀስቀሻነት ሊያገለግሉ ከሚችሉ ተግባራት ደግሞ የመቆጠብ ዘዴ ነው።
ጎረቤት ልጆች በአንዳች መንስኤ ቢጣሉ፣ እናትና አባት ነገሩን ከማብረድና ጥፋተኛው ልጅ ማን እንደሆነ አጣርተው ከመገሠጽ ይልቅ፣ በየፊናቸው በጭፍን ለየራሳቸው ልጅ ተደራቢ ሆነው ጸብ ውስጥ ከተቀላቀሉ፣ ነገሩን ይባብሱታል።
በጉርብትና የሚኖሩ ብዙ ወላጆች ይህን ያውቃሉ።
ልጆች ከተጣሉ፣ በቅድሚያ የራሳቸውን ልጅ በመያዝና በመገሠጽ ነው ለመገላገል የሚሞክሩት። ገና ሳያጣሩ “ጥፋተኛ ነህ” እያሉት አይደለም። ነገር ግን፣ ለማጣራትና እንደየጥፋታቸው ለመገሠጽ፣ በቅድሚያ ጸብን መከላከል ወይም መግታት ያስፈልጋል። እናም፣ ወላጆች የየራሳቸው ሐላፊነት ለመወጣት፣ የየራሳቸውን ልጅ ከጸብ ለመግታት ቅድሚያ በመስጠትና በመያዝ ጸብን ያበርዳሉ፤ ይገላግላሉ።
እንዲሁ በጭፍን ለልጃቸው አግዘው ጸብ ውስጥ ተደራቢ ሆነው ከገቡ፣… ወይም የራሳቸውን ልጅ ትተው ሌላኛውን ለመያዝ ቢሞክሩና “ለማስመታት” የሚፈልጉ መስለው ከታዩ፣… ጉርብትናቸው የወዳጅነትና የመተሳሰብ አይሆንም። ግቢያቸው ሰላም አይኖረውም።
መልዕክቱ ምንድነው?
በጭፍን የመወገንና ተደራቢ የመሆን ጸበኛ ስሜት እንደሌለን ማሳየት፣
የመከባበርና የመተሳሰብ ሰላማዊ ግንኙነትን እንደምንፈልግ ማስረዳት፣
በቤታችን ከአገራች ውስጥ ለነውጠኞች መንገድ እንደማንከፍትና በይሁንታ አጃቢ እንደማንሆንላቸው ማረጋገጥ፤ ጭፍን ጥላቻን ለመከላከል መጣር፤
በጎረቤት አገራት ውስጥ ለሚኖሩ ነውጠኞችም የመቀስቀሻ ሰበብ እንዳንፈጥር መጠንቀቅ…
ብለን የጦርነት መከላከያና የሰላም ማሰንበቻ መንገዶችን መዘርዘር እንችላለን።
Saturday, 13 January 2024 00:00
የጦርነት መከላከያና የሰላም ማሰንበቻ መንገዶች
Written by ዮሃንስ ሰ
Published in
ነፃ አስተያየት