Monday, 15 January 2024 13:33

ትላንት የሌለው ህላዌ

Written by  -ኤርሚያስ ከበደ በቀለ-
Rate this item
(0 votes)

 ሁለንታዋን ባሸተው፤ የማውቀው መዓዛ በአፍንጫዬ ተዛወረ። ይሄን ጠረን አውቀዋለሁ፤ አልኩ ለራሴ - ዝቃ ቅቤ።
ልጅነቴ መደብ ላይ ሄጄ ተንጋለልኩ በምልሰት፤ ከቤታችን ጓሮ አያቴ የሚኮተኩታቸውና የሚያሳድጋቸው ተክሎች ነበሩ። ጤና አዳም፣ ዝቃ ቅቤ፣ ናና ቅመም፣ እንጆሪ፣ ቃርያ ብዙ ብዙ ሌሎች አይነት አይነታቸው የተለያየ ተክሎች ነበሩት። ታድያ የከተማዋ ማስተር ፕላን ሲስተካከል በጓሯችን በኩል እስከ ቤታችን ደፍ ድረስ አስፓልት ተጋደመበት። አያቴም ቤት ተቀምጦ ራዲዮ መጎርጎር ጀመረ፣ ታድያ ትንሽ ህመም ቢጤ ዘወር ስትለው፤ ”ኤድያ እንዳልንቀሳቀስ አስረውኝ እንጂማ ከአትክልቶቼ ጋር ብካረም ሞትን በቀለድኩበት” እያለ ያጉተመትማል።
ዝቃ ቅቤ ዝቃ ቅቤ አለቺኝ፣ ጠረኗ ነፍሴን ነጥቆ ከዛፍ ላይ ያንጠለጠለው መሰለኝ፣ ንፋስ በልቤ ሽው አለኝ። ልጅነቴን የመለሰችልኝና ዛሬ በሌለው ባዶ ትዝታ ውስጥ ጥላኝ ያስበረደችኝ ያህል ወረጨኝ። ጠይም ናት። ጠይሟ ውስጥ ሕይወት ሲዛወር ይታያል። የለበሰችው ሽንሽን ግርማዋ ነው። ፀጉሯን ገልብጣ ወደ ውስጥ ሦስት ቦታ አሽማዋለች። ከገረረው ከንፈሯ፣ በሥራ ከሻከረው እጇ፣ ቁርና ሐሩሩ ከተፈራረቀበት የደደረ ቆዳዋ ጀርባ ተስፋን ያነገበ ሕይወት ይርመሰመሳል።
መዳፏን የጨበጥኩበትን እጄን አሸተትኩት - አዎ! ዝቃ ቅቤ።
ቢሸመጥጧት ሕይወትን የሚያድስ ማጣፈጫ ቅመም ትሆናለች፣ እርጥቧን ከዛሬ መኖር ላይ ቢዶሏት ጣዕምናዋ ሌላ ኅላዌን ያጎናፅፋል።
ተመልሼ ወደ ቀድሞ መንደሬ ሄድኩ። መንደራችን ብዙ ተለውጧል፣ ትላንት የምለው ትዝታ ከመሬት ተነስቶ በምናቤ ከትሟል - ሃሳብ ብቻ ፣ በፊት የነበረው አሞራ ክንፍ ቤታችን ተሰውሯል ፣ አካባቢው ሌላ የተዥጎረጎረ ነፋስ ይዋኝበታል - የሚያፍን አየር፣ በየቦታው የተገደገዱት የድንጋይ ንብርብሮችን ተመለከትኩና” የዛሬ ልጆች ትዝታቸው እዚህ ውስጥ ይመሰረታል፡ የእኛን ትላንት አያውቁትም። ነገ የእነርሱ ዓለም ይህ ነው ። እነርሱስ ግን ነገ ይህን ትላንት የሚጠብቅላቸው ይኖር ይሆን? ነገ ላይ ሆነው ዘወር ቢሉ የሚምጉት ዝቃ ቅቤ ፣ የሚናፍቃቸው የጤና አዳም መዓዛ አላቸው? ትዝታቸውን ምን ላይ ነው የሚያሳርፉት? “
ጥያቄዬን እያመነዠኩ በጊዜ ፈረስ (time travel) ወደ ፊቱ የእነርሱ ዘመን ላይ መጣሁ፤ 2016 ን እንደ ማረፊያ ሰገነት ተጠቅሜ የእነርሱን ዛሬ ቁልቁል ተመለከትኩት አወይ ሰው መሆን ሌላ አጀብ ከተማዋን ሲወራት ታዘብኩ።
 የሚፈርሱትን የእኛን የቀደመ ትላንት ያፈረሱትን ትላንቶች ተመለከትኳቸውና ሁለት ሃሳብ ሸበበኝ “ ከተማ እድገቷን የሚመጥን ህንፃዎች ሊኖሯት አይገባም? ከዘመናዊቷ የሚተካከል ሥራን ለመስራት ግድ አይለን ይሆን?” ወዲያ ደግሞ “ ትላንታችን ይታፈርበት ይሆን እንዴ? ለዛሬ እንኳ ታድሶ ባለበት መዘመን የማይችል ትላንትን አውርሰውን አለፉ ይሆን እንዴ ወገኖቻችን? በውጪ በሎንዶን፣ በሮም፣ በኢስታንቡል ፣በማድሪድ፣ በአቴንስ እና ሌሎች ከተሞች የምናየውን የቀደመውን ትላንት የመጠበቅ አሰራር አልቻልንበት ይሆን?”
አዲስ አበባ ህንፃዎቿ የት ናቸው? ታሪኮቿስ ምን ደረሱ? ሰላም ነው ወይ ፒያሳ?
“ከተማው ለመድሽው ወይ መንደሩን
ሀገሩን መንደሩንስ አየሩን “
ብቻ ከሄድኩበት ተመልሼ ድክ ድክ የሚሉትን ልጆች ተመልክቼ አዘንኩላቸው። “ተዉ በየመኖሪያችሁ ትዝታን አትጣሉ። ተዉ ነገ የእናንተም ትዝታ መጨረሻው ምናባችሁ ውስጥ ይቀራል ተው። የእናንተም ነገ በፍርስራሽ ይሞላል ተዉ” ልላቸው ብፈልግም አነቀኝ። በመኖር ብዙ ያውቃሉ ይሁን እንዳሻቸው ብዬ የቀደመውን መንደሬን ከወረሱት ዛሬዎች ገለል አልኩ። በመንገዴ የእኛን ቤት አሰስኩት፣ ጓሮው ላይ ተኝቶ የነበረው አስፓልት ሰፍቶ መሃል መንገድ ላይ ገተረኝ። የመኪናዎቹን ታምቡር በጥስ ድምፅ እየሸሸሁ ነጎድኩ።
ወደ ልጅቷ ብመለስ ያቆምኳት ቦታ ላይ እንዳለች ናት። በሕይወቴ ውስጥ ቆማ የጠበቀችኝ እርሷ ብቻ ናት። ተንደርድሬ አቀፍኳት፣ ወደ ውስጧ ራሴን አጠለምኩት። ዝቃ ቅቤ፣ ዝቃ ቅቤ - ጤና አዳሜን ጤና አዳሜን እየማግሁ ራሴን እውስጧ ገደልኩት።
ትላንት የሌለው ኅላዌ ያፍነኛል ፣ እናም ዛሬዬን እርሷ ውስጥ ቀበርኩት - ከትዝታዬ ተጋብቼ ለመኖር።

Read 289 times