Thursday, 18 January 2024 16:50

አንገቴን ታስደፋኛለህ…

Written by  ዳንኤል ወርቁ-
Rate this item
(1 Vote)

ወደ አዳራሹ ስገባ አስፈሪ ድምፅ ተቀበለኝ። አስፈሪ!
“አታስመስል! … አታስመስል!” የሚያንባርቅ ድምፅ! “ወደዚህ የገባኸው ሠዓሊውን ስለምታከብረውና ስለምትወደው ነው?”
ድምፁ ከየት እንደመጣ የማን እንደሆነ ለማወቅ ያስፈራል። ቤቱ የእርሱ ነው እና እንዲህ እንደልቡ የሚያንባርቀው የገብረ ክርስቶስ ደስታ መንፈስ ይሆን? ከፍርሃቴ የተነሳ አዕምሮዬን ለማረጋጋ¬ት የመታሁት መላ ምት ነበር። ድምፁ ቀጠለ።
“አታስመስል! ልታነጋግረኝ ነው የመጣኸው አይደል? አነጋግረኝ። አንድም በእውቀትህ ያገኘኸውን፣ አንድም በስሜትህ የተረዳኸውን”
አሁን ድምፁ ቁጣ የለውም። ግን ያስፈራል። ዙሪያዬን ቃኘሁ። አላበኝ። “አትፍራ ፈሪ አልወድም፣ እርግጥ ነው አጉራ ዘለል ደፋርም አልወድም። ተረጋግተህ አነጋግረኝ።” አለኝና ፀጥ አለ። ከዚያም “ምን አየህ? ምን ተረዳህ? ማን ነኝ? ምን ለማለት ነው ወር ሙሉ እዚህ የተንጠለጠልኩት? የተዘረጋሁት? የተለጠፍኩት? በበድን ዓይኖችህ አይተህ በድን አታድረግኝ። ሕያው የምሆነው አስተዋይ ዓይኖችና አሰላሳይ አዕምሮዎች ሲያነጋግሩኝ ነው። የምለውን ለመረዳት ሲሞክሩና በገባቸው ልክ ሲያነጋግሩኝ ነው፤ አየህ” ወደ መጨረሻው ላይ እዝን ያለ መሰለ፤ “ሕያው የምሆነው በናንተ በተመልካቾቼ ውስጥ ምላሽ መሆን ወይ ጥቆማ መሆን ስችል ብቻ ነው።”
ተረጋጋሁ። የሚያነጋግረኝ ማን እንደሆነ የተረዳሁ መሰለኝ። ቀስ እያልኩ ዓይኖቼ ፊት ለፊቴ የተሰቀለው ልጠፋ፣ ፅሁፍና ቅብ የተቀላቀሉበት ትልቅ መደብ ላይ አረፉ። ተጠግቼ አየሁት። ልቤን ማላብ ጀመረኝ። የማይታይ ላብ። አስጨናቂ ላብ። በእጆቼ አፌን ያዝኩ።
“አፍህን ልቀቅ!” ድምፁ አምባረቀ። “አታስመስል! እያስተዋልክ ተራመድ። ለምን ዘለልከው?”
ዞር አልኩ፤ ፈርቼ ወዳለፍኩት የጥበብ ስራ። ዓይኖቼ ተጭበረበሩ። መፈራረስ፣ መውደቅ፣ ከሞቱ በኋላ በሕይወት መቆየት ያስፈራል። የተፈረካከሰ አካሌን ማየት፣ የተሰባበረ የደረቀ ሆኖም በደም የተጨማለቀ፣ ግን የቆመ የሚመስል አካሌን ማየት በጣም ያስፈራል።
“አስተውለህ እየው!” ትዕዛዝ የመሰለ ድምፅ።
አናደደኝ “አላየውም!” አልኩ ጮክ ብዬ።
የሥነ-ጥበብ ሥራው ረቂቅነትን ለመፍጠር የተለያዩ ቁሶችን ያካተተ ውስብስብና ትኩረት የሚስብ ነው። የተለያዩ ከፍታ ያላቸው ሽቅብ በተለያየ ልክ የተደረደሩት ጣሳዎች የከተማችንን ህንፃዎች ያስታውሳሉ። እላያቸው ላይ ከተደፋው ቀይና ጥቁር ቀለም ጋር አደገኛነትን፣ ድፍረትን፣ እሳታማ ኃይልን፣ በሌላ ገፅ ደግሞ የማስጠንቀቂያ ደወል የሚደውሉ ይመስላሉ።
በቅርፅ በየደረጃው በግድና በውድ የተጠቀጠቁት፣ የተዝረከረኩት ቀለመ ብዙ ብጥስጣሽ ወረቀቶች በመሠረቱ ዙሪያ ተዝረከርከው ይገኛሉ። ይህም ባህላችን ውስጥ የተለያዩ ሥርዓቶች እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን ሊያመለክት ይችላል አልኩ። ለራሴ ነው። እነዚህ ሥርዓቶች በዓይን የማይታዩ የተበላሹ መሆናቸውንና የመበታተን ስሜትን ጨምሮ የሚጠቁሙ ይመስላል።
ዝብርቅርቅ፣ በተደራጀ መልክ የተሞሉ፣ ሥርዓት አልበኝነት የሞላባቸው። ያለፍላጎታቸው የተጨናነቁ። ይህ ልዩነት የምንተዳደርባቸውን መዋቅሮች ሥርዓታማ የሚመስሉትን፣ ደግሞም በጭንቅንቁ ብዛት የተደቆሱትን ይመስላል። የእርስ በርስ ትስስራችን፣ አስተዳደራችን፣ አወቃቀራችን፣ ውጥንቅጣችን፣ የተዛባነት ሰሜትን፣ እያየነው የማናየውን የሥርዓት ብልሹነት በጩኸት ይናገራል። የማናውቀው አጠቃቀም፣ ኡደተ ጥፋት። በእርግጠኝነት፣ እምምምም፣ አዎ በእርግጠኝነት ዘላቂነት ያላቸውን አሠራሮች አስፈላጊነት የሚጠቁም ጩኸት።
ምን ያህል እንዳፈጠጥኩ አላውቅም። በዚህ ውስብስብና ድንቅ የጥበብ ሥራ በዙሪያችን ያሉ አገልግሎታቸው ያበቃ ቆሻሻዎችና ሥነ ጥበብ ሲዋሃዱ ምን ያህል ሊተርኩንና ሊያስደምሙን እንደሚችሉ እያሰላሰልኩ፣ ወደ ቀጣዩ ክፍል ተንፏቀቅሁ። ብዙም አልሄድኩም፤
የሚንከተከት ሣቅ ሰማሁ። ከዚያም
“እዚያ ክምር ውስጥ፣ እዚያ ድርድር ውስጥ የመኖርና አለመኖር ትግል፣ ጦርነት፣ ረብሻ፣ የተዳፈነ ጩኸት አልሰማኽም። ሕይወት ማለት ሞት፣ ሞትም ሕይወት ነው የሚል አይመስልኽም። በየቀኑ፣ በየሰዓቱ አጠገብህ እነዚህ ረብሻዎች፣ ግርግሮች፣ በግርግር ውስጥ ዝም፣ ፀጥ እረጭ ያለ ግን በጫጫታና በነውጥ የተሞላ ውህደት።”
ሊያዞረኝ የጀመረ መሰለኝ። አይኖቼን ከፊቴ ከተንጠለጠለው ግዙፍ ሥዕል ላይ አፍጥጬ ዝም አልኩ። ድምፁም ዝም አለኝ። ከልቤ የሚንጠባጠበው ላብ በውስጤ ጎርፍ ፈጥሮ ማዕበል ያስነሳ መሰለኝ። አንዱ ጥግ ላይ ቆም ብዬ ራሴን ለማረጋጋት አሰብኩና ዞር አልኩ።
“ግባ ወደ ሚቀጥለው ክፍል” አለኝ ድምፁ።
“አልገባም!” አልኩ ጮክ ብዬ። “በቁጣና በንዴት፣ በጭንቀትና ፍርሃት እስክወድቅ ድረስ ማየቴን እቀጥላለሁ።” ድምፁ ድምፁን አጠፋ። አሁን ንዴቱ የኔ ተራ ሆነ። የውስጤ ነውጥ፣ የቁጣ ጎርፍ ወደ ጉሮሮዬ ከዛም ወደ አፌ መጣ። ወጣ።
“እንደዚህ ልትሰድበን አትችልም!“ አልኩት። “ራሳችሁን የናቃችሁ፣ ለሆዳችሁ ብቻ የምትሞቱ፣ ለመንቃት፣ ራሳችሁን ችላችሁ ለመቆም አቅምም፣ ልብም፣ አዕምሮም፣ ወኔውም የሌላችሁ ናችሁ ልትለን አንተ ማን ነህ?”
“የእናንተ ታሪክ ነኝ። ሌላ ማን ልሆን እችላለሁ። እኔ ላይ አንድም ባዕድ ማንነት አይተሀል? እኔ እናንተን ነኝ።”
“ምን ለማለት ነው?”
“አንብበኝና ጨርሰኛ፤ ገና መቅድም ላይ ነው እኮ ያለኽው” የምፀት ሳቅ ሳቀ። “ይህንኑ ነው
እያልኩ ያለሁት፤ ልክ አሁን እንዳንተ መፅሀፉን አንብባችሁ ሳትጨርሱ፣ ስለማወቃችሁ የምትደሰኩሩ፣ ድኩማን ናችሁ። ሆዳችሁ የሞላ ሲመስላችሁ በያገኛችሁበት ማግሳትና ማቀርሸት ከሌላው ያስበለጣችሁ የሚመስላችሁ ግብዞችና አስመሳዮች ናችሁ።”
አንገቴን አቀረቀርኩ።
“ሂዳ ምን ይገትርሃል። ሂድና የሀገርህ ታሪክ ውስጥ ሀገርህን ፈልጋት። ራስህን ፈልግ።” አለኝ፤ እጅግ በተጎዳ ስልተ ድምፅ።
እንደተገተርኩ ቀርቼያለሁ።
“ሂድ” አለኝ በተለሳለሰና አንጀት በሚያላውስ ድምፅ። “ምዕራፎቼን ሁሉ አንብበህ ስትጨርስ ተመልሰህ ና እና ታነጋግረኛለህ። ታስረዳኛለህ? የት ጋ እንደሳትኩህ? የት ጋ እንደ ናቅሁህ? የት ጋ እንዳከበርኩህ? ትነግረኛለህ። አትጨነቅ፤ አንድም በዕውቀት፣ አንድም በስሜት እንወያያለን።”
እየተንቀራረፍኩ ወደሚቀጥለው ሥዕል፣ ከዚያ ወደሚቀጥለው ሥዕል፣ ከዚያ ወደ ሚቀጥለው ሥዕል። ድግግሞሹ ሰለቸኝ። ግብዝነቱ አደከመኝ። ምድጃ እየለዋወጡ ያንኑ አሳፋሪ ምግብ መብላት ሰለቸኝ። የልብ ግብዝነታችን፣ የአዕምሮ ድህነታችን፣ ርሃብ ሆነን ርሃብን መፍራታችን፣ አራደኝ። ከልቤ እያስጨነቀ የሚጎርፈው ጭንቀት አንሸራቶ ወለሉ ላይ ዘረፈጠኝ። ባዶ፣ ምንም፣ ለዘመናት ራሳችንን እንዴት እንዲህ እንዋሻለን። እንዴትስ ውሸታችን ሳይገለማን፣ በኩራት በየአደባባዩ እንበጠረቃለን። ሁሉንም በእነዚያ በተለያየ መጠን የተወጠሩ ጆንያዎች፣ የተቀዳዱ ወረቀቶች፣ የተበጣጠሱ ሥዕሎች፣ እጅግ በሚያስገርም ድርደራ፣ አሽሟጣጭ ድርደራ፣ ውጥንቅጥ ድርደራ፣ በንቃት ስናዳምጣቸው ሥዕሎቹ አተካራ ገጥመው እስከምንሰማቸው ድረስ እያንዳንዳቸው ምዕራፍ የሆኑ ብዙ ገፆችን አነበብኩ። ድምፅ አልነበረኝም፣ ውስጤ የቀረ ጉልበት አልነበረም። ሆኖም በመከራ ተንፏቅቄ ተነሳሁ። ተነሳሁና ቆምኩ። አሰብኩ። አንብቤ በጨረስኩት የሀገሬ ታሪክ ላይ እንዳለሁት ሰው ሳይሆን ተስፋ እንደተሞላ ሰው። የፎረሸውን ህዝቤን እንደሚያነቃ ሰው ማሰብ። ግን እንዲህ ነው ያልኩት። “እኔ ከዚህ ወለል ላይ ተንፏቅቄ ተነሳሁ። ሀገሬም እንዲህ ተንፏቃ ትነሳ ይሆን። ከድጡ፣ ወደ ማጡ ከመላቆጥ የሚያወጣት ትውልድ ይመጣ ይሆን? እየመጣ ይሆን? ውርደቱን ተቀብሎና ውርደቱን አሸንፎ በራሱ የሚቆም ትውልድ። በየደጃፉ የመፅዋቾቹን ፎቶግራፍ ለጥፎ መፎከር የሚያሳፍረው ትውልድ። እኔ አይደለሁም። አብቅቻለሁ። ከዚያ ድምፅ ጋር የመነጋገር አቅምም ወኔም አልነበረኝም። እየተጎተትኩ ወጣሁ። ጩኽት ይሰማኛል፤ ከኋላዬ። ግን ወጣሁ። አስታውክ አስታውክ አለኝ። ድንቁርናዬ፣ አለማወቄ፣ ግብዝነቴ በትውከቴ የሚወገድ ይመስል።
ራሱን ፈልጎ የሚያገኝ በሥራው፣ በእጆቹ፣ በጭንቅላቱ፣ ራሱን ከዚህ ፈልቅቆ የሚያወጣ ትውልድ ያስፈልጋል። የሌለውን ቢጭኑበት፣ አሽቀንጥሮ የሚጥል፣ ነጩ ጆንያ ላይ ፊደላትን እየቀያየረ በእፍረቱ ሸክም ከመኮፈስ ይልቅ የሚያፍር፣ የሚቆጣ ትውልድ።
መብራቱ ሲጠፋ፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ፣ ኩራዝም ሆነ ጧፍ፣ ሻማ የለንም ብለን በድቅድቅ ጭላማ በተኮራመትንበት ሰዓት ለራሱ የበራለትን ጭላንጭል ይዞ ብቅ ያለ ሠዓሊ፣ ተመራማሪ፣ ፈላስፋና ቀባጣሪ ነው፤ ኢዮብ ኪታባ። ኢዮብ እግዚአብሔር ይይልህ። አሳቢ፣ አንባቢ፣ የተረጋጋህና ጥልቅ ሰው እንደሆንክ አውቅ ነበር። እንዲህ ተመንጭቀህ ወጥተህ፣ እንዲህ ለሳምንታት ልቤን ታስነባዋለህ፣ አንገቴን ታስደፋኛለህ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም ነበር።
ስሜቴ ይኽንን ነው ያለኝ።
 
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 1385 times