Saturday, 20 January 2024 00:00

የአስፋው መሸሻ አስከሬን ወደ ኢትዮጵያ ይገባል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

…ደግነትና ቅንነት ቆመው ቢሄዱ አስፋው ናቸው…”

በአሜሪካ  ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ ያረፈው የኢቢኤስ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጁና አቅራቢው አስፋው መሸሻ አስከሬን ነገ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ተነግሯል። እዚህ አዲስ አበባ የቀብር ሥነ-ስርዓቱን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ-ስርዓቱ ከነገ ወዲያ ሰኞ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ተወዳጁ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁና አቅራቢው አስፋው መሸሻ ከኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ አስቀድሞ በኤፍኤም አዲስ 97.1 “አይሬ”  የሙዚቃ ፕሮግራሙ ዕውቅናና ተወዳጅነትን ማትረፉን ይታወቃል። ከዚያም በኢቢኤስ ይተላለፍ ከነበረው “ኑሮ በአሜሪካ” እስከ “እሁድን በኢቢኤስ” መሰናዶ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል።
አስፋው መሸሻን በሥራ ባልደረባነትና በጓደኝነት ለ20 ዓመታት ገደማ የሚያውቀው በአሜሪካ የኢቢኤስ ባልደረባ ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ ለቪኦኤ በሰጠው ምስክርነት፤ “…ደግነትና ቀናነት በእግር ቆመው ቢሄዱ አስፋው ናቸው…” ብሏል።
አስፋው በአሜሪካ  በህክምና ላይ ሳለ ያስተዋልኩት የህዝብ ድጋፍና ፍቅር ከአዕምሮዬ በላይ ነው ሲል የተናገረው ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ፤ “ሆስፒታል መጥቶ ልጠይቅህ ላስታምህ ከሚለው ባሻገር… በፀሎትም በገንዘብም…. በስልክም በመንፈስም… ሁሉም ሰው አብሮት ነው የቆመው” ብሏል። “አስፋው በህዝብ ፍቅር ታጅቦ ነው የኖረውም ያለፈውም” ሲልም ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በአሜሪካ የስንብትና የሽኝት ፕሮግራም እንደሚደረግለት ለሬዲዮ ጣቢያው የገለፀው አበበ ፈለቀ፤  ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም የአስፋው መሸሻ አስክሬን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላክ ጠቁሟል።
ከአባቱ አቶ መሸሻ አስፋውና ከእናቱ ወ/ሮ ዘነበወርቅ አሻግሬ ሃምሌ 19 ቀን 1959 ዓ.ም የተወለደው አስፋው መሸሻ፤ የአንድ ልጅ አባት ነበር።የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በአንጋፋው የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ አስፋው መሸሻ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለስራ  ባልደረቦቹና ለወዳጆቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል። ፈጣሪ ነፍሱን በአፀደ ገነት ያኑርለት።

Read 808 times