Monday, 22 January 2024 07:58

ለብዙ በሽታዎች መንስኤ የሆነው ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም...

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ በመውለጃ እድሜ ላይ ከሚገኙ ሴቶች መካከል ከ8 እስከ 13 በመቶ የሚሆኑት በፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም (polycystic ovary syndrome) የተጠቁ ናቸው። ከነዚህ ሴቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ይህ የጤና ችግር እንዳለባቸው በምርመራ እንዳላረጋገጡ ይገመታል።
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙከሚል ታደለ እንደተናገሩት ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ወደ አማርኛ ሲተረጎም ብዛት ያለው፣ ውሃ የቋጠረ እና የእድገት ውስንነት ያለው የቁንቁላል ማምረቻ ከረጢት መኖር ማለት ነው። ይህ የጤና ችግር የተለያዩ በሽታዎችን የሚያስከትል ነው እንጂ በራሱ በሽታ የሚባል አይደለም። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር ከበሽታ ትንሽ ዝቅ ባለ ደረጃ የሚገኝ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን የተለያየ እና ከባድ የጤንነት ችግሮችን ያስከትላል።
አንዲት ሴት በፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ተጠቅታለች የሚባለው የወርአበባ መዛባት፣ በወንድ ላይ በብዛት የሚገኘው የአንድሮጂን ሆርሞን ከፍ ማለት እና የእንቁላል ማምረቻ ውስጥ የዘገየ ወይም የእድገት ውስንነት ያለበት እንቁላል በብዛት ሲኖር ነው። ነገር ግን ሶስቱም በአንዲት ሴት ላይ ላያጋጥም ይችላል። ስለሆነም ሁለቱ ምልክቶች ከተገኙ የጤና እክሉ ሰለባ ናት ይባላል። ነገር ግን የችግሩን መኖር ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። “በአንዲት ሴት ልጅ እንቁላል ማምረቻ ውስጥ ብዙ እንቁላል በ1 ወር ውስጥ የሚዘጋጅ ቢሆንም አንድ ወይም ሁለት እንቁላል ግን ከሌሎቹ ተለይተው (ተጋነው) ይወጣሉ። ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ሲስተዋል ግን የሁሉም እንቁላሎች ደረጃ ፍፁም ተመሳሳይ ስለሚሆን ወደ ሚቀጥለው ደረጃ(ለዘር) መዘጋጀት አይችልም” ብለዋል ዶ/ር ሙከሚል ታደለ።
የፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም መንስኤ(አጋላጭ ሁኔታዎች)
በቤተሰብ ውስጥ በዚህ የጤና እክል የተጠቃ ሰው መኖር (በዘር); እናት፣ እህት እና አክስት
ከመጠን ያለፈ ውፍረት
ስኳር ወይም ቅድመ ስኳር እና መሰል በሽታ
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሙከሚል ታደለ እንደተናገሩት የፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም መንስኤ (ምክንያት) ሙሉ በሙሉ የሚታወቅ አይደለም። በዓለምአቀፍ ደረጃም ገና በጥናት ላይ ያለ እና መንስኤው ሙሉበሙሉ ያልታወቀ ነው።
ምልክቶች
የወርአበባ መዛባት; መዘግየት ወይም ሙሉበሙሉ መቅረት
ከመጠን ያለፈ ውፍረት
የቡጉር መኖር፣ ፊት፣ ጀርባ እና ትከሻ ላይ
የፀጉር መሳሳት (ራሰበርሃ መሆን)
ፊት ላይ ፀጉር መኖር(ፂም)
ሆድ አከባቢ ያለ ውፍረት (ቦርጭ)
የቆዳ መሻከር(ለስላሳ አለመሆን)
የጡት አለመጉላት(ማነስ) እና ጡንቻማ መሆን
የአንድሮጂን ሆርሞን በብዛት መኖር
ልጅ ያለመውለድ ችግር
የፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ምልክቶች እንደየ ሰዉ የሚለያይ ነው። እንዲሁም ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት በመጀመሪያው እስከ 2 ዓመት ባለው ወቅት የመዘበራረቅ ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ስለሆነም የፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው ከመጀመሪያው ወቅት በኋላ ያለው የወር አበባ ኡደት መዛባት ነው።
የጤና ችግሩ በብዛት የሚከሰተው በአማካይ እድሜያቸው ከ10 እስከ 13 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ታዳጊ ሴቶች(ጉርምስና) ላይ ነው። ነገር ግን ከዚህ እድሜ ውጪ ባሉ በየትኛውም የመውለጃ እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ ሊያጋጥም ይችላል። እንዲሁም የጤና እክሉ ያለባቸው ሴቶች የወርአበባ ማየት ካቆሙ[ካረጡ] በኋላም የችግሩ መዘዝ ሲቀጥል ይስተዋላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ከተጠቁ ሴቶች መካከል ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ልጅ ላለመውለድ ችግር(መሀንነት) ተጋልጠዋል።
ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም የሚያስከትለው ችግር; የማህፀን ግድግዳ ካንሰር፣ ልጅ ያለመውለድ ችግር፣ ቅድመ ስኳር እና ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የልብ እና ተያያዥ ችግሮች፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የወርአበባ መዛባት፣ የስነልቦና ችግር [ጭንቀት፣ ድብርት እና መሰል የስነልቦና ችግሮች] እንዲሁም ማህበራዊ(በማህበረሰብ ዘንድ የሚያጋጥም) ችግር እንደ መገለል፣ ተቀባይነት አለማግኘት እና ሌሎች በማህበረሰቡ ዘንድ የሚኖሩ ጫናዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ሌሎች በሽታዎችን በማስከተል ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ ህክምና ይሰጣል እንጂ ችግሩን ሙሉበሙሉ ማጥፋት(ማዳን) አይቻልም። በተመሳሳይ ችግሩ እንዳይከሰት ለማድረግ ሙሉበሙሉ መከላከል እንደማይቻል የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። የጤና ችግሩ ላስከተለው የወርአበባ መዛባት፣ ያለመውለድ ችግር እና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ህክምና ይሰጣል። እንዲሁም ፓሊሲስትሪክ ኦቫሪ ሲንድረም እንዳይከሰት እና ከተሰተም በኋላ ከባድ ችግር እንዳያስከትል ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላል። ይህም ለእራስ የሚደረግ እንክብካቤ እና በህክምና ተቋም እንዲሁም ባለሙያ የሚሰጥ ህክምና ነው።
መከላከያ መንገዶች
በፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም የተጠቃ ቤተሰብ ካለ ቅድመ ምርመራ እና ህክምና ማድረግ
በልጅነት ያለ ከመጠን ያለፈ ውፍረት መቀነስ
የሰውነት ክብደት ማስተካከል
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
ችግሩን የሚያስከትሉ በሽታዎችን መታከም
ነፍሰ ጡር ሴት ጤናዋን መጠበቅ
የአንድ ሰው ጤንነት የሚጀምረው ከእርግዝና(ከእናት ሆድ ውስጥ) ጀምሮ ነው። ስለሆነም እናቶች ቅድመ ወሊድ የህክምና ክክትል እና ተገቢ የሆነ በእርግዝና ወቅት የሚያስፈልግ የሰውነት ክብደት እንዲኖር በማድረግ(የቁመት እና የሰውነት ክብደት በማመጣጠን) የፅንስ ጤናን መጠበቅ ይችላሉ። እንዲሁም ይህ ለፅንስ የሚደረግ እንክብካቤ በጉርምስና ወቅት የሚኖርን ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለመከላከል ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ የፓሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ተጠቂ፣ የወርአበባ መዛባት፣ ልጅ ያለ መውለድ እና ሌሎች የጤና ችግሮች ካሉ የፅንስ እና የማህፀን ስፔሻሊስቶች ጋር በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚያስፈልግ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሚከሚል ታደለ ተናግረዋል።

Read 256 times