Monday, 22 January 2024 07:53

የጥምቀት እንግዳ - ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

· ወልዲያ--የህዝቡ ፍቅር ለማዘንና ለመተከዝ ፋታ የሚሰጥ አይደለም
· የባህል ሙዚቃ በሜጀር ደረጀ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አይሰጥም
· ምርጫ ሲመጣ---ከማንም በላይ የሚጎዳው አርሶ አደሩ ነው
· እናቴ ወይፈን ሸጣ ጊታር ገዝታልኛለች


የአገው ምድር ቻግኒ ናት ያበቀለችው፡፡ ከክራር ጋር የተዋወቀው ገና የ11 ዓመት ለጋ ታዳጊ ሳለ መሆኑን ይናገራል፡፡ የበዓል እንግዳችን የባህል ሙዚቀኛና ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ፤ “እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም” የተሰኙትን ከቱባው ባህል የተቀዱና ለ“ኮራ አዋርድ” እጩ እስከመሆን ያደረሱትን ዘፈኖች እስኪያወጣ ድረስ እምብዛም አይታወቅም ነበር፡፡ ዝምታና ጥሞናን ገንዘቡ ያደረገው ድምፃዊው፤ ሁለቱን ነጠላ ዘፈኖቹን ባወጣ ማግስት በሀገር ውስጥና በውጪ ለሙዚቃ ኮንሰርት ቢጋበዝም፣ ”በሁለት ዘፈን ህዝብ ላይ መፈንጨት ተገቢ አይደለም” በሚል ሚሊዮን ብሮችን ወደ ጎን ትቶ፣ ለተጨማሪ ሥራዎች ውሎና አዳሩን ስቱዲዮ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ከሁለት ዓመት ከስምንት ወራት የስቱዲዮ ምናኔ በኋላም ከሰሞኑ “አስቻለ” የተሰኘውን አዲስ የሙዚቃ አልበሙን እነሆ በረከት ብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነን ቦሌ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን  ጀርባ  በሚገኘው የሙዚቃ ስቱዲዮው ተገኝታ በስፋትና በጥልቀት ስለ ሙዚቃ ህይወቱ አነጋግረዋለች፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ስለ ሙዚቃ ብቻ ግን አይደለም ያወጉት፡፡ ስለ ትምህርቱና ፍቅር ህይወቱ፣ ስለ ግብርና ሙያው እንዲሁም በፖለቲካ ምክንያት ስለደረሰበት ውጣ ውረድም ተጨዋውተዋል፡፡ አንብቡት - ትወዱታላችሁ፡፡አስቻለው፤ ስለ አዲሱ አልበምህ እንኳን ደስ አለህ---
እንኳን አብሮ ደስ አለን፤ በጣም አመሰግናለሁ!
ከ“እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም” ነጠላ ዘፈኖችህ በፊት ብዙ ልብ ያላልናቸውና ስላንተ ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ እስኪ በደንብ እንተዋወቅህ?
ከሙዚቃ ጋር የተዋወቅሁት ገና በ11 ዓመቴ አካባቢ ነው፡፡ አባቴ ነፍሱን ይማርና የተከበረች ማንም የማይነካት ቆንጆ ክራር ነበረችው፡፡ በር ላይ ቁጭ ይልና “ፋኖ ፋኖ”ን በደንብ ነበር የሚጫወተው፡፡ እኔ አሁንም የማስታውሳቸው ከግጥሞቹ ሁለት ጊዜ የሚደጋግማቸው ነበሩ፡፡
እስኪ ንገረን?  
“ሰው ሁሉ ይዋሻል እኔ አላውቅም ውሸት፤
 እንሂድ አገራችን እንብላ መስኖ እሸት
 ብቻዬን ነኝ ብዬ ዞሬ ዞሬ ሳይ
 ለካስ ዳሞቶቹ አሉ ከኋላዬ” ይላል፡፡
 ሁልጊዜም በጥር መድሃኒያለም የአባቴ ዘመዶች እኛ ቤት ይመጣሉ፡፡ መጥተው ይሰበሰቡና ታዲያ፤
”እቴ መላ ዘውዴ ዘውዴ
እቴ መላ ዘውዴ ዘውዴ--እቴ መላ ዘውዴ ዘውዴ” ይላሉ (በድምጹ እየዘፈነ)፡፡ ያንን ነው እኔ ”ካሲናው ጎጃም” ላይ ግጥሙን ቀይሬ የሰራሁት እንጂ የአባቴና የዘመዶቼ የጥንት ዘፈን ነው፡፡ ያኔ ፉከራ ሽለላም አለ፤ በደንብ አስታውሳሁ፡፡ አባቴም ዘመዶቹን በቅጥያ ስም ነው የሚጠራቸው፡- “ጋርጣው” ይለዋል አንዱን፡፡ “አፈንዳው ጎርድም” ይለዋል ሌላውን፡፡ ለምሳሌ አባቴ እኔን “የእኔ እንግዳ” ብሎ ይጠራኛል፡፡ ስሜ አስቻለው ሆኖ ሳለ በራሱ ልዩ ምክንያት ነው ”የእኔ እንግዳ” የሚለኝ፡፡ ታዲያ ዘመዶቻችን ሲመጡ የማንኩሳና የቡሬ አገዳ ይዘው ስለሚመጡ እሱን እንጠብቃለን፡፡ ደሞ የእናቴ ዘመዶች በፈረስ ከግምጃ ቤት ይመጣሉ፡፡ እነ አባ ጓንጉልና አባ ገዳሙ የተባሉ ዘመዶቻችን ይመጣሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የአገው ፈረስ አለ፤ ቻግኒ ውስጥ ጥቅምት መድሃኒያለም በደንብ ይከበራል፡፡ እኛ አገዳ ከዘመዶቻችን እንቀበላለን፡፡ በጣም የሚኮሰኩስ ጢማቸው ውስጥ እያሹ ይስሙናል፤ ፍቅር ይሰጡናል፤ ያ ድባብ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ቱባው ባህል ውስጥ ነው ያደግሁት ለማለት ነው፡፡
በትምህርትህ ጎበዝ እንደነበርክ ሰምቻለሁ --?
አዎ! በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩኝ፤ 12ኛ ክፍል ማትሪክ ሒሳብ “F” መጣብኝ፤ እንደገና ተፈትኜ ግን 3 ነጥብ 8 አመጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ለአማራ ክልል  ስትሬት A ብቻ ተባለ፡፡ እኔ ደግሞ ማምቡግ ነበር የተማርኩት፤ ክልል 6 ማለት ነው፡፡ ከእኔ ጋር ተምረው 3 ነጥብ 2 ያመጡት ተጠሩ፡፡ ያኔ እኔ በጣም ተሰማኝ፡፡ እኔ ከአማራ ክልል ሄጄ ነበር የተፈተንኩት፤ ይሄ በክልል የሚባል ነገር ነው ችግሩን ያመጣውና በጣም አዘንኩ፡፡ ቀጠልኩና ባህርዳር ሄጄ ደግሞ በሰባት ወርና በ1 ዓመት ህግ ለመማር ተወዳድሬ አለፍኩ፤ ግን ያ ኮታ ደግሞ ለከተማዋ ሰዎች ነበር የወጣውና እዛ ተወላጅ ነኝ ብላ 3.2 ያመጣች ልጅ ገባች፡፡ በዚያም ማሰልጠኛ ልገባ የነበረበት ዕድል ቀረ፡፡ በኋላ የማታ ተማር ስባል እናቴን ብር አላስወጣም ብዬ ተውኩት፡፡
ትውት ትውት--?
አዎ ሁሉም ነገር አስጠላኝ፡፡ ያን ጊዜ እናቴ ወይፈን ሽጣ ጊታር ገዛችልኝ፡፡ በነገራችን ላይ እናቴ በጣም አራዳ ናት፡፡ አሁን የጊታሩን ሳይንሳዊ አፈጣጠር አታውቀውም፤ ለኔ እንደሚያስፈልገኝ ግን አውቃ ነበር፡፡ ያን ጊዜ እንደዛ ጎበዝ ተማሪ የነበርኩት ልጅ  ከትምህርት ስቀር እናቴ ብቻ ሳትሆን፣ ሁሉም ነበር ያዘነው፡፡ ከዚያ የግብርና የ3 ዓመት ስልጠና እንድማር እኔ ባህርዳር ሆኜ ቻግኒ አስመዘገቡኝ፤ መርጡ ለማሪያም ሄድኩኝ፡፡ እዚያ ስሄድ ክራሬንም ጊታሬንም ይዤ ነበር፡፡ ያንን ትምህርት የጀመርኩት በትምህርቴ ሁኔታ እናቴ አዝና ስለነበር፣ እሷን ለማስደሰት ነው፡፡ ያኔ መርጡ ለማሪያም አካባቢውን ስዞር ስጎበኝ ብዙ አዳዲስ ልምዶችንም አካበትኩ፡፡ መርጡ ለማሪያም በዲፕሎማ ተመርቄ የግብርና ባለሙያ ሆኜ ቻግኒ ተመደብኩ፡፡ የጉምዞች አካባቢ ሳስ ዱባክቻ የሚባል ጉደር ጃቢ ቀጠና ውስጥ አኩሪ አተር እዘራ ነበር፤ ሰሊጥ በርበሬና ሌሎችንም እያዘራሁ ሚንጊ ላይ ሁለት ዓመት ያህል ኖርኩ፡፡ የጉምዞች አኗኗራቸውም አካባቢውም ተመቸኝ፤ እነሱ የኢትዮጵያ መሪ ማን ይሁን፣ ፖለቲካው ምን ይምሰል የሚያውቁልሽ ነገር የለም፡፡ በጋ ላይ ከእነሱ ጋር ቁጭ ብለሽ ቦርዴሽን ትጠጫለሽ፤ ቦያ የሚባል ምግብ አለ፤ ዱባ አለ፡፡ እኔ የግብርና ባለሙያ ነኝ፤ አስፈቅደው አደን ያድናሉ፡፡ አድነው ከተሳካ የሚዳቋዋን አንድ እግር ያመጣሉ፤ ያንን እየበላን ዙምባራ ይነፋል፣ ሁሌ ማታ ማታ ጨዋታ ነው፡፡ በጣም ከማልረሳው የህይወቴ ክፍል፣ ከጉምዞች ጋር የኖርኩት አንዱ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ “ዳንጉላ” የሚባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ገባሁ፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው አገውዎች በብዛት የሚኖሩበት ነው፡፡ እዚህ ደግሞ ሌላ ባህል፣ ሌላ ህይወት አወቅሁኝ፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ህይወቴ ጥሩ ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም ምርጫ ሲመጣ ነገሮች መበላሸት ጀመሩ፡፡
እንዴት ማለት?
ያው ምርጫ ሲመጣ በነገራችን ላይ ከማንም በላይ የሚጎዳው አርሶ አደሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የእከሌ ፓርቲ ነህ፣ እንዲህ ነህ እያሉ ካድሬዎች ምንም የማያውቀውን ህዝብ እያስፈራሩ ሙስና ይቀበላሉ፡፡ ምንም የለሁበትም ብሎ ቢያንገራግር ወስደው ያስሩታል፡፡ እናም በዚያ ጊዜ በሃያዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያ ላይ ነኝ፤ እናንተ “ፍንዳታ” እንደምትሉት አይነት ነኝ፤ ምንም አልፈራም ስራዬን እሰራለሁ፤ መንግሥት የማያቀርበውን ዘር እኔ በኮሙኒኬሽኔ እየገዛሁ አቀርብላቸዋለሁ፡፡ በዚህ በዚህ ህዝቡ ወደደኝ፡፡ አርሶ አደሩ አፈር እንዳይሸረሸር ክትር (እርከን) እንስራ ስላቸው ተንጋግተው ይወጣሉ፡፡ የመንግስት ካድሬዎች ሲጠሯቸው አንዳቸውም አይወጡም፡፡ “ይሄማ ነገር ልጁ ሌላ ተልእኮ ቢኖረው ነው” አሉና አንድ ስብሰባ ላይ አባል ሁን አሉኝ፡፡ እምቢ አልሆንም አልኩኝ፡፡ ስብሰባ ላይ ገመገሙኝና የአመለካከት ችግር አለበት ተባልኩ፡፡ ስራም አይሰራም ብለው ሀጢያቴን ሊያበዙ ሞከሩ፡፡ በአጋጣሚ እዚያ ቀጠና ላይ በምሰራው ውጤታማ ስራ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መጥቶ ቀርፆኝ ነበር፡፡ በግምገማው ላይ “እርግጠኛ ናችሁ ሥራ አልሰራም?“ ብዬ ጠየኳቸው፡፡ ሀላፊው ተነስቶ “ስራ ላይ ጠንካራና ጎበዝ ሰራተኛ ነው” ብሎ መሰከረ፡፡ ”እንኳንም ስራ መስራት አትችልም ያልተባልኩ፤ የእኛ አባል ሁን ካላችሁኝ ግን የእናንተን የአመለካከት ኮርቻ ለመፈናጠጥ በጣም ትጠቡኛላችሁ“ አልኳቸው፡፡ ተመልከቺ አዳራሹ ውስጥ ወደ አምስት መቶ የሚጠጋ ሰው አለ፡፡ ኧረረረ--- አሉ፡፡ ”የአመለካከት ችግር አለበት፤ አርሶ አደሩን በህቡዕ ያደራጅብናል“  አሉና ከስብሰባው ሁለት ሦስት ቀን በኋላ የእስር ትእዛዝ እንደወጣብኝ ወዳጆች ደውለው ሲነግሩኝ፣ ከዚያ ጠፍቼ ወልዲያ ገባሁ፡፡
ብዙ ውጣ ውረድ ገጥሞሀል ማለት ነው?
እጅግ በጣም፡፡ ከዚያ ወልዲያ ሄጄ አሁን ካናዳ የሚኖር ሀይለየሱስ የሚባል ወንድሜ ጋር መኖር ጀመርኩ፡፡ መታወቂያም አወጣልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ በየገጠሩ ታቦት ወጣ ከተባለ አርሴማ ብትይ ሌላው ቦታ በእግሬ እስከ 8 ሰዓት እየተጓዝኩ በዚያው አድሬ እመለሳለሁ፡፡ አዳጎ የሚባለውን የወልዲያ ተራራማ ቦታ፣ መቻሬ ሜዳ፣ ጎንደር በር ፒያሳ፣ መድሃኒያለም ሰፈር--- ሁሉንም በእግሬ እየዞርኩ ተዋወቅኋቸው፡፡ እንዳልኩሽ የገጠር ታቦት ሲወጣ ሁለት ሦስት ቀን እዚያ ብቀመጪ የወሎን ሰው ታውቂዋለሽ፤ ቸር ሩህሩህና ፍቅር ነው፤ ብቻ አለመዱኝ፡፡
አስቼ ቻግኒ እያለህ በፍቅር ያንገላታችህ ወሎዬ ልጅ እንደነበረች ሰምቻለሁና፣ እስኪ ለጨዎታው ድምቀት ስለዚያች ውብ ወሎዬ አጫውተኝ----
አሃ ይሄንንም ጋዜጣው ላይ ታስገቢዋለሽ?
ምን አለበት?
ካልሽ እሺ! ቻግኒ በጣም ቆንጆ ወሎዬ አፍቅሬ ነበር፡፡ በዚያ ሁሉ የህይወት ምስቅልቅል ውስጥ ሳለሁ፡፡ ብቻ ተለያየን፤ ብዙ ታሪክ አለው፡፡ እዚያ ከደረሰብኝ ውጣ ውረድ ጋር እንደዚያ የምወዳትን ልጅ ማጣቴ በጣም ጎድቶኝ ነበር፡፡ ወሎ ገባሁ፤ ወሎየዎቹ መከፋቴን ቁስሌን ቶሎ አሻሩት፡፡ ከችግሬ ከሀዘኔ እንድወጣ አደረጉኝ፡፡ ህዝቡ ቁንጅናው ደግነቱ ልዩ ነው፡፡ መደብ ላይ ቁጭ ብለሽ ትበያለሽ ትጠጫለሽ፤ ያንቺ ገንዘብ መኖር አለመኖር ለወሎ ህዝብ ጉዳዩም አይደል፡፡
ብቻ ወሎ፣ ነውር የሌለበት ፍቅርና ደግነት ብቻ ነፍስያውን ያረሰረሰው ህዝብ ነውና ህይወቴን ቀየረው፡፡
ያቺን ቻግኒ ያፈቀርካትን ቆንጆ አስረሱኝ ነው የምትለኝ?  
መርሳት ሲባል እንዴት መሰለሽ---በፊት ብቻዬን ስሆን እያሰብኳት አዝን እተክዝ ነበር፡፡ ወልዲያ ስመጣ የህዝቡ ፍቅር ለማዘንና ለመተከዝ ፋታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ልጅቷን መቶ በመቶ ባልረሳትም ግን በቃ በብዛት ረሳኋት፤ ከጭንቅ ወጣሁ፡፡ በዚህ ፍቅር ህዝብ መሃል ሁለት ዓመት ቆየሁና እንደገና እንዴት ልውጣ? ህዝቡን ወደድኩት፡፡
ድጋሚ ወልዲያ ከአንዷ ጉብል ፍቅር ያዘህ ይሆን?
እንዲያው ፍቅር የሚባል ነገር እንኳን አይደለም፤ ብቻ ከእነ ገምሻሪት ጋር ተገማሽረናል ተይውማ…. (ተያይዘን በሳቅ….)
ከሁለት ዓመት የወልዲያ ቆይታ በኋላ ነው አዲስ አበባ የመጣኸው? እስኪ ወደ አዲስ አበባ ስለመጣህበት አጋጣሚ አውራኝ?
አዎ፤ ከወልዲያ ነው የመጣሁት፤ ብቻ መጣሁ፤ ግን ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ሰው ሲመጣ ውጣ ውረዱ ከባድ ነው፡፡ ፍሬ የምትባል እህት አለችኝ፤ እሷ ጋ መጥቼ ፈረንሳይ ጉራራ የሚባል ሰፈር ገባሁ፡፡ እዚያ እህቴ ጋር እየኖርኩ ቻግኒ ደግሞ ትንሽ ቪዲዮ ቤት  ያላት ፊልምና ሙዚቃ የምታከፋፍል ታናሽ እህቴ ነበረችና (አሁን ለንደን ነው ያለችው)፣ ለሷ የፊልም ሲዲ በአውቶቡስ ለመላክ ሌሊት 11 ሰዓት እነሳና በ12 ቁጥር አውቶቢስ ተሳፍሬ መርካቶ እገባለሁ፡፡ ከዚያ ሳንቲም ለመቆጠብ ከመርካቶ በእግሬ ፈረንሳይ ለጋሲዮን እሄዳለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ከአንድ አመት በላይ ነበር የቆየው፡፡ ይህን ሁሉ የምለፋው እሷ ገንዘብ አጠራቅማና እቁብ ጥላ የኔን የሙዚቃ አልበም ለማሳተም ነበር፡፡
ወቸጉድ! ብዙ ውጣ ውረድ ነዋ ያለፍከው?
ውጣ ውረድ ብቻ!? በጣም ተፈትኛለሁ፡፡ አልፎ ሲወራ ቀላል ነው የሚመስል፡፡ ብቻ ይህንን እየሰራሁ አዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) ማስታወቂያ ወጣ፡፡
የምን ማስታወቂያ?
የድምጻዊነት ማስታወቂያ ነበር የወጣው፡፡ እኔ በአገውኛና በጉምዝኛ ተወዳድሬ አለፍኩ፡፡
በእኔ እምነት፣ ወደ ህዝብ አፍና ጆሮ መግባት የጀመርከው ክራርህን ይዘህ ግጥም በጃዝ ላይ ብቅ ስትል ነው----
አመሰግናለሁ! ምን መሰለሽ---አንድ ቀን የአድዋ በዓል ሲሰራ ማዘጋጃ ቤት ክራር መጫወቴን ማንም አያውቅም፡፡ ከዚያ እዚያው ማዘጋጃ ቤት የዘመናዊ ዳንሱ ቡድን ሀላፊ የሆነው ከድር የሚባል ልጅ አየኝ፡፡ እንግዲህ ከተቀጠርኩ ከሁለት ከሦስት ዓመት በኋላ እኮ ነው፡፡ “እንዴ አስቼ ክራር ትችላለህ እንዴ!” አለኝና “ቆይ ቆይ ከእኛ ጋር ተዋህደህ ትሰራለህ“ ብሎኝ ሰራን፡፡ ሰው ሥራዬን በጣም ወደደው፡፡ እዚያች መድረክ ላይ ደግሞ የፖየቲክ ጃዝ አዘጋጇ ምስራቅ ተረፈ ነበረች፡፡ “እኛ ጋ ግጥም በጃዝ የሚባል ፕሮግራም አለ፤ እዚያ ስራ“ አለችኝ፡፡ እዚያ ገብቼ ስሰራ ደግሞ ሥራዬ በጣም ተወደደ፡፡ በዚሁ ቀጥል ተባልኩ፡፡ ኧረ ቆይ እስኪ ብዬ ግጥም በጃዝ ላይ ሦስት ወይም አራት መድረክ ከሰራሁ በኋላ ተወት አደረግሁት፡፡
ሌላው የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ስለ ህዳሴው ግድብ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ በሸራተን አዲስ “አባይ” የሚል ሙዚቃ ተጫወትኩ፡፡ አዘጋጁ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር፡፡ በእለቱ በርካታ ሚኒስትሮችና ሌሎች የስራ ሃላፊዎችም ነበሩ፡፡ በዚያ መድረክ ላይ አባይን ስጫወት በጣም ወደዱት፡፡ በዚህ መርሃ ግብር ላይ በዚያን ወቅት ባህልና ቱሪዝም በሚባለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ በአሁኑ ባህል ሚኒስቴር የሚሰራ አበበ (የሀብከ) የሚባል ልጅ “ይህን ነገር ለሚኒስትሯ ላሰማት” ብሎ ለዶ/ር ሂሩት ካሳው አሰማ፡፡ በእርግጥ ሚኒስትሯ በመድረኩም ላይ ነበረች፡፡ ይህንን ደግማ ከሰማች በኋላ ፕሮጀክት ንደፉና በደንብ ይስራ ተባለ፡፡ ይሄ ነገር እውነት ሆኖ ከተሰራማ ሰው መሆን ይሰማው (ሶሚክ) ነው የሚሰራው ብዬ ደወልኩለት፤ አላነሳም፡፡ እኔ ደግሞ ስለ አባይ በክራር የተጫወትኩትን ላኩለት፤ በሌሊት ደወለ፡፡ “ፈጣሪ ያክብርልኝ፤ እንኳን ላክልኝ” አለና እንገናኝ አለኝ ተገናኝተን አወራንና ወደ ቀረፃ እንግባ ተባለ፡፡ ቀረፃው ግን ቆየ፡፡
ለምን ቆየ?
ሶሚክ አስቦበት አሰላስሎ አውጥቶ አውርዶ ነው የሚሰራው በፈጣሪ የሚመራ ልጅ ነው፡፡ በየክረምቱ ለአባይ ብዙ ይባል ነበር- ለግድቡ፡፡ ክረምቱ አለፈ አልደረሰም፡፡ አራት አምስት ወር ሆነው፡፡ ከዚያ ተነስቶ አልበም እንስራ አለ፡፡ አንድ ሁለት ብለን “እናትዋ ጎንደር” አሰራ ምናምንኛ ነው የተቀረፀው፡፡
ተው እንጂ?
የምሬን ነው፡፡ ሁሉም ሰው በዚህ ዘፈን ስለሆነ በደንብ ያወቀኝ የመጀመሪያዬ ይመስለዋል፤ ግን አይደለም፡፡ “ፍየሌን ነብር በላት”፣ “ትዝታ”፣ ሌሎቹ የሰማሻቸው ናቸው የቀደሙት፡፡ በአልበሙ ያልተካተቱ በቁጥር ሁለት አልበም የሚወጡ ያለቀላቸው ብዙ ስራዎች አሉ፡፡ አይነታቸውም ሁሉ ነገር በዚህ አልበም ከተካተቱት ይለያል፡፡ በአጠቃላይ ኮሶሚክ ጋርም የተገናኘነውና እዚህ የደረስነው በህዳሴው ግድብ ስራ ነው ማለቴ ነው፡፡
ከህዝብ ጋር በጣም የተዋወቅህባቸውን “እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም”ን ያቀናበረልህ እስራኤል ማረፉን ሰምተናል ብዙ ሰውም ሲያዝን ነበር፡፡ እስራኤልን ምን ገጠመው? በህይወት ቢኖርስ አልበሙን በሙሉ ያቀናብር ነበር ወይ? እሱ ካረፈስ በኋላ ከማን ጋር ሰራህ?
በመጀመሪያ የሰራኋቸው “እቅፍ አርጊኝ በናትሽ”፣ “በላይ ዘለቀ” እና የአገውኛው “እርግብ ዳባኔ” የተሰኙ ዘፈኖች አሉ፡፡ እነዚህ ዘፈኖች መጀመሪያ ቀበሌሽ፣ ከዚያ ከተማሽ፣ ከዚያ ክልልሽ እየሰማቸው ይመጣና ከዚያ ነው አገር አቀፍ የምትሆኚው፡፡ ከላይ የገለፅኩልሽ ዘፈኖች እዚያው አባይ ማዶ ነበሩ፤ በነገራችን ላይ፡፡ “በላይ ዘለቀ”ን አሻሽዬ ሰርቼ ነው በአልበሙ ያካተትኩት፡፡ ከዚያ “እናትዋ ጎንደር” እና “ካሲናው ጎጃም” በጣም ምርጥ ሆነ፡፡ ወደ እስራኤል ስመጣ ህልፈቱ በጣም የሚያሳዝነኝ ነው፡፡ ሳስታምመው ነበር አልሆነም አንድ ልጅ አለችው፡፡ እሱን የምክሰው ልጁን በማሳደግ ነው፡፡ ከአልበሙም ዘጠኙን ዘፈኖች አቀናብሮ ነው ያለፈው፡፡ “ትዝታውን”፣ “እናትዋ ጎንደርን”፣ “ካሲናው ጎጃምን”፣ “አባይን እስኪ ስሚው” እነዚህን ሁሉ ሰርቶ ነው ያረፈው፡፡ ሌሎቹን ሶስቱን ቢን አንዴ የተባለ ልጅ ሰራ ሰለሞን ሀይለማሪያም  ሁለቱን ሰራ፡፡ እስራኤል ምን አገኘው ላልሽኝ ታሞ ነበር፡፡ ህንድ ለህክምና ተልኮ ነበር ተለፋ ተለፋ አልተቻለም፡፡ “እናትዋ ጎንደር” ሲለቀቅ እኔ እሱን እያስታመምኩት ነበር፡፡ “ካሲናው ጎጃም”ን ከለቀቅን በኋላ ሌላውን አዘጋጅቶ በዳታ አድርጎ ነው ያረፈው፡፡ እንዳልኩሽ በወለዳት ልጅ እንካሰው በሚለው ነው እንጂ የምፅናናው ስለ እስራኤል ሳስብ በጣም አዝናለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ መስራት የሚችል የተለየ ተሰጥኦ ያለው ጀግና ልጅ ነበር፡፡ ተደማምጠን መልካም አመለካከትን ተጋርተን ያለ ኢጎ ተናበን ነበር የምንሰራው፡፡ ነፍሱን ይማረውና፡፡ በእርግጥ የአሁኑም ቢን አንዴ የወሎውንና “አስቻለ” የተሰኘውን የሠራ ጀግና ልጅ ነው መቼም። የስራውን ከፍታ ሳውንዱን ሰምተሽዋል፡፡ በጣም ተናበን እየሰራን ነው፡፡ እድለኛ ነኝ መሰለኝ ሰለሞን ሀይለማሪያም ደግሞ ከቴአትር ቤት ጀምሮ ያሰለጠነኝ ሰው ነው፡፡ ሪትም አያያዝ ብትይ… ምን በደንብ አሰልጥኖኛል፡፡ አሁንም እኛ የመሰረትነው “ቡር ቧክስ” ባንድ አስተባባሪ ነው፡፡ ሦስቱም አብረውኝ የሰሩት ምርጥ የምትያቸው ናቸው፡፡ ማሲንቆውን የተጫወተው እንድሪስ ሀሰንም ቢሆን አለ የተባለ ልጅ ነው፡፡ እነ አቡ ገብሬ፣ ብርሃኑ ሞላና እነመሰለ እምቢልታ ተጫዋች፣ እነ ዘሪሁን ሁሉንም ብጠቅስ ጊዜውም አይበቃ። በደንብ ተቀናጅተን ስለሰራነው መሰለኝ ተዋጥቶልናል። እግዜር ያሳይሽ አሁን እምቢልታ እዚህ የለም፣ ትግራይ ብቻ ነው ያለው፡፡ እምቢልታ የሚነፋ አጥተን እደምንም ነው ያካተትነው፡፡
በእኔ መረዳት በአልበሙ የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ መሳሪያ ሰፊውን ድርሻ ይዟል፡፡ ዘመናዊ መሳሪያ በአልበሙ ውስጥ ብዙ ቦታ ያገኘ አልመሰለኝም። ልክ ነኝ?
በጣም ልክ ነሽ!
ታዲያ በዚህ ልክ ሙዚቃን የሚያነግስ የሙዚቃ መሳሪያ እያለን ለምን የውጪው ሙዚቃ ላይ ሙጭጭ ማለት አስፈለገን ትላለህ?
በአልበሙ ላይ ትዝታው ላይና የበርታው ሙዚቃ ላይ ሳክስ አስገብተናል። እና ፒያኖ ላይቭ አለው። ከዚያ በተረፈ 95 በመቶው በአልበሙ የተካተቱ ዘፈኖች ህይወት በባህላዊ መሳሪያ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የእኔን ቁጭት ልንገርሽ፡- ሰፈሬ ስድስት ኪሎ ነው አሁን፡፡ አንዳንዴ እህቴ ጋር ወደ ቦሌ ጎራ ካላልኩ በስተቀር ያው አላገባሁም፤ ወ/ሮ ተሰሩን ስሚው፡፡ ታዲያ የምኖርበት ሰፈር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው በታላቁ የዜማ ሊቅ ስም የተሰየመው “ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት” አለ። ቅዱስ ያሬድን በደንብ ፕሮሞት ስላላደረግነው የዓለም ቲፎዞ ወደእነ ሞዛርት አዳላ እንጂ ከእነሞዛርት የቀደመ የዜማ ሊቅ ያለን እኛ ነን፡፡ እነሞዛርት ፕሮሞት ስለተደረጉ ገነኑ፡፡ ታዲያ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የቅዱሱን የሊቁን ስም ይዞ አንድም ቀን ተማሪዎቹን በባህላዊ ሙዚቃ አስመርቆ አያውቅም፡፡
አሃ ታዲያ እነ ጋሽ ዓለማየሁ ፋንታን የመሰሉ አንጋፋ የባህል ሙዚቃ መምህራን ያሬድ ውስጥ ምንድን ነው የሚሰሩት?
እየውልሽማ… እነጋሽ ዓለማየሁ ፋንታ ማይነር ነው የሚያስተምሩት፡፡ ለምሳሌ ፒያኖ ሜጀር ትማሪና ማይነር ማሲንቆ ወይም ሌላ ነገር ትወስጃለሽ። የባህል ሙዚቃ በሜጀር ደረጃ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አይሰጥም፡፡ እኔ ባህል ዘመናዊ በሚባለው አባባልም አላምንም፡፡ የኢትዮጵያና የውጪ የሙዚቃ መሳሪያ ብዬ ነው የምጠራውም። የምቀበለውም። አንድም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተጫዋች መድረክ ላይ ከሚታዩት  ከያሬድ የወጣ የለም፡፡ በልምድ ነው የሚጫወቱት፡፡ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ት/ቤት ሆኖ፣ የያሬድን የዜማ ሊቁን ስም ይዞ የኢትዮጵን የሙዚቃ መሳሪያ የማያስተምር መሆኑን ሳስብ፣ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ሳቅ ነው የሚፈጥርብኝ፡፡ ምርጥ ምርጥ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያ ባለሙያዎች እያሉ ከዚያ የወጣ ተማሪ ስታነጋግሪ በትሪምፔት ዲግሪዬን ይዣለሁ ይልሻል፡፡ ብቻ አገሩ ሰው እንደሌለው መደረጉ ይቆጨኛል፡፡
ስለዚህ ቁጭትህን ለመወጣት ነው “አስቻለ”ን በኢትዮጵያ ሙዚቃ የሞሸርከው?
በትክክል! እኔ ለምሳሌ የተለያየ ድምጽ ያላቸው ከቅል የተሰሩ ስድስት ክራሮች አሉኝ፡፡ እና ክራሮችን ሳያቸው ያሳዝኑኛል፡፡
ታዲያ ይሄ ሁሉ ቁጭት ካደረብህ ዘንዳ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ት/ቤት የመክፈት ንሸጣስ የለህም?
የረጅም ጊዜ እቅድ አቅጄ አላውቅም። በእጄና በጊዜዬ ላይ ያለውን ነገር በደንብ እሰራለሁ፤ እየሰራሁ መሄድ ነው ደስ የሚለኝ፡፡ እንጂ ብከፍት ደስ ይለኛል፡፡
አሁን ለመክፈት ምን ያግድሃል?
አሃ ገና  አሁን ቁጥር አንድ ላይ ነኝ፡፡ ማለቴ ገና ጅማሪ ላይ ነኝ፤ የብቃት የተወዳጅነትና ሌሎች ነገሮችን አሳድጌ 40 እና 50 ቁጥር ላይ ፈጣሪ ካደረሰኝ ያኔ ይሆናል እንጂ፤ አሁን ላይ ሆኜ እከፍታለሁ፤ እንዲህ አደርጋለሁ ማለት ግብዝነት ነው፡፡ አሁን ላይ ከት/ቤቱ በፊት የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያን ባንድ እንዴት አስተባብረን መድረክ ላይ እናብቃው የሚለውን ባስቀድም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ አሁን ያ አልበሙ ላይ ያማረውና የተቀናጀው የሀገራችን የሙዚቃ መሳሪያ በባንድ ደረጃ ተዋህዶ እንዴት ጣዕም ይፍጠር የሚለው ነው የሚያሳስበኝ፡፡
ወደ ሙዚቃዎችህ እንምጣ፣ “እንገር ወሎ”፣  “እመት ሸዋ”፣ “አድዋ”፣ “ወ/ሮ ተሰሩ እንደምን አደሩ”ን “በላይ ዘለቀ”ን፣ “ትዝታው”ን ሌሎችንም በደንብ ሳዳምጥ ነበር። ከ”እንገር ወሎ” እንጀምር?
ይቻላል።
እኔ እንገር የማውቀው ላሞች ሲወልዱ የመጀመሪያ ወፍራሙ ቢጫ መልክ ያለው ቅድመ ወተቱን ነው፡፡ ሴትም ስትወልድ የመጀመሪያው ልጁ የሚጠባው እንገር እንደክትባት እንደሚቆጠር ሳይንስ ይናገራል፡፡ እንገር ለጤና እንደክትባት ነው፣ ይጣፍጣል፤ መልኩም ያምራል። እንዴት ነው ወሎን “እንገር” ያልከው?
እየውልሽ በጣም ትክክል ነሽ፤ “እንገር” ወተቱ ነው ያ ወተት የሚሰጠው ከአምላክ ነው፡፡ በትክክል ተናግረሽዋል እንደክትባት ይቆጠራል፤ ልጁ እንዲጠነክር ጤናው እንዲስተካከል አምላክ ቀምሞ የስራው ነው እንገር፡፡ ወሎን እንዴት “እንገር” አልከው፤ ላልሽኝ ቃል አጣሁ ወሎን የምገልፅበት እንደገና ደግሞ አዳምጥ አዳምጥና አዳምጥ የሆነ ሀሳብ ብልጭ ይልልኛል፡፡
“ቁኒ ተቀባብታ የኔ ስለውላዋ
የተነደፈ ጥጥ እንገር ነው ገላዋ”፡፡ ይላል። የተነደፈ ባዘቶ ጥጥ አይተሸ ታውቂያለሽ? ጥራቱ ንጣቱ። እንደገና እንገር ጣፋጭም መድሃኒትም ነው። እንገር ብዙ ትርጉም አለው፡፡ የለፋንበት ግጥም ነው። ወሎ የአራቱ ቅኝት መፍለቂያ፣ የውበት፣ የጀግንነት፣ የደግነት የፍቅር፣ የመንዙማ የቅዳሴው ሁሉ መገኛ ነው። ይህንን ሁሉ የቦረና፣ የከሚሴ፣ የራያ፣ የሰቆጣ፣ የመሃል ወሎን ሁሉ… በስድስት ደቂቃ ለመግለፅ መሞከር ምጥ ነው መቼም።
“ፈረንጅ ደሴ ገባ ቁንጅናሽን ሰምቶ
ላብሽን አንቆርቁሮ ሊያሰራው ነው ሽቶ” ነው‘ኮ ያልከው…
ይሄ ግጥም መጀመሪያ ሌላ ነበር አላረካ ሲለኝ ነው እንደገና ይሄን የፃፍኩት። እንዳልኩሽ ለወሎ ቃል አጥሮኝ ነው እንጂ ብዙ ሊባልለት ይገባ ነበር።
…. ይቀጥላል።

Read 1431 times