Saturday, 27 January 2024 00:00

ኢዜማ መንግስትንና ታጣቂ ሃይሎችን ወቅሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንፁሃን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው ያለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በመንግስት የፀጥታ ሃይሎችና ታጣቂዎች መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች ዜጎች ህይወታቸውን ማጣትን ጨምሮ ክፉኛ እንደተጎዱ አመልክቷል።
ኢዜማ ይህንን ያለው ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።የዜጎች ደኅንነት፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ፣ በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅና ረሀብን እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የቀጠለውን ጦርነት በተመለከቱ ጉዳዮች ላይም አቋሙን አስታውቋል።በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተደረገ ያለው ጦርነት “ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ” መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው ፓርቲው፤ “በጦርነቱ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት ሳይቀር” ይህንን ጉዳት ይገነዘቡታል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
በክልሎቹ ባለው ጦርነት ምክንያት የግብርና፣ የትምህርት፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች እንደተስገጓጎሉ ጠቅሶ፤ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችም ለችግር መጋለጣቸውን ጠቁሟል።ከዚህም ባሻገር በክልሎቹ ውስጥ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሚወሰዱ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች “ንጹሃን ዜጎች ሰለባ” እየሆኑ እንደሆነ ኢዜማ በመግለጫው አስታውቋል።ኢዜማ ከዐይን እማኞች በሰበሰበው መረጃ መሠረት፤ በተለይም በድሮን የሚደረጉ የአየር ላይ ጥቃቶች ንፁሃን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እየደረሱ መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል።“ከመንግሥት ጋር የሚፋለሙ ታጣቂዎችም ‘ከተሞችን እንቆጣጠራለን’ በሚል በሚያደርጉት የከተማ ውስጥ ውጊያ በሰው ሕይወትና ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲል ኢዜማ ታጣቂዎችን ከሷል።
“አሁን ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ከዚህም የባሱ ለአገር ህልውና አስጊ የሆኑ ቀውሶች መፈጠራቸው የሚቀር አይመስልም። በእነዚህ ጦርነቶች እንደ አገር ሁላችንም ከስረናል። ያተረፈም ካለ ኢትዮጵያን በዐይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ጠላቶቿ ብቻ ናቸው” ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ኢዜማ ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ማጣት መንግሥትና ታጣቂ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል። ባለፉት ኅዳርና ታኅሣሥ ወራት በኦሮሚያና ጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች የተፈጸሙ ሰባት ጥቃቶችን የጠቀሰው ፓርቲው፤ በእነዚህ ጥቃቶች መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አለመቻሉን አስታውሷል።ኢዜማ በሰሞኑ መግለጫው፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ታጣቂዎች “ንጹሃንን የሚጎዳ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸም” እንዲያቆሙ አሳስቧል።
“መከላከያ ሠራዊትን እየወጋችሁ ያላችሁ ታጣቂዎችም የጠመንጃው መንገድ ደጋግሞ አክስሮናልና ጠመንጃችሁን አስቀምጣችሁ ቢያንስ “ቆመንለታል” የምትሉትን ሕዝብ ከገባበት አጠቃላይ ቀውስ ለማውጣት የየበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል-ኢዜማ በመግለጫው።
መንግሥትም “በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በሚገባ” እንዲመረምር ፓርቲው አሳስቧል። “ጦርነት እንዲቆም ትጥቅ ላነሱ አካላት ሀቀኛ የሆነ ይፋዊ የሰላም ጥሪ” መንግስት እንዲያቀርብም በመግለጫው ጠይቋል።

Read 795 times