Saturday, 27 January 2024 00:00

“ምላስ ደህና ቦታ ተቀምጣ፤ ጭንቅላት ታሰብራለች”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንድ ጊዜ አንድ የትግያ (Wrestling) ጥበብ አዋቂ፤ ለአንድ ተማሪው፤ “ና ትግያ ላስተምርህ” ይለዋል፡፡
ተማሪውም፤
“ምን ያህል የአስተጋገል ዘዴ ታውቃለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አስተማሪውም፤
“360 የትግያ አይነቶች እችላለሁ” አለው፡፡
“እነዚህን ሁሉ ለመማር ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብኛል?”
“እሱ እንደቅልጥፍናህ ነው፡፡ አንዱ ጥበብ ከሌላኛው ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እስቲ ሞክረውና ከዚያ ጊዜውን ለመገመት ትችላለህ” ሲል ይመልስለታል፡፡
ከዚህ በሁዋላ መምህሩ ወጣቱን ማስተማር ጀመረ፡፡ የተወሰነ ዓመታት ፈጅቶበት ወጣቱ 359 የትግያ ጥበብና ዘዴዎችን ተማረ፡፡ የመጨረሻዋን ጥበብ ግን ሳይማር ቀረ፡፡ ወራትና ዓመታት እየገፉ በሄዱ ቁጥር ወጣቱ በትግያ እየተራቀቀ በገመድ ቀለበት ውስጥ የመጡ ተጋጣሚዎችን ሁሉ ተራ በተራ እየተጋጠመ እያሸነፈ የተዋጣለት አሸናፊ ሆነ፡፡ ዝናንም አተረፈ፡፡ በዚህም ከፍተኛ ኩራት ተሰማው፡፡
አንድ ቀን ሰው ሁሉ በተሰበሰበበት ለአስተማሪው፡-
“ሰማህ ወይ መምህር፤ እስከዛሬ ባስተማርከኝ ጥበብ በጣም ተራቅቄበታለሁ፡፡ ወደ ትግያ የገመድ ቀለበቴ የገቡትን ተጋጣሚዎች ሁሉ አንድ ባንድ እያነሳሁ አፍርጬ በአሸናፊነት ተወጥቻለሁ፡፡ አንተንም ቢሆን በማክበር ነው እንጂ ብገጥምህ እጥልሀለሁ” አለው፡፡
መምህሩም በዚህ በተማሪው ድፍረት በጣም ተናደደና፡-
“ለመሆኑ አሁኑኑ የትግሉ ገመዱ እንዲዘጋጅ ባደርግ ለመታገል ዝግጁ ነህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ተማሪውም፡-
“ከተዘጋጀሁ ቆይቻለሁ” አለው፡፡
መምህሩ በተማሪው መልስ በጣም ተበሳጭቷል፡፡
“እንግዲያው በል ና የአገሩ ሡልጣን ፊት ሰው ባለበት አደባባይ ላይ እንጋጠማለን” አለውና ወደ መታገያው የገመድ ቀለበት ውስጥ ገቡ፡፡
እንደተጀመረ ወጣቱ እየጮኸና እየዘለለ የመምህሩን ወገብ ጥብቅ አድርጎ ይዞ ሊጥለው ይወዘውዘው ጀመረ፡፡ ሆኖም አልጣለውም፡፡
እንደገና በሌላ ወገን ይይዘውና ዘርጥጦ ሊጥለው ይሞክራል፡፡ አሁንም አልሆነለትም፡፡
ወጣቱ 359ኙንም የመታገያ ዘዴዎቹን ተጠቅሞ ሊጥለው ሞክሮ ሳይሳካለት ቀረ፡፡ በኋላ መምህሩ መጠናከር ጀመረ፡፡ በመጨረሻም፡-
ወጣቱን በሁለት እጆቹ ወደ ላይ አንስቶ ቁልቁል ወደ መሬት ወረወረው፡፡ ወጣቱ ተሰባበረ፤ ሰውነቱ ደቀቀ፡፡
ተመልካቹ አካባቢውን በሆታ ሞላው፡፡
ሡልጣኑ መምህሩን አሰጠርቶ፡-
“ይሄ ወጣት በከተማችን የተነገረለትና በጣም እየጠነከረ የመጣ ነው፡፡ ማንም ሲጥለው አላየሁም፡፡ አንተ አርጅተሃል፡፡ አቅምህ ደክሟል፡፡ ታዲያ እንዴት ልትጥለው ቻልክ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
መምህሩም፤
“ሡልጣን ሆይ! ወጣቱን ሳስተምረው 359 ጥበቦችን ነው ያስተማርኩት፡፡ ይቺ አሁን የተጠቀምኩባት ጥበብ 360ኛዋ ናት፡፡ ይቺ የኔ የራሴ የክቴ ናት፡፡ ለእንዲህ ያለው ጊዜ ነው የምጠቀምባት፡፡ አንድ ጊዜ አንድ የቀስት ውርወራ አስተማሪ ያለ የሌለውን ጥበብ በሙሉ አስተምሮ ሲያበቃ አንዱ ተማሪው ውድድር ገጥሞ አሸነፈው፡፡ አስተማሪውም ‘ሳይቸግረኝ ያለኝን ዘዴ ሁሉ ሰጥቼ ነው ጉድ የሆንኩት!’ አለ ይባላል” ሲል በምሳሌ አስረዳቸው፡፡
***
ዘዴና ጥበብን ሁሉ ሙልጭ አድርገው ሰጥተው ባዶ መቅረት ኋላ ማጣፊያ ሊያሳጥር እንደሚችል ነው ከላይ ያለው አፈ-ተረት የሚነግረን፡፡ “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” እንዲል የአበሻ ተረት፡፡ አሊያም በዚህ በውድድር ዓለም ተወዳዳሪህ ወይም ተፎካካሪህ ውሎ አድሮ ምን እንደሚያስብ በማጤን የክትህ የሆነ በልጦ መገኛ ዘዴ ሊኖርህ እንደሚገባ አስተውል ማለቱ መሆኑን እረዳለን፡፡ አንድም ብዙ ባሸነፍክ ቁጥር አቅምህን ሳትለካ መንጠራራት አሊያ ደግሞ አላስፈላጊ ግጥሚያ ውስጥ ገብቶ መቀናጣት ለምን አይነት ሽንፈት እንደሚዳርግ እንድናስተውል ይጠቅመናል፡፡ በሀገራችን በርካታ ፍልሚያዎች ወይ የእንቅስቃሴ ሂደቶች ውስጥ የባላንጣን ስስ ብልት በማየት በጎላ ፕሮፓጋንዳ ላይ ብቻ በማተኮር ሲደነቋቁሩ መክረም፣ ሀሰተኛ ቅስቀሳን በመደጋገም ከጊዜ ብዛት ይታመንልኛል ብሎ ማሰብ፣ ያገኙትን ትንሽ ድል እጅግ አጋኖ ግነን በሉኝ ማለት አልያም በጊዜያዊ ድል መኩራራት ወዘተ  ከግብ ላለመድረስ ጥቂት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ከታሪክ ለሚማር ታሪካዊ እሴቶች ናቸው፡፡ ከቶውንም በሌሎች ላይ የምንሰነዝረው ትችትና ጥቆማ እኛ  ከምንሰራው ተጨባጭ ተመክሮ አንፃር ተግባራዊ ትርጉሙ ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ ግንዛቤ ውስጥ ቢገባ ደግ ነው፡፡ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያየኸውን ጉድፍ…. እንዲል መፅሀፍ፡፡
ከማናቸውም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂደት የምናገኘው ተመክሮ ጠርዝ ያለው መሰረት ይሆን ዘንድ ከ359ኛው ጥበብ ባሻገር 360ኛውን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ የሀገራችን ችግሮች ሁልቆ-መሳፍርት ናቸው፡፡ ሁልቆ-መሳፍርት ጥበብንና በብዙ ጭንቅላት ማሰብ ይጠይቃሉን፡፡ እኔ ብቻ ነኝ መፍትሄ ልሰጣቸው የምችለው ማለት ብዙ አያራምድም፡፡
ሆደ-ሰፊና ተቻቻይ ከሁሉ ጋር ተባብሮ፣ ተግባብቶ ሙያን አክብሮ ልምድን በአግባቡ ተጠቅሞ መንቀሳቀሰስ አግባብ ነው፡፡ ያቅም፣ ካቅም በላይም አሊያም ካቅም በታች፣ አቅሜ ነው ብሎ መዋሸት ቀኑ ሲደርስ “ምላጭ የዋጠ ማስወጣቱ ይጨንቀዋል” የሚባለውን ተረት ነው የሚያረጋግጠው፡፡
አያሌ በሀገርም ደረጃ፣ በዓለምም ደረጃ የምንገባቸው ውሎች የምናልማቸው ትርፎች፣ የምናቅዳቸው ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች፣ “እዚያ ቤት እሳት አለ” ብለን የምናጤናቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ዐይነ-ውሃቸው የሚያምር ወይም ከጊዜያዊ ጣር የሚያላቅቁን የሚመስሉ አያሌ ጉዳዮች ኋላ የማይያዙ የማይጨበጡ እዳዎች፣ ውል-የሌላቸው ችግሮች እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ አብዛኞቹ የኢኮኖሚ መስተጋብሮች ረጋ ተብለው ሲታሰቡ፣ ሙስናዊ ቀዳዳዎቻቸው የበዙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዳቸው ቀዳዳዎች እያደር እየሰፋ የሚሄዱ እንዳይሆኑ ግለሰቦች ላይ ከጣለው ፖለቲካዊ እምነት ባሻገር በሀገር መንፈስ ማውጠንጠን፡፡ ሲሞን ቦሊቫር የተባለ የአዲሲቱ የላቲን አሜሪካ ሪፑብሊክ መሪ “በሦስቱ ጥምር ችግሮች ማለትም - ድንቁርና ጭቆናና ሙስና ተጠፍረን ታስረን፣ ትምህርት፣ ሥልጣንና  ሥነምግባር ሊኖረን አልቻለም፡፡ እናም የተማርነው ባልሆኑ መምህራን ስለሆነም ያገኘናቸው ልምዶችም ሆኑ ያናናቸው ምሳሌዎች ወደ ጥፋት የማምራት ባህሪ ነው ያላቸው፡፡ ከጉልበት የበለጠ በመታለል ተጠቅተናል፡፡ ሙስናም ከአጉል አምልኮ የበለጠ ቁልቁል አርጎናል፡፡…. ምኞትና ተንኮል ሁነኛ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ወይም የሲቪክ እውቀት የሌላቸው ሰዎች፣ ልምድ የለሽና በቶሎ አማኝ ያደርጋቸዋል፡፡ ቅዠቶቹን እውን አድርገው እንዲያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ፈቃድን ከነፃነት ያምታታባቸዋል፡፡ ክህደትን ከጀግንነት ያወነባብድባቸዋል፡፡ በቀልንም ከፍትህ ያምታታባቸዋል” ይላል፡፡ ከዚህ ይሰውረን ማለት ደግ ነው፡፡
ነባራዊና እሙናዊውን ቀና መንገድ ይዞ መጓዝ ከበሽታ ያድነናል፡፡ ከኢኮኖሚ ድቀት ያወጣናል፡፡ ከስህተታችን እንድንማር ያደርገናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የገባነውን ቃል እንድናከብር ያግዘናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የምንለው ከምናደርገው ካልተገናኘና አልፎ ተርፎም አገርና ህዝብን የሚጎዳ ከሆነ “ምላስ ደህና ቦታ ተቀምጣ፣ ጭንቅላት ታሰብራለች” የሚለውን አባባል ነው የሚተረጉም፡፡

Read 847 times